Saturday, 15 November 2014 10:45

የደብረዘይት ጉዞዬ ነገር መጨረሻ

Written by  ነቢይ መኮንን-
Rate this item
(0 votes)

ካለፈው የቀጠለ    -


“ለብቻ አሪፍነት የለም፤” አብረን እንሥራ፣ አብረን እንደግ!
***
“የዘመኑ ወጣት ራሱ ከነገር፣ ምላሱ ከሱስ፣ እጁ ከፌስ-ቡክ ቢላቀቅ፤ ትልቅ ሥራ እንፈጽማለን”
ከአዲሳባ ደብረዘይት 4.45 ሰዓት ፈጅቶብን የመጣንበት ስብሰባ እንደቀጠለ ነው፡፡ የጄክዶ ሥራ አስኪያጅ ከ2013 እስካሁን ያለውን የሥራ ሂደት ገለፁ፡፡ የ36 ምስርት ድርጅቶች አቅም መገንባቱን፣ ከትንሽ ወደሰፊ ማደጋቸውንና ሲዳ ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ካለፉ 6 ድርጅቶች መካከል የኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት አንዱ እንደሆነ አስረዱ፡፡
ለምን እንዳሸነፉ ያስረዱበት መንገድ ገርሞኛል፡፡ ምክንያቱም ማንም ለህብረተሰብ ዕድገት የሚሰራ አካል እነዚህን ማጠየቂያዎች (justifications) ቢያቀርብ መልካም መንገድ ነው ብዬ ስለማምን ነው፡፡ እስቲ እንያቸው፡-  
በምሥርት ማህበራት የባለቤትነት         ስሜት አለ ብለን እናምናለን፡፡
ተጠሪነት አለ ብለን እናምናለን፡፡
ስለምትተዋወቁ ትተማመናላችሁ -    ብለን እናምናለን፡፡
በአካባቢያችሁ ሀብት አለ - ባላችሁ    ሀብት ላይ ነው እየጨመራችሁ    የምትሠሩት - እንጂ ከ0 አትነሱም         ብለን እናምናለን፡፡
ውጤታማ ትሆናላችሁ ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም የባለቤትነት ስሜት ካለ፣ ተጠሪነት ካለ፣ መተማመን ካለ ውጤት አለ
ዘላቂ (Sustainable) ናችሁ ብለን         እናምናለን፤ በማንም ግፊት ሳይሆን     በራሳችሁ እየተንቀሳቀሳችሁ ስለሆነ፡፡
ልማቱም፣ ጥፋቱም፣ የችግሩ         መነሻም፣ መፍትሔም፣ ለውጥም፤         እዛው እናንተጋ አለ ብለን             እናምናለን፡፡
እኛ እንግዲህ ተወዳድረን ፍሬያማ የሆነው እነዚህን ይዘን ነው፡፡
ቀጥለው ከ72 ማህበራት የዛሬዎቹን ተሳታፊዎች እንዴት እንደለዩ ሲገልፁ፤ “72 ምሥርት ማህበራት ከተለያየ የአገሪቱ ክፍል አመለከቱ፡፡ 40ዎቹን ለመለየት የአማካሪ ቡድን ባለሙያዎች ከውጪ መሠረትን፡፡ በርካታ የምዘና ሥራዎች ተካሄዱ፡፡ ማንም ያንን መጠየቅ ይችላል፡፡ እናንተ ተመረጣችሁ - እንኳን ደስ አላችሁ” አሉ፡፡ ጭብጨባው አስተጋባ፡፡
በመጨረሻም ስለመፈራረም ያሳሰባቸውን ጉዳይ አነሱ፡- “ከተፈራረማችሁበት ሰዓት ጀምሮ ገንዘቡን በትክክል በሥራ ላይ ለማዋል ብርቱ መሆን ይኖርባችኋል፡፡ ለውጤት መሥራት አለባችሁ፡፡ ሥራ ተሠራ የሚባለው ውጤት ሲመጣ ነው፡፡ የ10 ልጆች ህይወት ቀይረናል፤ ስንል የእነዚህ ልጆች ህይወት መቀየሩን የሚያሳይ ተጨባጭ ነገር መኖር አለበት፡፡ ት/ቤት አይሄዱ ከሆነ መሄድ መቻላቸውን፣ አልባሳት ማግኘታቸውን፣ ደብተር ማግኘታቸውን ወዘተ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ከህብረተሰቡ ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠራቸውን ማረጋገጥ ያሻል፡፡ በተጨባጭ!”
