Saturday, 29 November 2014 11:26

አዲስ የተዘጋጀው የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ችግሩን ይፈታ ይሆን?

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(16 votes)
  • የዜጎችን መብት፣ ክብርና ደህንነት የሚያስከብር ህገ - ወጥ ደላሎችን የሚያስቀር ነው        
  • 8ኛ ክፍል ያልጨረሰና የሙያ ፈተና (CoC) ያላለፈ አይሄድም.                
  • ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ክፍተቶች አሉት ፤ ለሕገ -ወጥነት በር ይከፍታል..

              
       ለሥራ ወደ ተለያዩ የአረብ አገራት የሄዱ ዜጎች (አብዛኞቹ ወጣት ሴቶች) ከፎቅ መወርወር፣ አካል መጉደል፣ በሽተኛ መሆን፣ ሞት፣ የሰሩበትን ደሞዝና ያፈሩትን ንብረት ሳይዙ ሙልጫቸውን መባረር፣ …. ብዙዎችን ያስቆጣ ድርጊት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡
በተለይ ሳዑዲ አረቢያ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን የውጭ አገር ዜጎች (በተለይ ኢትዮጵያውያን) በ6 ወር ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ካላወጡ ከአገሬ አባራርላሁ ስትል፣ እዚያ ከነበሩት በስተቀር እውነት ይሆናል ብሎ ነገሬ ያለውና ስጋት የገባው ብዙ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ቀነ ገደቡ አልቆ አትዮጵያውያን ከየነበሩበት እየተለቃቀሙ ክብራቸው ተዋርዶ፣ ሰው መሆናቸው ተክዶ በኢ-ሰብአዊነት ተንቆ ሲደበደቡ፣ ሲሞቱ፣ ሲታሰሩ፣ ሲሰቃዩ፣ … የብዙዎችን ትኩረት ስቦ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡
መንግሥትም፣ የታሰሩ ዜጎችን ወደ አገር ከመለሰ በኋላ፣ የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት ህገ ወጥ ደላሎች መሆናቸውን ደርሼበታለሁ፤ አሁን ያለው የውጭ አገር የስራ ስምሪት አዋጅ ለህገ ወጥ ደላሎች በር የሚከፍት ስለሆነ በ6 ወር ውስጥ አሻሽዬ እስከማቀርብ የውጭ አገር ጉዞ ተሰርዟል በማለት አወጀ፡፡
በ6 ወር ተጠናቅቆ ይቀርባል የተባለው አዋጅ ዓመትም አልፎት አልተጠናቀቀም፡፡ ኤጀንሲዎች ቢሯቸውን ቢዘጉም፣ አሁንም ድረስ የውጭ አገር ጉዞ ክልክል ቢሆንም፣ ከውጭ አገር ተባርረው የመጡና በፊቱንም ወደ አረብ አገራት ለመሄድ አኮብኩበው የነበሩ ዜጎች፣ በህገወጥ መንገድ በድንበርም ሆነ በቦሌ ወደ አረብ አገራት እየሄዱ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ሪፖርት ባለፉት 6 ወራት ከ40 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውን በጦርነት እየታመሰች ወዳለችው የመን መሰደዳቸውን አመልክቷል፡፡
አሁን መንግስት የኢትዮጵያ የውጭ አገር የስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ ጨርሷል፡፡ ስለዚህ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት በአዳማ ከተማ፣ ከየክልሉና ከሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ለሶስት ቀን ውይይት አካሂዷል፡፡
አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ማለት ይቻላል አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በአፈጻጸም ረገድ ተግባራዊነታቸው የሚያጠራጥሩ ጥቂት አንቀፆች ቢኖሩትም የሰራተኞችን መብት፣ ደህንነትና ክብር ከማስጠበቅ አኳያ፣ ከበፊቱ አዋጅ ጋር ሲነፃፀር በጣም የተሻለና ጠበቅ ያለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ተሳታፊዎች ያልተዋጡላቸው አንቀፆችም አሉ፡፡ ኤጀንሲዎች በውጭ አገር ቢሮ መክፈት አለባቸው፣ ወደ ውጭ ለስራ የሚልኳቸው ሰራተኞች 8ኛ ክፍል ያጠናቀቁና የሙያ ምዘና ፈተና (CoC) ወስደው ያለፉ መሆን አለባቸው፣ ኤጀንሲዎች ሰራተኛ ወደሚልኩባቸው አገሮች መግባትና መውጣት አለባቸው፣ … የሚሉት ተፈፃሚነታቸው አጠራጥሯል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በአምስት ቡድን ተከፍለው ሊቀመንበርና ጸሐፊ መርጠው በረቂቅ አዋጁ ላይ አንቀጽ በአንቀጽ ተወያይተዋል፡፡ በመጨረሻም በየአንቀጹ ላይ በስፋት ከተወያዩ በኋላ ይህ አንቀጽ ለምን ገባ? መስተካከል አለበት፣ አሻሚ ነው፣ ግልጽ አይደለም፣ እንዲህ ዓይነት ዓረፍተ ነገር ወይም ቃል ካልተጨመረበት ለህገ ወጥ አሰራር በር ይከፍታል፣ ይህ አንቀጽ ቢወጣ ይሻላል፣ … በማለት የተወያዩባቸውን ነጥቦች ለመድረኩ አቅርበዋል፡፡ አዘጋጁ ክፍልም የተሰጡትን አስተያየቶች አዳምጦ፣ ከቀረቡት ነጥቦች ከ70-80 በመቶ ለረቂቅ አዋጁ መሻሻል ገንቢ በመሆናቸውና፣ አንዳንድ ነጥቦች አዘጋጅ ኮሚቴው ያላያቸው ስለሆኑ እንደሚቀበላቸው፣ አንዳንዶቹ ማብራሪያ የሚሹ ሌሎቹ ደግሞ ጥያቄዎች መሆናቸውን ጠቅሶ ባለድርሻ አካላቱ ላደረጉት የነቃ ተሳትፎ ከልብ አመስግኗል፡፡
በውጭ አገር የስራ ስምሪት አገልግሎት ሰጪ ማህበር አመራሮች የውይይቱ ታዳሚ ብቻ ሳይሆኑ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ረቂቁን እንዴት አያችሁት? አልኳቸው፡፡ አቶ መዝገቡ አሰፋ የማህበሩ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ስለረቂቁ ያላቸውን አስተያየት እንዲህ ገልጸዋል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ ከበፊቱ 632/2001 ጋር ሲነፃፀር የራሱ መልካም ጎኖች አሉት ያሉት አቶ መዝገቡ፣ ኤጀንሲዎች፣ መንግስት ለመንግስት ተነጋግረው የሁለትዮሽ ስምምነት ወዳላደረጉት አገር ኤጀንሲዎች ሰራተኛ እንዳይልኩ መከልከሉ እኛም የምንፈልገው ስለሆነ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የዜጎችን  መብት፣ ደህንነትና ክብር ስለሚያስጠብቅ በጣም ጥሩ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው የዚህ ረቂቅ አዋጅ መልካም ጎን ነው ያሉት ቀደም ባለው ጊዜ ሰራተኞች ወደ ውጭ አገራት ሲላኩ፣ ምንም ወጪ ስለማያወጡ አንዳንድ ሰራተኞች ለምን ሄጄ አይቼ አልመጣም? በማለት ይሄዱና አሰሪያቸውና አገሩ ከተስማማቸው ይቆያሉ፤ ካልተስማማቸው በወርና በሁለት ወር ጥለው ይመለሳሉ፡፡ ብዙ ወጪ አውጥተን ብንልካቸውም ሰራተኛዋ ስለተመለሰች፣ አሰሪው ምንም ስለማይከፍለን እንከስራለን፡፡ በዚህ አዋጅ ግን ሰራተኛዋ ምንም ሳትሰራ ብትመለስ እሷን ለመላክ ያወጣነውን ወጪ መጠየቅ እንድንችል በአዋጅ መደንገጉ ለእኛ በጣም ጥሩ ነው፤ ሰራተኞችም ኃላፊነት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡ ቀደም ሲል ያልነበረ በተቀባይ አገር ሌበር አታሼ እንዲመደብ መደረጉ ሌላው የአዋጁ ጥሩ ጎን ነው፡፡ የዜጎችን መብት ከማስከበር አኳያ ለእኛም አቅም ይሰጠናል በማለት የአዋጁን መልካም ጎኖች ገልፀዋል፡፡
