Saturday, 15 November 2014 10:50

ኒቼ እና እኛ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

        ቀዬውን ጥሎ ከተራራ ላይ ከመሸገ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬ ከምሽጉ ጋር ሰማኒያ ለመቅደድ የቆረጠበት ቀን ነው፡፡ ድንገት የስደት ባልንጀራውን ተራራውን ወደ ኋላ ጥሎ ቁልቁል ወደ ሰፊው መስክ ለመውረድ ተንደረደረ፡፡ ጥቂት ኪሎ ሜትሮችን ፈቀቅ እንዳለ፣ ቀዝቃዛው ንፋስ የሰዎችን ሁካታ እየቆነጠረ ከጆሮ ላይ ብትን ሲያደርግበት ተሰማው፡፡ ጠደፍ ጠደፍ እያለ ደረቱን የገለበጠውን አውላላ ሜዳ ከሩጫ ባልተናነሰ እርምጃ እንደ አጋመሰ በሰዎች ሁካታ ድብልቅልቅ ያለ የደራ ገበያ አገኘ፡፡ ገበያተኛው ይህንን ጸጉረ ልውጥ ልብ አላለውም፡፡ ከእዚህ ይልቅ አስማታዊ ትርኢት ለሚያሳየው አርቲስት ሁለመናውን ሰጥቷል፡፡ ጸጉረ ልውጡ ሰው ወደ ተሰብሳቢው ገበያተኛ ተጠጋና ይህንን አዋጅ ተናገረ፡-
“እዚህ እናንተ ዘንድ የተገኘሁት ከሰመመናችሁና ከድንዛዜያችሁ ትነቁ ዘንድ ጠቃሚ ዲስኩር ሹክ ልላችሁ ነው፡፡ የዲስኩሩ አርእስት ልዕለ ሰው ይባላል፡፡ ጆሮ ያለህ ስማ .. ጆሮ ያለህ ስማ …” አለ ድምጹን ከገበያው ሁኡካታ በላይ ከፍ ለማድረግ የአቅሙን እየተውተረተረ፡፡
ለእዚህ መጤ መንገደኛ ጆሮውን ያዋሰ አንድም ገበያተኛ አልነበረም፡፡ ሁሉም እንደ ለፍላፊ ወፈፌ በመቁጠር ወደ ጉዳዩ  ተመለሰ፡፡
ይህ መጤ ነብይ፣ ይህ የብዙሀን ጆሮን የተነፈገ ብጹሁ የኒቼ ዛራስቱስራ ነው፡፡ ፍሬደሪክ ኒቼ የሰው ልጅህ በመንፈሳዊ ጉስቁልና ተቀፍድዶ አበሳውን የሚያይ አሳዛኝ ፍጡር እንደሆነ ይናገራል፤ ስለዚህም ነው ብስራት አብሳሪውን፣ የንቃት ባልደራሱን ዛራስቱስራን እየደጋገመ የሚያውጅልን፡፡ የሰው ልጅ ካለበት ድቅድቅ ጨለማ ወደ ንቃት ጸሃይ ይወጣ ዘንድ ዛራስቱስራ በነብይነት የግድ መከሰት አለበት፡፡ ኒቼ የምናብ አብራክ ክፋዩን ዛራስቱስራን፣ መንፈሳዊ አዳኛችን አድርገን እንድንቀበለው በጥበብ እያዋዛ ሊሸነግለን ይሞክራል፡፡
የኒቼን ፍልስፍና ውስጠ ምስጢር በፈለፈልን ቁጥር ተመዘው ከማያልቁ ስነልቦናዊና ማህበራዊ ገበናዎች ጋር ፊት ለፊት መላተማችን አይቀሬ ነው፡፡ ፈላስፋው፤ ዛራስቱስራ የተባለውን ብጹህ ስብእናን ሲያስተዋውቀን እግረ መንገዱን የስነልቦና እርከኖቻችንን ጎሸም አድርጎ ያልፋል፡፡ በኒቼ አመለካከት የሰው ልጅ ሶስት የእድገት እርከን አለው፡፡ የመጀመሪያው