Saturday, 13 December 2014 10:44

“ለሚስቱ የፍየል ሙክት ገዝቶ ሴቶቹን…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(8 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
የዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ፉት አለ አይደል!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ለሴት ጓደኛው ስጦታ መስጠት ይፈልግና ምክር ይጠይቃል፡፡
“ለጓደኛዬ ምን ስጦታ ብሰጣት ጥሩ ነው?”
“ትወድሃለች?”
“እንደምትወደኝ እርግጠኛ ነኝ፡፡” “እንግዲያው፣ ምንም ነገር ብትገዛላት ደስ ይላታል፡፡”
‘ቢሆን ኖሮ አሪፍ ነበር’ የሚባለው እንዲህ ነው፡፡ አሀ… ስጦታ መስጠትና መቀበል ራሱ ‘ትርፍ ነገር’ መሆኑ ቀርቶ ‘የመዋደድ’ ማረጋገጫ ምልክት እየሆነ ነዋ! በፊት እኮ ስጦታ…አለ አይደል… ‘ጉቦ’ ቢጤ ነገር ነበር፡፡ “ማስቲካ ብሰጥሽ ምን ትሰጭኛለሽ?” ምናምን አይነት የልጅነት ዕቃ፣ ዕቃ ጨዋታ ትዝ አይላችሁም! እና ማስቲካው ‘ጉቦ’ ነበር፡፡ ዕቃ፣ ዕቃ ጨዋታው ደግሞ የትያትር ምናምን ሰዎች እንደሚሉት ‘ኢምፕሮቫይዜሽን’ ነገር ነበር፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
ይቺን ጨዋታ ስሙኝማ…በበፊት ጊዜ ነው አሉ፡፡ ሰውየው በዘመኑ ‘የተከበሩ’ የሚባሉ አይነት ናቸው፡፡ ታዲያላችሁ… አንድ ቀን ሚስታቸውን ደስ ለማሰኘት ብለው ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው… እኔ ነኝ ያለ የፍየል ሙክት በሠላሳ ብር ገዝተው ቤታቸው ይመጣሉ፡፡ ፍየሉ ተጎትቶ ግቢ ሲገባ አገሬው ሁሉ በየበሩ ብቅ ብሎ ያያል አሉ፡፡ (‘በየበሩ ብቅ ብሎ ማየት ዘንድሮም እኮ በተለያየ መልኩ በሽ፣ በሽ ነው፡፡) ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…በግ ቆዳ መልስ አሥራ አምስት ብር የሚገዛበት ዘመን አልፎ አሁን ክትፎ ሳህን መልስ መቶ ስድሳ ብር ሆኖ አረፈው! የዘንድሮ አንድ ክትፎ እኮ ከጥቂት አሥርት ዓመታት በፊት ስምንትና ዘጠኝ ሙክት ይገዛ ነበር ማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ በሠላሳ ሳንቲም ‘ያላበው ቢራ’ እግር ሰቅሎ ማንደቅደቅ ነው፡፡ ዘንድሮ በሠላሳ ሳንቲም ግፋ ቢል አንድ በጣም ቀሺም ማስቲካ ቢገዛ ነው፡፡ በግ አሥራ አምስት ብር ይገዛበት የነበረበት ዘመን ‘ዶኩሜንታሪ’ ይሠራልንማ!  
እናማ…የሌሎች ሚስቶች ሁሉ ዓይኖቻቸው ተቁለጨለጩ፡፡ “እንዲሀ ነው እንጂ ባል ማለት፣ ለሚስቱ የፍየል ሙክት የሚገዛ!” ማለት ይጀምራሉ፡፡ ይሄኔ…ባሎች ሁሉ ምን አሉ ተባለ መሰላችሁ… “ለሚስቱ የፍየል ሙክት ገዝቶ ሴቶቹን አጠገባቸው…” ብለው እርፍ!
