Saturday, 22 November 2014 12:06

ልማት “እንበለ” ባህል…!

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(0 votes)

“ከመወለዳችን በፊትም ሆነ ከሞትን በኋላ የምናካሂዳቸው ነገሮች እንዲሁም የየእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን ከንጋት እስከ ንጋት በሙሉ ባህላዊ ናቸው፡፡” ይሉናል እውቁ የፎክሎር (ባህል) ጥናት መምህርና ተመራማሪ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር)፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ የሰው ልጅ በራሱ ባህልም ነው ብሎ መፈረጁ የሚገድ አይመስልም፡፡ ስለ ምን ቢሉ… ኑሮውም ሆነ አኗኗሩ በብዙም ቢሉ በጥቂቱ፣ ከረቂቅ እስከ ግዙፍ ባህል ነውና፡፡
የጽሑፌ ማጠንጠኛ ባህልና ልማት ያላቸው ትስስር ነው፡፡ በዚህም ባህልና እሴቶቹ ለልማት ያላቸውን ፋይዳ፤ እንዲሁም ለባህል ትኩረት ያልሰጠ ልማት (ልማት ያለ/እንበለ ባህል) ምን እንደሆነ በወፍ በረር ለማስቃኘት እሞክራለሁ፡፡ ማስረገጫዬም ልማት እንበለ ባህል፤ ጭንጫ መሬት ላይ ዘር ዘርቶ ምርትን እንደ መጠበቅ አጉል ተስፋ መሆኑን ማተት ነው፡፡  
የባህል ጥናት የአንድን ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ማንነት ለማወቅ ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ የአንድን ማህበረሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ደረጃ በአስተማማኝ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ ማሳደግ ከተፈለገ ቀድሞ የማህበረሰቡን ባህል ማጥናትና እሴቶቹንም መነሻ ማድረግ እንደሚገባ የፎክሎር/ባህል ጥናት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ማንኛውም ማህበረሰብ የእኔ የሚላቸው መንፈሳዊ እና ቁሳዊ እሴቶች አሉት፡፡ እነዚህ እሴቶች የማንነቱ መገለጫና የህልውናው ማዝለቂያ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ባህላዊ እሴቶቹን ማጥናት እና መረዳት ማህበረሰቡን ማወቅ ነው የሚባለው፡፡ ይህ አስተሳሰብ አሁን አሁን በበርካታ የጥናት መስኮች ከፍተኛ ተቀባይነትን እያገኘ መጥቶአል፡፡
ባህልና ልማት ያላቸውን ቁርኝት/ትስስር ከማውሳቴ በፊት የነገሩን ጭራ ለመያዝ ያግዘን ዘንድ ሁለቱን ፅንሰ ሀሳቦች (ባህልን እና ልማትን) የመስኩን ተመራማሪዎች ጥናቶች እማኝ አድርጌ ለመፍታት ልሞክር፡፡ ባህልን ላስቀድም፡፡ ራስወርቅ አድማሴ የተባሉ የዘርፉ ተመራማሪ “ባህልና ልማት፦ ምንነታቸውና ትስስራቸው” (2004) በተባለው ጥናታቸው ላይ ባህልን እንዲህ ይበይኑታል፡-
“ባህል አንድን ህብረተሰባዊ የወጎችን ስርዓትን (a system of social norms) እንደሚያመለክት፤ ይህም ህብረተሰባዊ የወጎች ስርዓት ሲወርድ ሲዋረዱ የመጡ ወጎችን፣ ልምዶችንና፣ እርሞችን፣ ልማዳዊ-ሕጎችን፣ ድንጋጌዎችንና ከነዚህ ጋር የተዛመዱ እምነቶችን፣ አመለካከቶችንና፣ ጠባዮችን ያቅፋል፡፡”
የባህል ባለቤት ህብረተሰብ፣ ዝቅ ሲልም ማህበረሰብ እንደሆነ የሚገልጹት ተመራማሪው፤ ሰዎች ባህልን በመማር እንጂ በደም እንደማይወርሱት፣ አንድ ህብረተሰብ አባላቱ በሙሉ የሚጋሩት አንድ ነጠላ ባህል ብቻ ወይም ብዙ ባህሎችን ሊያስተናግድ እንደሚችል፤ እንዲሁም ባህል በሂደት እንደሚለወጥና ፍጹም እንደነበረ ሆኖ እንደማይቀጥል/እንደማይኖር ይገልጻሉ፡፡
ይህ አስተሳሰብ በበርካታ የመስኩ ምሁራን ዘንድ ቅቡል ቢሆንም የባህልን ሂደት አስመልክቶ ግን የመስኩን ምሁራን ያቧደኑ ሁለት ርዕዮቶች አሉ፡፡ እነሱም “ባህልን አንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደተፈጠረ ግግር የሚቆጥረው ስታቲክ (static) ርዕዮት” እና የዚህ ተቃራኒ የሆነው ባህልን እንደ “ተለዋዋጭ ወይም ታዳጊ (dynamic) ፍሰት” የሚመለከተው ርዕዮት ናቸው፡፡
የባህልን ምንነት እንዲህ በግርድፉ ከጨበጥን እሱን እያሰላሰልን ወደ ልማት እንለፍ፡፡ (አሁንም ዋቢዬ የራስወርቅ አድማሴ ጥናት ነው፡፡) ልማት የሚባለው “አንድ አይነት ህብረተሰባዊ ለውጥ ሲሆን፣ ማንኛውንም ህብረተሰባዊ ለውጥ ግን ልማት ነው ማለት አይደለም፡፡ ልማት አዎንታዊ፣ በጎ ወይም ጠቃሚ ህብረተሰባዊ ለውጥ ማለት ነው፡፡” መልካም፡፡ ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስ፡፡ ባህልና ልማት ምንና ምን ናቸው?
