Friday, 06 January 2012 10:21

ኢህአዴግ - የአላዲን ተዓምረኛ ፋኖስ!

Written by  አልአዛር ኬ
Rate this item
(0 votes)

የዲሞክራሲን ናዳ ለማምለጥ ዲሞክራሲን ከእስር መፍታት…

የአቶ በረከት መፅሐፍ የለመድነውን የፕሮፓጋንዳ ፅሁፍ ይመስላል…

የአቶ በረከት ስምኦን የበኩር ስራ የሆነው “የሁለት ምርጫዎች ወግ” መፅሀፍ የኢህአዴግ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ መለስ ዜናዊ ከምርጫ 97 በፊት ለድርጅታቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባቀረቡት ሪፖርት የዘረዘሩትን ከናዳ ለማምለጥ የሚደረግን ሩጫ ሁኔታ እንደዋናና ማዕከላዊ የሀሳብ መሰረትነት ወስዶ በመጠቀም ከ1997 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ፣ ከዚያም በሁዋላ ባሉት ጊዜያቶች ድርጅታቸው ኢህአዴግ ሊጨፈልቀኝ እየመጣብን ነው ያለውን ናዳ ለማምለጥ በእንዴት ያለ ፍጥነት እንደሮጠና የሚመራውን ሀገርና ህዝብም እንዴት አድርጐ እንዳሯሯጠ በሰፊው ዘርዝሮ ያስረዳል፡፡

አሁን መነሳት አለባቸው ካልናቸው ሶስት መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ የመጀመሪያውን እናንሳ፡፡

አቶ በረከት በሁለት አብይ ክፍልና በአስር ምዕራፎች ዘርዝረው በመፅሀፋቸው ባቀረቡት የኢህአዴግ ናዳን የገታ አገራዊ ሩጫ ዝክረ ታሪክ ምን ምን ጉዳዮችን አረጋገጠልን? ይህ ጥያቄ በእርግጥም አብይ ጥያቄ ነው፡፡ ለምን ቢባል አቶ በረከትም ሆኑ ድርጅታቸው ኢህአዴግ በመፅሀፉ አማካኝነት ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት ዋና መልእክት ያለው እዚህ ጉዳይ ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡በ”ሁለት ምርጫዎች ወግ” አቶ በረከትም ሆኑ በእርሳቸው አማካኝነትም ኢህአዴግ በግልፅ ያረጋገጠልንና ሊነግረን የፈለገው ዋነኛ ጉዳይ፣ ኢህአዴግ ይህችን ሀገርና ህዝቧን እኔና እኔ ብቻ ካልመራሁዋት የሁለተኛውን ቀን የማለዳ ጀንበር ሳታይ ትፈራርሳለች በሚለውና ሁለት አስርት አመታትን ካስቆጠረው አቋሙ ዛሬም ድረስ በግትርነትና በአግላይነት እንደፀና መሆኑን ነው፡፡ ይህ ጉዳይ የሀገሪቱና የህዝቧ የእለት ተእለት ህይወት ላይ ቀጥተኛ ተፅእኖ ያለው ዋናና መሰረታዊ ጉዳይ ነው ያልነው በሌላ ሳይሆን ከሁለቱ ምርጫዎች በፊትም ሆነ በሁዋላ ባሉት ጊዜያቶች ሀገሪቱና ህዝቧ ያጋጠሟቸውና የተጋፈጧቸው የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ችግሮች በዋናነት የመነጩት ከዚህ የኢህአዴግ ግትርና አግላይ አቋም ውስጥ ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡

ሸሚዛችንን ስንለብስ የመጀመሪያውን አዝራር የምንቆልፍበት ሁኔታ የሸሚዛችንን ጠቅላላ አለባበስ ሁኔታ ይወስነዋል፡፡ አዝራሮቹን ከተገቢው ቦታቸው አዛንፈን ከቆለፍናቸው ሸሚዛችንን በትክክል ለመልበስ እንደማያስችለን መናገር የአንባቢን ንቃተ ህሊና በድፍረት እንደመሞገት ይቆጠራል፡፡ ልክ እንደዚሁ ሁሉ አንድ መሪ የፖለቲካ ድርጅት ስለ አገርና ህዝብ አመራር ያለው አስተሳሰብና አቅም የአመራር ዘይቤውንና ተግባራዊ አሰራሩን በዋናነት ይወስነዋል፡፡ በርካታ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ፍላጐትና አቋሞች የሚደግፉና የሚያራምዱ በርካታ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ባሉበትና ይህንን ተግባር በህጋዊ መንገድ ለማከናወን ማንም ጉልበት አለኝ ባይ የማይሰጥና የማይነሳቸው የተፈጥሮ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸው ህገመንግስታዊ ጠበቃና ማረጋገጫ ባለባት ሀገር ውስጥ ሀገሪቱንና ህዝቦቿን እኔና እኔ ብቻ ካልመራሁዋቸው እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ ይጠፋሉ ብሎ በማሰብ አቋም መያዝና የያዙትንም የመንግስት ስልጣን በዚህ አቋም ላይ በመመስረት መጠቀም መቻል የሸሚዙን አዝራር አዛንፎ እንደመቆለፍ አይነት ነው፡፡

