Saturday, 15 November 2014 11:00

ስነ - ልቦናዊ ክትባት

Written by  ሞገስ ገ/ማርያም
Rate this item
(8 votes)

ብዙዎቻችን ክትባትን የምናውቀው በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ ሊመጣ የሚችልን በሽታ ለመከላከል ጥቅም ላይ ሲውል ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በሥነ ልቦናና በስነ አዕምሮ መስክም የአእምሮ ጤናን ለመጠበቅና ከጉዳት ለመከላከል የሚውል ክትባት አለ፡፡ ስነ ልቦናዊ ክትባት /Psychophulaxis/ ወይም ቫክሲን ፎር ሳይክ /Vaccine for psyche/ ይባላል፡፡
ስነ - ልቦናዊ ክትባት /psychological vaccine/ ከተለመደው ክትባት የተለየ ሲሆን የስሜት ወይም የአስተሳሰብ መመረዝ እንዳይነካን ብሎም የስነልቦናና የአእምሮ ቀውስ ደረጃ ላይ ሳንደርስ የመከላከያ ስልት ነው፡፡ የተለመደው የክትባት አይነት የተዳከመ ቫይረስን/weakened virus/ ወደ ሰውነታችን ውስጥ በማስገባት የተፈጥሮ በሽታ የመከላከል አቅሞን አንቅቶ በሽታ እንዲከላከል ማድረግ ሲሆን ስነ ልቦናዊ የክትባት ዘዴ ግን መራዥ ስሜቶችና አመለካከቶች ወደ ውስጣችን እንዳይገቡ በመከላከል አእምሮአዊ ጤንነትንና ደህንነትን መጠበቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ ስነ - ልቦናዊ ክትባት ማለት ጤናማ ስሜትንና አስተሳሰብን የማዳበር ልማድ ማለት ነው፡፡ ይህም በጐና አዎንታዊ አመለካከትን፣ አስተሳሰብን፣ ስሜትንና ድርጊትን የሚያካትት ሲሆን ዋነኛ አላማውም የስነ ልቦና ቀውስንና የአእምሮ ጤና መታወክን መከላከል ነው፡፡ በአጭሩ ስነ ልቦናዊ ክትባት፤ ስነልቦናዊ ደህንነትን እንዲሁም አእምሮአዊ ጤንነትን የምንጠብቅበትና የምንከባከብበት ዘዴ ሲሆን አእምሮአዊ ንጽህና ወይም የአእምሮ ምግብ ልንለውም እንችላለን፡፡
የስነ ልቦና ክትባት ፅንሰ ሃሳብ በህክምና የመጀመሪያ የጤና ክብካቤ መርህ ውስጥ የተካተተ ቢሆንም እንደሌላው ዘርፍ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ባለመሰራቱ በማህበረሰባችን ዘንድ ትኩረት ሲሰጠው አይስተዋልም፡፡ በዚህም ምክንያት በአጭሩ መቀጨት የሚችሉ ችግሮች ለከፋ አደጋ እየዳረጉ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ የግለሰብን፣ ትዳርን፣ ቤተሰብን፣ ማህበረሰብንና ሀገርን ማፍረስ ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህን የመፍረስ አደጋና ውድቀት የሚፈልግ ግን የለም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በስሜትና በሃሳብ መመረዝ የተነሳ እነዚህ መዋቅሮች እንዳይፈርሱ ግንዛቤ ማስጨበጥና መከላከል ነው፡፡
ሚስት፤ እንደ ስነ - ልቦና ሃኪም
አንዲት ባሏ ደንታ ቢስና ግድ የለሽ የሆነባት አዕምሮ - ብሩህና ቆንጆ ሴት ነበረች፡፡ ባሏ ፈጽሞ ለውበቷና ብሩህነቷ ግድ ያለው አልነበረም፡፡ ለእሷ የሚሆን ጊዜ ኖሮት አያውቅም፡፡ ይሄ ሚስትን ዘወትር የሚያበሳጫትና ውስጧን የሚያሳምማት ጉዳይ ነበር፡፡
አንድ ምሽት ላይ ባሏ እንደወትሮው በመጽሐፍቱ ውስጥ ተደብቆ፣ በራሱ ዓለም ውስጥ እየዋኘ ነበር፡፡ ብሩኋ ሚስትም በፈገግታ ተሞልታ ወደ ባሏ ጋ በመጠጋት፣ ማራኪ በሆነ ስሜት ታወራው ጀመር፡፡ “ፀጉሬ ወርቅ አይደለም?” ስትል ጠየቀችው፡፡
ባሏም ቀና ብሎ ሳያያት “አዎ…ትክክል ነሽ” ሲል መለሰላት
“ጥርሶቼስ እንደ እንቁ አያበሩም?” ሚስት ቀጠለች
“ኦ…በትክክል” አሁንም እንዳቀረቀረ፡፡
“እጆቼስ እንደ ጠዋት ነፋስ ለስላሳ አይደሉምን?”
