Saturday, 13 December 2014 10:47

ነቄዎቹ የ6 ኪሎ ልጆች! ምናባዊ ወግ

Written by  አዲስ አለማየሁ
Rate this item
(10 votes)

    ከ6 ኪሎ ወደ ምኒሊክ በሚወስደው መንገድ በምናብህ እየኳተንክ ነው፡፡ መቼም የ6 ኪሎ ሰው ምሁር ነው፡፡ አንድ ጐረምሳ የአንስታየንን ሬላቲቪቲ ቲዎሪ እንደ አቡነዘበሰማያት በቃሉ ሲወጣው ብታይ፤ “ምን የእብድ ሰፈር ገባሁ” ብለህ እንዳትደነግጥ፡፡ እዚህ ላይ፡-
አወይ 6 ኪሎ አወይ ምኒሊክ ሆይ
አፈሩም ቅጠሉም ምሁር ይሆናል ወይ፡፡
የሚለውን የቆየ የአበው ተረት ማስታወስ አይከፋም፡፡ በስተግራህ እንደ ግራር አጥንት ችምችም ብለው የተገነቡ ሳይሆን የበቀሉ የሚመስሉ የ6 ኪሎ ልጆች በሌላው ሰፈር ላይ የተቆናጠጡትን የአእምሮ ልዕለ ሃያልነት እውን ያደረጉ ጫት ቤቶችን ታገኛለህ፡፡
ነገሩ የሆነው ልማታዊ መንግስታችን ወታደራዊውን ጁንታ መንግስት በግማሽ ቂጡ ሳይደላደል ከተቀመጠበት ወንበር ጠልዞ ከመጣሉ በፊት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲ በገቡ የ6 ኪሎ ልጆች ቀስቃሽነት ዘንድሮ ስታወራው “ፐ” አልያም “ንክር” ከሆንክ አጀብ የምትልበት የተማሪዎች ንቅናቄ በኋላም የEPRP ምስረታ እውን ሆነ፡፡
ታዲያ በ6 ኪሎ ልጆች የህቡእ ስብሰባ ላይ ሰርገው የገቡ የጨርቆስ ልጆች፤ በሰፈራቸው የለመዱትን “ጨርቄ ሽብር” ነጭ ሽብር የሚል የሃሳብ ሽርጥ አልብሰው አቀረቡ፡፡
ለነገር ችኩል የሆኑ የቦሌ ልጆች፣ ደርሶ ደም የሚሸታቸው የመርካቶ ልጆች፣ ሰፈራቸው ያለውን የጅብ መንጋ በመፍራት መቧደን ያደገባቸው የኮተቤ ልጆች፣ ነጭ ሽብርን በአንድ ድምፅ ደገፉ፡፡ ታዲያ ነቄዎቹ የ6 ኪሎ ልጆች ድምፀ ተአቅቦ አደረጉ፡፡
 ቅሉ ምን ዋጋ አለው? ደርግ መች ድምፀ ተአቅቦ ያውቃል እቴ! በየአደባባዩ እውቀትን ይሰብኩ፣ ጥበብን ይዘምሩ የነበሩ የ6 ኪሎ ልጆችን አናቶች እናቱ የተከለችለት ዱባ ይመስል አፈንድቶ ጨረሰው፡፡ ያኔ ታዲያ 6 ኪሎ የሀዘን ደመና ወረሳት፡፡ ለጠቢብ ልጆቿ አምርራ አለቀሰች፡፡ ይህንን ያየ የባሻ ወልዴ ችሎት አዝማሪ እንዲህ ሲል ሙሾ አወረደ፡-
አያችሁልኝ ጉድ የ6 ኪሎን
ወረቀት አንስቶ ብረት ሲፈትን!
ከሰለሞን ይሆን ጥበብ የወረሰው?
ከደሙ እኩሌታ እውቀት የፈሰሰው
አገር የሚያቀና አደይ አሳብባ
6 ኪሎ ጉዷ ልጇ ገደል ገባ፡፡
የ6 ኪሎ እናቶች አልቅሰው አላቆሙም፤ በእድል የተረፉ ልጆቻቸውን ከመጣው መቅሰፍት የሚታደጉበትን ዘዴ ዘየዱ፡፡ እነሆ የነሱ ጥንስስ ለግራር መደዳ አወዳይ መወለድ ምክንያት ሆነ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው የ6 ኪሎ ልጅ ቢጤውን ፈልጐ “ጥግ እንያዝ” አልያም “ጭቁ እንበል” የሚለውን ሀረግ ማዘውተር የጀመረው፡፡
ከግራር መደዳ አወዳይ ቤቶች ጠርዝህን ይዘህ በመጓዝ ላይ እንዳለህ፣ ከ6 ኪሎ ሻሸመኔ ያሾልካል እንዴ እስክትል ድረስ ድሬዶች ከበዙብህ፣ በሀገራችን የዜማ ሊቅ የተሰየመው ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ደርሰሀል ማለት ነው፡፡