አንዴ መሰረቱ ከተዛነፈ ደግሞ ስለሌሎቹ ጉዳዮች ትክክለኝነት ማውራት ጨርሶ አይቻልም፡፡ በእንዲህ አይነት የተዛነፈ አቋም ህዝብን የሚያስተዳድር መንግስት ስለግለሰብም ሆነ የቡድን መሰረታዊ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጉዳይ ሊያነሳ ጨርሶ አይቻለውም፡፡ ለምን ቢሉ የዜጐቹን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ንዶ የረገጠው ገና ከጅምሩ ከእኔ በቀር ሌሎች ከመሯት ሀገሪቱ ትፈራርሳለች የሚለውን አይረቤና አደገኛ የሆነ የተሳሳተ አቋም ሲይዝ ነው፡፡የችግሮቹ ሁሉ አናትና ዋነኛ መፈልፈያቸውም ይህ አቋም ነው የሚባለውም የመንግስትነት ስልጣኑን በዋነኛነት የሚጠቀምበት የያዘውን ይህን የተሳሳተና አደገኛ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አቋም ለመጠበቅና በተግባር ለማዋል ብቻ ስለሚሆን ነው፡፡ከምስረታው እስከአሁን ድረስ አቶ በረከት በአንጋፋ የአመራር አባልነት የሚመሩት ኢህአዴግ ይህችን ታላቅ ሀገርና ህዝቦቿን ኢህአዴግና ኢህአዴግ ብቻ ካልመራት በብርሀን ፍጥነት እነደ ሀገር መቆም እንደማትችልና እንደምትፈራርስ ዘመን የጠገበና መቼውንም ጊዜ ቢሆን የማይናወጥ አቋም እንዳላቸው በፃፉት በዚህ መፅሀፋቸው ቸል በማለት እንዳንዘነጋው ደግመው ደጋግመው አስገንዝበውናል፡፡ ኢህአዴግ የሸሚዙን አዝራር ከመጀመሪያው አለ አግባብ አዛንፎ በመቆለፍ ለመልበስ የሞከረውና የአለባበሱ ነገር አለሙ ሁሉ አይሆኑ ሆኖ የተበላሸውም እዚህ ላይ ነው፡፡ኢህአዴግ በስልጣን በቆየባቸው ባለፉት ሃያ አመታት የዜጐችን የግልም ሆነ የቡድን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት አያያዝና ጠበቃ በወጉ ያልቻለበት ለዜጐች በህገ መንግስቱ አማካኝነት የተደነገጉትን መብቶችና ጥበቃዎች አክብሮ የማክበር ግዴታ የሌሎች እንጂ የእሱም ጭምር መሆኑን መረዳት ሁሌም ስለሚደናገርበት ይመስለኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ነው የፖለቲካ ምህዳሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማስፋትና የሁሉንም ወገን እኩል ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ይልቅ ይህቺን ሀገር ያጠፉዋታል ብሎ አለአግባብ የረገማቸውን ተቃዋሚዎች የእግር መትከያ ቅንጣት ታህል ቦታ እንዳያገኙ አስቦና አቅዶ እለት በእለት የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳውን ለማጥበብና የጨዋታውን ህግ ለማዛነፍ ሌት እንቅልፍ ቀን እረፍት አጥቶ መከራውን የሚበላው፡፡ ይህ ደግሞ የሆነው የአርባ ቀን እድሉ ሆኖ ወይም ደግሞ የፖለቲካና የስልጣን አማልእክቶች ረግመውትና ድግምት አስቋጥረውበት ሳይሆን ለዘመናት በተጣባው እኔና እኔ ብቻ እንጂ ሌሎቹ ይህችን ሀገር ያጠፉዋታል በሚል ክፉ ዛሩ የተነሳ ነው፡፡ተቃዋሚዎች ይህችን ሀገር ያጠፏታል የሚለው ይህ የኢህአዴግ ፀረ ዲሞክራሲያዊ አቋም በርካታ ችግሮችን እንዲፈጥር ብቻ ሳይሆን በሀገራችን የዲሞክራሲ ግንባታ ትግል ውስጥ ሌሎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ህዝቦችና የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ባለፉት ዘመናትም ሆነ አሁን እየተጫወቱት ያለውን ሚና እውቅና በመንፈግ እንዲክድ አድርጐታል፡፡ከአቶ በረከት መፅሀፍ መረዳት እንደምንችለው ኢህአዴግ ደርግን ከመጣል ጀምሮ አሁን እስካለንበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ደረጃ ድረስ የተካሄደውን ትግል አውራ መሪነት በመውሰድ፣ የድሉንም ቅድስናና ሙገሳን ለራሱ ብቻ በማድረግ ለሌሎቹ ሚናና ጥረት ተራ እውቅናን እንኳ ነፍጓል፡፡ እኔ ያመጣሁት ዲሞክራሲ፣ እኔ የፈጠርኩት ባለሀብትና ሚሊዬነር አርሶ አደር ወዘተ… በማለት ራሱን የሁሉም ነገር ምንጭ የአላዲን ተአምረኛ ፋኖስ አድርጐአቅርቧል፡፡ተቃዋሚዎች ከያዟት ይህችን ሀገር ያጠፏታል የሚለው የተሳሳተ አቋሙ፣ የዚህች ሀገር ሁሉም ቅዱስ ነገሮች ባለቤት እኔ ብቻ ነኝ ከሚለው ግብዝ አስተሳሰብ ጋር ተዳምሮ የመንግስት ስልጣንን እንደ የድካም ውለታ ካሳና መለኮታዊ ተቀብኦ አድርጐ እንዲቆጥር አድርጐታል፡፡ኢህአዴግ በስልጣን ላይ ከቆየባቸው ሃያ አመታት ውስጥ ባለፉት ስምንት አመታት ሀገሪቱ በኢኮኖሚና