“በትክክል …በትክክል…”
“እግሮቼስ እንደ ዝሆን ኩምቢ በአግባቡ የተቀረፁና የተዋቡ አይደሉም?”
“…ትክክል ነሽ…”
“ሰውነቴስ እንደ እምነበረድ የሚያበራ አይደለምን?”
“የተናገርሽው እውነት ነው፡፡” ባሏ የሞት ሞቱን መለሰ፡፡
በሚስቱ የማያባሩ ጥያቄዎች ስራው ላይ ማተኮር ያልቻለው ባል፤ ሚስቱን ቀና ብሎ ማየት ጀመረ፡፡ እሷ ግን ቀጠለች…
“መቀመጫዬስ ጥሩ የአበባ ማስቀመጫ አይመስልምን?”
“ኦህ በትክክል”
“ጡቶቼስ እንደ ጣፋጭ ኮክ ሞላ ያሉ፣ ትኩስና ጠንካራ አይደሉምን?”
“ልክ ነሽ የኔ ጣፋጭ ባልየው በመጨረሻ ተንፍሶት የማያውቀውን የአድናቆት ቃል ተናገረ፡፡ በዚህ የተደሰተችው ሚስት ባሏን አቀፈችውና “ልቤን በጣፋጭ ቃላት የምትሞላልኝ ድንቅ ባል ነህ!” ስትል አወደሰችው፡፡ (ፕሮፌሰር ናስራት ሰስኪያን፤ “አባባሎች ለአዎንታዊ ስነልቦና ህክምና”)
ሴትየዋ ጋግርታም ባል ምን ያደርግልኛል ብላ ለመፍታት አልቸኮለችም፡፡ ተስፋ በመቁረጥና በሃዘን ስሜት ውስጥም አልዋኘችም፡፡ ባሌ ችላ ያለኝ ቆንጆ ባለመሆኔ ነው ብላም ከራሷ ጋር አልተጣላችም፡፡ ይኸ ሰው አይፈልገኝም ማለት ነው ወይም ሌላ ቆንጆ ማየት ጀምሯል ስትል በቅናት አልተንጨረጨረችም፡፡ በአጠቃላይ የደንታ ቢስ ባሏን ህይወት አውካ ራሷንም አልረበሸችም፡፡ ከባሏ ጋር ያላትን አለመግባባት የፈታችው በብልህነት ነው፡፡ ታዲያ ይህቺ ባለብሩህ አዕምሮ ሴት ባሏን እንዲናገር በመገፋፋትም ትዳሯን አላከመችም? እሱንስ ከጋግርታምነቱ አላዳነችውም? ድክመቱ ላይ ሳይሆን ጠንካራ ጐኑ ላይ በማተኮር እሱንም ራሷንም አስደስታለች፡፡ በጥረቷና በብልህነቷ  ከተደበቀበት ዓለም እንዲወጣና ትኩረቱ ወደ እሷ እንዲሆን አድርጋለች፡፡
ብዙዎቻችን ግን ችግራችንን እንደዚህች ሴት በብልሃት አንፈታም፡፡ ሌላ ሰው ጋ የተለየ ስሜት ካየን፣ “የሆነ ነገር ሆኖ ነው እንጂ በደህናው እንደዚህ አይሆንም” ብለን አናስብም፡፡ ለመርዳትም አንሞክርም፡፡ ይልቁንም “ጀመረው፣ መጣበት ደግሞ፣ ተነሳበት፤ ወዘተ” አይነት ፍረጃ ውስጥ ገብተን ችግሩን እናባብሳለን፡፡ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ የችግሩ አካል እንሆናለን፡፡ በግለሰብ፣ በጥንዶች (ባልና ሚስት)፣ በቤተሰብ፣ በማህበረሰብ እና በሀገር ደረጃ የምናየው ይህን ዓይነት አጉል ፍረጃ ነው፡፡ ፍረጃው ወደ ጠብ፣ አለመተማመን እንዲያም ሲል ወደ ጦርነት ይወስደናል፡፡ በዚህ ሂደት ደግሞ አእምሮአችንም ይታወካል፡፡
እኔ በሙያዬ እንደታዘብኩት፤ በየእለቱ የስነልቦና ድጋፍና እገዛ የማደርግላቸው ሰዎች በአብዛኛው ከስሜት ወይም ከአስተሳሰብ መመረዝ ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ ችግሩ እንደገጠማቸው ስሜታቸውንና አስተሳሰባቸውን ቢያክሙ ኖሮ የስነ ልቦናም ሆነ የአእምሮ ችግር ውስጥ ባልገቡ ነበር፡፡
  ክትባቱን እንዴት መውሰድ ይቻላል?