ካሜል እስቴጅ ይባላል፡፡ በግመል ተፈጥሮ ብዙ ማጠራቀም ወይም ማከማቸት እንደ አንድ የስሜት ህዋስ ነው የሚቆጠረው፡፡ አንዲት ግመል አንዴ የጠጣችውን ውሃ እስከ ስድስት ወር ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ በእዚህ እርከን ላይ ያለ ሰው ልክ እንደ ግመሏ የማህበረሰቡን ባህል፣ እምነት፣ አመለካከት ብሎም የአኗኗር ዘይቤን እንደ ወረደ በውስጡ እያከማቸ የሚያመነዥግ ግብዝ ይሆናል፡፡ በእዚህ ሰውዬ መቃብር ላይ ሊነበብ የሚገባው መልእክት ይህ ነው፡-
“ከርሴ ተጭኖኝ ወደ ከርሰ ምድር ወርጃለሁኝ”
ሁለተኛው እርከን ላየን ስቴጅ ነው፤ ስለ አንበሳ ስናስብ ቁጡ ባህሪው፣ አልገዛም ባይነቱና ነውጠኛነቱ ውልብ ይልብናል፡፡ ይህኛውን እርከን የሚቆናጠጥ ሰው በድራጎን ከተመሰለው የማህበረሰብ አመለካከትና አገዛዝ ስርዓት ጋር ፊት ለፊት ይላተማል፡፡ በእዚህም ምክንያት  ብዙ ውክቢያና እንግልት ይደርስበታል፡፡ አሟሟቱ ከካሜል እስቴጅ ጋር ሲነጻጸር የጀግና ነው፡፡ እዚህኛው ሰው መቃብር ላይ ቃላት ሲደረደር ይሄንን ይመስላል፡-
አጥንቴም ይከስከስ ደሜም ይፍሰስላት
የማንም አይደለች ይህች ነፍስ የእኔ ናት
ወደ ሶስተኛው ደረጃ ስናልፍ ቻይልድ ስቴጅን እናገኛለን፡፡ ህጻናት በእምነቱም ሆነ በሳይንሳዊው ዓለም ያላቸው ተክለ አቋም አንድ አይነት ነው፡፡ የህጻናት ቤተመቅደስ ፍቅር እና ሰላም ነው፡፡ ወደ እዚህኛው ደረጃ የተሰቀለ ሰው ውስጡንም ሆነ አካባቢውን በቅድስና ይባርካል፡፡ ድንኮች ከሚበዙበት ግርግር መካከል ዘለግ ብሎ ይስተዋላል፡፡ መቃብሩ ላይ ቃላት ተሰካክተው ሲቆሙ ይህንን አይነት ቅርጽ ይይዛሉ፡-
“ህጻናትን ወደ እኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው ብለህ ባዘዝከው መሰረት ወደ አንተ መጥቻለሁኝ”
እኛነታችን እና ሶስቱ እርከኖች እንዲህ ተዛምደዋል፡-
ካሜል ምሁር
በግመል ልቦና ውስጥ ሁሉ ነገር አራት ነጥብ … ተከርቸም … ነው፤ ለፈጠራ ለመመራመር ከፍት የሆነ ስነልቦና ይነጥፋል፤ ግራ ቀኝ ከማያማትር እንደ ጋሪ ፈረስ ፊት ለፊቱን ከሚሸመጥጥ ግትር ስብእና ጋር ይወዳጃል፤ ሳይጠይቁ መቀበል፣ ሳይፈትሹ ማጥለቅ፣ ሳያላምጡ መዋጥ የግመል እስትንፋስ ነው፡፡
ኒቼ የዘር አጥር ሳይቸክል ለሰው ልጅ በሙሉ ያወጀውን የግመል ስብእናን ለመሰለል ስንነሳ፣ የእውቀት ባህላችንን ገበና መታዘብ እንጀምራለን፡፡ ግመል እና የእውቀት ባህላችን አንድ ሳምባን ነው የሚጋሩት፤ መሳ ለመሳ ኩታገጠም ስብእናዎች ናቸው፡፡ እንደ ግመሏ ብዙ ስናቁር፣ ስናከማች፣ ስንደራርብ የደህንነት ስሜት ይሰማናል፡፡ መጠየቅ፣ መገዳደር፣ ማፈንገጥ ከእውቀት መዘገበ ቃላታችን ላይ ተፍቀው ጠፍተዋል፡፡