በተለይ ደግሞ በመሰረተ ልማት ግንባታው ዘርፍ ላስመዘገበችው ድንቅ የእድገት እርምጃ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ጨርሶ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ ውጤት የሌሎችን በተለይ ደግሞ የህዝቡን ውለታ ቸል በማለት ከእኔ ወዲያ ማን አለ በሚል መታበይ ሊፈጥርበት ባልተገባ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ባለፉት ስምንት አመታት የሀገሪቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ቀያሽ መሀንዲስ በመሆን ኢትዮጵያን ላለፉት በርካታ መቶ አመታት ከተኛችበት እንቅልፍ ቀስቅሻታለሁ እያለ እንደሚሸልለው ሁሉ ቀሪዎቹን አስራ ሁለት አመታት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚውና በማህበራዊው መስክ በእውር ድንብርና በአቦ ሰጡኝ የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ህዝቡን መሞከሪያ (ጊኒፒግ) በማድረግ የራሱን ስህተት ኪሳራውን እንዲያወራርድ ሲያደርገው እንደኖረም ሊዘነጋው አይገባም፡፡ የመንግስታቸውን ቅጥ ያጣ የፖሊሲ የመመሪያና ደንብ ኪሳራ ያለ አበሳቸው እየከፈሉ ለአስራ ሁለት አመታት የዘለቁ እንደ ኢትዮጵያውያን ያሉ ህዝቦችን የዲሞክራሲ ስርአትን በሚከተሉ ሀገራት የትም ቢሆን ፈለጐ ማግኘት ጨርሶ አይቻልም፡፡ በእንደዚህ አይነት አመራር ሁለት ተከታታይ ብሔራዊ ምርጫዎችን ማሸነፍ የሚችል መንግስትም በዲሞክራሲያዊ ሀገራት ውስጥ ጨርሶ አይገኝም፡፡ ኢህአዴግ በእንደዚህ አይነት አመራርና የምርጫ አፈፃፀም የመጀመሪያዎቹን ሁለት ምርጫዎች ማሸነፍ መቻሉ፣ ህዝቡ ከእኔ በቀር ሌሎችን የሚሰማበት ጆሮም ሆነ የሚያይበት አይን የለውም ብሎ እንዲያስብ፣ ስለዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊ አሰራር ያለውን የተንሸዋረረ አመለካከት በጊዜ እንዳያስተካክልና የህዝቡን ስሜትና ድምፅ በትክክለኛ ቀለማቸው ሳይሆን በራሱ ኢህአዴጋዊ አተያይ ብቻ እየመዘነ እንዲቀጥል ዋና ሰበብ ሆኖታል፡፡ ሊጨፈልቀኝ መጣብኝ ያለው ናዳ ቁልቁለቱን መውረድ መጀመሩን ከረፈደ የተረዳውና የነፍሴ አውጭኝ ሩጫ የጀመረውም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡“የሁለት ምርጫዎች ወግ” እቅጩን በግልፅ ባያብራራልንም ኢህአዴግን በቁሙ ሊቀብረው መጣ የተባለው ናዳ የተፈጠረው በተቃዋሚዎች የስልጣን ጥመኛነት ወይም ደግሞ በእነሱ “ዱአ” እና እርግማን አለያም ኢህአዴግ ወደን እስክንጠላ ድረስ እንደሚነግረን በሀገሪቱ ሞልቶ በተረፈው የዲሞክራሲ መብት ጥበቃና ዲሞክራሲያዊ አሰራር ሳቢያ ሳይሆን በተቃራኒው በእነዚህ የዲሞክራሲ መብት ጥበቃና የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ነው፡፡ ናዳውና የሚያስከትለው ጉዳት ከዲሞክራሲ በሽታዎች አንዱ ነው፡፡ አሜሪካዊው ፖለቲከኛ አልስሚዝ እንዳለው፤ የዲሞክራሲ በሽታዎች የማያዳግም ፈውስ የሚያገኙት በሌላ ሳይሆን በበለጠ ዲሞክራሲ ነው፡፡ከአቶ በረከት መፅሀፍ መረዳት የቻልነው፤ የዚህ ናዳ አፈጣጠርና አመጣጡ፣ በኢህአዴግ በኩል የፈጠረው ቁጭት መስራት የሚገባኝን ተገቢ ስራ በወቅቱና በብቃት በመስራት ናዳው እንዳይመጣ ሳይሆን ቀድሞውኑም እንዳይፈጠር ማድረግ እችል ነበር የሚል ሳይሆን የእኔና የእኔ ብቻ መሆን ያለበትን ስልጣን ለሌሎች ሊሰጥብኝ ነበር የሚል የሥልጣን ስስትና ስጋት ነው፡፡ መቼም ቀደም ብለን እንደገለፅነውና ማንም ሰው ቢሆን በቀላሉ ሊረዳው እንደሚችለው፤ የዲሞክራሲን ናዳ ለማምለጥ ዋነኛ መፍትሄው ዲሞክራሲን ካሰሩበት ወህኒ ቤት አለያም ከቆለፉበት ሳንዱቅ ከፍቶ ነፃ መልቀቅ ብቻ ነው፡፡ ይህንን እውነት ኢህአዴግ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን በምርጫ 97 ሂደት ወቅት መገንዘብ ችሎና አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምሮ፣ ወዳጅ ጠላቶቹ ሁሉ አበጀህ እንዲሉት ማስገደድ ችሎ ነበር፡፡ “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንደሚሉት ሆኖ የሙጢኝ ብሎ የያዘው እኔና እኔ ብቻ የሚለው አቋሙና የተንጋደደው የዲሞክራሲ አስተሳሰቡና አሰራሩ በጀመረው አዲስ የብርሃን ጐዳና ገፍቶ እንዲጓዝ ሳያደርገው ቀረ፡፡