ነገርዬው ምን መሰላችሁ… በጊዜው የናጠጠ ‘ዲታ’ ቤት ቢሆን እንኳን የፍየል ሙክት መግዛት የተለመደ አልነበረም፡፡ አለው የተባለ ‘ባል ተብዬ’ (ቂ…ቂ…ቂ…) አሀ… ሴቶቹ እንደዚያ ነው የሚያስቡት ብዬ ነዋ!) ግፋ ቢል ትልቅ ነገር ገዛ ከተባለ የሀያ ብር የበግ ሙክት ነው፡፡ እናላችሁ…“ሚስቶችን አጠገባቸው…” ያሉ ባሎች… አለ አይደል… ነገርየውን በወሬ፣ ወሬ ጃንሆይ ዘንድ አድርሰውት ነበር፡፡ ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ የዘንድሮ የስጦታ ነገር አስቸጋሪ ሆነ እኮ፡፡ ‘እንደ አቅም’…ስጦታ መስጠት ብሎ ነገር የለም፡፡ “ዋናው ነገር የስጦታ ዕቃው ሳይሆን ሀሳቡ ነው…” አይነት ነገር ለፊልም ፖስተር ‘ማሳመሪያ’ ይሆን እንደሁ እንጂ በዓረፍተ ነገር አሰካክ የሰዋሰው ትምህርት ውስጥ እንኳን የለም፡፡
ልክ ነዋ… የባለ አበባ ቀሚስ ዘመን አልፎበታላ! የድቡልቡል ማስቲካ ዘመን አልፎበታላ! የሁነኛው መራ ሽቶ ዘመን አልፎበታላ! የሀር ውስጥ ልብስ ዘመን አልፎበታላ! (ቂ…ቂ…ቂ…) የምር ግን…አንዳንዴ እንደዚያ አይነት ዘመን ነበረ እንዴ ያሰኛል፡፡ ልክ ነዋ…መጀመሪያ ነገር እንትናዬዎች ስጦታ ፈላጊዎች አልነበሩም፡፡
እናላችሁ… ዘንድሮ…የስጦታ ነገርም በብዙ ‘ዲጂት’ አድጓል፡፡
“ለሚስቱ የፍየል ሙክት ገዝቶ ሴቶቹን አጠገባቸው…” የሚያሰኙ ነገሮች መአት ናቸው፡፡
እናላችሁ… ‘ስጦታ’ ተብሎ ምን የመሳሰሉ መኪኖች የሚሰጡበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ እንደውም አንድ ‘የከተማው ነገር የሚገባው’ ወዳጃችን ምን አለን መሰላችሁ…“ውድድሩ የመኪና ስጦታ በማግኘት ላይ ሳይሆን በመኪናው አይነት ነው፡፡”  
ኮሚክ እኮ ነው! ስሙኝማ…አንድ ሰሞን ለስጦታ ተብላ የተፈበረከች መኪና አሁን ‘ሁሉም’ ያዛት አይደል! “…አገኘኋት በምናምን…” ተብሎ ከአሥራ ስምንት ዓመት በታች መናገርም፣ መስማትም መከልከል ይገባው የነበረ አባባል ቢጤ ነገር ሁሉ ተፈጥሮላት ነበር! ብቻ የሆነ የሚገርም ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
ዘንድሮ…አለ አይደል… “ለሚስቱ የፍየል ሙክት ገዝቶ ሴቶቹን አጠገባቸው…” የሚያሰኙ ነገሮች በዝተዋል፡፡
“ስሚ፣ እንትና እኮ ቦይፍሬንዷ የመኪና ስጦታ ሰጣት፡፡”
“አትዪኝም!”
“አይ ስዌር!”
“ምን አይነት መኪና ሰጣት?”
“ያቺ ብራዚሊያ የሚሏት የድሮ መኪና…”
“ውይ!  ውይ! አፈር በበላሁ!”
“ምነው፣ ምነው! እሷን መኪና ነው ስጦታ ብሎ የሰጣት፡፡ ስታሳዝን!”
ልክ ነዋ…ልጄ ዘንድሮ የመኪና ስጦታ የተሰጣት እንትናዬ እኮ ከፈለገች ሸጣው እኔ ያለሁበትን መንደር መግዛት ትችላለቻ!