ቀጥለው ገንዘብ (Fund) ማግኘት እየከበደ መምጣቱንም ገልፀዋል፡፡ የሁላችን፣ የአገራችንም ችግር ነውና እናስተውለው:-
“ገንዘብ ማግኘት በዓለም ላይ እየጠበበ መጥቷል፡፡ ብዙዎቹ አገሮች ወደ አገራቸው ውስጥ ጉዳይ ማተኮር ጀምረዋል፡፡ ስለሆነም ወደኛ አያዩም፡፡ ገንዘብም ቢሰጡ እነሱን የሚጠቅም ነገር እስካለ ብቻ ነው፡፡ ከእርዳታ ይልቅ ንግድ፣ ከማህበራዊ ልማት ይልቅ ኢንቨስትመንት ይቅደም ተብሏል፡፡ ዓለም ተለውጧል፡፡ ከዓለም ጋር መሄድ አለብን፡፡” …  
“ዋናው ነገር” አሉ በመጨረሻ፤ አገራዊ ፋይዳ ያለው ማጠቃለያ ነው የሰጡት:-
“በጋራ የሚያስመሰግን ሥራ ሠርተን፣ የምንሠራውን ወደን፣ ወገኖቻችንን ጥቅም ሰጥተን፣ በሥራችን ደስተኛ ሆነን፣ የመንፈስ እርካታ አግኝተን፣ የዜግነት ግዴታችንን እንደምንወጣ እርግጠኛ ነኝ! ለዚህ አደራዬ የጠበቀ ነው!” ብለዋል፡፡
የማህበራት አባላቱ እርስ በርስ በመተዋወቅ ሳሉ ደጅ የተፃፈውን የማስተዋወቂያ ሰሌዳ ሳነብ ቆየሁ - መሪ - ሰሌዳው፤
“የኢህማልድ ሲዳ የልማት አጋርነት ፕሮግራም የማህበረሰብ ምሥርት ተቋማትን አቅም በማሳደግ ማህበረሰብን መሠረት ያደረገን ወላጆቻቸውን ያጡና ለችግር የተጋለጡ ህፃናት ድጋፍና ክብካቤ ፕሮግራም የፕሮጄክት ውል ስምምነት ሥነስርዓት” ይላል፡፡
ከማዶ “ምክረ - ሀሳቦች” የሚል ርዕስ ያለው ሰሌዳ ይታየኛል፡፡ ለማንኛችንም የሚጠቅሙ ነጥቦች ተነቁጠውበታል:-
የውል ሰነዱን በሚገባ መገንዘብ፤ የሁኔታዎችን ሪፖርት በመከታተል መሰነድ፣ የተጠቃሚዎችን የፆታ ስብጥር ማመጣጠን፡፡ የንዑሣን ኮሚቴ አባላት መተካካት፤ ዕገዛና ምክርን መሻት፤ ከአካላት ጋር መሥራት ውሳኔዎችን በቃለ - ጉባዔ ማስደገፍ፡፡ ሌላው ዐቢይ ርዕስ ለውጤት መትጋት ይላል፡፡ የመንግሥት አካላትን ጨምሮ ከሌሎች አካላት ጋር መሥራት፣ የአካባቢ ሀብትን ማንቀሳቀስ፣ የእርስ በርስ መግባባትን ማዳበር፡፡ በጐ ፈቃደኞችን ማብዛትና ሁሌም የተሻሉ ሆኖ ለመገኘት መጣር” ይላል ከታች፡፡ ተመልሼ ወደ ስብሰባው ገባሁ፡፡
የዕለቱ የመድረክ መሪ፤ አቶ ተዋበ ይዘንጋው፤
“የፕሮግራሙ አተገባበርና የሚጠበቁ ውጤቶች የምዘና ሥርዓት፤ ፕሮጀክቱ የሚያመጣቸው ተጨባጭ ለውጦች፤ የሚለውን አቶ ተስፋዬ የሰው ኃይል ማደራጃና የአቅም ግንባታ ኃላፊ፤ ያቀርባሉ፤ በጥሞና ተከታተሉ፣ ነጥብ ያዙ፤ ብለው አስገነዘቡ፡፡
አቶ ተስፋዬም፤