ባህል የአኗኗር ዘዴን፣ ስልትን፣ ሥርዓትን፣ ደንብን፣ ኑሮን ራሱን ከመግለጫ ጥበቡ ጋር ጠቅሎ ይይዛል፡፡ ልማትም የሰው ልጆችን ህይወት አዎንታዊ በሆነ መንገድ ለመለወጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ውጤት በመሆኑ ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህልን መሰብሰብ፣ ማጥናትና መተንተን ለልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡
ባህል በልማት ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖና ለፖሊሲም ያለውን ተፈላጊነት በተመለከተ አሁንም ድረስ በመስኩ ምሁራን መካከል ልዩነቶች ቢኖሩም አብዛኞቹ የስነ ማህበረሰብ  ተመራማሪዎች በአንድ ነጥብ ይስማማሉ፡፡ ይኸውም በባህልና በልማት መካከል መደጋገፍ እንዳለና፤ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የሚካሄድ “የልማት እንቅስቃሴም” የማህበረሰቡን ባህላዊ እሴቶችን እና ከእነዚህ የሚመነጨውን አስተሳሰቡን ማዕከል ማድረግ እንደሚገባው፡፡
በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በመስኩ ምሁራን የተደረጉ ጥናቶችም ባህላዊ ጉዳዮች ለልማት ያላቸው ፋይዳ እጅጉን ወሳኝ መሆኑን የሚያስረግጡ ናቸው፡፡ አስተማማኝ ልማት እንዲኖር ከተፈለገም የህብረተሰቡን ባህልና ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባና እቅዶችና ፖሊሲዎችም ለማህበረሰቡ ባህል ትኩረት መስጠትና እሱ ላይ መመስረት እንዳለባቸው ጥናቶቹ ይገልጻሉ፡፡ የዚህም ምክንያቱ ባህልና የባህሉ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ ያላቸው ቁርኝት የሥጋና አጥንትን ያህል የጠበቀ በመሆኑና የማህበረሰቡም አስተሳሰብና ፍላጎት ከባህሉ ውጪ ስለማይሆን ነው፡፡
ማህበረሰብና ባህል ሕይወት ያላቸው/የሚኖሩ፣ ያለ ማቋረጥ የሚታደሱና ራሳቸውንም እንደወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚለዋውጡ ናቸው፡፡ ባህል እየተለወጠና እሴቶቹ እየተለወጡ በሄዱ ቁጥርም የሰዎች አስተሳሰብ ይለወጣል፡፡ አንድ ነገር ልብ እንበል፡፡ ባህልና እሴቶቹ ሲለወጡ የባህሉ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ አስተሳሰብም ይለወጣል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አለም አቀፋዊ ፖሊሲ ቀራጮችና “እቅድ አርቃቂዎች” ህብረተሰባዊ ወጎች (Social norms) እና ሌሎች ባህላዊ እሴቶች በሰዎች አመለካከትና ምርጫ ላይ የሚያሳድሩትን ተፅእኖ በመገንዘብ ለባህላዊ ጉዳዮች እውቅና እየሰጡ መጥተዋል፡፡ ሀገሮችም ይህንን እውነት በከፍተኛ ደረጃ እየተቀበሉና እየተገበሩት ነው፡፡ በዚህም በብዙ ሀገሮች የባህል ጉዳይ በልማት ዙሪያ በሚካሄዱ ውይይቶች፣ እቅዶች እና ተግባራት ውስጥ ቦታ እየተሰጠው መጥቷል፡፡ የዚህም ምክንያቱ ከሁሉ አስቀድመን “ልናለማው” የምንፈልገውን ማህበረሰብ በቅጡ ማወቅ ስለሚገባን ነው፡፡
