Saturday, 08 November 2014 11:13

የአዲስ አበባ ቅርሶችና መልሶ ማልማት -በባለሙያ ዕይታ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

ከአዲስ አበባ ከተማ የመልሶ ማልማት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ የቅርስ ጥበቃ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ አንዳንድ ወገኖች የከተማዋ ቅርሶችና ታሪክ የልማቱ ሰለባ ሆነዋል በሚል ይተቻሉ፡፡ ለአንድ ከተማ የቅርስ ፋይዳ ምን ያህል ነው? በአሁኑ ወቅት ያለው የቅርስ አጠባበቅስ ምን ይመስላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ኤልሳቤት ዕቁባይ፤ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን የአለም አቀፍ ቅርሶች ምዝገባ የቡድን መሪና በአለም አቀፍ ቅርሶች አስተዳደር ዕቅድ ዝግጅቶች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑትን አቶ ኃይለመለኮት አግዘውን አነጋግራቸዋለች፡፡

አዲስ አበባ የቅርሶች ከተማ ናት ይባላል፡፡ እስቲ ያብራሩልኝ…
አዲስ አበባ ቅርሶች ያሏት ከተማ ናት፡፡ ስለ አዲስ አበባ ቅርሶች ስንናገር፣ በዘመን ከፍለን ብናየው፤ ለምሳሌ በአርኪኦሎጂ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ የሚገኘው የዋሻ ሚካኤል ተክለሃይማኖትን፤ በታሪክና በአርኪኦሎጂ ደግሞ የመናገሻ የደን ታሪክን መጥቀስ እንችላለን፡፡ በከተማዋ ውስጥ ከሚገኙት ቀደምት አብያተ ክርስቲያኖች የቀራኒዮ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያንን ስንመለከት፣ በ1836 በንጉስ ሳህለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የተሠራ ነው፡፡ የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያንና ኡራኤልን እንዲሁም ሌሎችንም ማንሳት እንችላለን፡፡ እነዚህ ከከተማዋ መቆርቆር ከ1879 በፊት የነበሩ ናቸው፤ ስለዚህ አዲስ አበባ ቅርስም ታሪክም ያላት ከተማ ነች፡፡
የአዲስ አበባ የቅርሶች ምዝገባ ምን ይመስላል?
የከተማዋ ከፍተኛ መሀንዲስ የነበሩት ዶክተር ወንድሙ የሚባሉ ባለሙያ በ1964 ዓ.ም በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ላይ የ”አዲስ አበባ ቅርሶች ከየት እስከ የት” የሚል ጽሑፍ በእንግሊዝኛ አቅርበው ነበር፡፡ ሊሴ ገብረማርያም ት/ቤት ጋ የሚገኘውን የራስ ናደው ወሎ ቤት ወይም በተለምዶ “ዋይት ሃውስ” ተብሎ የሚጠራውን ቤት ፎቶ ጋዜጣው ይዞት ወጥቶ ነበር፡፡ ጥናቱን መሠረት በማድረግ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት አንዳንድ ስራዎችን ሲሰራ ነበር፡፡ እሳቸው በወቅቱ በጋዜጣ ላይ የፃፉት ስጋታቸውን ነው፡፡ ስለ አዲስ አበባ ከተማ የቅርስ ስጋት መፃፍ የተጀመረው ከዚህን ጊዜ ጀምሮ ነው ማለት ነው፡፡ በ1979 ዓ.ም አዲስ አበባ መቶኛ አመቷን ስታከብር፣ ከተማዋ ሙዚየም ያስፈልጋታል በመባሉ፣ ኤግዚቢሽን ማዕከል አጠገብ የሚገኘው የራስ ብሩ ወልደገብርኤል መኖሪያ ቤት ታድሶ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች የከተማዋን ታሪክ ሊተርኩ በሚችል መልኩ ፊንፊኔ፣ እድገት፣ አድዋ ወዘተ የተባሉ አዳራሾች እንዲቀመጡ ተደረገ፡፡ ቤቱ ቀደምት የኪነጥበብ ህንፃ የሚታይበት ነው፡፡