አዲሱ አዋጅ መልካም ብቻ ሳይሆን መጥፎ ጎኖችም እንዳሉት የጠቀሱት አቶ መዝገቡ፣ ቀደም ሲል በነበረው ህግ፣ በተለያዩ ምክንቶች የታገዱ ኤጀንሲዎች ወይም አባሎቻችን በአዲሱ አዋጅ እንዳይሳተፉ መከልከላቸው ከባድ ቅጣት ነው፡፡ በጥቃቅን ጥፋቶች የታገዱ ስላሉ ጥፋታቸው ነጥሮ ካልወጣ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሌላው ተግባራዊ መሆን አይችልም ያልነው፣ ፈቃድ ስናወጣ ወደ ተቀባይ አገር መግባትና መውጣት የምንችልበት ማረጋገጫ አምጡ መባሉ፣ በእኛ አረዳድ ብዙ የታሰበበት አይመስልም፡፡ በተሰጠው መግለጫ ይኼ ጉዳይ መንግሥት ለመንግሥት በሚያደርጉት ውል ይታቀፋል የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እኛ ካለን ልምድ የሚሆን አይመስለንም፡፡
ሌላው አሳሳቢ ነገር፣ በተቀባይ አገር ሄደን ቢሮ እንድንከፍት የሚጠይቅ አንቀጽ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገር በቀድሞው ሕግ የለም፡፡ ይኼ ህግ የዚያኛውን አገር ህግ እንዴት ነው የሚያየው? ይኼ አዋጅ የሚሰራው አገር ውስጥ እንጂ ድንበር ተሻጋሪ አይደለም፡፡ የሌላ አገር ኤጀንሲ እዚህ ቢሮ ልክፈት ቢል የእኛስ መንግስት ይፈቅዳል ወይ? ይኼ ከዓለም አቀፍ ሕግም ጋር የሚጣጣም አይመስለንም፡፡
በአንቀጽ 36 እንደሰፈረው፣ ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የፍ/ቤትንም ስራ እኛው እንሰራለን እያለ ነው፡፡ እነሱው ጠያቂዎች፣ እነሱው ከሳሾች እነሱው ፈራጆች ሆነው የሚቀርቡበት ሁኔታ መሆን ያለበት አይመስለንም፡፡ የህግ አግባብ ያለው አካልስ እንዴት ነው ይህን ሁሉ ስልጣን የሚያጎናጽፋቸው? በማለት አስረድተዋል፡፡
አቶ መዝገቡ ህግ ስለወጣ ህገ ወጥ አሰራር ይቀራል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ እንዲያውም ይህ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለህገ ወጥ አሰራር በር ይከፍታል ባይ ናቸው፡፡ ከትምህርት ጋር በተያዘ 8ኛ ክፍል ወይም 1ኛ ደረጃ ያላጠናቀቀ ወደ ውጭ አይሄድም የሚለው ለህገ ወጥ አሰራር በር የሚከፍት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ “እኛ ከልምድ እንደምናውቀው ለስራ ወደ ውጭ አገራት የሚሄዱት፣ በአብዛኛው 1ኛ ደረጃ ያላጠናቀቁ ናቸው፡፡ አረብ አገር ሄደው ሁለት ወይም አራት ዓመት ቆይተው የዚያን አገር ባህል፣ ቋንቋ፣ ስራ፣ … ለምደው የተመለሱትን 1ኛ ደረጃ ስላላጠናቀቃችሁ አትሄዱም ቢባሉ እሺ! ይላሉ ወይ? በህጋዊ መንገድ ስለተከለከሉ በህገ ወጥ መንገድ ይሄዳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በህገ ወጥ መንገድ ተባርረው ወደ መጡበት አገር የሚሄዱት አብዛኞቹ ቋንቋና የስራ ልምድ ያላቸው ናቸው፡፡
“ሌሎችም አሉ፡፡  ሾፌር፣ ግንበኛ፣ ቴክኒሻን፣ አናጢ፣ … አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ 1ኛ ደረጃን ሳያጠናቅቁ አቋርጠው ሙያ የቀሰሙ ናቸው፡፡ ሕጉ 1ኛ ደረጃን ያጠናቀቁና የሚሰጠውን የሙያ  ፈተና ያለፉ መሆን አለባቸው ይላል፡፡ እነዚህ ሰዎች የሙያ ፈተናውን አልፈው 1ኛ ደረጃን ስላላጠናቀቁ ያገኙትን የስራ ልምድ መከልከል አለባቸው ወይ? ይሄ ፍትሃዊ አይመስለንም፡፡ እነዚህ ሰዎች የተከለከሉትን ዕድል በህገ ወጥ መንገድ ይሞክራሉ እንጂ ‹አሜን› ብለው የሚቀመጡ አይመስለንም፡፡ በዚህ ዓይነት ይህ ህግ ለህገ ወጦች በር ስለሚከፍት ሊታሰብበት ይገባል” በማለት አሳስበዋል፡፡