ይህንን ዘመናዊና አለም አቀፋዊ ስምምነት ይዘን ወደ ሀገራችን ፊታችንን ስንመልስ ግን የምንመለከተው ምናልባትም የዚህን ተቃራኒ ነው፡፡ በሀገራችን የሚደረጉ ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ባህልንና እሴቶቹን ያገናዘቡ ናቸው ማለት ድፍረት ነው፡፡ ያገናዘቡ  ይመስለን ይሆናል እንጂ አላገናዘቡም፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት የአንድን ማህበረሰብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ደረጃ በአስተማማኝና ዘላቂ በሆነ መልኩ ማሳደግ ከተፈለገ ቀድሞ የማህበረሰቡን ባህል ማጥናትና እሴቶቹንም መነሻ ማድረግ የሚገባ ቢሆንም እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ይመስላል፡፡ ይህም የልማቱን ሂደት በጭንጫ መሬት ላይ ዘርን ዘርቶ ምርትን እንደመጠበቅ አጉል ተስፋ አድርጎታል፡፡
ለማህበረሰቡ እንዲተዳደርባቸው ብሎም እንዲገዛላቸው የሚቀረጹት ፖሊሲዎች፣ እንዲፈጽማቸውና “እንዲለማባቸው” የሚታቀዱት እቅዶች ወዘተ… የሀገሬውን ባህላዊ እሴቶችና ከነዚህ የሚመነጭ አስተሳሰቡ ላይ ከመመስረት ይልቅ የሌሎች ሀገሮች ህዝቦች ላይ ተመስርተው የተቀረጹ ፖሊሲዎችና ስልቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ለማህበረሰቡ እጅጉን ባዕድና ከሚጠብቃቸውና ከሚገዛላቸው ባህላዊ እሴቶቹ ጋር በጥቂቱም ቢሆን የማይሰምሩ በመሆናቸው ነገሩ ሁሉ አጓጉል መወራከብ ሆኖአል፡፡
የሌሎች ሀገሮችን መልካም ነገሮች ማምጣት የለብንም የሚል እምነት የለኝም፡፡ የማይጠቅሙንንም ጭምር ሳይሆን የሚጠቅሙንን ብቻ ለይተን ማምጣት እንዳለብን አምናለሁ፡፡ ከዚህ አስቀድሞ ግን ያሉንን ጠንቅቆ ማወቅና የሌሉንን/የሚጎድሉንን መለየት ያስፈልጋል፡፡  የሌሉንንም ከሌሎች አምጥቶ እንደወረደ መተግበር ሳይሆን ከእኛ አውድ ጋር ማልመድና መግራት፣ በነገሩም ላይ የጠራ ግንዛቤን ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህ እስካልሆነ ድረስ አሁንም እናልማለን፣ በከንቱ እንደክማለን እንጂ የምንፈልገውን አንጨብጥም፡፡ ለዚህም ነው በርካታ “ልማታዊ” እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሶባቸው ሳይሳኩ ባክነው የቀሩት፡፡
በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች (በተለይም በአርሶ አደሩ አካባቢዎች) በርካታ “ልማታዊ” እንቅስቃሴዎችና ተግባራት ተደርገዋል፡፡ ሆኖም እንዳለመታደል ሆኖ እንቅስቃሴዎቹ  የማህበረሰቡን ባህልና እሴቶቹን ግምት ውስጥ ያላስገቡና እንደተቀዱ የተተገበሩ በመሆናቸው ውጤታቸው ከትርፍ ይልቅ ኪሳራ የጎላበት ሆኖአል፡፡ የዚህም ምክንያቱ አስቀድሞም ማህበረሰቡ ለነገሩ የነበረው አመለካከት ወይንም ግንዛቤ አዎንታዊ አለመሆኑ ነው፡፡ ባህልን ያላገናዘበ “ልማት” ውጤቱ ይህ ነው፡፡ ከንቱ ድካም!
የሰው ልጅ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ከግለሰብ እስከ ህዝብ ከሚያከብራቸውና እንዲከበሩለት ከሚፈልጋቸው ነገሮች መካከል ምናልባትም ዋነኛው ባህሉ ነው፡፡ በመሆኑም ከባህላዊ እሴቶቹ ውጪ የሆኑና ምናልባትም በባህሉ ውስጥ አሉታዊ ትርጉም ለሚሰጣቸው ነገሮች ያለው ምላሽ ከሚፈለገው በተቃራኒው ነው፡፡ ስለሆነም ሲጀመርም ማንነቱን ያልተረዱ ተግባራትን አይቀበልም፡፡ በአስገዳጅ ሁኔታዎችና ተፅዕኖዎች እንዲቀበል ብናደርገውም ከመቀበል ባለፈ ለውጤቱ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ስለማያደርግ፣ የሚፈለገው ውጤት “ላም አለኝ በሰማይ” አለፍ ሲልም ጭንጫ መሬት ላይ ዘር ዘርቶ ምርትን እንደመጠበቅ አጉል ተስፋ ነው፡፡ ከንቱ ድካም!
መልካም ሰንበት!!

Read 3596 times