Monday, 08 December 2014 14:36

ማንነት ፍለጋ!

Written by  አሰፋ ጫቦ Corpus Christi, Texas, USA
Rate this item
(3 votes)

ክፍል ፩

        እንዲያው ዘው ተብሎ አይገባ ነገር! ”ቤቶች!” ተብሎ ”ደጆች!” ተብሎ “ይግቡ/ግባ!” ተብሎ ነው እንጅ። ጠፍቼ ሰነበትኩ። ከረምኩ ሳይሻል አይቀርም። “ለመሆኑ አሰፋ ጫቦ የት ገባ” ብለው በአደባባይ የጠየቁት ወሰንሰገድ ገ/ኪዳንንና እንዳለ ጌታ ከበደን እንዲሁም ሌሎች እዚህ በስም ያልጠቀስኳቸውን ሁሉ አመስግናለሁ። ለክፉም ለደጉም ጠያቂ አያሳጣችሁ! እኔማ ሌላ ምን እላለሁ! የቤተ ክህነት አባቶች እንደሚሉት ሱባዔ ገብቼ ነበር። ከዚያው ከቤተክህነት ተውሼ፤ (ነበርኩበትምና) “ዘኀሀለፈ ሥርየት ወለዘይመጽዕ እቅበት” እላለሁ። ነጠላ ትርጉሙ “ያለፈው ይሰረዝ ይደለዝ ለመጭው መታቀብን/መቆጠብን  ስጠኝ/ስጠን!” እንደማለት ነው። በምወደው መጽሐፍ Gone with the Wind ላይ ስካርሌት ኦሐራ (Scarlet O’Hara) Tomorrow is Another Day ትላለች። “ነገም ሌላ ቀን ነዉ” ብሎታል ተርጓሚው ነቢይ መኮንን። እኔም እንዲያ እንዳልኩ ይቆጠርልኝ!
ሁለት ወንድሞቼ፤ ዩሱፍ ያሲን ”አሳሳቢ ማንነት፤ባንድ ሀገር ልጅነት፤የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ” እና እሸቱ ጫቦ Gamo/Amharic/English Dictionary የሚል ጽፈው ታትሞ ገበያ ላይ ዉሏል።
ኩራት ኩራት አይልህም ወይ ኩራት አይልህም ወይ?
የኛ ወንድም አይደለህም ወይ  ኩራት አይልህም ወይ? የሚሉኝ
መሰለኝ። አሁን የፈልግሁት የዩሱፍን መጽሐፍ በሁለት ከፍዬ ለማየት ነው። በመጀመሪያ፤ በዚህ፤ መጽሐፉ ኢላማ አድርጎ ሊስላት የሚመኛትን፣ የሚፈልጋትን ኢትዮጵያ ለማሳየት ነው። ለዚህ ሰበብ አስባብ ከመጽሐፉ ውስጥ አገኘሁ። መጽሐፋ ዜናሁ ለጋላ በሚለው በአባ ባህርይ መጽሐፍ ይጀምራል። የአባ ባህርይ መጽሐፍ የተጻፈው ደግሞ ብርብር ነው። ብርብር ደግሞ የጋሞ አገር ነው። ጋሞ መሆኔ ደግሞ አንዳንድ የማውቀውን፤ የነበር፤ ያለ፤ ያልታወቀ እንዳነሳ ምክንያት ፈጠረልኝ። “በልጅ አመካኝቶ ይበሏል አንኩቶ” እንዲሉ። በክፍል ሁለት መጽሐፉን ራሱን ለማስኬድ እሞክራለሁ።
ዩሱፍ ያሲን “ይህን ያማጥኩትን ልጅ ስሙን ማን ልበለው?” ቢለኝ ኖሮ “ማንነት ፍለጋ!” ወይም “እኔነት ፍለጋ!” በለው ባልኩኝ። አልነበርኩምና አልጠየቀኝም።