አንዳንድ በሀገራችን የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ላይ አንቱ የተባሉ ያሬድ ቀመስ አቀናባሪዎች፤ በያሬድና በድሬድ መካከል ያለውን ትስስር ሲያስረዱ፤ ቅዱስ ያሬድ በትል ከተፈተነ በኋላ፣ በዓፄ ገ/መስቀል አንካሴ እግሩ ከመሬት ከመሰፋቱ በፊት የሆነ በብዙ መዛግብት ያልሰፈረ ታሪክ ይነግሩሃል፡፡
ቅዱስ ያሬድ ዜማ በመድረስ ላይ እያለ በአዕምሮው የፈጠረው ዜማ አንደበቱ ሳይደርስ፣ በአናቱ ሲያሻው ቡልቅ ቡልቅ እያለ፣ ሲለው እየተነነበት ተቸገረ፡፡ ለገጠመው እክል አምርሮ ሲፀልይ መላዕክ ተገለፀለት፡፡
መላዕኩም፤ “ፀጉርህን እንደ ጠፍር አብጀው፤ እንደ መጫኛም ግመደው” የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶት ተሰወረ፡፡ ታዲያ ያሬድ የተባለውን ቢያደርግም የጎንደርና የአክሱም ቀሳውስት “ገዳም ሳይገባ መነኮሰ” የሚል ሽሙጥ ፍራቻም፣ ነጭ ጥምጣም ጠቀለለበት፡፡ እነሆ ዛሬ አንተም በ6 ኪሎ ያገኘኸውን ድሬድ ሁሉ “ራስ-ተፈሪያን” ብለህ አትፈርጅ፡፡ “ያሬዳውያንም” ሞልተውልሃል፡፡
ፀጉርህን በእጅህ እያበጃጀህ፣ የያሬድን አጥር ታከህ ስትሄድ፣ አጥሩ ካለቀብህ ከነሙሉ  ግርማ ሞገስህ ቸሬ ሰፈር ገብተሃል፡፡ ቸሬ ሰፈር ከ6 ኪሎ ሰፈሮች ውስጥ ምትሃተኞች የሚበዙባት መንደር ነች፡፡ ከነባር ህልም ፈቺዎች 15 ቤተሰቧን በግማሽ ጆግ ቅንጬ እስከምታጠግብ አስማተኛ ልጃገረድ ድረስ በየፈርጁ ሞልተውልሃል፡፡ ምነው ታዲያ ስሙን ቸሬ አሉት፤ መቼም የታወቁ ሊቅ አስማተኛ መሆን አለባቸው፡፡ ጠጠር ለቅመው ለፈለገ ቡና፣ ለሌላው እጣን አድርገው የሚያድሉ ናቸው ካልክ ፍፁም ርቀሀል፤ በሄድክበት የሀሳብ እግርህ ተመለስ፡፡
ታሪኩ የሆነው ጣልያን ዳግመኛ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ነው፡፡ በጊዜው የነበሩ መኳንንት ከነጀሌያቸው “እንቢ ላገሬ” ብለው በዱር በገደሉ አርበኝነት ቢገቡም የነበራቸው የጦር መሳሪያ አነስተኛ ነበር፡፡ ያኔ ታዲያ ከመኳንንት ወገን የሚወለዱት አቶ ቸሩ አንድ መላ አበጁ፡፡ ሁለት ወደል አህያ ገዝተው፣ ከገጠር የገበሬ ቤት የሰበሰቡትን ብረት በፍልጥ መሃል እየዶሉ፣ ለአርበኞች ያቀብሉ ጀመር፡፡ በዚህም ብልሃታቸው የብዙ አርበኞችን ህይወት ታድገዋል፡፡
መቼም ለሰው ጠንቁ ሰው ነው፡፡ ይህንን ግብራቸውን ያወቀ ባንዳ፤ ለጣልያን ከረቢኛሬ በመንገሩ፣ ተወልደው ባደጉበት መንደር ለእናት ሀገራቸው በክብር ተሰዉ፡፡
በጊዜው የነበሩ አርበኞች ጓደኞቻቸውም እንዲህ ሲሉ አለቀሱላቸው፡-
ቸሬ ከዲነግዱ ብልሃት የወረሰ
ሶላቶን ሳንጥል ውላችን ፈረሰ፡፡
ብረቱ ይቅርብን ቸሬ አንተ ተመለስ
ብናጣህ እኮ ነው ወኔያችን የሚፈስ፡፡