የስነ-ልቦናዊ ክትባት የሚከተሉትን ተግባራት ያካትታል፡-
አዎንታዊ አስተሳሰብን /Positive thinking/ ማዳበር፡-
በጎና አዎንታዊ አስተሳሰብን ማዳበር ጥሩ ስሜት እንደሚሰማን፣ ምክንያታዊ አስተሳሰባችን እንዲጐለብትና ወደ በጎ ተግባር እንድንገባ የሚረዳ መሳሪያ ነው፡፡ የአዎንታዊ አስተሳሰብ ጠንቆች ከሚባሉት መካከል ዘወትር ጎደሎ ጎደሎውን ማየት፣ አእምሮአዊ ግነትን መፍጠር፣ አልችልም ብሎ ማሰብ፣ ይህቺ አለም ኢ-ፍትሃዊና አድሏዊ ነች ብሎ መደምደምና መትከንከን ይጠቀሳሉ፡፡
ጥሩ ስነ-ምግባርን ማጐልበት /Cultivating good conduct/
ጥሩ ስነ-ምግባር ጥሩ የአእምሮ ምግብ ማለት ነው፡፡ ስራችንን፣ ማህበራዊ ግንኙነታችንንና አካላችንን በጥሩ ስነ-ምግባር የተቃኘ ማድረግ እንደ አንድ ስነ-ልቦናዊ ክትባት ይቆጠራል፡፡
ግብረ ገብነትንና ጥሩ መንፈሳዊ ባህሪን መላበስ /Having morale and good spiritual life/፣ ህይወታችንና ኑሯችን የእኛ ብቻ አይደለም፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሌሎች ጋር ይገናኛል፡፡ ማህበረሰባዊና መንፈሳዊ እሴቶች ሌላኛዎቹ የስነ-ልቦና ክትባት ምንጮች ናቸው፡፡ ከነዚህ ምንጮች አለመራቅ እንዲያውም ከምንጩ ቀድተን መጠጣት ይኖርብናል፡፡ ይህን ስናደርግ ከግጭት ነፃ የሆነ ህይወት እንመራለን፡፡
አእምሮን ማሰልጠን /Training the mind/:-
ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በየእለት ተእለት ህይወታችን ለመተግበር አእምሮአችንን ማለማመድና ማሰልጠን ተገቢ ነው፡፡ የዚህ ልምምድ የመጀመሪያ መርህ “አለምን መቀየር ስለማትችል አለምን የምታይበትን መነፅር ቀይር” የሚል ነው፡፡ እኛ መቆጣጠር የምንችለው የራሳችንን ስሜትና አስተሳሰብ ብቻ ነው፡፡ የሌሎችን አስተሳሰብ ለመቆጣጠር ስንሞክር ሚዛናችንን እንስታለን፡፡ አስተሳሰባችንንም በማይመለከቱን ክፉ ሃሳቦች እንመርዛለን፡፡
ስነ-ልቦናዊ ክትባትን የት ማግኘት ይቻላል?
ስነ-ልቦናዊ ክትባት ከሌላው የክትባት አይነት የሚለየው ክትባቱ ሁልጊዜ በእጃችን በመሆኑ ነው፡፡ ተከታቢውም ከታቢውም እኛ ራሳችን ነን፡፡ “በእጅ የያዙት ወርቅ …” እንዲሉ ግን ዋጋውን አናውቀውም፡፡ አንጠቀምበትምም፡፡ ይህን ክትባት በአካባቢያችን፣ በቤታችን፣ በቤተሰብ፣ በጎረቤት፣ በማህበረሰብ፣ በትምህርት ቤት፣ በጤናና  በሐይማኖት ተቋማት ጭምር እናገኘዋለን፡፡
 በአካባቢያችን የምንመለከታቸው በጎና መጥፎ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ግን እስቲ ለአፍታ የተቸሩንን በጎ ፀጋዎች ብቻ እናስብ፤ በእነሱም እንደሰት፡፡ የሌሉንን ነገሮች እንርሳቸው፡፡ እጃችን ላይ ባሉ ነገሮች ስንደሰት፣ በእርግጠኝነት ከፍርሃትና ከፀፀት ነፃ እንሆናለን፡፡
 አእምሮአችንና ስሜታችንም በቅንጅት መስራት ይጀምራሉ፡፡ ያን ጊዜ ችግሮችን የመፍታት አቅማችን ብቻ ሳይሆን የመፍጠር ችሎታችንም ከወትሮው ይጨምራል፡፡ ሆኖም የስሜት መረበሽ ወይም ከአስተሳሰብና ከባህሪ ጋር የተያያዙ የስነ-ልቦና ችግሮች ሲያጋጥሙ የባለሙያ ድጋፍ ማግኘት እንዳለብን አንርሳ፡፡  

Read 5060 times