Saturday, 15 November 2014 10:52

ነፃ ገበያ ይለምልም!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለምን መሰላችሁ ነፃ ገበያን ያወደስኩት? በእኛ አገር “ጨመረ” እንጂ “ቀነስ” የሚባል ነገር ጠፍቶ፣ “ቀነሰ” የሚለው ቃል ካልጠቀመን ምን ያደርግልናል? ከመዝገበ ቃላት ይፋቅልን! በምንልበት ጊዜ የቀነሰ ነገር በማየቴ ነው፡፡
ባለፈው ሰሞን፣ ዘመድ ሞቶብኝ በተለምዶ ዓለም ባንክ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ነበርኩ፡፡ ከቀብር መልስ ውሃ ጥም ሲያቃጥለኝ፣ አንድ ቢራ ልጠጣ ብዬ ግሮሰሪ ቤት ገባሁ፡፡ የምመርጠውን ቢራ ስጠይቅ “አለ” ተባልኩ፡፡ አካባቢው ሩቅ በመሆኑ ዋጋው ይጨምራል በማለት ሰግቼ “ስንት ነው?” አልኩ፡፡ አስተናጋጁ “12 ብር” አለኝ፡፡ መኻል ከተማ ከ13-16 የሚሸጠው ቢራ፣ እዚያ በ12 ብር መገኘቱ እያስገረመኝ ጠጥቼ ወጣሁ፡፡ በሳልስቱም ወደለመድኩት ቤት አመራሁ፡፡ ሁሉም ሰው ፊቱ ያስቀመጠው አዲሱን ቢራ ነው፡፡ የለመድኩትን ቢራ ጠየቅሁ፡፡ የለም ተባልኩ፡፡ ሌላ ቢራ ምን እንዳለ ስጠይቅ፤ አስተናጋጁ ሰዎች ፊት ያለውን እያሳየኝ “ከዚህ በስተቀር ምንም የለም” አለኝ፡፡ ዋጋውን ጠየቅሁ፡፡ 10 ብር አለኝ፡፡ ሌላ አካባቢ 12 እና 13 ብር የሚሸጡ ስላሉ፣ እየተገረምኩ ጠጥቼ ወጣሁ፡፡
በሌላ ጊዜ ደግሞ የረር-ጎሮ አካባቢ ነበርኩ፡፡ የምወደውን ቢራ ስጠይቅ አስተናጋጁ “እሱ የለም፤ ይኼን ይጠጡ ጥሩ ነው” አለኝ፡፡ ችግሬ ዋጋው ላይ ነውና “ስንት ነው?” አልኩት፡፡ “10 ብር ነው፡፡ ፋብሪካው‘ኮ  ከዚህ አስበልጠን እንዳንሸጥ አስጠንቅቆናል” አለኝ፡፡ የቢራውን ዋጋ የቀነሰው - ፋብሪካው መሆኑን ስሰማ፣ አዲሱ ቢራ ገበያ ውስጥ ለመግባት የቀየሰው ዘዴ ነው በማለት ደስ አለኝ፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ሌላ አስገራሚ ነገር አየሁ፡፡ ቢጂአይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ) አርማውን በያዘ ወረቀት ላይ የድራፍት ብርጭቆ እያሳየ ማክሰኞ፣ ሐሙስ፣ ቅዳሜ “Happy Hour” በማለት በየመጠጥ ቤቱ ለጥፎ አየሁ፡፡ እኔ ጊዮርጊስ ቢራም ሆነ ድራፍት ባልጠጣም የንግድ ውድድር የፈጠረው ነው በማለት በጣም ደስ አለኝ፡፡ ድራፍቱ፣ ከሆነ ጊዜ በፊት ዋጋ ጨምሮ ጃንቦው 11 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ አሁን ማክሰኞ፣ ሐሙስና ቅዳሜ 3ብር ቀንሶ በ8 መሸጥ ጀምሯል፡፡
ጊዮርጊሶች በአንድ ጊዜ 3ብር የቀነሱት፣ ደንበኞቹ በ10 ብር ወዳገኙት አዲስ ቢራ ስላዘነበሉ ጭራሽ እንዳይሸሹት ለማባበል ነው የሚል ግምት አደረብኝ፡፡ ወደፊትም ወደ ገበያው አዳዲስ ቢራ ፋብሪካዎች ሲገቡ የንግድ ውድድሩ ይጦፋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ የንግድ ውድድር ማን ተጠቀመ? ሸማቹ ህብረተሰብ፡፡ ለዚህ ነው ነፃ ገበያ ይለምልም ያልኩት፡፡ 

Read 2004 times