ከ1979 እስከ 1983 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የሙዚየሙ የበላይ ጠባቂ ስለነበሩ፣ ሙዚየሙ በጀትና የቅርብ ክትትል ነበረው፡፡ በ1983 የመንግስት ለውጥ ሲመጣ በፌደራል የሚገኘው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሠራተኞች ዲሴንትራላይዝድ ሲሆኑ የቅርስ ሃላፊነት ሊኖራቸው የሚገቡ ሰዎች ለአዲስ አበባ ተመደቡ፡፡ መጀመሪያ የተዋቀረው የከተማዋ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ቡድን ነው፡፡ የከተማዋን ታሪካዊ ቤቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበርን በማስተባበርና ከተመደቡት ባለሙያዎች ውስጥ የተወሰኑት ቤቶቹን ቆጥረው ከተሰበሰበው መረጃ ውስጥ ወደ 130 የሚሆኑ ታሪካዊ ቤቶች የአዲስ አበባ ማስተርፕላን ክለሳ በተሰራበት ወቅት እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ ቤቶቹ በእድሜያቸው መርዘም ምክንያት ብቻ የተመዘገቡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የአዲስ አበባ ቅርሶች በአፄ ምኒሊክ ዘመን የተሠሩ ቤቶች ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ በወቅቱ የተመዘገቡ ቦታዎችም ነበሩ፡፡ ለምሳሌ መስቀል አደባባይ፣ ጃንሜዳና እንጦጦ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህ ቦታዎች እንዴት ነው የተመረጡት?
ህዝብ በብዛት ወጥቶ የተለያዩ ክንዋኔዎችን የሚያደርግባቸው ስለሆኑ ነው፡፡ ወደ አስራ ሰባት የሚጠጉ የከተማዋ ሀውልቶችና አደባባዮችም ተመዝግበዋል፡፡ ቀደምት የሆኑ አብያተ ክርስቲያናትም ተመዝግበዋል፡፡
አዲስ አበባ ልትናገራቸው የምትችላቸው የራሷ የእድገት ደረጃዎች ያላት ከተማ ናት፡፡ ከ1879 እስከ 1928 ዓ.ም የምኒልክ ዘመን ኪነ ህንፃን እናያለን፡፡ ይሄ ዘመን በተለይ መጀመሪያ ላይ ወደ ቤተመንግስቱ የመጡትን የአርመኖችና ህንዶች ኪነጥበብ ህንፃ ያሳያል፡፡ ለምሳሌ የአርመኖቹን ብናይ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ህንፃ አጠገብ የቦጐሲያን ቤት ይገኛል፡፡ ይህ ቤት እስከ አሁን ድረስ ውበቱ እንደተጠበቀ ያለ ቤት ነው፡፡ ጐጆ ቤት ነው፤ እዚያ ቤት ውስጥ ነው የአፄ ምኒልክ የሬሳ ሳጥን የተገጣጠመውና የተሠራው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ስትጀመር የነበረውን ገፅታ ያሳያል፡፡ እነ ሰባ ደረጃና እነ አርባ ደረጃን የምናይበት ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንዳልኩት ከላይ በተጠቀሰው ጊዜ፤ የአርመኖች፣ የህንዶችና የግሪኮች አሻራ ያረፈባቸው ኪነ ህንፃዎች እናያለን፡፡
ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ደግሞ ጣሊያኖች የራሳቸውን አሻራ ጥለው አልፈዋል፡፡ እነ ቤላ፣ ፖፓላሬ፣ ካዛንቺስ እንዲሁም የጣሊያን እስር ቤትና ፖሊስ ማዘዣ የነበረውን ራስ ሆቴልና ኢሚግሬሽን፣ የጣሊያን ዘመንን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከጣሊያን መውጣት በኋላ ከ1933 እስከ 1966 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ የተለያዩ ህንፃዎች ተሠርተዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረትን፣ ማዘጋጃ ቤቱን፣ ብሔራዊ ትያትር አካባቢ ያሉትን ህንፃዎች፡- መከላከያ ሚ/ር፣ ብሄራዊ ባንክን… መጥቀስ ይቻላል፡፡ እስከ አሁን ድረስ የከተማዋን ውበት የሚያደምቁ ህንፃዎች ናቸው፡፡ ከ1966 እስከ 1983 የደርግ ዘመን ማብቂያ ድረስ ደግሞ የራሺያና የቡልጋሪያ የኪነ-ህንፃ ባለሙያዎች ስራ የሆኑ ህንፃዎችን እናያለን፡፡ ለምሳሌ ሰሜን ኮሪያውያኖቹ የሠሩት ጥቁር አንበሳ ጋ ያለው ሀውልት፣ ከጀርባው ደግሞ የዩጐዝላቪያ ባለሙያዎች ያነፁትን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን እናገኛለን፡፡ በቦሌ መስመር ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚኖሩበት አፓርታማዎች በራሺያዎች የተሠሩ ናቸው፡፡ ኢህአዴግ አገሪቷን ማስተዳደር ከጀመረ በኋላም አዲስ አበባ እጅግ በጣም ፈጣን የከተማ እድገት እያሳየች ነው፡፡
ከተማዋ በስፋትም ሆነ በነዋሪዋ ብዛት ከፍተኛ ለውጥ ያመጣችበት ጊዜ ነው፡፡ ከተማዋ እንደ ገርጂ፣ አያት፣ ላፍቶ፣ ገላን፣ አየር ጤና የተባሉ አዳዲስ ሰፈሮችን አካትታለች፡፡ መሀል ከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ የግንባታ ስራ እየተሠራ ነው፡፡ እዚህ ላይ ትልቁ ጥያቄ፣ “አዲስ ስንሰራ መነሻችን የሆነውን እንዴት በማድረግ ነው?” የሚለው ነው፡፡ አዲስ የባቡር መስመር ዝርጋታ እየተካሄደ ነው፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያው የባቡር ሀዲድ ታሪካዊነቱ ቦታ ተሠጥቶት ጥበቃ አልተደረገለትም፡፡ የከተማዋ ነዋሪ ሳይቀር አፈር እያለበሰ ቤት ሠርቶበታል፡፡ ኤርትራ ውስጥ ከአቆርዳት እስከ ምፅዋ ያለው የባቡር መስመር ለቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ልማቱ ሠለባ ያደረጋቸው ቅርሶች አሉ፡፡ የአልሜክ ስልጣኔን የሚያሳየውና ሜክሲኮ አደባባይ የነበረው የራስ ቅል የተነሳ ሲሆን ተመልሶ ይሠራል የሚል ቃል ተገብቷል፡፡
ከመልሶ ማልማቱ ጋር ተያይዘው የሚነሱ የቅርስ ጥበቃ ጉዳዮች በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
ከተማዋ አማካሪ አላት ወይ? የሚያስብሉ ስህተቶች ተፈፅመዋል፡፡ ለምሳሌ የአራት ኪሎ ሀውልትን የሚሸፍን ድልድይ መስራት ተገቢ አልነበረም፡፡ መስቀል አደባባይ የተሠቀሉ ትልልቅ የማስታወቂያ ሠሌዳዎች የቦታውን ታሪካዊነት ጋርደውታል፡፡ አደባባዩን ባቡሩ ማቋረጡ በራሱ አካባቢውን ለውጦታል፡፡ በአጠቃላይ ስርአት ይመጣል፤ ስርአት ይሄዳል፡፡ ያለፈው የሚባለው ትውልድ ጥሎት የሄደው መቀመጥ አለበት፡፡ የአዲስ አበባን ልማት በተመለከተ ለመነጋገር ማነፃፀር ያስፈልጋል፡፡ የምናነፃጽረው የድሮውን አሳይተን ነው፡፡ ሠፈሮቹን፣ በየሠፈሩ ውስጥ የነበሩ መስተጋብሮችን፣ ማህበራዊ ግንኙነትንና ትስስሩን ማቆየት አለብን፡፡ ስልጣኔ ማለት ትስስሩን ማጥፋት አይደለም፡፡ የተለያየ ርዕዮተ አለም ያልበገራቸውን ትስስሮች መጠበቅ አለብን፡፡ የመጀመሪያው ሲኒማ ቤት ሰይጣን ቤት ይባላል፡፡ ለምን እንደዚያ እንደተባለ የአሁኑ ትውልድ ሊያውቀው በሚገባ መልኩ መተረክና እዛው ቤት ውስጥ መፃፍ አለባት፡፡ በአለም ላይ ሲኒማ ከተፈለሠፈ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቴክኖሎጂው ከደረሳቸው አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡
የፊልም ኢንዱስትሪውን ለማነፃፀር፣ ያንን ቤት መጠበቅ አለብን፡፡ አዲስ አበባ ከተመሠረተች 125 አመቷ ነው ብለን፣ አዳዲስ ህንፃዎችን ብቻ የምናሳይባት ሳይሆን ዕድገቷን ራሷ ማሳየት የምትችል መሆን አለበት፡፡
ቅርሶች በማን ነው የሚያዙት?