አቶ በረከት በመፅሀፋቸው፣ ኢህአዴግ የመጣውን ናዳ ለማምለጥ በከፍተኛ የጥድፍያ ሩጫ የተካለበው ያልሰራቸውን ስራዎች ለመስራትና ያልፈፀማቸውን ጉዳዮች ለመፈፀም ብቻ ነበር ቢሉንም ክልቢያው ከዚህ የዘለለ አጀንዳ ይዞ እንደነበር ለማናችንም ግልፅ ነበር፡፡ ኢህአዴግ ያኔ በ”ጊዜ የለንም” ፈጣን ሩጫ ያልሰራውን ለመስራት ሲዋከብ እግረመንገዱንም ተቃዋሚዎች ይህቺን ሀገር ከያዙዋት ያፈርሷታል የሚለውን የምንጊዜም አቋሙን ለማረጋገጥ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማጥበብ ለተቃዋሚዎች የእግር መትከያ ቦታ ለመንፈግና ተቺ ወቃሽና በተለይ ደግሞ ተቃዋሚዎችን የሚያስተናግድ ነፃ ሚዲያ እንዳይኖር ለማድረግ ቀን ከሌት በትጋት ይሰራ እንደነበር የትናንት ትዝታ ነው፡፡ከምርጫ 97 በሁዋላ የነበሩት ጊዜያቶች በግልፅ እንዳሳዩን፣ ኢህአዴግ የመጣበት ናዳ ዋነኛ መነሻውና ፍቱን መድሃኒቱም የበለጠ ዲሞክራሲ መሆኑን ተረድቶ ዲሞክራሲን ጨምድዶ ይዞበት የነበረውን የእጁን መዳፍ ይበልጥ ይዘረጋዋል ተብሎ ቢገመትም ማድረግ የመረጠው ግን ተቃራኒውን ነው፡፡አቶ በረከት በመፅሀፋቸው “ክርስቶስ ለስጋው አደላ” እንዲሉ ኢህአዴግ በምርጫ 97 ሂደት ከጅምር እስከ ፍፃሜው ድረስ ያደረገው እንቅስቃሴ “ሙሉ በኩልሄ” ነበር፡፡ በወቅቱ የተፈጠሩት ችግሮችም በተቃዋሚ ድርጅቶች አማካኝነት የተፈጠሩ ነበሩ በማለት ለድርጅታቸው በማድላት እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ታጥበዋል፡፡ የምርጫ 97 ቅድመ - ውጤቱ ይፋ እስከተደረገበት ድረስ የነበረው ሂደት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ደማቅ አዎንታዊ ምዕራፍ ይዞ እንደሚኖር ለማናችንም የሚያከራክር አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን አቶ በረከትም ሆኑ የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ገምግሞ እንዳቀረበው ሙሉ ሂደቱ “እንከን አልባ” ሆኖ ተጠናቋል ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ መቼም ምንም ቢሆን “ማን ያርዳ የቀበረ ማን ይናገር የነበረ” ነውና ከአቶ በረከትም ሆነ ከኢህአዴግ “እንከን አልባ” የምርጫ ሂደት ግምገማ በተቃራኒው በተለያዩ ክልሎች በርካታ ኢህአዴግ ሰራሽ ችግሮች የምርጫውን ሂደት ሲያውኩና የምርም ሲያደናቅፉ በአይናችን እያየን ታዝበናል፡፡የተቃዋሚዎችን የስልጣን ጥመኝነትና አይረቤነት ሀገሪቱን የመምሪት እድል ካገኙም የሁለት ጀንበር እድሜ እንኳ ሳታገኝ እንዳልነበረች አድርገው እንደሚያፈራርሷት ለማስረገጥ እያንዳንዷን ድክመትና ችግራቸውን እየነቀሱ በመፅሀፋቸው ላይ ለማሳየት ረጅም ርቀት የተጓዙት አቶ በረከት፤ በተለያዩ ክልሎች ኢህአዴግና የሚመራው መንግስት የፓርቲና የመንግስት መዋቅሮችን በተናጠልና በጣምራ እንደፈለገ በመጠቀም በተቃዋሚ ፓርቲ እጩዎች፣ አባላትና ደጋፊዎች ላይ የፈፀመውን የማዋከብ፣ በሰበብ አስባብ የማንገላታት፣ ፅህፈት ቤቶቻቸውን የመዝጋት፣ ቢሮና የመሰብሰቢያ አዳራሾችን በኪራይ እንዳያገኙ የተለያዩ ተፅእኖና እንቅፋቶችን የመፍጠር፣ የህዝባዊ ስብሰባና የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄን ማዘግየት ወዘተ. ችግሮች አንዱንም እንኳ ሳይገልፁ ይህቺን ሀገር ያጠፏታል ባሏቸው ተቃዋሚዎች ላይ ብቻ መፈፀሙን “እሰይ” በማለት ንቀው አልፈውታል፡፡ ይህ ሁኔታም ፀሀፊውን ለትዝብት ሲዳርግ መፅሀፋቸው ደግሞ ከተለመደው የኢህአዴግ ተራ የፕሮፓጋንዳ ፅሁፎች እንደ አንዱ አድርገን እንድንቆጥረው አስገድዶናል፡፡የሆኖ ሆኖ አቶ በረከት በመፅሀፋቸው ኢህአዴግ እኔና እኔ ብቻ እንጂ ሌሎቹ ይህችን ሀገር ያፈራርሷታል የሚለውን የዘመናት አቋሙን ለመተግበር አስፈላጊና በቂ ነው የሚለውን መስዋዕትነት ለመክፈል ያለውን የማያወላውል ቁርጠኝነት ዘርዝረው በማስረዳት አረጋግጠውልናል፡፡ እናም ታዲያ ቅዱስ ነው የሚለውን የራሱን አቋም ለማረጋገጥና ለመጠበቅ ህይወቱን ለመስዋእትነት እየዘመረ ለማቅረብ ቁርጠኛ አቋም ያለው ፓርቲ፤ የዚህ አቋሙ ተፃራሪና እርኩስ አቋም ይዘዋል ያላቸውን ባላጋራዎቹን ከምድረ ገፅ ቢያጠፋና ሊያጠፋም ቢፎክር ምኑ ያስገርማል?