ወዳጄ የቸሬ ሰፈርን ገድል ከሰማህ በኋላ ከፊል ልብህ አስማተኛ፣ ከፊል ልብህ አርበኛ ልሁን እያለ አልረጋ ብሎ አዕምሮህን ሲሞግተው ሰማሁ፡፡ ባታውቀው ነው፡፡ በ6 ኪሎ ታሪክ ሰሚ እንጂ ታሪክ ደጋሚ መች ይመሰገናል፡፡ ባይሆን የ6 ኪሎ ልጆች እሳት ከበው፣ ሞኝ-አንግሳቸውን እየጨለጡ፣ ከሰሟቸው ጥዑም የሰፈራቸው ታሪኮች መሃል አንዱን እነሆ፡-
አባባ ጃንሆይ፤ ከእንግሊዝ አብረው ጣልያንን ካባረሩ በኋላ፣ 6 ኪሎ ወደ ቀድሞ ፈንጠዝያዋ ተመለሰች፡፡ ልጅ ሳይል አዋቂ ሁሉም የ6 ኪሎ ውልድ ወርቁ ጠጅ ቤት ከተመ፡፡
 ከሸክላ ማጫወቻው የሚተመው ዘፈን ሲያቆም ብቻ ሁሉም ጨዋታውን ገታ አድርጐ፣ በቀጣይ የሚሆነውን ይጠብቃል፡፡ አንድ ልጅ - እግር ከወደ ጓዳ ወጥቶ የመሞዘቂያውን መነዌላ አጡዞት፣ ወደ መኳንንቱ መደዳ አይኑን ጣል ያደርጋል፡፡ ነገሩ የገባቸው ፊታውራሪ ኢብሳ፤ በጥቅሻ ሲያነሱት ከበር መልስ ላለው ሁሉ ጠጅ ያድላል፣ ሙዚቃው ከፍ ይላል፣ ሁካታው ይቀልጣል፣ 6 ኪሎም ጠጅ ትራጫለች፤ እንደዚያ ታመሻለች፤ እንዲያም ታነጋለች፡፡
ከዚያ ሁሉ ሁካታ መሃል አንድ ዘለግ ብሎ የሚሰማ ዝምታ ነበር፤ የሚጨንቅ ዝምታ…ፍርሃት የወለደው ዝምታ! የአየለ ስብሀቱ ዝምታ…
አየለ ስብሀቱ ሞቅ አለው፡፡ በፊትአውራሪ ግብዣ የጠጣውን ጠጅ ነገ እንደማያገኘው ተረዳ፡፡ አጥንተ - ድህነቱ ከበደው፡፡
እላዩ ላይ እንዳለው ቡትቶ አሽቀንጥሮ ሊጥለው ፈለገ፡፡ ተሳካለትም፡፡ በመንገድ ላይ ያገኛቸውን ፈረንሳዮች ጃንሜዳ ይዟቸው ገባ፡፡ “ይህ የምታዩት ሁሉ የአያት የቅድመ - አያቴ ርስትና የኔ ቤት ነው፡፡ ንብረቴን ሁሉ ሸጬ ወይራ - አምባ እናቴ ጋ መግባቴ ስለሆነ፣ 10ሺህ ብር ግዙኝ!?” አላቸው፡፡ አላቅማሙም ተስማሙ፡፡
በበነጋው አንኮላ ፈረንጅ ሁሉ አጥር ሊያጥር፣ ችካል ይዞ ጃንሜዳ ገባ፡፡ በነገሩ ግራ የተጋቡት ክቡር - ዘበኞች፤ አየለንም ፈረንሳዮቹንም ይዘው ዙፋን ችሎት ቀረቡ፡፡ ጃንሆይም በወገናቸው ብልጠት ደስ ቢሰኙም ፍርደ - ገምድል ላለመሆን እየጣሩ፣ “ልጅ አየለ ብሩን ከወዴት አደረስከው!?” አሉ፡፡ አየለም ኩታውን አደግድጐ መሬት ለጥ አለና፤ “በአገራችን ነፃ መውጣት የደስ ደስ ከበር መልስ ጠጥቼ አጠጣሁበት” አላቸው፡፡ አሁንም በመልሱ ደስ የተሰኙት ጃንሆይ፤ ብሩ ከግምዣ ቤት እንዲከፈል አዘው አየለን በሰላም አሰናበቱት፡፡ ወረኛው ወርቁ ጠጅ ቤት ሲደርስም፤ “አየለ ስብሃቱ ጃንሜዳ ነው ቤቱ!” ሲሉ አቃበጡት፡፡
 (ውድ አንባቢያን፤ ከላይ የቀረበው ወግ በቅርቡ በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በተካሄደ የስነፅሁፍ ውድድር ያሸነፈና ለፀሃፊው የደራሲ አዳም ረታን “መረቅ” አዲስ ልብወለድ መፅሃፍ ያሸለመ እንደሆነ የውድድሩ አዘጋጆች ገልፀውልናል፡፡ እኛም ይሄን በማህበራዊ ድረገፅ የተጀመረ አዲስ የጥበብ ባህል ለማበረታታት በማሰብ፣ መጠነኛ አርትኦት አድርገንበት አትመነዋል፡፡)


Read 7087 times

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.