Saturday, 08 November 2014 11:00

የኛ ቤት ጠማማነት እኛን ይጨርሳል፤ አለ እንጨት ኑሶ ጌለይ ኑነ ውርሴስ ጌስ ምተይ - የወላይታ ተረት

Written by 
Rate this item
(10 votes)

አንዳንድ ታሪክ ጊዜው እጅግ ሲርቅ ተረት ይሆናል፡፡
በጥንት ዘመን አንድ ሮማዊ ጀግና ወታደር ነበር ይባላል፡፡ አያሌ ጦርነቶችን በአሸናፊነት ተወጥቷል፡፡ አብዛኛውን ህይወቱን በጦር ሜዳ ስላሳለፈ በአካል የሚያውቀው ሰው የለም፡፡ ዝናው ግን በሰፊው ይወራል፡፡
አንድ ጊዜ ታዲያ አጠቃላይ ምርጫ በሀገሪቱ ሲካሄድ ያ ጀግና ፖለቲካ ውስጥ መግባት አለብኝ ብሎ ወሰነ፡፡ ስለዚህም በምርጫው ለከፍተኛው የፓርላማ ቦታ ይወዳደር ጀመር፡፡ በዚያን ጊዜው የሮማውያን የምርጫ ባህል ጥሩ ዲስኩር (ንግግር) ማድረግ ግድ ነበር፡፡ ጀግናው ንግግሩን የጀመረው ለዓመታት ለሮማ ሲዋጋ በጥይት ብዙ ቦታ ቆስሎ ነበርና ገላው ላይ ጠባሳዎቹን በማሳየት ነበር፡፡ ህዝቡ ከንግግሩ ይልቅ ጠባሳዎቹን እያየ ዕንባ በዕንባ ተራጨ፡፡ የዚያ ጀግና በምርጫው አሸናፊነት ከሞላ ጐደል የተረጋገጠ መሰለ፡፡
ታዲያ የዋናው ምርጫ ቀን ያ ጀግና በመላው የፓርላማ አባላትና በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ታጅቦ ወደ መድረኩ ብቅ አለ፡፡ ህዝቡ ግራ ተጋባ፡፡ “በእንዲህ ያለ የምርጫ ቀን ይሄ ሁሉ ጉራ ለምን አስፈለገ?” ይባባል ጀመር፡፡   ያ ጀግና ንግግር ሲያደርግ አጃቢዎችንና ሀብታሞችን የሚያወድስ፣ በትዕቢትና በጉራ የተሞላ፣ የጦር ሜዳ ድሎቹን እያሳቀለ ከኔ ወዲያ ጀግና ላሳር ነው ይል ጀመር፡፡ ተፎካካሪዎቹንም አንተና አንቺ እያለ ያዋርድ ገባ፡፡ ቀልድ አወራሁ ብሎ የሚናገራቸው ወጐች ራሳቸው የሰው ሞራል የሚነኩና ህዝቡን የሚያበሳጩ ሆኑ፡፡ “ለሮማም እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቅ ልማትና ሀብት አመጣላታለሁ!” እያለ በከፍተኛ መወጣጠር መድረኩ ላይ ተንጐራደደ፡፡
ህዝቡም “ያ እንደዚያ ዝናው የተወራ የጦር ሜዳ ጀግና እንዲህ ያለ ቱሪናፋ ነው እንዴ?” አለ፡፡ ወሬው በአገሪቱ ሙሉ ወዲያው ተሰማ፡፡ “ይሄንንማ ፈፅሞ አንመርጥም፡፡ እንዳይመረጥም ላልሰማው ህዝብ መናገር አለብን”፤ አለ ህዝቡ፡፡ ጀግናው ድምፅ አጣ! ሳይመረጥ ቀረ፡፡ ወደ ጦር ሜዳው ተመለሰ፡፡ “ያልመረጠኝን ህዝብ አሳየዋለሁ፡፡ እበቀለዋለሁ!” ይል ጀመር፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ሮማ የእርዳታ እህል በመርከብ መጣ፡፡ ምክር ቤቱ በነፃ ይታደል አለ፡፡ ያ ጀግና “ይሄ እህል በነፃ መታደል የለበትም፡፡ እምቢ ካላችሁ ጦር ሜዳውን ትቼላችሁ እመለሳለሁ” እያለ ያስፈራራ ጀመር፡፡ ይሄን ወሬ ምክር ቤቱ ለህዝቡ ነገረ፡፡ ህዝቡ ተቆጣ፡፡ “ያ ጀግና እፊታችን ቀርቦ ያስረዳ” አለ፡፡ ጀግናው ደግሞ “ህዝብ ብሎ ነገር አላቅም፡፡ ዲሞክራሲም አልቀበልም፡፡ አልመጣም” አለ፡፡ ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ጮኸ፡፡ ምክር ቤቱ ያን ጀግና የግዱን እንዲመጣ አደረገውና ሸንጐ መድረክ ላይ ቆሞ እንዲናገር ታዘዘ፡፡ ጀግናውም አሁንም በእልህና በትእቢት ሁሉንም መሳደቡን ቀጠለ፡፡ ህዝቡ በሆታ አስቆመው፡፡ ለፍርድ ይቅረብልን አለ፡፡ ምክር ቤቱ ምንም ምርጫ አልነበረውም፡፡ ለፍርድ አቀረበው፡፡ በዚያን ዘመን ወንጀለኛ ቀጣበት በነበረው፤ ከከፍተኛ ተራራ ወደ መሬት ይወርወር፤ የሚል ሀሳብ ቀረበ፡፡ ሆኖም አስተያየት ተደርጐ ቅጣቱ እድሜ ልክ ይሁንለት ተባለና ዘብጥያ ተወረወረ! ህዝቡ በሆታና በዕልልታ መንገዱን ሞላው፡፡
                                                           ***
ሰዎችን በንግግር እንማርካለን ብለን ብዙ በለፈለፍን ቁጥር ብዙ ከቁጥጥራችን የሚወጡ ነገሮች ይከሰታሉ፡፡ ጠንካራና ልባም ሰዎች ጥቂት ምርጥ ነገሮችን ብቻ በመናገር የሰውን ልብ ይነካሉ፡፡ ስለዚህ ከአንደበታችን በመቆጠብ፣ ትሁት በመሆን፣ ህዝብን ባለመናቅ፣ ለምንናገረው ነገር የቤት-ሥራችንን ጠንቅቀን በመስራትና ጉዳያችንን በማወቅ ነው ለውጥ ለማምጣት የምንችለው፡፡
ከሁሉም በላይ ተአብዮ አገርንና ህዝብን ይጐዳል፡፡ ከማንም በላይ ነኝ እና አምባገነንነት የተአብዮ (የእብሪት) ልጆች ናቸው፡፡ ንቀት፣ ሰው-ጤፉነት፣ ሁሉን አውቃለሁ ባይነት፣ ቆይ-አሳይሃለሁ - ባይነት፤ ብቆጣም እመታሻለሁ ብትቆጪም እመታሻለሁ ማለት፤ የማታ ማታ ከላይ የተጠቀሰውን የጦር-ሜዳ ጀግና ዕጣ-ፈንታ የሚያሰጠን መሆኑ አሌ አይባልም፡፡ ከበደ ሚካኤል፤
“ኩራትና ትእቢት፣ የሞሉት አናት
ሰይፍና ጐራዴ፣ የመቱት አንገት
አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ
እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ”
የሚሉን ለዚህ ነው፡፡
ከልክ ያለፈ ውዳሴና ማሞካሸትም ከጥቅሙ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ ተወዳሹ እስኪታዘበን ድረስ ብናሳቅለው ለማንም የማይበጅ ንግግር እንዳቀረብን ነው የሚቆጠረው፡፡
ፀጋዬ ገብረመድህን፤
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት”
የሚለን ለዚህ ነው፡፡
እናስተውል፡፡ ብዙ እዩኝ እዩኝ ደብቁኝ ደብቁኝን እንደሚያስከትል አንርሳ፡፡ ብዙ በተናገርን ቁጥር አልባሌና ዝቅ የሚያደርጉንን ጥፋቶች ለመስራት በር እንከፍታለን፡፡ ታዋቂው ሳይንቲስትና የጥበብ ሰው ሊዮናርዶ ዳቬንቺ፤
“ኦይስተሮች (Oysters) ጨረቃ ሙሉ በሆነች ሰዓት አፋቸውን ሙሉ በሙሉ ይከፍታሉ፡፡ ይሄኔ ክራቦች (Crabs) የባህር አረምን ኦይስተሮቹ አፍ ውስጥ ይሰገሰጋሉ፡፡ አፋቸው መንቀሳቀስ ያቅተዋል፡፡ ከዚያ የክራቦቹ ምግብ ይሆናሉ፡፡ አፉን ያለልክ የሚከፍት የማንም ሰው ዕጣ-ፈንታ ይሄው ነው፡፡ የአድማጩ ሰለባ ይሆናል” ይለናል፡፡
ባልባለቀ አእምሮና ባልበሰለ አንደበት ስንቶችን ልናስቀይም እንደምንችል እናጢን፡፡ “እዛም ቤት እሳት አለ” የሚለውን ተረት ከልቦናችን አንለይ፡፡ ከቶውንም እኔ አውቃለሁን ስንፈክር ሌላውም ያውቃልን አንርሳ፡፡ ባደባንበት ሊደባብን እንደሚችል፣ ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን መሆኑን፣ ሥራ ለሰሪው እሾክ ላጣሪው እንደሚሆን አንዘንጋ፡፡ የወላይታው ተረት - “የኛ ቤት ጠማማነት እኛን ይጨርሳል፤ አለ እንጨት” የሚለን ይሄንኑ ነው!










Read 4636 times