Friday, 06 January 2012 10:55

አዲሱን ታሪፍ ሹፌሮች ተቃውመውታል “ውዥንብር ለመፍጠር ስለሚፈልጉ ነው”

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(0 votes)

“ሹፌሩንም ተሳፋሪውንም ይጐዳል”

የታሪፍ ማስተካከያው ኪሎ ሜትርን ያገናዘበ አይደለም፡፡ መንገዱ በትራፊክ ባይጨናነቅም 6 ኪሎ ሜትር ነው በሊትር የሚነዱት፡፡ በ2.80 ሲሠላ ሰባት ኪሎ ሜትር ማለት አያዋጣም፡፡ ይሄ ሹፌሩን ይጐዳል፡፡ ተሳፋሪውን በተመለከተ ደግሞ ቀድሞ 1.40 የነበረው 2.80 ገብቷል፡፡ እነዚህን ሰዎች ትንሸ ኪሎ ሜትር እርቀን ነው የምናገኛቸው፡፡ በትንሽ ኪሎ ሜትር ርቀት ደግሞ እጥፍ ይከፍላሉ፡፡ አንድ ታክሲ በደርሶ መልስ 14 ኪሎ ሜትር ይሄዳል፡፡ ቤንዚን በሊትር 20 ብር ነው፡፡ ለ14 ኪሎ ሜትር 3 ሊትር ይፈጃል፡፡

የሚገኘው 65 ብር ነው፡፡ ትርፉ ምንድነው? ትንሽም ቢሆን ጥቅም የምናገኘው በዜሮ እየነዳን ነው፡፡ ያለጥቅም የትኛው እረዳት ነው ጉሮሮው የሚደርቀው? ይሄ አሰራር በማቆራረጥ እንድንጭን ያደርገናል፡፡ እኔ ለምሳሌ አቆራርጣለሁ፤ ያለአግባብ እንደማስከፍል አውቃለሁ፤ ግን መንግሥት ሹፌሩና ህብረተሰቡ እንዲቀራረብ አላደረገም፡፡ ትርፍ ለመጫንም የምንገደደው ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቱም ረጅም መንገድ ስንሄድ ወጪ ወራጅ የለም፤ አንድ ቦታ ሄደን የተሳፈሩት ከወረዱ ታክሲው ባዶ ነው የሚሄደው፤ ግን ወጪ ወራጅ ቢኖር ትርፍ ሳይጭኑ መሄድም ያዋጣል፡፡ አንዳንዴ ለምነውን ጭነናቸው የሚያስቀጡን ሰዎች አሉ፡፡ ትራፊኩም የሚሰማው ተሳፋሪውን ብቻ ነው፡፡ አጭር መንገድ 2 ብር ከ80 ሳንቲም እየሄዱ፣ ረጅም መንገድ በዚሁ ሂሳብ ይሁን ሲባል አያዋጣም፡፡ ሲጀመር የቀጠና መኖር እራሱ ህዝቡን አጉላልቶታል፡፡ እኛ ቀጠናችንን ጠብቀን ከመነሻ ስንወጣ መሀል ያሉትን ሳንጭን እንመጣለን፡፡ መድረሻችን ላይ ግን ሰው አጥተን መኪና ከመብዛቱ የተነሳ ማቆምያ አጥተን እንሽከረከራለን፤ እናም የታክሲ እጥረት አለ ይባላል፡፡

 

መንግሥት ተጠቃሚውን ብቻ ሳይሆን እኛንም መስማት አለበት፤ እኛ ሁሌ ሌባና አጭበርባሪ ናቸው ነው የምንባለው፡፡

ጌታሁን ካሳሁን

(ከቦሌ ድልድይ በ22 ካሳንቺዝ ሀናን)

“ታሪፉ የሹፌር እዳ ነው”

