Monday, 03 November 2014 09:10

ዛምቢያ በሟቹ ፕሬዚዳንቷ ቦታ የመጀመሪያውን ነጭ መሪ ተካች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በመጪው ጥር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይደረጋል
ከደ/አፍሪካው ዴክለርክ በኋላ የመጀመሪያው ነጭ አፍሪካዊ መሪ ናቸው

        ዛምቢያን ላለፉት ሶስት አመታት ያህል ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት ሚካኤል ሳታ፤ ባለፈው ማክሰኞ በ77 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በነጭ ጊዜያዊ መሪ መተዳደር መጀመሯን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ለንደን ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምናቸውን ለሳምንታት ሲከታተሉ የቆዩት ሳታ መሞታቸውን ተከትሎ  የዛምቢያ መንግስት ምክር ቤት በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ፣ በአገሪቱ ህገመንግስት በተቀመጠው መሰረት በቀጣዮቹ ሶስት ወራት ውስጥ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ማካሄድን ጨምሮ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር በሚደረግበት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲሰሩ የቆዩትን ጋይ ስኮት ጊዜያዊ መሪ አድርጎ መርጧል፡፡
ሟቹ ፕሬዚዳንት በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለህክምና ወደ እንግሊዝ ሲሄዱ፣ አገሪቱን በተጠባባቂነት የመምራቱን ሃላፊነት ለመከላከያ ሚኒስትሩ ኤድጋር ሉንጉ ሰጥተው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ሞታቸውን ተከትሎ ግን፣ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምርጫ እስከሚካሄድና አዲስ ፕሬዚዳንት እስኪመረጥ ድረስ፣ ጋይ ስኮት አገሪቱን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡እ.ኤ.አ በ2001 “ፓትሪዮቲ ፍሮንት” የተባለውን ፓርቲ በመቀላቀል በወቅቱ በተካሄደው ምርጫ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ሲሰሩ መቆየታቸውን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ የስኮትላንድ ዝርያ ያላቸውና ወላጆቻቸው ከዛምቢያ ውጭ የተወለዱ በመሆናቸው የአገሪቱ ህገመንግስት ስለሚከለክላቸው በመጪው ጥር በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ላይ ላይሳተፉ እንደሚችሉም ገልጿል፡፡
የ60 አመቱ የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ምሩቅ ጋይ ስኮት፣ ከደቡብ አፍሪካው መሪ ዴክለርክ በኋላ አንድን የአፍሪካ አገር ለመምራት የቻሉ የመጀመሪያው ነጭ መሪ እንደሆኑ ተነግሯል፡፡
ሟቹ ፕሬዚዳንት ሳታ ላለፉት አራት ወራት ከአደባባይ መራቃቸውን ተከትሎ፣ የከፋ ህመም ላይ ወድቀዋል የሚል ወሬ በስፋት ሲናፈስ መቆየቱን ዘገባው አስታውሶ፤ ፕሬዚዳንቱ በመስከረም ወር አጋማሽ በተከናወነው የአገሪቱ ፓርላማ የመክፈቻ ስነስርአት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የከፋ የጤና ችግር ላይ ናቸው በሚል በስፋት የተሰራጨውን ወሬ በተመለከተ ዘና ያለ ምላሽ ሰጥተው ነበር - “እስካሁን አልሞትኩም” በማለት፡፡ከዚህ የመክፈቻ ስነስርዓት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኒውዮርክ ጽህፈት ቤት ሊያደርጉት የነበረው ንግግር መሰረዙን ተከትሎ በአሜሪካ ባረፉበት ሆቴል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው እንደነበር ፖሊስ አስታውቶ ነበር፡፡የአገሪቱ መንግስት ፕሬዚዳንቱ በውጭ ሃገር እየታከሙ እንደሚገኙ ከመግለጽ ባለፈ፣ የት አገር እንደሚገኙ ሳይጠቁም መቆየቱንና የዛምቢያ ተቃዋሚ ቡድኖችም ፕሬዚዳንቱ አገሪቱን የመምራት ብቃት እንደሌላቸው ሲናገሩ እንደነበር ዘገባው አስታውቋል፡፡
የተባ አንደበት ባለቤት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በአገሬው ዘንድ ‘ንጉስ ኮብራ’ በሚል የቅጽል ስም የሚጠሩትና በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነት ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ ተወዳድረው በ2011 ስልጣን የያዙት አምስተኛው የዛምቢያ ፕሬዚዳንት ሳታ፤ ታጋሽነት የሚጎላቸው መሪ ናቸው” በሚል ሲተቹ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ፕሬዚዳንቱን ለሞት የዳረጋቸው ህመም ምን እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም፡

Read 2655 times