Print this page
Saturday, 15 November 2014 10:44

“…እኔስ ይሉኝታን እንዴት ልገላገለው!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው ሚስት ፈላጊ ነው፡፡ እናማ…አገባታለሁ ለሚላት ሚስት መስፈርቶች ያወጣል፡፡ ለጓደኛውም … “እኔ የምፈልጋት ሚስት መልካም ባህሪይ ያላት፣ ብልህና ቆንጆ መሆን አለባት…” ይለዋል፡፡
ጓድኝዬው፣ “ታዲያ አስቀድመህ  እንደዚህ በግልጽ አትነግረኝም ነበር፣“ ይለዋል፡፡
ሰውየውም፣ “ይኸው ነገርኩህ እኮ…“ ሲል ይመላሳል፡፡
ጓደኝዬው ምን ቢል ጥሩ ነው… “ገና አሁን ነው ግልጽ የሆነልኝ፡፡ አንተ እኮ የምትፈልገው አንድ ብቻ ሳይሆን ሦስት ሚስት ነው፡፡ አንዲት መልካም ባህሪይ ያላት፣ አንዲት ብልህና አንዲት ቆንጆ፡ ሦስቱንም አንድ ላይ የያዘች ሴት ከፈለግህ ልብ ወለድ አንብብ!” አሪፍ አይደል!  በቃ… እዚህ ላይ እኮ ይሉኝታ አያስፈልግም፡፡ እሱ ማን የማይሆን ጥያቄ ጠይቅ አለው! ልክ ነዋ… ዘንድሮ እኰ እንትናዬዎቹ በአንዱ ነገር “ክንፍ አላት…” ሲባሉ በሌላው ደግሞ “ከእነጭራዋ ብቅ አለች…” ይባላሉ፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…እንዲህ አይነት ያለ ይሉኝታ እቅጯን የሚናገሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ነገርዬው “…ሦስቱንም አንድ ላይ የያዘች ሴት ከፈለግህ ልብ ወለድ አንብብ!”  
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው…ብዙም ከሰው አይገጥምም አሉ፡፡ እናላችሁ…ሠርግ አይሄድ፣ ሀዘን ላይ አይገኝ፣ አብሮ ‘ብርጭቆ አያጋጭ’…በቃ ምን አለፋችሁ በራሱ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነው፡፡ እናላችሁ… አንድ ቀን ምን ይሉታል…
“ያቺ ዱሮ ትወዳት የነበረችው ቆንጆዋ ገርል ፍሬንድህ ባል ሞቷል፡፡ ሁልጊዜ ሀዘን ላይ አትገኝም ስለምትባል ቀብር እንዳትቀር …” ሲሉት ምን ቢል ጥሩ ነው… “እንኳን ሞተ፣ እኔም የምፈልገው እሱን አልነበር…” ይላል፡፡
በሌላ ቀን የሚስቱ ወንድም ይሞታል፡፡ ይህን ጊዜ ቀብር ላይ ተገኝቶ ሳይሰናበት እንኳን በዛው ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ሚስቱና ሌሎች ዘመዶች ሠልስት፣ አርባ ምናምን ሲሉ እሱ አይገኝም፡፡ በዚህ የራሱ ዘመዶች ሳይቀሩ ይበሳጩበታል፡፡ “አሁንስ አበዛው! አንድ ነገር ይደረግ…” ይባባሉና ሄደው የሚያናግሩት ሦስት ሽማግሌዎች ይመረጣሉ፡፡
ታዲያላችሁ…አንደኛው ሽማግሌ “ለዚህስ ሌላ ሰው አያስፈልግም፣ እኔ ብቻዬን ሀሳቡን አስለውጬ ወደ ጥሩ ኢትዮዽያዊነት እመልሰዋለሁ…” ይላሉ፡፡
ከዛ ይሄዱና እንዲህ ይሉታል…
“አንተ ችግርህ ምንድነው? እኛስ ምን አድርገንሀል! ማንም ሰው ሀዘን ላይ አትገኝም፡፡ አሁንም የሚስትህ ወንድም ሞቶ ቀብር ላይ ብቅ ብለህ በዛው ጠፋህ፡፡ ይሄ ነገር ይብቃ፡ ሰው ቀብር ላይ መገኘት ልመድ...” ይሉታል፡፡
እሱዬው ምን ይላቸዋል… “እኔ ትልቁን በሽታ ገድዬ ቀብሬዋለሁ…” ይላቸዋል፡፡
የተላኩት ሰው ግራ ይገባቸውና… “ምን የሚሉት በሽታ?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡
እሱም… “ይሉኝታ የሚባል በሽታ…” ይላቸዋል፡፡
ሽማግሌ ሆነው የሄዱትም ሰው ትንሽ አሰብ አድርገው ምን ቢሉ ጥሩ ነው… “አንተስ ተገላገልከው፣ እኔስ ይሉኝታን እንዴት ልገላገለው!” ብለው ቁጭ፡፡
እሳቸውም ነገሮችን የሚያደርጉት በይሉኝታ ነዋ!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… እዚህ አገር ተጋፍቶ ይቅርታ መጠየቅ ከሲኒማ አድዋ ጋር አብሮ ፈርሷል እንዴ! እኛ ‘ደቃቆቹ’ ግራ ገባና! (በነገራችን ላይ…በአካልም የደቀቅን፣ በፈራንካውም የደቀቅን፣ በሞራሉም የደቀቅን፣ በተስፋውም የደቀቅን… ሰብሰብ ብለን “አይዞህ ለደግ ነው…” “አይዞሽ ሊነጋ ሲል ይጨልማል…” እያልን የምንጽናናበት ማህበር ቢጤ ብኗቋቋም አሪፍ አይደል!