አሁን ደግሞ ወደ ሁለተኛው ነጥብ እንሸጋገርና አቶ በረከት በዚህ መፅሀፋቸው ውስጥ ሳይነግሩን የደበቁን ወይም አዛብተው ያወጉን ጉዳዮች እንዴት ያሉት ናቸው የሚለውን እናንሳ፡፡

ሃቁን ለመናገር አቶ በረከት በመፅሀፋቸው በምርጫ 97 ድርጅታቸው ኢህአዴግ የተጫወተውን ሚና አግዝፎና “ሙሉ በኩልሄ” አድርጐ ለማቅረብ የተጠቀሙበት አገላለፅ ምርጫዎቹ እዚህ አገራችን ውስጥ ሳይሆን እኛ በሌለንበት አውሮፓ ወይም አሜሪካ ውስጥ የተካሄዱ ምርጫዎች እንዲመስሉን አድርገውናል፡፡

በሁለቱ ምርጫዎች ወቅት የኢህአዴግ አባላት አርቆ አሳቢ፣ የህዝብ ወዳጅ፣ ምንም አይነት ስልጣንና ጥቅም የማይፈልጉ፣ ሆደ ሰፊ፣ ትእግስተኛ፣ በከፍተኛ ስነምግባር የታነፁ፣ ባጠቃላይ የድርጅቱ ሊቀመንበር በተደጋጋሚ ከገለፁት በተቃራኒው “የመላእክት ስብስብ” አስመስለው ሲያቀርቧቸው፤ የተቃዋሚ ድርጅት አባላትን ደግሞ የኢህአዴግ ቀጥተኛ ተቃራኒ ባህርያት የተላበሱ አድርገው አቅርበዋቸዋል፡፡ አቶ በረከት በሁለቱም ምርጫዎች ሂደት ወቅት ህዝቡ ከሚያውቀው በተጨማሪ የምርጫ ታሪክ ባስገኘላቸው ልዩ አጋጣሚ አማካኝነት እርሳቸው ብቻ በግል ያወቋቸውን የተለዩ ጉዳዮች ለማብራራት በሚል በዘረዘሯቸው ጉዳዮች ውስጥ ልክ በበርካታ የህፃናት መፅሀፍት ውስጥ እንዳሉት ታሪኮች ኢህአዴግንና አባላቶቹን እንደ ጀግናው ልኡል፤ ተቃዋሚዎቹንና አባላቶቹን ደግሞ እንደ ጭራቁ አስመስለው እንዲስሏቸውና በወቅቱ የተፈጠሩትን ችግሮች አንዷንም እንኳ ላመል ሳያስቀሩ በተቃዋሚዎችና በደጋፊዎቻቸው ላይ እንዲያላክኩ ያደረጋቸውም ይሄው የቀድሞ አቋምና ውሳኔአቸው ይመስላል፡፡ይሁን እንጂ አቶ በረከት ይህንን ሲያደርጉ በቅጡ ያልተረዱት ዋነኛ ጉዳይ ተቃዋሚዎችና መሪዎቻቸው የቱንም ያህል አስከፊ ሆነው ገፅታቸው ተበላሽቶ ቢሳልና የተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ እላያቸው ላይ ቢደፈደፉ የኢህአዴግን የዘመናት በተግባር የተገለጠ ባህርይ ሊቀይረው የማይችል መሆኑንና የተቃዋሚዎች ድክመት የቱንም ያህል ሰማይ ቢነካ የኢህአዴግን ድክመቶች በመሸፈን “አሪፍ ድርጅት” ሊያደርገው የማይችል መሆኑን ነው፡፡በምርጫ 97 መገባደጃ ግንባር ቀደም የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች የፈፀሙት የአመራር ስህተት በተለይ ደግሞ በህዝብ ድምፅ ያገኙትን የፓርላማ ወንበር ላለመያዝ ያሳለፉት ውሳኔና እርምጃ በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክና በዲሞክራሲ ግንባታ ትግሉ ላይ ትቶት ያለፈው ጠባሳ ቀላል የሚባል ስላልሆነ ከታሪክ ተወቃሽነት ከቶውንም ቢሆን ማምለጥ አይችሉም፡፡ ይህ ማለት ግን ኢህአዴግ በበኩሉ የሰራቸውን በርካታ ስህተቶች ትክክል ያደርጋቸዋል ወይም ይሽራቸዋል ማለት አይደለም፡፡ የሁሉም ወገን ሚዛን እንደየእጅ ስራው መጠን ብቻ ነው፡፡ እናም በወቅቱ የቅንጅት ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ገብረክርስቶስ ሃይለስላሴ “ቅንጅት ከየት ወዴት” በሚለው መፅሀፋቸው ለህሊናቸውም ለታሪክም ሲሉ ፓርቲያቸው ቅንጅት በወቅቱ የነበሩበትን ጉድለቶች ቁልጭ አድርገው በማቅረባቸው አቶ በረከት በመፅሀፋቸው ለማስረጃ ማጣቀሻነት እንዲጠቀሙበት የረዳቸውን ያህል እሳቸው በግል የሚያውቋቸው የድርጅታቸው የኢህአዴግ ስህተቶች ቢቀሩ እኛ በግልፅ የምናውቃቸውን ችግሮች ለመጥቀስ አለመቻላቸው እሳቸው ከለመዱት የፕሮፓጋንዳ ፅሁፍ በቀር ለታሪክ የሚቀርብ ፅሁፍ መፃፍ የማይችሉ ፀሀፊ ብለን እንድናማቸው እድሉን ሰጥተውናል፡፡ኢህአዴግ ከናዳው ለማምለጥ በከፍተኛ ፍጥነት ይሮጥ በነበረበት ጊዜ የራሱን አባላት ሲመለምልና ሲያደራጅ፤ ተቃዋሚዎች አባሎቻቸውን ለመመልመልና ለማደራጀት ያደርጉት የነበረውን እዚህ ግባ የማይባል ትንሽዬ መፍጨርጨር እንኳ ያለ አንዳች ወከባና እንግልት በነፃ እንዳያከናውኑ ፈቀደላቸው? የተመለመሉና የተደራጁ አባሎቻቸውን እንዴት አደረጋቸው?ኢህአዴግ የከተማ አባሎቹን ሲመለምል እንደ ገጠሮቹ ራሳቸው ለራሳቸው በሀቅ ሰርተው እንዲጠቀሙ ወይስ ለሚሰጡት ድጋፍ በአፀፋው እርሱ እንደጠቀማቸው በአቶ በረከት አገላለፅ “ኢህአዴግ አባብሎአቸው?” ለእነዚህ ቀላል ጥያቄዎች ትንሽዬ ማብራሪያ አክለውበት ቢሆን ኖሮ ለእሳቸውም ለመፅሀፋቸውም ክብር መሆን በቻለላቸው ነበር፡፡አቶ በረከት በመፅሀፋቸው ውስጥ ተቃዋሚዎቹን ከወቀሱበትና ከተቹበት እጅግ በርካታ ህፀፆች ውስጥ አንዱ ተቃዋሚዎች የዜሮ ድምር ፖለቲካ አራማጅና ሰለባ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የአቶ በረከትን ትችትና ወቀሳ በመካድ መከራከር ምናልባት ተቃዋሚ ድርጅቶችን ባለማወቅ አለያም በእነሱ ጭፍን ደጋፊነት ሊያስገምት ይችላል፡፡ ለምን ቢባል? ትችቱ እውነተኛ ትችት ስለሆነ ብቻ ነው፡፡ይሁን እንጂ እዚህ ላይ መጠየቅ ያለበት አንድ ጥያቄ አለ፡፡ ለመሆኑ አቶ በረከት ደጋግመው እንደገለፁት፤ እርሳቸውም ሆነ ድርጅታቸው ኢህአዴግ በዜሮ ድምር ፖለቲካ ተቃዋሚዎቹን ብቻ በመነጠል መውቀስ የሚያስችላቸው የሞራልም ሆነ የተግባር መሰረት አላቸውን?ሁላችንም አሳምረን እንደምናውቀው የዜሮ ድምር ፖለቲካ ዛሬም ድረስ ያልተላቀቀን የሀገራችን የፖለቲካ ባህል ክፉ ዛር ነው፡፡ ትናንትም ሆነ ዛሬ ያሉት ፖለቲከኞቻችን የፈለቁት እንዲህ ያለ የፖለቲካ ባህል ከተንሰራፋበት ህብረተሰብ ውስጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ብቻ ተነጥሎ ከሰማይ አልወረደም፡፡ የኢህአዴግም ሆነ አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ተሳታፊ የነበሩበት የ1960ዎቹ የፖለቲካ እንቅስቃሴና እሱን ተከትሎ በተነሳው አብዮት ወቅት አንድ ሙሉ ትውልድ ያለ አንዳች ስስት ለሞትና ለስደት የገበርነውም በዚህ በተጠናወተን የዜሮ ድምር ፖለቲካችን ሰበብ ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን ይሄው ክፉ ዛር እንደተላቀቀን የሚያሳይ የተግባር ማስረጃ በኢህአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎች በኩል የለም፡፡ አቶ በረከትም ቢሆኑ ይህን እውነት አልደበቁም፡፡ ኢህአዴግ አይነኬ በሚላቸው አቋሞቹ ሞት አለም ቢመጣ እንደማይደራደር ደጋግመው ነግረውናል፡፡ የኢህአዴግም ሆነ የተቃዋሚዎች ነገረ ስራ በአሳር ተፈልጐ ከሚገኝ ጥቃቅን ልዩነቶች በቀር “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምን ይመራርጧል” የተባለው አይነት ነው፡፡ እናም የኢህአዴግ ተቃዋሚዎችን በዜሮ ድምር ፖለቲካ የመክሰስ ነገር ውሀ አያነሳም፡፡ሌላም ጥያቄ አለ፡፡ አቶ በረከት “ሙሉ በኩልሄ” ሲሉ ያሞካሹት የ2002 ምርጫ ውጤት የተገኘው በእርግጥ ኢህአዴግ ምርጫውን አምስት አመት የፈጀ የማራቶን ሩጫ ስላደረገውና ይህንንም ሩጫ የእነ አበበ ቢቂላንና የእነ ኃይሌ ገብረስላሴን የረጅም ርቀት ሩጫን ክብረወሰን የማሻሻል ልምድና ባህል በመጠቀም አዲስ ክብረወሰን በማሻሻሉ ብቻ ነውን? አምስት አመታትን በፈጀው በዚህ የማራቶን ሩጫ ወቅት ማን የማንን እግር ጠለፈ? ማን የማንን የመሮጫ ጫማ አስወለቀ? ማንስ የትኛው ኪሎ ሜትር ላይ መሮጡን ትቶ የውድድሩ ፍፃሜ መስመር መግቢያ ድረስ መኪና ላይ ተንጠለጠለ? አቶ በረከት እኔ ብቻ የማውቀው ሚስጥር ካሉት ውስጥ ይህንንም ነግረውን ቢሆን ኖሮ እውነቱን በመናገራቸው እርሳቸው፣ እውነቱን በማወቃችን ደግሞ እኛ፤ መጭው ትውልድና ታሪክ በጋራ መጠቀም በቻልን ነበር፡፡