“ሥራዎቹ የሚካሄዱባቸውን ቦታዎች “ብሾፍቱ፣ ድሬዳዋ፣ ሻሸመኔ፣ ደብረ ብርሃን፣ ሽኒሌ፣ ቡታጅራ፣ ጂማ፣ አዲሳባ፣ እንድብር፣ ደብረሲና፣ ደብረማርቆስ፣ ባህርዳር፣ ላይ ጋይንት ወዘተ ጠቅሰው ሲቆጠሩ ወደ 17 ገደማ መሆናቸውን በጥቀስ ጀምረው ስለህፃናት እንክብካቤ የከፋ ገጽታ፡፡ አስረዱ፡፡ ከዚያም ስለ አሳዳጊዎች የኢኮኖሚ አቅም ማጐልበት አወሱ፡፡ “የየማህበሮቻችሁን አቅም አጐልብቱ” አሉ፡፡ ቀጥለውም፤ “በጋራ ልናመጣቸው የምንችል 15 ውጤቶች አሉ ብለው ቀጠሉ፡፡ ያሉን 42 ማህበራት ናቸው 2ቱ በኤልማ የተካተቱ ናቸው፡፡ ለ540 ልጆች አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት መስጠት፣ ድጋፍ በማጣት ከት/ቤት የወጡ ተማሪዎችን መርዳት (በ10% ይገመታል)፣ 80% የልጆች ትምህርት ሁናቴ ማሻሻል፣ ሴቶችን መደገፍ (600 ያህል ታቅፈዋል)፤ ለ1ኛ ደረጃ ያልበቁ 60 ያህል ህፃናት ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ፣ 3300 ጐልማሶች አቅም ማዳበር፣ 180 ወጣቶች ተምረው ሥራ ያልያዙትን ሥራ ማስያዝ (ሥራ መፍጠር)፣ ጥቃት የደረሰባቸው ህፃናትን ማገዝ፣ 2000 ሰዎች በህፃናት ዙሪያ ግንዛቤ ማስገኘት፣ እናንተ ማህበራቱ አቅማችሁ መገንባቱን ማረጋገጥ ነው፡፡ ዘንድሮ አበረታች ፕሮፖዛሎች በመቅረባቸው እጅግ ደስተኞች ነን” ብለዋል፡፡
መልክ ያለው ፕሮፖዛል ስለሆነ መልክ ያለው ስብሰባ ዛሬ ፈጥሮልናል” የሚል ቁልፍ ሃሳብ አስቀምጠዋል፡፡ “የሚያነክስ የገቢ ማስገኛ በፈፁም አይፈቀድም” ያሉት ሌላ ፋይዳዊ ዐረፍ-ነገር ነው፡፡ ያቅም ማጐልበት ሥራ ኃላፊ ስለሆኑ ጉዳዩ ጉዳያቸው መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡
ገንዘብ የሚጠየቀው ማዕከላዊ ጽሕፈት ቤት መሆኑንና ከዛ ውጪ አስፈቅዶ አሳምኖ ሌላ ሥራ ለመሥራት ማስፈቀድ እንደሚቻልም አበክረው ገልፀዋል፡፡ ከዚያም ቦታዎችንና ማዕከላዊ ኃላፊነት ያላቸውን ጽ/ቤቶች አጣቅሰው አሳውቀዋል! ለምሳሌ ሽንሌና ድሬዳዋ ከድሬዳዋ ሲፒኦ ጋር ይሠራሉ” ብለዋል፡፡ ስለአመራር አሠራርና ውሳኔም አሳስበዋል፡፡
“ባትጣሉ ደስ ይለናል፡፡ በሥራው ምክንያት በተለይ ግን አትጣሉ!” “የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር የህዝብ ቁጥር መጨመር ባግባቡ ከተጠቀምንበት በጣም ይጠቅማል” ያሉትንም አስምረውበታል፡፡ ቀጥለውም “የዘመኑ ወጣት ራሱ ነገር፣ ምላሱ ከሱስ፣ እጁ ከፌስቡክ ቢላቀቅ ትልቅ ነገር እንፈጽማለን!” ያሉት ትውልድ - አቀፍ ቁም - ነገር ነው፡፡
በመጨረሻም “የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን “ሲቢኦ”ዎች Community Based Organization) እንሸልማለን” ያሉ ሲሆን “በፈረንጆች ታህሣሥ 19 አውደ ርዕይ ይኖራል፡፡ ለሌሎች ሥራችሁን ማስተዋወቂያ ነው” በሚል መረጃዊ ማስታወሻ ሰጥተዋል፡፡
አባላቱ በተሰጠው ማብራሪያ ላይ ጥያቄዎችን አቅርበው የሰው ኃይል ጉልበት ማደራጃ አላፊው ማብራሪያ ሰጥተውበታል፡፡
