Monday, 03 November 2014 08:09

ደሞ የደብረዘይት ጉደኛ ጉዞ ገጠመኝ

Written by  ነቢይ መኰንን
Rate this item
(5 votes)

         የዛሬው ጉዞዬን እጅግ ልዩ የሚያደርገው ከአዲስ አበባ ደብረዘይት ለመሄድ 4 ሰዓት ተኩል መፍጀቱ ነው፡፡
በተለይ አዲሱ፣ ፈጣኑ የአዲሳባ - ናዝሬት/አዳማ መንገድ ከተሠራ በኋላ ይሄን ማሰብ በአያሌው ያስደምማል፡፡ ይሄ ለምን ሆነ?
ከኢየሩሣሌም ህፃናትና ሕብረተሰብ ልማት ድርጅት ጋር ወደ ደብረዘይት ለመሄድ የተቃጠርነው ሲአርዲኤ ፊት ለፊት - ከመኪና ማሰልጠኛው ማዶ ነው፡፡ እኔ አንድ ሰዓት ደርሻለሁ፡፡
ለወትሮው ቀድመው የሚጠብቁኝ የድርጅቱ መኪናዎች ዛሬ አይታዩም፡፡ ደቂቃዎች ሲገፉ “ቀጠሮውን የሰጠችኝ የድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት ልጅ ቦታ ወይም ሰዓት ተሳስቷት ይሆን?” አልኩኝ፡፡ ትንሽ ልታገስ ብዬ የመታገሻዬን አረፍ የምልበት ቦታ በዓይኔ ማትሬ አንድ ሻይ ቤት መሣይ ቤት ጐራ አልኩኝ - እዚያው መንገዱ ዳር፡፡ ፓስቲና ብስኩት (ጃፓን) አዘዝኩ፡፡ ቅርፁ ከኔ ዘመን ፓስቲና ብስኩት የተለየ ሆኗል፡፡ ዋጋውማ የትና የት፡፡ ያም ሆኖ ፓስቲና ብስኩት ሳይ የተነጠቀ ልጅነቴን ያስመለስኩ ስለሚመስለኝ አንዳች ያሸናፊነት ስሜት ይሰማኛል፡፡ በከፊል ዐይኔ ከአስፋልቱ ዳር የሚቆሙትን መኪኖች እየማተርኩ፣ በከፊል ዐይኔ ፓስቲ - ብስኩቴን እጠብቃለሁ፡፡ (“ፓስቲ - ብስኩት” ያልኩት ዛሬ ብስኩት ሲባል በተለይ ያሁኖቹ ልጆች የፋብሪካው ብስኩት እንዳይታያቸው ከመስጋት ነው) ብስኩቴን እየኮረሸምኩ በላስቲክ ውሃ እያማግሁ ቁርሴን በላሁ፡፡ አሁንም መኪናው እንዳልመጣ ሳውቅ ስጋት ገባኝ - አንዳንድ አደጋ አጋጥሞስ ቢሆን ብዬ፡፡
ስለዚህ ደወልኩ፡፡ የደወልኩት ሰው አጣርቶ እንደሚደውልልኝ ነገረኝ፡፡ ቆይታ፤ ከፕሮግራሙ ያገናኘችኝ ልጅ “የትራፊክ jam (ጭንቅንቅ) ስለሆነ ነው - ሦስት መኪናዎች በተለያየ አቅጣጫ ወጥተዋል - ቀድሞ የደረሰ ይወስድሃል” አለኝ፡፡ መጠበቄን ቀጠልኩ፡፡ ብዙ በዙሪያዬ ያለው ሰው መኪና መጠበቅ እንዳይሰለቸው ይመስለኛል ከፊሉ ሞባይል ይጠቀጥቃል፣ ከፊሉ የግል ወሬ ያወራል፣ ከፊሉ ሰርቪስ ጠባቂ ስለሆነ አሥር አሥሬ ሰዓቱን ያያል፡፡ አብዛኛው አውቶብስ ጠባቂ ግር ብሎ እጁን ወደ ትኬት ቆራጯ ይሰቅላል - አሁንም ግን የእኔ መኪና አልመጣም፡፡
“አንዳንድ ቀን አለ፣
አንዳንድ ቀን አለ፣
ኮረኮንች የበዛው ሊሾ እየመሰለ”
