Monday, 08 December 2014 14:19

የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ተማሪዎች አዲስ አድማስን ጐበኙ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

40 ገደማ የሚሆኑ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች ከትናንት በስቲያ የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን ጐበኙ፡፡
ካዛንቺስ በሚገኘው የአዲስ አድማስ ዝግጅት ክፍል ተማሪዎቹ ለሰዓታት ባደረጉት ቆይታ የዝግጅት ክፍሎቹንና “ዕውቀትና ትጋት የአሰፋ ጎሳዬ መታሰቢያ ቤተ መፃሕፍት”ን የጎበኙ ሲሆን በጋዜጣው የዲዛይን ክፍልም የሌይ አውት አሰራር ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፤ ስለ ጋዜጣው አመሰራረትና የ15 ዓመት ጉዞውን የሚመለከት አጭር ገለፃ ያደረገላቸው ሲሆን ስለጋዜጠኝነት ሙያም ከልምዱ አካፍሏቸዋል፡፡
የጋዜጠኝነት ሙያ ከንድፈ ሃሳብ ይልቅ የተግባር ትምህርትን የበለጠ የሚጠይቅ አንደሆነና፣ መረጃዎችን አግኝቶ፣ ሚዛናዊነታቸውን ጠብቆ ለህብረተሰቡ በማድረስ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማለፍ ብርቱ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ለተማሪዎቹ ያስረዳው ዋና አዘጋጁ፤ የሙያውን ሥነምግባር ጠብቆ፣ ሁልጊዜም ለማወቅና ለመማር ዝግጁ ሆኖ መገኘት የአንድ ጋዜጠኛ ተግባር ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡
በጉብኝቱና በተደረገላቸው ገለፃ መደሰታቸውን የጠቆሙት ተማሪዎቹ፤ ጋዜጣው ሙያዊ ስነ ምግባርን ጠብቆ በመስራት ለዚህ በመድረሱ ከፍተኛ ከበሬታ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመትም የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል 40 ተማሪዎችን ለተመሳሳይ ጉብኝት መላኩ ይታወሳል፡፡  

Read 2090 times