“ለሚስቱ የፍየል ሙክት ገዝቶ ሴቶቹን አጠገባቸው…” አይነት ነገሮች በዝተዋል፡፡
እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን አንድ ሰውዬ አላት የተባለች ነገር ስሙኝማ፡፡ “ባለፈው የገና በዓል ለሴት ጓደኛዬና ለወንድሜ ስጦታ ልኬላቸው ነበር፡፡ የሴት ጓደኛዬ በዚያ ሰሞን ደስተኛም ስላልነበረች እሷን ደስ ለማሰኘት ነበር ስጦታ መላኬ፡፡ ለእሷ አሪፍ ሽቶ፣ ለወንድሜ ደግሞ የሽጉጥ ስጦታ ነበር የላኩላቸው፡፡ ለእሷ በላኩት ስጦታ ላይ ‘ይህንን ስጦታ ራስሽ ላይ እንደምትጠቀሚው እርግጠኛ ነኝ…’ ብዬ ጽፌ ነበር፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል በስህተት የላኩላት ሽጉጡን ነበር፡፡ እንዳልኳትም ራሷ ላይ ተጠቀመችው፡፡”
‘ለአቅመ ስጦታ መስጠት’ ከደረሳችሁ ስጦታ ከማሳሳት ይሰውራችሁማ!
ስሙኝማ ዘንድሮ እኮ ለእንትናዬዎች ስጦታ ሲሰጥ…አለ አይደል…አይደለም ለተቀባዮቹ ለእኛ ለሰሚዎችም የደም ዝውውር ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ እነ ሽቶና መዋቢያዎች እንኳን ሚጢጢዋ ብልቃጥ አራትና፣ አምስት ሺህ ብር ገብተዋል፡፡ከተማው ውስጥ ልወዝወዘው በእግሬ እያላችሁ…አለ አይደል…ከአንድ ከሁለት ወር በፊት ሀይገር ላይ ለመሳፈር ስትጋፋ ያያችኋት እንትናዬ ምን በመሰለች መኪና ስትፈስ ታዩዋታላችሁ፡፡ ግራ ይገባችኋል፡፡ በዚያ ሰሞን የመኪና የሎተሪ እጣ መሰጠቱን በሬድዮ ምናምን ነገር አልሰማችሁማ!
በኋላ ለሆነ ወዳጃችሁ… “አንተ… እንትና ምን የመሰለ መኪና ይዛ አየኋት…” ትሉታላችሁ፡፡
እሱም “ልጄ እሷ ጎበዝ ነች፣ አውቃበታለች…” ይላችኋል፡፡  
አውቃበታለች ብሎ ነገር ምንድነው?
“ምኑን ነው ያወቀችበት?”
“አንተ ደግሞ ዘለምህን ቢያጥቡህ፣ ቢፈትጉህ የማትጠራ ፋራ አትሁን እንጂ! የጨዋታውን ህግ አወቀችበታ! የያዘችው ቦይ ፈሬንድ አይደለም መኪና አንድ ሙሉ የሪል ስቴት መንደር መግዛት የሚችል ነው፡፡”
“ለሚስቱ የፍየል ሙክት ገዝቶ ሴቶቹን አጠገባቸው…” አይነት ነገር በዝቷል፡፡
እናላችሁ…‘ያወቁበት’ እንዲህ በመኪና ሲፈሱ፣ ‘ያላወቁበት’ ደግሞ ግፋ ቢል ‘ዊንዶው ሾፒንግ’ የሚከለክላቸው የለም፡፡ ቂ…ቂ…ቂ… (‘ያላወቃችሁበት’ እንትናዬዎች… የምክር አገልግሎት ከፈለጋችሁ ስልክ ምቱማ! ቢያንስ፣ ቢያንስ የምታንዣቡባቸውን ካፌዎች መጠቆም አያቅተንም፡፡) (“ቦሌን ባትዝናናበትም ማንም ሳይከለክልህ በእግርህ ትወዘወዝበታለህ…” ያልከኝ ወዳጄ …‘የሚወድቅ ሞራል’ ያገኘህ መስሎሀል!)
ብቻ ምን አለፋችሁ…“ለሚስቱ የፍየል ሙክት ገዝቶ ሴቶቹን አጠገባቸው…” አይነት ነገር በዝቷል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2379 times