በፊት ከቦሌ ሜክሲኮ 3 ብር ከ90 ሳንቲም ነበር የምናስከፍለው፡፡ አሁን 2 ብር ከ80 ሆኗል፡፡ ይሄ ከህዝቡ ጋር እያጨቃጨቀ ያለ ነገር ነው፡፡ ከቦሌ ደንበል 2 ብር ከ80 ሆኖ ሜክሲኮም አንድ አይነት ዋጋ መሆኑ ከዛ በኋላ በነፃ ይሂዱ እንደማለት ነው፡፡ ታሪፉ የሹፌር እዳ ነው የሚሆነው፤ ባለቤት ገቢውን ያገኛል፤ እኛ ግን ምሳና ቁርስ አንድ ላይ እንበላለን፡፡ በፊት አንድ ሺም ብር ልናስገባ እንችላለን፤ አሁን ግን ግማሹም በመከራ ነው፡፡ አንድ ሊትር ቤንዚን ሰባት ኪሎ ሜትር ተብሎ ነው ዋጋው የወጣው፡፡ ሆኖም ያን ያህል አይወስድም፡፡ ከአምስት ኪሎ ሜትር አያልፍም፡፡ ታፔላና ዋጋ ማስተካከያ ከሚሉ ታክሲውን እያስገደዱ ረጅም መንገድም ቢሆን ጫን ቢሉት ይሻላል፡፡

አበጋዝ ሀይሌ

(ከቦሌ ሜክሲኮ)

“ከታክሲዎች ጋር ያጣላናል”

ታክሲዎች ሲማረሩ ለእኛም ስራ ጥሩ አይሆንም፡፡ የታክሲዎች አንድ ቦታ መቆየት የእኛን ስራ ያቀዘቅዛል፡፡ አሁን ቦሌ ድልድይ ሠባ ተራ አስከባሪ ሆነናል፡፡ በፊት በቀን 100 ብር ሊገኝ ይችላል፡፡ አሁን በወር 600 ብር ተብሏል፡፡ በታሪፍ መውጣት የተነሳ አቆራርጠው የሚጭኑ ታክሲዎችን ለማስገደድ ስንል ልንጣላ እንችላለን፡፡

ህሩይ ባህሩ

(ቦሌ ድልድይ - ታክሲ ተራ አስከባሪ)

“ነዳጅ የሰራነውን ሁሉ ይወስደዋል”

ሁለት ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር ሳይሞላ እየተሸጋሸገ ዋጋ የወጣባቸው ታሪፎች አሉ፡፡ ተሳፋሪው የሚጐዳበትም ሁኔታ ተፈጥሮአል፡፡ በፊት የነበረው የታሪፍ ልዩነት የሃያ እና የሰላሳ ሳንቲም ነበር፡፡ ህብረተሰቡም ልዩነቱን የዚህን ያህል አያውቀውም ነበር፤ አሁን ግን ኪሎ ሜትር ተብሎ ይሸጋሸግ የሚሉት ነገር አለ፡፡ ያችን መንገድ የምንሄደው በነዳጅ ነው፡፡ አንዱ ተሳፋሪ ግማሽ መንገድ ሄዶ ቢወርድ ሌላ ሰው መጫን አትችሉም ይባላል፡፡ በወረደው ሰው ፋንታ ካልጫንን ምን ማድረግ ነው ያለብን? ታሪፍ መጨመር የሌለበት ቦታ ተጨምሯል፤ መቀነስ የሌለበት ደግሞ ተቀንሷል፡፡ ባለፈው የታክሲ ባለንብረቶች ተሰብስበው በጠየቁት መሰረት፣ አስርና አስራ አምስት ሳንቲም ለመለዋወጫ ብለው አስጨምረው ነበር፡፡ ባለቤቶች በፊት 250 ብር የነበረ ገቢያቸው አሁን 300 ብር ሆኗል፡፡ ያንን አድርገን ትርፍ ገቢ ማስገባት አንችልም፡፡ ቀደም ሲል የወጣውን ኪሎ ሜትር አገናዝቦ ቢሰራ ነው የሚሻለው፡፡ ማታ ነዳጅ ስንቀዳ የሰራነውን ሁሉ ይወስደዋል፡፡ በትንሹ በቀን 700 ብር መስራት ይጠበቅብናል፡፡

እሸቱ በፍቃዱ

(ከፒያሳ በ22 ካዛንቺስ ቦሌ ድልድይ)

“እንደፈለጉ መጫን የለም”

አዲሱ ታሪፍ ብቻ ሳይሆን የበፊቱ ታሪፍም በጣም ጐድቶናል፤ ምክንያቱም ዳገት ነው፤ በዚያ ላይ ቀጥታ ነው የምንጭነው፡፡ ማቆምያ ቦታ ከሌለ ትራፊክ ዓሊስ ውጡ ይለናል፡፡ ስለዚህ እንደፈለጉ ተዘዋውሮ ለመጫን አይቻልም፡፡ የቀጠና ስምሪት የሚባል አለ፡፡ ከመንገዱ ርቀት አንፃር የወጣው ታሪፍ ከባድ ነው፡፡ መኪናው የሚሄደው በነዳጅ ነው፤ ነዳጅ ደግሞ ገዝተን ነው፡፡