አቶ በረከት በመፅሃፋቸው ካወጉን ወጐች ውስጥ የዋሹን ኢህአዴግ ለ2002 ምርጫ የማራቶን ዝግጅት ሲያደርግ በምንም ተአምር ሁሉንም ወንበሮች ሙጥጥ አድርጐ ለመውሰድ ከመጀመሪያው አስቦበት የገባበትም ሆነ የሰራው ሥራ አልነበረም የሚለውና ከዚህ በተመሳሳይ ኢህአዴግ በገጠር የፈጠረው ሰፊና ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር ለምርጫ ብሎ የፈጠረው አይደለም የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ምናልባት አቶ በረከት ልብ አላሉት ይሆናል እንጂ ድርጅታቸው ባጭር ታጥቆ ሲዘጋጅ የነበረው ብቻ ሳይሆን ያደረገውም በተቻለው አቅም ሁሉ ለተቃዋሚዎች የሚተው አንድም ወንበር እንዳይኖር መትጋት ነበር፡፡ በተለያዩ ክልሎችና በአዲስ አበባ የሚገኙ ትንፋሽ የሚያሳጣውን የምርጫ ዝግጅት ሩጫ ከመጀመሪያው ተርታ ተሰልፈው ሲሮጡና አባልና ደጋፊአቸውን ሲያሯሩጡ የነበሩ የኢህአዴግ ካድሬዎች በግልፅ ያስረዱን የነበረው እውነት፤ እየሰሩት ያለው ድርጅታዊ ስራ ተቃዋሚዎችን የእግር መትከያ ቦታ ለማሳጣት መሆኑን ነበር፡፡

እንዲህ አይነት ስራ ደግሞ ከፓርቲው ላእላይ አመራር ካልወረደ በቀር ካድሬውም ሆነ ተራው አባል በራሱ ፈቃድና ተነሳሽነት ብቻ የማይሰራው እንደሆነ እኛም እናውቃለን፡፡ ተቃዋሚዎችን የእግር መትከያ ቦታ የማሳየት ስራ ደግሞ እንዴት ያለና ምን ምን አይነት ነገሮችን የሚያካትት ስራ እንደሆነም በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ አቶ በረከት እንደመሰከሩት ሁሉ ኢህአዴግ ድሮም ቢሆን ተፋላሚውን በቆረጣ የማሸነፍ ልዩ ጥበብ ያለው ድርጅት እንደሆነ ላለፉት ሃያ አመታት በሚገባ ያየነው ጉዳይ ነው፡፡