የትምህርት ተቋሞቻችንም ቢሆኑ ይህንን የማቆር ግብር ከትውልድ ትውልድ እንዲሻገር ላይ ታች ከማለት አሰልሰው አያውቁም፡፡ እውቀትን እንደ መነባንብ ቃል በቃል ከመደጋገም ጋር የሚተካከል የተኮላሸ ስነልቦና በመዝራት የማይተካ ሚና ሲጫወቱ ኖረዋል፡፡ በተቋማቱ ውስጥ ያለፉ ደብተራ ሊህቃን እውቀት ማለት እንደወረደ የሚጠለቅ፣ እንደ ድግምት የሚደገም፣ መጠይቅን የሚያኮላሽ፣ እንደ ምፅአት ቀን የሚሰበክ፣ ከንፈር እየመጠጡ ጭንቅላትን እየወዘወዙ የሚደመጥ ብቻ እንደሆነ ለዘመናት ተሳስተው እያሳሳቱን ዛሬ ላይ አድርሰውናል፡፡ በእዚህም ምክንያት የእውቀት ምድረ በዳ ላይ የምንርመሰመስ ካሜል ምሁራን እንድንሆን ተፈረደብን፡፡ እኛም ትውልድ ለማስቀጠል መሃላችንን ላለማጠፍ መሰሎቻችንን ካሜል ምሁራንን ላይ ታች ብለን ለማብዛት ወገባችንን ሸብ ማድረጋችንን ተያያዝነው፡፡
በእርግጥ ካሜል ምሁራንን በማቆር ግብራቸው ብቻ አንኮንናቸውም፡፡ ማቆር በራሱ አጥፊ አይደለም፤ ማቆር እንደውም በሰው ልጅ እና እንስሳት መካከል ጠቃሚ ግንብ በመገተር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ዛሬ የተወለደች ድመት ከዛሬ አንድ ሺ አመት በፊት ከተወለደች ድመት ጋር በአስተሳሰብ አንድ አይነት ነች፤ የዛሬዋ ድመት ከዜሮ ነው የምትጀምረው፣ ከእዚህ ቀደም ከነበረው የድመት ማህበረሰብ ምንም አይነት ተሞክሮ እና ልምድ ቀስማ የዛሬውን ህይወቷን አትጀምርም፡፡ እኛ ግን በእዚህ ረገድ ለማቆር ምስጋና ይግባውና በተጻራሪ ጽንፍ ላይ መቆም ችለናል፡፡ ከባዶ፣ ከዜሮ አንጀምርም፡፡ ካቆርነው መሰረት አሀዱ እንላለን፡፡
ስለዚህ ማከማቸት፣ መከመር በራሱ መርገምት አይሆንም፡፡ ወደፊት ለመስፈንጠር እንደ መነሻ ንጣፍ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ችግሩ የሚመጣው የቃረምነውን እውቀት እንደ ሃይማኖት መቁጠራችን ላይ ነው፡፡ መተቸት ኩነኔ እየሆነብን፣ በአእምሯችን ያከማቸነውን እውቀት እንደ ድግምት እየደገምን፣ እንዴት የተለየ የፈጠራ ሰው ልንሆን እንችላለን፡፡
ላየን ማህበረሰብ