ለመሆኑ እኔ ማነኝ? የምናስበውን ያህል፤ እኔ ስለ እኔ ያማስበውን ያክል ቀላል ሆኖ አይገኝም። ከመክበዱ የተነሳ ወይም ይኼ “ማንም የሚያውቀው” የታወቀ የተረጋገጠ፤ ወይም ልብ ካለማለት ”አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው” “Given” ብለን እናልፈዋለን። ወይም ጥያቄው ከነአካቴው ላይነሳ ይችላል። ምነው ቢሉ ”አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው” ነዋ! ወይም ነው ብለን፤ ብዬ ተዘግቷል። ግና ቀን ጠብቆ፤ ምክንያት ፈልጎ ከውስጥ የሆነ ቃጭል ጢ..ሪ..ሪ..ሪ ሲል ይሰማል። እንሰማለን። እኔ እሰማለሁ። የቃጭሉን ጥሪ ሰማሁ አልኩ እንጅ ገባኝ፤ ተረዳሁት አላልኩም። መስማትና መረዳት ከዚያም ለጥቆ ገባኝ ማለት የየራሳቸዉ የሚፈጩበት፤ የሚቦኩበት፤ የሚጋገሩበት፤ ከዚያም በግልም ሆነ በጋራ የሚበሉበት፤ የሚሳተፉበት መስክ፤ አዳራሽ፤ ጓዳ፤ ጐድጓዳ አላቸዉ። ለየቅል ናቸዉ። መስማት! ተረዳሁት! ገባኝ… ማለት ቀላል አይደለም፤ አይሆንም ለማለት ፈልጌ ነው።
ወንድሜ፤ ዩሱፍ ያሲን መጽሐፉን የሚጀምረው ዜናሁ ለጋላ በተሰኘው የአባ ባህርይ መጽሐፍ ነው። የጋሞ መነኩሴ ናቸው ይላል። ናቸው እንዴ? የዚህ ጥያቄ መልስ የዩሱፍ መጽሀፍ ላነጣጠረበት ግብም ሆነ ለኢትዮጵያ፤ በኢትዮጵያ ያልተነሱትም ሆነ ሊነሱ ለሚችሉት የሚያናቁሩ ጭብጦች ሙሉ ለሙሉ ባይሆንም በከፊል ቁልፉን የያዘ ነው። እኔ ነው ብዬ አምናለሁ። ላስረዳ:-
አባ ባህርይ እርግጥ የጋሞ መነኩሴ ነበሩ። የብርብር ማርያም መነኩሴ ነበሩ። ጋሞ ግን አልነበሩም። የማርያምን ጽላት አቅፈው፤ ሸሽገው በእምነታቸው ምክንያት ከሚያሳድዷቸው ጋሞ፤ ብርብር መጥተው ጥገኛ የሆኑ አማራ መነኩሴ ነበሩ። ትግሬም ሊሆኑ ይችላሉ። ግን ለዚህ አሰሳ አማራ ናቸው በሚለው ብሔድ የሚሻለኝ መሰለኝ። ታሪክ ወደዚያ ስለሚያዘምም።
ብርብር የጋሞ ቃል ነው ብዬ እወስዳለሁ። መሀል ጋሞ ዴሬ (አገር) ውስጥ ነውና። የአማርኛው አንድምታው አሁን በዚህ በዩሱፍ መጽሐፍ አንጻር ሳየው ገረመኝ። ብርብር ያው በረበረ፤ አሠሠ፤ ምንም አላስቀረ፤ አደባባይ አወጣው እንደ ማለት አይደል? “ልጅን መልአክ ያናግረዋል ይባላል። የልጅ አንድምታም ትርጉሙ ቀና፤ ንጹሕ ማለት ነው። እየሱስ “እንደ ህጻናት ካልሆናቸሁ ወደ መንግስተ ሰማያት ዝር አትሉም” ይላል በወንጌሉ ውስጥ። ታዲያ ይህንን አፋር፤ እስላም ወንድሜን መላክት አናግረውት ይሆን የኢትዮጵያን ጓዳ ሊፈትሽ በአባ ባህርይና በብርብር ያስጀመረው? በል በል ያሰኘኛል።