በ2002 ብሔራዊ ምርጫ በተለያዩ ክልሎች የምርጫ ጣቢያዎች አንድ ለአምስት በተባለው የኢህአዴግ የአባላት አደረጃጀት፣ በምርጫ ጊዜ በግድ ሊኖር ከሚገባው ምስጢራዊ የድምፅ አሰጣጥ ስነስርአት በተቃራኒ ጠርናፊው አምስቱንም የቡድኑ አባላት እየመራና ማንን መምረጥ እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን እንዲመርጡም ጭምር እየተቆጣጠረ ሲመርጥና ሲያስመርጥ ያየነው ኢህአዴግ በየአካባቢው በፈጠረው ሰፊና ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር አማካኝነት ከድርጅቱ በቀጥታ በወረደ መመሪያ ሳይሆን እንዲሁ በአጋጣሚ የተደረገ ነገር ነው በሚል ከአይናችን የተሻለ የመከራከሪያ ማስረጃ አቶ በረከት ከየት ሊያቀርቡልን ይችሉ ይሆን?ኢህአዴግ የቤት ስራዎቹን አጠናቆ ሲቀርብ አሸናፊነቱ የማያጠራጥር ድርጅት እንደሆነ ከምርጫ ዘጠና ሰባት በስተቀር በሌሎቹ ሦስት ብሔራዊ ምርጫዎች በተግባር አሳይቶናል፡፡ ኢህአዴግ ቤቱ ወስዶ እንዲሰራቸው በሚሰጡት የቤት ስራ ጥያቄዎች ውስጥ ዲሞክራሲን የተመለከቱ ጥያቄዎችን (ምንም እንኳ እንደበጐ አድራጊው ባለፀጋ ሼህ መሀመድ አልአሙዲ አይነቶች የወዳጅ አማካሪ ቢኖረውም) እንዴት አድርጐ እንደሚሰራቸው ወይም እንደሚመልሳቸው ከቃል ይልቅ ተግባር ዋነኛ ቁልፉ ማስረጃ ነውና በሚገባ እናውቃለን፡፡አቶ በረከት በአምስቱ አመት የምርጫ ማራቶን ኢኮኖሚያዊ ልማትን የማጣደፍና ዲሞክራሲያዊ ምህዳሩን በማስፋት ህዝቡ የዳር ተመልካች ሳይሆን ዋናው ተዋናይ የሚሆንበትን ሁኔታ የመፍጠር ጉዳይ ገና ከጠዋቱ ኢህአዴግ የያዛቸው የምርጫ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች እንዲሆኑ ተደረገ ያሉት ጉዳይ በረጅም ወታደራዊ ትግል በሶሻሊዝም/ኮሙኒዝም ርእዮተ አለም እየተመራ ልክ እንደ ኢህአዴግ ሁሉ የመንግስት ስልጣንን የተቆጣጠሩ የሞዛምቢክ የቪየትናምና ኩባን የመሳሰሉ ሀገራት ፓርቲዎችን ታሪክ ያስታውሰኛል፡፡ በእነዚህ ሀገራት ፓርቲዎች አስተሳሰብ ህዝብ ሲሉ ምን ማለታቸው እንደሆነ ትርጉሙ ከሌላው የህብረተሰብ ክፍል የተለየ ነው፡፡ለእነዚህ አብዮታዊ ፓርቲዎች ህዝብ ማለት የትግላቸው / የድርጅታቸው አባላትና ደጋፊዎች ማለት ሲሆን ሰፋ ሲል ትግላቸውንና ድርጅታቸውን የማይደግፉ ነገር ግን ሌሎችን በመደገፍ የማይቃወሙትን ይጨምራል፡፡ ሌላው ተቃዋሚ ሃይል ነው፡፡ ተቃዋሚ ደግሞ እንደ ዋነኛ የጠላት ሃይል ይቆጠራል፡፡ የኢህአዴግን ቀደም ያሉትን ብቻ ሳይሆን የቅርብ ጊዜ የቅስቀሳና የርእዮተ አለም ፅሁፎችን ስታገላብጡ ይህን በደንብ ማረጋገጥ ትችላላችሁ፡፡በአምስት አመቱ የምርጫ ማራቶን ወቅት የዲሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ህዝቡ ዋናው ተዋናይና ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ የኢህአዴግ የምርጫ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂ እንዲሆን ሲወሰን አላማውም ግቡም ግልፅ ነበር፡፡ ከምርጫ 97 በሁዋላ ኢህአዴግ ያወጣቸው የተለያዩ አዋጆችና ህጐች ምን ያህል በክልከላና በግደባ የተሞሉ እንደሆኑ፣ ዋነኛ አላማቸውም የትኛውን የፖለቲካ አካል ከልክሎና ገድቦ የትኛውን አካል በተሻለ ለመጥቀም እንደሆነ እኛም ሆንን አቶ በረከት አስረግጠን የምናውቀው ጉዳይ ስለሆነ እንለፈው፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ፤ ወጣቶች ሴቶችና አርሶ አደሮች የኢኮኖሚና የፖለቲካ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ካደረገበት የተለያዩ አደረጃጀቶች ውስጥ በ2002 ምርጫ ድል ማግስት፣ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር መርህና መንፈስ መሰረት፤ የእርሻ መሬትም ሆነ ስራ የለሽ የሆኑ ወይንም ሌሎች የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ደጋፊዎችን የኢህአዴግ ታሪካዊ መለያ ባህሪው ነው በተባለው የራስ ተነሳሽነት ትእግስት፣ ሆደ ሰፊነትና ይቅር ባይነት አደራጅቶና እንደ ሌሎቹ የኢህአዴግና የአብዮቱ ልጆች ከሲሳዩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸው ከሆነ ወይም ደግሞ ራሳቸውን በተቃዋሚ ፓርቲ አንድ ክንፍነት አለያም አባልና ደጋፊነት ተለይተው በመደራጀት ለቀረቡ ዜጐች ያለ አንዳች ተፅእኖ አድልኦና ማጉላላት ለአባሎቹና ለደጋፊዎቹ ካፈለቀው ፀበል ፀዲቁን አቋድሷቸው እንደሆነ፣ ያ የግል ፕሬስ ጋዜጠኛው ነገረኝ እንዳሉን ሳይሆን በተጨባጭ ማስረጃ ሊያስረዱን ቢችሉ ኖሮ በጣም ጥሩ ይሆን ነበር፡፡