አንበሳ የእኛ ኢትዮጵያውያን የመንፈስ ጥንካሬ መግለጫ ነው፡፡ ነጭ፣ በበርሊን ሸንጎ ጥቁር ህዝብን በግዞት ለማኖር ምሎ ተገዝቶ አፍሪካ ላይ ሲዘምት፣ ፊት ለፊት በብቸኝነት የተፋለሙት አባቶቻችን ሁልጊዜም በታሪክ የሚዘከሩ ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ አልበገር ባይነታቸው፣ የአላማ ጽናታቸው የጥቁር ህዝብ ለደረሰበት የልብ ስብራት ጠጋኝ ሆኖ ኖሯል፡፡ በእዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ የሚለው ቃል፣ ከቃል በላይ ሆኖ የመንፈስ ጥንካሬንና ሀይማኖታችን እስከ መወከል ይደርሳል፡፡
ግራ አጋቢ አመክንዮ ላይ የምንደርሰው ግን አንበሳውን ወደ ቤታችን ስናመጣው ነው፡፡ አንበሳው በቤቱ ጭምት መሆንን ይመርጣል፡፡ ለወንዙ ለአድባሩ ለማዳ ባህሪውን ከመጋበዝ አይቦዝንም፡፡ ለውጪ ቀጋ ለውስጥ አልጋነቱን በግብሩ ይመሰክራል፡፡ አንበሳው ዱካ ከእንደራሴዎቻችን ፊት ባይተዋር ነው፡፡
የእኛው አፈር ያበቀላቸውን ገዢዎቻችንን እንደ ባእድ ጸጉረ ልውጦቹ በግሳታችን፣ በጩኸታችን ለማስበርገግ ጎሬያችንን ለመክፈት ስንዳዳ አካላችን አልታዘዝ ይለናል፡፡ ከማጉረምረም ይልቅ እጣ ፈንታ ላይ በማላከክ ከንፈር እየመጠጡ ማዝገምን ምርጫችን እናደርጋለን፡፡ ከፍ ዝቅ ለሚያደርጉን እንደራሴዎቻችን ሆደ ሰፊ የምንሆንበት ወሰን በእጅጉ የተጋነነ ነው፡፡
እዚህ ጋ የሰጎኗን ታሪክ ማንሳት ተገቢ ነው፤ ሰጎን በበረሃ ውስጥ ሊበላት የመጣን አውሬ እንዳመለጠችው የምታስበው ጭንቅላቷን፣ አሸዋ ውስጥ በመቅበር ነው፤ አውሬው ጥፍሩን እየሳለ ጥርሱን እያንቀጫቀጨ ከአጠገቧ ደርሶ ሰጎን ሆዬ አውሬውን ስላላየችው ብቻ ከመበላት እንደምትተርፍ ከአጓጉል ድምዳሜ ላይ ትወድቃለች፡፡
ሆደ ሰፊነቱ በዋለ ባደረ ቁጥር እኛም በሰጎኗ መላ ምት ከመደባበስ አንተርፍም፤ ገራገሩ መላ ምት አቅላችንን እንደ መርግ ተጭኖ ድብታውን ያበዛብናል፡፡ አንበሳውን ስብእናችንን ለጉሞ የበይ ተመልካች እንድንሆን ይፈርድብናል፡፡
ቻይልድ መሪ
የጥንቱ የጠዋቱ ግመል በጊዜ ሂደት ጥፍርና ጥርስ አብቅሎ ከአገኘው ጋር የሚላተም ነውጠኛ አውሬ ሆኖ ነበር፡፡ አውሬውም ጊዜው አለፈበትና ከንቃት ከፍታ ላይ ተሰቅሎ የነውጡን አለም ለአፍታ ከሰለለ በኋላ ሰላምና ፍቅር ወደ ሚፈነጩበት ኤደን ገነት ከተመ፡፡ የጨቀየውን የነውጥ አለም ክፉኛ ተጠየፈው፡፡
አሁን የሚናከሰው የሚያቆስለው አንበሳ ወደ ሰላማዊ ህጻን ተቀይሯል፡፡ ስለታም ጥፍሮቹ እንደ ሀር ለሚለሰልሱ መዳፎች ቦታቸውን አስረክበዋል፡፡ መዳፎቹን የነካ በሙሉ ከቅድስናቸው በረከት ይቋደሳል፡፡ አድሎዎና መድሎዎ የመዳፎቹ ደመኛ ጠላት ናቸው፡፡ ጡቻና ሀይል በፍቅር እዝ ምርኮ ስር ይወድቃሉ፡፡ የመዳፎቹ ጠረን እንደ ሰባሰገል እጣን በመልካም መአዛ ያውዳል፡፡