የብርብር ማርያም ገዳም የሚገኘው፣ ጋሞ፤ በደቡብ ስምጥ ሸለቆ (Southern Rift Valley) ተራራ ምእራብ አገጩ ላይ ነው። ወደ ምስራቅ፤ ወደ ፀሐይ መውጫ ሲመለከቱ፤ “ወደ ምስራቅ ተመልከቱ” ይላልና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዳሴ፤ የሲዳማ፤ የጌዴኦ ተራሮች ከአድማስ ባሻገር ፍንትው ብለው ይታያሉ። ወደ ምድር ሲመለከቱ ሸለቆው እምብርት ላይ የተነጠፈው የአባያ ሀይቅ ይታያል። እይታው ማለዳ፤ ጎህ ሲቀድ ከሆነ ደግሞ ሽህ ምላሱን አባያ ላይ የቀሰረው የፀሐይ ጨረር ሀይቁን የውሃ ሳይሆን የቀለማት ሽብርቅ፤ የቀስተ ደመና ሀይቅ ያደርገዋል። የተፈጥሮ ውበት ድምቀት ማምለኪያ ቦታ ይመስላል። እኔን እንዲያ እንዳስብ ያደርገኛል። የዩሱፍ ያሲን መጽሐፍ የሚጀምረው ከዚህ ብርብር ማርያም ነው። ከጨንቻ፤ ከኔ ከተማ፤ የሁለት ሰአት መንገድ ነበርና በልጅነቴ ሄጃለሁ። ዝርዝሩ የደመቀው ሌላ ተመሳሳይ ተራራ ላይ ቆሜ ካየሁት ነው። መልአክም ይምራው ምናቡ፣ አርቆ ለማየት ምቹ፤ የሰጠ፤ የተመቻቸ ከብርብር የተሻለ ቦታ ያለ አይመስለኝም። ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱምነቴ እንደተጠበቀ ሆኖ!
የኦርቶዶክስ አማኞች እምነታቸውንም ነፍሳቸውንም ለማዳን ከጋሞ የተሻለ ቦታ ሊኖሩም፤ ሊያገኙም የሚቻላቸው አይመስለኝም። የብርብር ማርያም ብቸኛዋ አልነበረችም። የዶርዜ ጊዮርጊስ፤ የዶይና ኪዳነምህረት፤ የኤሌ ገብርኤል፤ የቤሌ ኪዳነምህረት ጥቂቶች ናቸው::
ከላይ ለማሳየት የሞከርኩት የብርብር ገዥ መሬት ምንኛ ካድማስ ባሻገር ለማየት የሰጠ መሆኑን ነው። ጥንት፤ ጥዋት የብርብር ማርያም፤ ብሎም የአባ ባህርይ እዚህ ቦታ መምጣት ሌላ ገጽታ፤ ሌላ አንድምታም ያለው ይመስለኛል። እስቲ እንየው።
ላለፈው ከ400 ዓመታት በላይ ለሆነ ዘመናት የብርብር ማርያም፤ የዶርዜ ጊዮጊስ፤ የኤሌ ገብርኤል፤ የዶይና ኪዳነምህረት፤ የቤሌ ኪዳነምህረት በጋሞ ዴሬ (አገር)፤ አገር ሆነው፤ ደብር ሆነው፤ ተቀድስው ተሰልሰው ኖረዋል። አሁንም አሉ። ያለፈ ታሪክ በቂ ምስክር ነውና ለወደፊቱም ህልዉናቸውን የእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለም ዓለም መቀጠሉን የሚያጠያይቅ ነገር የለም:: ሊኖርም አይችልም! ለምን ቢሉ ታሪክ ምስክር ነው!