ቀጥለውም ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ተስፋዬ የጄክዶ /ኢየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት/ የሂሳብ ክፍል ኃላፊ ስለ ስምምነቱ ሂሳብ አጠቃቀም አጠቃላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በትኩረት - ነጥብ ደረጃም፣ ማህበራቱ ከዚህ ቀደም ብዙ እንደተነጋገሩበትና ስልጠናም እንደወሰዱበት ገልፀው፤ እንደ መንደርደሪያ ለማሳሰብ፤ “የአሁኑ አሰራራችን እንደቀድሞው ተደጋግፈን የምናልፈበት አይደለም፡፡ እኛ ብናልፋችሁ ከሲዳ ይመጡና ይቆጣጠሯችኋል፡፡ ስህተት ከተገኘ አንዱ ሳይሆን 40ችንም እረብ ነው የምንለው፡፡ ስለዚህ የሚፈለገውን ማሟላት ግድ ነው ማለት ነው፡፡
…የገንዘብ መቀበያ ደረሰኝ፣ የገንዘብ መክፈያ፣ የዕቃ መረከቢያ ሰነድ፣ ዕቃ ማውጫ ሰነድ፣ የግዢ መጠየቂያ፣ የዕቃ መጠየቂያ ያስፈልጉናል፡፡ ተከታታይ ቁጥር ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ ካለን እሰየው! አለዛ መዘጋጀት! ሥራ ሳትገቡ እነዚህን ልብ በሉ!” ብለው አፅንኦት አድርገዋል፡፡ ከባንክ ጋር የሚሰራውን ሂሳባዊ ሂደትና ጥንቃቄም በሚገባ አብራርተዋል… የመንግሥት ቅድመ-ሁኔታዎችንም በቅጡ አውስተዋል፡፡
ወ/ሮ ኤልሣቤጥ እጅግ ጠቅላይ ሂሳብ - ነክ ማብራሪያ አቅርበው፣ የምሣ ፕሮግራም እንደሚኖር የመድረኩ መሪ አቶ ተዋበ አሳውቀው እግረ - መንገዳቸውን ግን ዋና ዋና የግንዛቤ ነጥቦች ያሏቸውን ተሰብሳቢዎቹ ልብ እንዲሉ ነቁጠው የምሣ ጊዜ ሆነ፡፡ ከምሣ መልስ አጠቃላይ ውይይት በሥራ አስኪያጁ በአቶ ሙሉጌታ ገብሩ መሪነት ቀጠለ፡፡ አያሌ ግር - ያሉ ነጥቦች ለምሳሌ “አንዱ ባጠፋ ለምን ሁሉ ይቀጣል?...ወዘተ” ተነስተውና የሚሰጠው ገንዘብ ትንሹ ብር 750,000 ትልቁ ብር 800,000 መሆኑ ተገልጦ፤ ወደ ውል ስምምነት ፊርማ ስነ - ሥርዓት ተገባ፡፡ የየማኅበራቱ ተወካዮች መጥተው ሰነድ መፈረሙን አካሄዱ፡፡
አጠቃላይ የስምምነት ፕሮግራሙ በዚሁ አበቃ
የመዝጊየ ንግግሩን አቶ ሙሉጌታ ገብሩ አደረጉ ህጋዊነትን አሰመሩበት፡፡ አደራቸውን አጉልተው ነገሩ፡፡ የህዝባዊ አገልግሎት ሥራ ግልጽነት እንደሚጠይቅ አበክረው ተናገሩ! ወገናዊነትን አጥፉ፤ ታገሉ - ለህሊናችሁ ሥሩ!! የአመራር አግባብና ቆራጥነትን አስቀድሙ፡፡ ፖለቲካ የእኛ ሥራ አይደለም፡፡ የእኛ ሥራ ልማትና ኢኮኖሚን ማገዝ ነው! የእኛ ማዕከል ደሀው ህዝብ ነው፡፡ ጥረታችንም የሁላችንም ነው! ሲሉ አበክረው ገለፁ! እንደመጣነው ሳይሆን ከደብረዘይት አዲሳባ በአርባ አምስት ደቂቃ ፉት አልናት! ተመስገን ነው!!


Read 1401 times