ደግሞላችሁ…አሁን፣ አሁን ደግሞ ክንድና ደረቱን እየተነቀሰ በ‘ቢጢሌ’ ካናቴራ ከተማዋ ውስጥ የሚንጎማለል በዝቷል፡፡ ታዲያላችሁ… በትከሻው ዘፍ ይልባችሁና…አለ አይደል… እሱ በተጋፋው እናንተ በተገፋችሁት ገላምጧችሁ ይሄዳል፡፡ (“ጡንቻ የሚያሳብጥ ኪኒን ከዱባይ እንደ ልብ ይገባል…” የሚባለው እውነት ነው እንዴ!
እናላችሁ…ሲመጡብን ‘ጥግ እንዳንይዝ’…አገሩ ሁሉ ተቆፍሮ ‘የምንለጠፍበት ጥግ’ አጣን፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…
እናላችሁ…ይሉኝታ የሚመስል ነገር መነሳት ካለበት እዚህ ላይ ነው፡፡ ‘መድቀቃችንን’ አይቶ ገፍትሮን ከመሄድ ይቅርታ ማለት ለመንግሥተ ሰማያት ‘ሲ.ቪ.’ ማጠናከሪያ ይሆናል፡፡ ልክ ነዋ…ዘንድሮ የምንገፈተረው መንገድ ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የህይወታችን መስኮች ሆኗላ!
ስሙኝማ…በዛ ሰሞን አንድ ሚኒባስ ውስጥ የሆኑ ሦስት ሰዎች ጓደኛቸው ለልጁ የስም መዋጮ እንዲያደርጉ ጠይቋቸው ግራ ገብቷቸው ሲጨቃጨቁ ነበር፡፡ አስቸጋሪ ነዋ…አሁን፣ አሁን እኮ አይደለም ጓደኛ ምናምን ወላጆችም ራሳቸው ስም በማውጣቱ ግራ የተጋቡ ነው የሚመስለው፡፡
ሀሳብ አለንማ…ወይም ወላጆች “ለልጄ ስም አውጣልኝ…” ምናምን ሲሉ…አለ አይደል…አብረው ‘ቲ.ኦ.አር.’ ምናምን የሚባለውን ነገር ይላኩልን፡፡ ስሙ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለውና ልጁ ድንገት የፊልም ተዋናይ ቢሆን ለአፍ የሚጣፍጥ ምናምን ተብሎ እቅጩ ይጻፍልን፡፡
ወይም ደግሞ…“የሚወጣው ስም የአሜሪካን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበና ልጁ በኋላ ዲጄ ሊሆን ስለሚችል ለእሱ የሚስማማ መሆን አለበት…” ተብሎ ይለይልንማ!