እንደ አጋጣሚ ሆኖ፤ በልጅነቴ ዲያቆን ስለነበርኩ እነዚህን አቢያተ ክርስቲያኖች ማወቅ ብቻ ሳይሆን ደጋግሜ ሄጃለሁ። ቀድሸባቸዋለሁም። ከጨንቻ በእግር ጉዞ ከ2-4 ሰዓት ቢሆን ነው። የኤሌው ገብርኤል የአባቴ አገር ስለሆነ ይበልጥ የማውቀው ነው። እምድር ለምድር ተጉዞ፤ ኮሮብታ ሰንጥቆ የሚንደቆደቅ ጠበል ስለ አለው በልጅነቴ ጠበሉ እንደ አሸንዳ ለሰዓታት ሲወርድብኝ እንደነበር አሁንም ትዝታ ነዉ::
ጋሞ በልምድ በሚታወቀው መልኩ ሐይማኖት የለውም። የተደራጀ መጠሪያ፤ ለምሳሌ እንደ ክርስትና፤ እስልምና፤ ሂንዱ የመገናኛ ማእከል እንደ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ለማለት ነው።
ጋሞ በአንድ አምላክ ያመልካል። ያ አንድ አምላክ የግሉም የማህበረሰቡም ነው። ሳሎ ጾሳ ይለዋል። የሠማዩ አምላክ ማለት ነው። ይህ ሳሎ ጾሳ ጾታ የለውም። እንደ አላህ ማለት ነዉ። በግሉ፤ በቤቱ ይህንን የሰማዩን፤ ያባቱን፤ የወንዙን፤ የተራራውን አምላክ ለመቀደስ፣ ለማወደስ የቤቱን ታላቅ መሥዋዕት ያቀርባል። መደበኛው መሥዋዕት ማር ነው። በዴሬዉ (አገሩ) ስም መስዋዕት የሚያቀርበው በየዓመቱ የሚመረጠው ሁዱጋ ወይም ሐላቃ ነው።
ጋሞ ዴሬ የተለያዩ ብሔረሰቦች ያሉበት ከተሞችን ጭምር ለመጀመሪያ የሚጎበኝ የሚገጥመው የጋራ ገጠመኝ አለ። ”ታሳ አሳ ዴሬ አሳ!” ይሏቸዋል። “እኔን! እኔን! የሰው አገር ሰው!” ለማለት ነው። ይህ በኢትዮጵያ ባንዳንድ አካባቢዎች እንደሚታወቀው መጤ የሚል የጥርጣሬ ቃና ወይም አንድምታ የለውም። አገራችንን የማያዉቅ ሰው መጥቷልና እንዴት እናስተናግደው ነው። ሌላ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ባህርይ ያየሁት ሲዳማ ህዝብ፤ ብሔረሰብ ውስጥና  በሶዶ  ጉራጌዎች ዘንድ ነው። ሲዳሞ፤ ለምሳሌ፤ ይርጋለም፤ የተለያየ ስብጥር  ብሔረሰብ የሚኖርበት ከተማ ሰላምታው “ዳኤ፤ ዓኔሬ ቡሼ!” ብሎ እቅፍ ነው። American Hugging type! የሶዶ ጉራጌም “በላሊዴ ይምጣ!” ነው የሚሉት። ”በላየ ላይ ናብኝ!” እንደማለት።
አባ ባህርይ፤ብርብር ማርያም ሌሎችም ታቦታት የመጡት እዚህ፤ እንግዳ መቀበል፤ ማረጋጋት፤ ማስተናገድ የተፈጥሮ ባህርዩ (pshychological makeup of the People) የሆነ ሕዝብ መሀል ነበር። የከተማው ህዝብ፤ የተለያየ ብሔረሰብ  ጥምሩ ይህንን ባህርይ የወረሰው፤ የተጎናጠፈው ከዚህ ህዝብ ነው። አማኞች እነአባ ባህርይ ወደዚያ የተሰደዱት  ዓምላክ  አሳይቷቸው፤ መርቷቸውም ነው ቢሉ አይገርመኝም። የ400 ዓመታት ታሪክ ምስክራቸው ነውና!