ከዚህ በታች የምናወራው አቶ በረከት በሁለት ምርጫዎች ወግ መፅሀፋቸው የነገሩንንና እርሳቸው ብቻ ያውቁአቸው ስለነበሩት አዳዲስ ነገሮች ነው፡፡ ኢህአዴግ ራሱን እንደ ህዝብ ጫማ በመቁጠር የሶሻሊስት/ኮሙኒስት ርእዮተ አለም አንግቦና ታጥቆ ህዝቡን ነፃ ለማውጣት ነፍጥ አንግቦ፣ ለበርካታ አመታት የታገለ እስከ ትናንት ድረስም ከዚህ የተቀደሰና ህዝባዊ ከሚለው አብዮታዊ ዲሞክራሲ አላማና መርሁ በቀኝ ሁዋላ ዙር አይነት ታጥፎ የከሰሩ ኒዎሊበራሊስቶች የሚያንጐራጉሩት የኪሳራ እንጉርጉሮ ነው በሚል ያወግዘው በነበረው በራስና ለስራ ቀጥተኛ ጥቅም ብቻ የመስራት ወንጌል መጠመቁ በጣም አዲስም አሪፍም ዜና ነው፡፡ ስለዚህ ኢህአዴግን ማርያም በሽልም ታውጣህ ልንለው ይገባል፡፡የዚህን አዲስና አስደሳች ለውጥ አፈፃፀሙ፣ ህዝቤ እያለ የሚጠራቸውን ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎቹንም እንዲያካትትና በእርግጥም ያለ ኢህአዴግ የአባልነት ልዩ ድጋፍ በራስና በራስ ህጋዊ ጥረት ብቻ እንዲሆን በተጓዳኝ ጥሪያችንን በትህትና እናቀርባለን፡፡የበርካታ የቢዝነስ ድርጅት ባለቤት እንደሆነ የሚነገረው ኢህአዴግ፤ እንደ አቶ በረከት አይነት ከፍተኛ ባለስልጣኖቹን የሚያሳክምበትና የፃፉትንም መፅሀፍ የሚያሳትምበት አጥቶ ከአንድ በጐ አድራጊ ባለፀጋ እጅ መውደቁ በጣም የሚያሳዝን ቢሆንም እንደ ድሮው ከካፒታሊስቶች ጋር መሞዳሞድ ነው በሚል መወረፍ ወይም ማውገዝ ማቆሙም አንድ አዲስ ዜና ነው፡፡እንደ ልዩ ዜና የግሉ ፕሬስ ጋዜጠኛ ነገረኝ ያሉትን ሁሉ ግን አቶ በረከት ባይፅፉት ደስ ይል ነበር፡፡ አሉባልታ ለመሪና ለከፍተኛ ባለስልጣን በተለይ አያምርም፡፡ ግን መቼስ ምን ይደረግ?ከዚህ በላይ ያነሳሁዋቸውን ጉዳዮች ያቀረብኩት የኢህአዴግን መልካም ስራዎች ዋጋ ለማሳጣት ወይም ደግሞ ለተቃዋሚዎች ልዩ ጥብቅና ለመቆም እንዳልሆነ ሁሉም ልብ እንዲልልኝ ቅን ፍላጐት አለኝ፡፡ ይልቁንስ የተጠናወተንን በየጊዜው በሀገራችን የሚከወኑ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳይ ክንውኖችን ታሪክ አሸናፊው ወገን በአሸናፊነት አይንና ልቦና፤ ተሸናፊው ወገን ደግሞ የተሸናፊነት ሰሜት በሚፈጥረው የራሱ ድክመትና ስህተት የፈጠረውን ሽንፈት በሌሎች ላይ የማላከክ ክፉ አባዜ እንዲሽርልንና ለቀጣዩ ትውልድና ለታሪክ እውነትንና እውነትን ብቻ እንድንተውለት ቢረፍድብንም ጨርሶ አልጨለመብንምና የግሌን ጉትጐታ ለማቅረብ ብቻ ነው፡፡ሌላው ፍላጐቴ ደግሞ ከምርጫ 97 ጀምሮ ባለው ጊዜ በሀገራችን በተከናወኑት የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ ክንውኖች ውስጥ ለተገኙት ድሎች ኢህአዴግ ብቸኛ ባለቤትነቱን ወስዶ በኩራትና በድል አድራጊነት ስሜት የሚሸልለውን ያህል ለተከሰቱት ጥፋቶችና ውድቀቶችም የድርሻውን ማንሳት እንዳለበት ለመጠቆም ነው፡፡ኢህአዴግ ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ፀጉሩ ድረስ የተጀቦነበትን ሁሉንም አይነት ጥፋት የሚያጠፉትና ለጥፋቶቹም ተጠያቂ መሆን ያለባቸው ሌሎች ናቸው የሚለውን ራሱን ንፁህና ቅዱስ አድርጐ በሌሎች ላይ ጣት የመቀሰር ቡልኮ አውልቆ በመጣል፣ በገሀዱ አለም እውነታ መገዛት ካልጀመረ የሀገራችን የዲሞክራሲ ግንባታ ሂደት “ውሀ ቢወቅጡት…” ከመሆን ጨርሶ አያልፍም፡፡ ምንም እንኳን መልካም ነገር በምኞት ብቻ እንደማይገኝ ብረዳም የተሻለች ኢትዮጵያ ለሁላችንም አጥብቄ እመኛለሁ፡፡

 

 

Read 3285 times Last modified on Friday, 06 January 2012 10:27