ማህበሩ፣ በአዋጁ ውስጥ መካተት አለባቸው ያላቸው ነጥቦችም አሉ፡፡ እነሱም የተቀባይና የላኪ ማኅበራት የሚያደርጉት ውሎች መንግሥት በሚያደርገው የሁለትዮሽ ስምምነት ውስጥ ተቀባይነት እንዲኖረው በህጉ ውስጥ እንዲካተት፣ አነስተኛ የኮሚሽን መጠን እንዲወሰን፣ እኛ ሰራተኞችን የምንልከው ለሁለት ዓመት ነው፡፡ ሁለት ዓመቱን ከጨረሱ በኋላ አሰሪው ከተመቻቸው ይቀጥላሉ፡፡ ይህ አሰራር በዜጎች ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ እንዴት ቢባል ኢንሹራንሳቸው ስላለቀ ጉዳት ቢደርስባቸው መካስ አይችሉም፤ ኮንትራታቸው ስላለቀ እኛም ሆንን መንግስት ወደ አገር እንደተመለሱ ነው የምንቆጥረው፡፡ እዚያ ሆነው ለሚደርስባቸው ጉዳት ወይም አደጋ ተጠያቁ አካል አይኖርም፡፡ ስለዚህ ኮንትራታቸውን ሲጨርሱ በፈቃዳቸው የሚቆዩ ከሆነ በአቅራቢያቸው በሚገኝ ቆንሲላ ጽ/ቤት ወይም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአሰሪያቸው ጋር ቀርበው ቪዛቸውና ኢንሹራንሳቸው እንዲታደስ በህጉ ውስጥ ይካተቱ በማለት መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡
ሚ/ር መ/ቤቱ ጥያቄዎቻቸውን ተቀብሎ በህግ አግባብ ካላቸው አይተው ፈትሸውና ተነጋግረውባቸው በአዋጁ እንደሚያካትት ቢገልጽላቸውም ማኅበሩ ግን እንዳሉት ያደርጋሉ የሚል እምነት የለውም፡፡ ምክንያቱም አሁን የተሻረው አዋጅ ከመጽደቁ በፊት በምክክር መድረክና በተወካዮች ምክር ቤት ውይይት በተደረገበት ወቅት፣ ለህገ ወጥ አሰራር በር የሚከፍቱ አንቀጾችን … ለይተው አቅርበው ነበር፡፡ ሚ/ር መ/ቤቱም ጥቆማቸውን ተቀብሎ እንደሚያርማቸው ቢገልጽም፣ አዋጁ ፀድቆ ሲወጣ ግን አንዳችም ማስተካከያ እንዳልተደረገበት ያስታውሳሉ፡፡ አሁንም፣ በውይይቱ ወቅት ያዩዋቸውን ድክመቶችና በአዋጁ መካተት አለባቸው በማለት ያቀረቧቸውን ነጥቦች ሚ/ር መ/ቤቱ በምስጋና ቢቀበላቸውም ይስተካከላሉ ወይም በአዋጁ ይካተታሉ የሚል ሙሉ እምነት እንደሌላቸው አልሸሸጉም፡፡
አቶ አበበ ኃይሌ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር የሥራ ስምሪት ማስፋፊያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ አቶ አበበ ባለድርሻ አካላቱ ባደረጉት የነቃ ተሳትፎና ውይይት በጣም መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡ አዘጋጁ ክፍል ያላያቸውንና ተወያዮቹ ቢጨመሩ፣ ቢቀነሱ፣ ቢስተካከሉ፣… በማለት ያቀረቧቸውን ነጥቦች በአድናቆት ተቀብለው ጥሩ ስለሆኑ በግብአትነት እንደሚጠቀሙባቸው አስታውቀዋል፡፡ አቶ አበበ በጥያቄ መልክ ለቀረቡት መልስ፣ ግልጽ ላልሆኑ ነጥቦች ደግሞ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በርካታ የቁጥጥርና የስራ አፈጻጸም ግምገማዎች የሚሰሩት በክልል ደረጃ ስለሆነ፣ ይህ አዋጅ የፌዴራልና የክልል ኃላፊነትን በተገቢው መንገድ ለይቶ ማስቀመጥ አለበት የተባለው ትክክል ስለሆነ ተቀብለነዋል ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ ፈቃድ የሚሰጠው ሰው በውጭ አገር ስራና ሰራተኛ የማገናኘት አገልግሎት ለመስጠት ብቻ መሆን አለበት በሚለው አንቀጽ “ብቻ” የሚለው ቃል የገባው ሆን ተብሎ ነው ያሉት አቶ አበበ፣ ይህ አገልግሎት ከሌሎች ሥራዎች ጋር ተቀላቅሎ መሰራት የለበትም ኃላፊነት የሚጠይቅ የዕለት ተዕለት ሥራ ስለሆነ ትኩረትና ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከሌሎች ስራዎች ጋር ተደርቦ መሰራት የለበትም፡፡ ላኪና አስመጪ በሚል የንግድ ፈቃድ ላይ ሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ … ይላል፡፡