ከ400 ዓመታት በኋላ፤ ወይም በዚያ ጉዞ ውስጥ የሆነ፤ የተከናወነ የሚደንቅ ታሪክ አለ። አሜሪካኖች አገራቸውን “Melting Pot” “የሕዝቦች መቅለጫ ሰታቴ (ድስት)” ናት ይላሉ። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ካርተር (ሲአድ ባሬ ኢትዮጵያን ሲወር የጦር መሳሪያ ማእቀብ ያደረጉት)” We become not a melting pot but a beautiful mosaic. Different people, different beliefs, different yearnings, different hopes, different dreams ይላሉ። ያ እንዳለ ይሁን።
የጋሞ ሕዝብ በ”ቆሞ” ይከፋፈላል። ቆሞን ማስረዳት አስቸጋሪ ይመስለኛል። ቆሞ በደረቁ መልክ፤ አይነት ማለት ነው። ”ሔሲ አይ ቆሞ?” የተባለ እንደሆነ “ይሕ ምን አይነት ነው?” ማለት ነው። በዚህኛው አባባል ቆሞ ምናልባት ቤት ማለት እንዳይሆን? “የእገሌ ቤት” እንደማለት። ወደ አስር የሚጠጉ ቆሞዎች ያሉ ይመስሉኛል። እርግጠኛ አይደለሁም። ከነዚህ ቆሞዎች አንዱ አማራ ነው።
ለማረጋገጥ ዶርዜን ይጉብኙ። ከአርባ ምንጭ በ30 ደቂቃ ቦዶ ይደርሳሉ። ቦዶ የዶርዜ ገበያ ነው። የገበያ ለት የደረሱ እንደሁ እሰየው ነው። ያልጠበቁትን ያገኛሉ/ያያሉ። ብቻ ቦዶ እንደደረሱ “ዶርዜ አማራ የት ነው?” ይበሉ። ማንም በጣቱ ያመለክትዎታል። ትንሽ ግር ቢለው አማራ አባባሉ ቅላጼው እኛ አማራ እንደምንለው ሳይሆን አባባሉ ለየት ይላል። ለስለስ ለቀቅ ያለ ነው። ኤሌ ቢሄዱ ይህንን ይጠይቁ። “ኤሌ አማራ የት ነው?” ያሳይዎታል። ታሪክም መስክረው የዶርዜ ጊዮርጊስንም የኤሌ ገብርኤልንም ተሳስልመው ጠበልም ተጠምቀው ይመለሳሉ። የዐይን ምስክር ነኝና እኔን አምኖ መጓዝ ነው። ስደተኛው አማራ በዘመናት አንዱ የጋሞ ቆሞ ሆነ። ሆኖም ለዘለዓለም ኖረ። ይኖራልም። አንዴ፤1967 ዓ.ም ይመስለኛል ወዳጄንና ሕግ ትምህርት ቤት የፈረንሳይኛ አስተማሪየን ሙሴ ዣክ ቢሮን፣ አርባ ምንጭ በአጋጣሚ አገኘሁትና ቤት ይዠው ሄድኩ። ዣክ በጋሞ ባህል መጽሐፍ ጽፏል። “ሳሮ ሶ አሶ!” አለ። እናቴ፤ መቱኬ አጆ ደነገጠች። ”አሴታ ኤሮንታ ኑ ደሬ አሲ ዲዜ!” አለች።
 ”ለካ እኔ የማላውቀው አይነት የኛ አገር ሰው አለና!” እንደ ማለት ነው። ጋሞ የዘር፤ የሀይማኖት ልዩነት አያዉቅም። አያውቅም ሳይሆን ሰው ሁሉ በየቤቱ እሱ የሚያደርገውን ያደርጋል ብሎ የሚያስብ ይመስለኛል። ያንን የታወቀ ነገር አድርጎ ስለወሰደ  ከሌሎች ጋር  ላለው ግንኙነት አሉታም  አወንታም  አያመጣበትም። ክርስቲያን ያልሆነው ጋሞ፤ (ክርስቲያኑ በጣት ይቆጠራልና) “ጋብሬሌ አሾ! ጎርጊሴይ  በይን!” እያለ  ሲምል  መስማት  የተለመደ ነዉ። ”የገብርኤልን ስጋ! ግዮርጊስ ባወቀ!” ማለቱ ነው።