እኔ የምለው…የስም ነገር ካነሳን አይቀር…ለልጆች የምንሰጣቸው ስሞቻችንና የቡቲኮቻችን ‘የፈረንጅ ስም’ እየተመሳሰሉብን ነው፡፡ አሀ… ምን ይደረግ… ይሄ ኢንተርኔት የሚሉት ነገር ‘ቆርጦ መለጠፍ’ አስለመደንና ስሞች ሁሉ ‘ከት ኤንድ ፔስት’ እየተደረጉ ነው፡፡
ከሀበሻ እናትና አባት እዚህቹ በግርግር ትንፋሸ ያጠራት ከተማችን ውስጥ የተወለደን ‘ፍራንክ’ ብሎ ስም መስጠት ትንሽ አያስቸግርም፡ ወዳጆቼ እንደዛ አይነት ስም መስማታቸውን ነግረውኛል፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል እዚህ አገር… “እሱን እንኳን ተወው፣ እንዲህማ አይደረግም…” ብሎ ነገር እየቀረ ነው፡፡ ሌላ ቦታ ሊደረግ የማይችለው ነገር… ‘አዲስ ነገር መፍጠር’ በማይሰለቻት፣ ‘ከአፍሪካ የመጀመሪያ ከዓለም ሁለተኛ’ ማለት ዓመል የሆነባት አገራችን ውስጥ ሊሆን የማይችል ነገር በጣም ጥቂት ይመስላል፡፡
እኔ የምለው…አንድ ሰሞን ፑሽኪን ‘የእኛ ነው፣ አይደለም’ ምናምን አይነት ሙግት ነበረላችሁ! ‘ቡና አብረን መጠጣት ያቆምናቸው’ ጎረቤቶቻችን በበኩላቸው “ፑሽኪንማ የራሳችን ነው!” እያሉ በላ ልበልሃ ነገሮች ነበሩ፡፡
እኔ የምለው…የፑሽኪን ዝርያዎች ራሳቸው ለመለየት ምስክርነት ቢጠሩ እኮ… “መጀመሪያ ነገር እነኚህ አገሮች የሚገኙት እስያ ነው ደቡብ አሜሪካ?” ብለው ይጠይቁ ነበር፡፡ “አፍሪካ ውስጥ ናቸው ወይ?” ለማለት መጀመሪያ አፍሪካ አገር ሳትሆን አህጉር መሆኗን ማወቅ አለባቸው፡፡ ዓለም ይሄን ያህል ነች፡፡
ልጄ እዛ ይሉኝታ ምናምን ብሎ ነገር የለማ!
ኮሚክ እኮ ነው…በተለይ በአውሮፓ በርከት ባሉ ሀገራት… “መጤዎች ይውጡልን…” “ማንም በራፋችን ዝር እንዳይል…” አይነት ነገር የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች ጉልበታቸው እየጠነከረ ባለበትና ‘ለዓይናቸው እየተጠየፉን’ ባሉበት ዘመን የልጅን ስም አውሮፓዊ እያደረጉ ከመሰረቱ ማንነቱ ላይ ጥቁር ነጥብ የሚያደርጉ ወላጆች ልብ ይግዙማ!
ሀሳብ አለን… ለአውሮፓ ህብረት የአባልነት ጥያቄ ይቅረብልንማ! ልክ ነዋ! ምድረ የአውሮፓ ከተማ ሁሉ የካፌና የሬስቱራንት መጠሪያ ሆኖ የለም እንዴ! ይህ ‘ወንድማማችነትን ለማጠናከር’ ያለንን ፍላጎት (ቂ…ቂ…ቂ…) ፍላጎታችንን የሚያሳይ አይደለም እንዴ! ቢያንስ ቢያንስ የታዛቢነት ወንበርማ ይገባናል፡፡
ለምሳሌ ‘ጆኒ’ ምናምን ድሮ ማቆላመጫ ነበር፡፡ አሁን ግን መደበኛ ስም ሆኖ ይወጣል አሉ፡፡
በ‘አብዮቱ’ ሁለት ልጆቻቸውን ‘ሆቺ ሚን’ እና ‘ቼ ጉቬራ’ ብለው የሰየሙ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ የምለው…እንግዲህ  ጨዋታም አይደል…ዘንድሮ የ‘ቦተሊካ ነፋስ’ የነካቸው ስሞች አሉ!
ስሙኝማ… ብሰማው ደስ የሚለኝ አንድ ስም ምን መሰላችሁ… ‘ያለው ሁኔታ ነው ያለው’ የሚል ስም፡፡ ልክ ነዋ…‘ፖፑላር’ ስም ይሆናላ! ደግሞላችሁ… በየስብሰባውና በየቃለ መጠይቁ ሲደጋገም ዘመድ ወዳጅ ሁሉ… “እንዴት ቢወዱት ነው ስሙን እንዲህ የሚደጋግሙት…” ማለታቸው አይቀርማ!
እናላችሁ…ከፍ ብለን የጠቀስነው የይሉኝታ ነገር አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ በአንድ በኩል በይሉኝታ ማድረግ የማንፈልጋቸውን ነገሮች እናደርጋለን፣ መቀላቀል የማንፈልጋቸውን ስብስቦች እንቀላቀላለን፣ መሄድ የማንፈልጋቸው ቦታዎች እንሄዳለን፣ በማያስቀው እንንከተከታለን…ብቻ ምን አለፋችሁ… ይሉኝታ ነገራችንን ሁሉ አርቲፊሻል ያደርገዋል፡፡እናማ… ለማግባባት የተላኩት ሰውዬ… “አንተስ ተገላገልከው፣ እኔስ ይሉኝታን እንዴት ልገላገለው!” እንዳሉት ከልማቱ ጥፋቱ ከሚብስ ይሉኝታ የምንገላገልበትን ዘመን አንድዬ ያፋጥልንማ!    ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 5764 times
Administrator

Latest from Administrator