በእዚህ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች በማህበረሰቡ ውስጥ ቢበዙ ፍርድ ቤቶች ስራ ይፈታሉ፡፡ የህግ ሙያ አዋጪ የስራ መስክ መሆኑ ይቀራል፡፡
በታሪክ በጣም ውስጥ በሆኑ አጋጣሚዎች ራሳቸውን ለህዝባቸው ክብርና ነጻነት አሳልፈው የሰጡ ብጹህ ህጻናት በሁሉም የአለማችን ጥግ ተስተናግደው አልፈዋል፡፡ ጋንዲ፣ ማንዴላ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ እያልን መዘርዘር እንችላለን፡፡ እነዚህ ሙሉ በሙሉ በህጻናት ካምፕ ውስጥ የተፈጠሩ ስብእናዎች ነበሩ፡፡ ህጻናት አለምን የሚተረጉምበት መዝገበ ቃላት ከብዙሃኑ ጋር አይገጥምም፡፡ በናዚ ጭፍጨፋ ወቅት አንድ ታሳሪ አይሁዳዊ የተናገረው ፍሬ ነገር የጨቅላ ማህበረሰብን ይወክላል፡-
“በእርግጥ የእናንተ እስር ስጋዬን መሸበብ ይቻለው ይሆናል፡፡ በእርግጥ የእናንተ ጎራዴ ጭንቅላቴንና አካሌና መቆራረጥ ይቻለው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ነፍሴን ሊሸራርፏት አይችሉም፡፡ ነፍሴ ከአደጋና ከበትር የራቀች ናት” ብሎ ነበር፡፡ በህጻናት አይን እስር ቤት እንዲህ ከፍ ያለ ትርጉም አለው፡፡ በእዚህ መሰሉ ፈተና ውስጥ ሆነው እንኳን የብርሃናቸው ጸዳል ለእልፍ አዕላፍ ይተርፋል፡፡ እነርሱ የሚያዩትን ብርሃን ብዙሃኑ እንደ ድቅድቅ ጨለማ ነው የሚቆጥረው፡፡ ስራቸው በሙሉ ከተራው ሰው ጋር አይገጥምም፡፡
እኛም በታሪካችን ብጹህ ህጻን አላጣንም፡፡
“ህዝቤ በባእድ ሀይል እንደ በግ እንዲነዳ ተባባሪ አልሆንም፣ ከእኔ ህይወት የሀገሬ ነጻነት ይበልጥብኛል፣ ሞትን ቀድሜ ሞቼ አቸንፌዋለሁ፤ የህዝብ ልእልና ከእኔ ስጋ ልእልና ጋር ለየቅል ነው፤ ህዝብ ይዳን ስጋዬ ይቀበር” ብለው ለህዝባቸው ክብር ጭዳ የሆኑት ታላቁ አቡነ ጴጥሮስ ህያው ተምሳሌታችን ናቸው፡፡
የእኛን ቻይልድ መሪ በአቡነ ጴጥሮስ ስብእና ውስጥ እናገኘዋለን፤ ጎተራውን ሙሉ ለማድረግ እጅ የማያጥረው፣ ተድላና ፍስሃን በየማጀቱ የሚረጭ፣ ፍትህና መብትን የማያጎድል፣ እንደ ገራገር አባት ራሳችንን በፍቅር የሚደባብስ፣ እንደ ሻማ ቀልጦ እኛን ለማኖር ፊት ለፊት የሚሰለፍ ሰማእት … የእኛ ህጻን … የእኛ … ብጹህ … የእኛ … አቡነ ጴጥሮስ …. ነው፡፡  
ህፃናትን ያብዛልን!!

Read 2882 times