 እንዳልኩት በክርስትና አማኝ ሆኖ ሳይሆን በዚያ አማኙን ማስተናገዱ ነው። ለመቻል፤ ለመቻቻል ከዚህ የላቀ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም። ከተገኘማ እሰየዉ! ነዉ።የዩሱፍ ያሲን መጽሐፍ የታሪክ መጽሐፍ አይደለም። የማሕበራዊ ሳይንስ መጽሐፍም አይደለም። የስነ ልቦና መጽሐፍም አይደለም። ከሁሉም በላይ የፖለቲካ መጽሐፍ አይደለም። ወይም እነዚህን ሁሉና ሌላም ሌላም አለው። የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ተረት፤ ተረት መሰል ታሪክ፤ የባህል፤ የሐይማኖት፤ የጎሳ፤ የብሔር ብሔረሰብ፤ የመንግስት ግኑኙነት፤ ግጭት፤ መፋጀት፤ መስማማት፤ መፋለስ ይዘክራል። ሊዘክር ይሞክራል። ኢትዮጵያ ጥንታዊትና ውስብስብ ሰምና ወርቅ፤ ማለፊያው፤ መጥፎው፤ አስጸያፊው አብሮ የቦካበት፤ የተጋገረበት፤ የተበላበት፤ የተባላበት አገር ስለሆነች  አጥነት ጉልጥምትዋ ውስጥ ገብቶ ለማሳየት መሞከር ቀላል የቤት ሥራ አይደለም። ሆኖም የዩሱፍን አቀራረብ ወድጀዋለሁ። በባለቤትነት፤ በኩራት፤ በፍቅር፤ በልበ ሙሉነት ነው የሚዳስሰው። ይህ ደግሞ ማለትም አንድ አፋር ከዳር አገርነት ይልቅ የመሐል አገርን ሸማ ተላብሶ መናገሩ፤ መጻፉ የበለጠ እንድናዳምጠው የሚገፋፋን ይመስለኛል። ከታሪክ አንፃር ስናየው ከዚህ ወግኖ ይሕንን ለራሱ፤ ለብሔረስቡ ሊያስገኝ ነው የሚል ጣት እንዳንዘረጋ የሚያቅበን ይመስለኛል።
 ለዚያውም ለማስረጃ ሊቃውንቱን ከየአህጉራቱ “ዘከመ ይቤ” ብሎ ጠቅሶ ነው። የአገራችንንም ጸሐፍት ወፈሪሳውያን ሊያሳይ ይሞክራል። እንደኔ እንደኔ የዩሱፍ ያሲን ”አሳሳቢ ማንነት፤ ባንድ ሀገር ልጅነት፤ የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ” ማንበብ ነው። ውስጣችንን የሚቦረቡር፤ ከዚህም ውስጥ ከሚያለያየን ይልቅ የሚያስተቃቅፈን ያመዝናል የሚለውን ለማሳየት ስለሆነ:: ያንን ማየት መቻል ደግሞ ሙሉ ፈቃደኝነትን የሚጠይቅ ይመስለኛል።
በተረፈ ጋሞን፤ አባ ባህርይን፤ ብርብር ማርያምንና ሌሎች ስደተኛ አብያት ክርስቲያናትን ያነሳሁት “ይኸም አለ!” ለማለት ነው። ”ይኸም አለ ለካ!” እንድትሉም ነው።
“ለካ መቻቻል ይቻላል!” እንዲባልም ነው። የወገንተኝነት ጠረን ካለው/ ካያችሁ “አይ የሰው ነገር!” ብሎ ማለፍ ነው። በተረፈ  የነዚህ አብያተ ክርስትያናት  ንዋየ ቅድሳት የሚቀመጠው እዚያው ጋሞዎቹ ቤት ነው። ቄሴ ገበዝ፤ አቃቤ ንዋይ መሆናቸው ነው። የዶርዜው ጊዮርጊስ የሚቀመጠው ሐላቃ ጩባሮ ቤት ነው ሲባል ልጅ ሆኜ የሰማሁ ይመስለኛል። የዳይና ኪዳነ ምኅረት ንዋየ ቅድሳት የሚቀመጥበት ቤት ካንዴም ሁለቴ የበላሁበት የጠጣሁበት ነው።
የጋሞን በር ከፍቶ መቀበል ያጎናጽፋችሁ! ምርቃት ሊሆን ይችላል?
በክፍል ሁለት ያገናኘን
ይነጋል
እናት ፍቅር ሐገር
ጥቁር ሸማ የለበሰ
ለምለም ምድር ተዘርግቷል፣
...................................
ወዳጃችን በኢሜይል የላከልን

Read 4089 times