 ይህ አሰራር ተገቢነት የለውም፡፡ እኛ አሁን እያወራን ያለው ስለቢዝነስ አይደለም፡፡ ከዚያም በላይ ስለሆነ የሰው ጉዳይ ነው፡፡ እውቀትና ጊዜ የሚጠይቅ ስለሆነ ከሌላ ስራ ጋር የምናስተሳስረው አይደለም፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮም የሚያሳየው ይኼንኑ ነው፡፡ እና ሌላ ስራ አትስሩ አላልንም፡፡ ምርጫው የባለቤቱ ነው፡፡ እኛ ያልነው ስራና ሰራተኛ የማግኘት አገልግሎትን ከሌላ ቢዝነስ ጋር ደርቦ መስራት አይቻልም ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
ካፒታሉ በዛ፣ ኤጀንሲዎችን ጥቂት ግለሰቦች በሞኖፖል እንዲይዙት ያደርጋል የሚለውን ስጋት እናየዋለን፡፡ ለስራ ወደ ውጭ አገር በሚሄዱ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው በደል እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረና እየባሰ ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን ዋስትንና መብት ማስከበሪያም መጨመር ስላለበት ነው፡፡ በኋላ ከፍተኛ ችግር ሲያጋጥም ገንዘብ ከኪስህ አምጣ ብለን ከምናሯሯጥ መጀመሪያውኑ አስበንበት መግባት ስላለብን ነው በማለት አስረድተዋል፡፡
አቶ አበበ ተሳታፊዎቹ ላነሷቸው ሌሎች ጥያቄዎችም ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ ለህገ ወጥ አሰራር በር ይከፍታል አሁንም ክፍተቶች አሉት … በመባል የቀረቡትን ነጥቦች ያብራሩት የመድረኩ መሪና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ዘሪሁን ከበደ ናቸው፡፡
ዶ/ር ዘሪሁን አንድ ኤጀንሲ ዜጎችን ወደ ሚልክበት አገር በነፃ ገብቶ መውጣት የሚችል መሆን አለበት የተባለው ካጋጠመ ልምድ በመነሳት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ሰራተኞን ወደላከበት አገር መግባት የተከለከለ ኤጀንሲ፣ የዜጎችን መብት ደህንነትና ክብር ማስጠበቅ ስለማይችል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
 ቀደም ሲል ፈቃዱ የታገደበት ኤጀንሲ በዚህ አዋጅ  ፈቃድ አይሰጠውም የሚለው በጥቃቅን የአስተዳደር ጉዳዮች ጉድለት የታገደን ኤጀንሲ ሳይሆን አቤቱታ ቀርቦበት (ለምሳሌ ሬሳ አላመጣ ብሎ) የተዘጋ ኤጀንሲ ለዜጎች መብትና ክብር ደንታ ስለሌለው እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄድ ሰው 8ኛ ክፍል ማጠናቀቅ አለበት የተባለው አንብቦ ሊረዳ የሚችልና ልናሰለጥነው የምንችል ዜጋ፣ አርሶ አደር … መሆን ስላለበት፣ ወደፊት 1ኛ ደረጃን ያላጠናቀቀ ዜጋ ይኖራል ብለን ስለማናስብና የእገሌ ልጅ 1ኛ ደረጃ ሳትጨርስ አይደለም ወይ የሄደችው? የሚለውን ህብረተሰብ ለትምህርት ያለውን ግንዛቤ ለመለወጥ ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Read 7314 times