ሹፌር አዲሱ ገረመው

(ከቦሌ ድልድይ 4ኪሎ ሚኒሊክ ት/ቤት)

“ከፈለጋችሁ በባስ ሂዱ እንላለን”

በፊት በአራት ብር ስንጭን ከተሳፋሪው ጋር ሰላም ነበር፡፡ ከቴሌ ካዛንቺስ 2 ብር ከ80 ሆኖ፣ ጣና ገበያም 2 ብር ከ80 መሆኑ የሌለ ታሪፍ ነው፡፡ “አንጭንም ከፈለጋችሁ በባስ ሂዱ” እንላለን፡፡ በዚህ የተነሳ ከተሳፋሪ ጋር እየተጋጨን ሰዎች እየተጣሉን ነው፡፡ ይሄንን የሰማ ሰው እራሱ ስለሚደነግጥ አያዋጣም ብሎ አራት ብር ይከፍለናል፡፡ ስለዚህ የተስማሙትን ብቻ እንጭናለን፤ በተለይ ውይይት ለምንነዳ ሹፌሮች ከባድ ነው፡፡

ሹፌር አብይ ሸምሱ

(ከቴሌ መድሃኒአለም በካዛንቺስ ጣና ገበያ)

 

“ታሪፍ ካወጡ መቆጣጠር…”

ታክሲ ስጠብቅ ይኸው 30 ደቂቃ ሆኖኛል፡፡ መጀመርያ ታሪፍ አለማውጣት አለያም መቆጣጠር፡፡ ለአጭር መንገድ ይጨምራሉ፤ ለረጅም መንገድ ይቀንሳሉ፡፡ ይሄ አግባብ ባለው ሁኔታ ለመስተናገድ አላስቻለንም፡፡ ከምንሄድበት እንስተጓጐላለን፡፡ መንግሥት አንድ ነገር በፍጥነት ማድረግ አለበት፡፡

ወ/ሮ ሶፊያ አሸናፊ

(ተሳፋሪ)

“ታክሲዎች ውዥንብር ለመፍጠር ይፈልጋሉ”

ህዝቡ ታፔላ አይቶ ነው የሚሳፈረው፤ ታክሲዎች መቆራረጥ አይችሉም፤ እነሱ ውዥንብር ለመፍጠር ነው የሚፈልጉት፡፡ የህብረተሰቡን መብት ማክበር አለባቸው፡፡ የ5 ኪሎ ሜትር ጉዞ ላይ 2ብር ከ80 እናስከፍል እያሉ ነው፡፡ ታሪፍ ሲወጣ አማካኝ ነው የሚወጣው፤ ስለዚህ የ7ቱ ወደ 5 ሲመጣ 2.5 ታሪፍ እየቀነሠ ይመጣና 5 ኪሎ ሜትር ላይ እነሱ የሚያገኙት 1 ብር ከ90 ይሆናል፡፡ የ1 ብር 40 ደግሞ ወደ ዘጠና እና ሰማንያ ሳንቲም ዝቅ ይላል፡፡ ይሔንን ስሌት ነው የሚፈልጉት፡፡ ስታንዳርዱን ያወጣው የፌደራል መንገድ ትራንስፖርት ነው፡፡ የእኛ አገር የታክሲ ጉልበት ካልሆነ በቀር በአንድ ሊትር ቤንዚን ትንሹ ሦስት ኪሎ ሜትር ትልቁ ሰባት ኪሎ ሜትር ይሄዳል፡፡ በእርግጥ የመኪናዎች አይነትና አቅም ይወስነዋል፡፡ አሮጌ ከሆነ 2.5 ኪሎ ሜትር ላይሄድ ይችላል፡፡ እነዚህ በቀጠና አጭር ቦታ እንዲሰሩ ይደረጋል እንጂ ዝም ብሎ የሚሰራ አይደለም፡፡

አቶ ከተማ ሀይሌ

(የአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት የቀጠና ስምሪት ቡድን መሪ)

 

 

Read 2934 times Last modified on Friday, 06 January 2012 10:58