ቅርሱን አድሰን እናስተዳድራለን ለሚሉ ወገኖች ይሰጣል፡፡ በግል የተያዙ ታሪካዊ ቤቶች እኮ አሉ፡፡ ልዕልት ማርያም፤ የመሐመድ አሊን ቤት “አዲስ ውበት” በሚባል ድርጅታቸው እንዲያድሱ ተደርጓል፡፡ ሞዴል ሊያ ከበደ፤ የደጃዝማች አያሌው ብሩን ቤት አድሳ ይዛዋለች፡፡ የቀድሞው የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የነበረው የቢትወደድ ሃይለጊዮርጊስ መኖርያ ቤት ለቅርስ ባለ አደራ ተላልፏል የሚባል ነገር አለ፡፡ ያ ቤት አሁን መታደስ አለበት፡፡
አቶ አሰፋ ተሰማ፤ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ በአንድ ወቅት ሲናገሩ፤ “ከተሜነት ወሳኝ ነው፤ የአዲስ አበባ አብዛኛው ነዋሪ ከገጠር የመጣ ነው፡፡ የከተሜ የአኗኗር ባህል ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ አመራሩ ላይ መንፀባረቅ ይኖርበታል፡፡ አመራሩ ከተሜ መሆን አለበት፡፡ ከተሜነት የግድ ከተማ መወለድ አይደለም፡፡ ከተሜነት ከተማዋ ሊኖራት የሚገባውን ደረጃ ማየት መቻል ነው፡፡ ለምሳሌ ከደብረ ዘይት መንገድ ወደ አዲስ አበባ የሚገባ ሰው መሃል አዲስ አበባ ከተማ መግባቱን እንዲያይ ተብሎ ነው መንገዱ ገለጥ ያለው፡፡ የአንበሳ ህንፃ ዲዛይንም መንገዱን ተከትሎ እንዲሠራ ተደርጐ ነበር…” ብለው ነበር፡፡ በከተማ ዕቅድ የታወቁ ከንቲባዎች የነበሯት ከተማ ናት፤ ለንደንን ዲዛይን ያደረጉ ሰዎች በአዲስ አበባ ማስተርፕላን ላይ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ የእነዚህን ሰዎች ግብአት መጠቀም አለብን፡፡ የግድ ሰዎች ይህ ቦታ ታሪካዊ ነው” እያሉ መጮህ የለባቸውም፡፡ ከተማው ራሱ መናገር አለበት፡፡ መርካቶ አሁን በህንፃ እየተሞላ፣ የቀድሞውን ታሪካዊ እሴት እያጣ ነው፡፡ የግድ ማፍረስ አይጠበቅም እኮ፡፡ ከተማዋ ሠፍታለች፤ ቅርሶቿንና ታሪኳን በማይነኩ ቦታዎች መጠቀም ይቻላል፡፡ ፀሐይ ሪል እስቴትን ማየት ይቻላል፡፡ በአለም ላይ አሮጌና አዲሱ ከተማ ያሉባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ካይሮ ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች፡፡ አዲስ አበባንም እንደዚያ መስራት ይቻላል፡፡ “ሠፈሮቹ ያለፈው ስርአት ገዢ መደብ ወይም የነፍጠኛ መቀመጫ ስለነበሩ…” እያለ የሚያስብ ካለ ጤነኛ አይደለም፡፡ ይህ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ከአመራር መወገድ አለባቸው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ቡድን ተቋቁሞ የቆየው እስከ 1995 ድረስ ነው፡፡ በ1995 መዋቅር ሲሰራ፣ የቅርስ አስተዳደር፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ ብዙ ጥፋት የደረሰው ያን ጊዜ ነው፡፡
በአንተ ዕይታ ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ ያሉት ህንፃዎች ከምን ይመደባሉ?
