Monday, 08 December 2014 14:21

ታጣቂዎችን ወደ ሰላም ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ነው ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(25 votes)

በሰላም እጦት ላለፉት ሶስት ወራት ደመወዝ ያልተከፈላቸው የመንግስት ሰራተኞች አሉ

         በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተቀሰቀሱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታትና ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ህይወት ለመመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑን የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት እንደገለጸው፤ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱና የተዳፈኑ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው፡፡ በአፋርና ሶማሌ (ኢሣ) መካከል የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ሲሆን አዳይቱ፣ እንድፎና ገዳማይቱ የተባሉት ቀበሌዎች በአፋር ክልል ሥር እንዲተዳደሩ ተወስኗል፡፡ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግም እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለፀው የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሪፖርት፤ ውሳኔው ተግባራዊ እንዳይሆን ለማደናቀፍ የሚሞክሩ አካላትን ለመቆጣጠር በአካባቢው የፌደራል ፖሊስና የሀገር መከላከያ ኃይሎች እንዲሰፍሩ ተደርጓል፡፡
በእነዚህ ሶስት ከተሞች ከመስከረም ወር ጀምሮ ደሞዝ ያልተከፈላቸውን የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ለመክፈልም መረጃዎችን በማጠናከር ላይ እንደሆነ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡
መንግስት ከቤኒሻንጉል ህዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ቤህነን) ጋር በተፈራረመው ሰነድ መሰረት፤ ሁለተኛ ዙር የቤህነን አመራር አባላትና ታጣቂዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲመለሱ ጥረት እያደረገ ሲሆን ጉዳዩን የሚከታተሉ 6 አባላትን ያቀፈ ቡድን ወደ ሱዳን እንደላከም መረጃው ጠቁሟል፡፡  


Read 6788 times