በኔ ዕይታ በአጠቃላይ ብሔራዊ ትያትርና አካባቢው ቅርስ ነው፤ ዘመን ተናጋሪ ህንፃዎች ናቸው፡፡ ብሔራዊ ትያትር ጋ ያለው አንበሳ የከተማዋ አርማ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ከንቲባ ዘውዴ በላይነህ ሀውልቱን ሲመርቁ፤ “ይህ አንበሳ አንበሳ ባይመስልም የወጣበት ወጪ ግን አንበሳ አድርጐታል” ማለታቸው ይነገራል፡፡ ሰዓሊ ደስታ ሃጐስም ለቱሪዝም “የ13 ወር ፀጋ”  የሚለውን ስትሰራ የአንበሳውን ፊት በመውሰድ አርማ አድርጋዋለች፡፡ ህንፃዎቹ ብቻ አይደሉም፤ ከፍል ውሃ እስከ ሜትሮሎጂ ጫፍ ያሉት ዛፎች ጭምር ቅርስ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሆቴል አጠገብ ምን አይነት ህንፃ ይሠራ ይሆን? ከባድ ነው፡፡ የህንፃው ርዝመትስ ከመከላከያ ሚ/ር አንፃር እንዴት ሊሆን ነው?
ቅርስ በዩኔስኮ ማስመዝገብ ፋሽን እየሆነ የመጣ ይመስላል፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ…
ብዙ ሰው ቅርሱ የሚጠበቀው ዩኔስኮ ስለመዘገበው ይመስለዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ቅርስ ማስመዝገብን ክልሎች ፉክክር የያዙበት ይመስላል፡፡ “የትኛውን መስቀል ነው ያስመዘገባችሁት?” ብሎ የጠየቀ ሃላፊ አለ፡፡ የተመዘገበው አከባበሩ ነው፤ ዩኔስኮ ሃይማኖት አይመዘግብም፡፡ የሶፍኦመርና ድሬ ሼክ ሁሴንን ለማስመዝገብም ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ባህላዊ አመጋገቦች፣ ከእምነት ጋር የተያያዙ ባህሎች አሉ፡፡ ለነዚህ ሁሉ ዩኔስኮ መዝገቡን ከፍቶ ይጠብቃል ማለት አይደለም፡፡ እንደ ኦሎምፒክ ተወዳድሮ ነው የሚመዘገበው፡፡ ሚ/ር መ/ቤቱም ምዝገባውን በተመለከተ መመሪያዎችን እያወጣ ነው፡፡ ዩኔስኮ አንድን ቅርስ ሲመዘግብ ቅድመ ሁኔታዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ታንዛኒያ አንድ የሆነ ቦታን ቅርስ ብለው ካስመዘገቡ በኋላ፣ ቦታው ላይ ነዳጅ ተገኘ ተባለ፡፡ ነገር ግን ነዳጅ ማውጣት ተከልክለዋል፡፡
ቅርሶችን በዩኔስኮ ማስመዝገብ ምንድን ነው ጥቅሙ?
ቅርሱን ለመጠበቅ የተወሰኑ ዕገዛዎች ይደረጋል፡፡ እኛ አገር በአንዳንድ ቦታ ባህሉን ትተው ለቱሪዝሙ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ለቱሪዝሙ ዋናው ነገር ባህሉ መሆኑን ይረሱታል፡፡
በቅርቡ ለመመዝገብ የደረሰ ቅርስ አለ?
አዎ፤ ደቡብ ክልል ውስጥ ብራይሌ/አንጐይታ በመባል የሚታወቅና በአሁኑ ወቅት ስምንት ሰዎች ብቻ የሚናገሩት ቋንቋ አለ፤ እሱን ለማስመዝገብ ጥያቄ አቅርበን፣ ማስተካከያዎች እንድናደርግ ወደኛ ተልኳል፡፡ የገዳ ስርአትንም ለማስመዝገብ በሂደት ላይ ነን፡፡  

Read 4587 times