የሚለው ግጥሜ ውል አለኝ፡፡ በራስ ግጥም መትጋት ያጋጥማል አልፎ - አልፎ አንዳንድ ሰዓት ጐታታ ነው፡፡ የዛሬው ሰዓት ግን ሌላ ቃል ሊፈጠርለት ይገባል፡፡ “ቀኝ ኋላ ዙር የተባለ ሰዓት” ይመስለኛል፡፡
ከቀኝ ኋላ ዙር ኋላ የእኛ መኪና መጣ፡፡ ተደወለልኝ፡፡ እፎይ ብዬ ገባሁ፡፡ የማላውቃቸውን አብሮ - ተጓዦቼን ተዋወቅሁ፡፡ ሶስት ሴቶች ስድስት ወንዶች ሆንን፡፡ መንገዱ ተጀመረ፡፡ ጥቂት እንደሄድን የጭቃ ጅራፉ መጣ! - ለምን እንደሆነ በማናውቀው ምክንያት የመኪና ሰልፍና ጭንቅንቅ ተጀመረ፡፡ እኛ መኪና ውስጥ ያሉት የሥራ ኃላፊዎች የደብረዘይቱን የኢህማልድ ማዕከልን የሥራ እንቅስቃሴ በስልክ አመራር ሊሰጡ ይሞክራሉ፡፡ “መኪናዎቹ አይንቀሳቀሱም፡፡ በአራትም ከደረስን መልካም ነው” አለ አንደኛው፡፡ ከደብረዘይት የሚያናግረን ሰው “አቃቂ አካባቢ የመኪና አደጋ ደርሶ ነው - አንድ የኛ መኪናም በመከራ ነው እዚህ የደረሰው” አለ፡፡ አሁን ዳር - ዳሩ ገባን፡፡ እንግዲህ መንገድ የዘጋ መኪና/መኪኖች ቢኖሩ ነው፡፡ በተለምዶ በፈረንጆቹ አጠራር Bottle-neck (የጠርሙስ - አንገት ማነቆ) እንደሚባለው ቃሊቲ ክራውን ሆቴል አካባቢ የመኪናዎች “ስክ” ይመስላል፡፡ (“ስክ” ማለት እሥር ቤት ሆነን እግር - ከአንገት ተቃቅፈን የምንተኛበት የቦታ ቁጠባ ሥርዓት ነው፡፡ ድንገት ቃሉ ባርቆብኝ ነው!) ሁሉም ተጓዥ ለሁለት ሰዓት የታቀደውን ፕሮግራም ከአዕምሮው መደምሰስ ይዟል፡፡
አንደኛው - “ስድስትም ብንገባ ደግ ነው” ይላል፡፡
“ፕሮግራሙን ወደ ከሰዓት ሺፍት እናድርገው በለው” ይላል የሥራ ኃላፊው
ሌላው - ኋላ ወደቀረው መኪና ሲደውል “ገና ቦሌ ተቀርቅረናል” አለው ያኛው፡፡
“ሌላ መንገድ ነበርኮ በሲኤምሲ ተገብቶ በደብረዘይት አትክልት መሸጫ የሚያወጣ - ወደኋላ ተመልሰው - ይሂዱ” አለ አንዱ አብሮ ተጓዥ፡፡
ሌላው - “ካለ ጥሩ ነው፡፡ ግን ከቦሌው ሰልፍ እንዴት ወደኋላ ይወጣል?”
ለላዋ - “ንቅንቅ አይሉም”
ይሄ ሁሉ ሲወራ መኪናው አንድ ጋት ነው ፈቀቅ የሚለው፡፡  
አሁን ጭራሽ ከወዳኛው የመኪና አቅጣጫ እየዘለለ ወደኛ መስመር እየበረከተ የሚረባው መኪና እየጨመረ መጣ፡፡
ይሄኔ አንዱ ከእኛ ጋር ያለ - ኢኮኖሚስታዊ አስተያየት ሰነዘረ፡-
“የመስመሩን ሰልፍ ርዝመት ታዩታላችሁ፤ ጫፉ አይታይምኮ!...ይገርማችኋል - ይሄ ስንት ኪሣራ እንደሚያስከትል አስቡ - የነዳጅ - የፍሬሲዮን - የጊዜ - የሥራ ቦታ፤ በአስቸኳይ - ድረስ የተባለ - የሞራል - ስንት የኢኮኖሚ ነገር ባንድ መኪና መገልበጥ ደረሰ!”
ሌላው - “ዱሮም እኛ አገር ችግር የሚመጣው በአንድ ሰው ምክንያት ነው” አለ፡፡
ሌላው - “በአንድ ሰው መገልበጥ ማለትህ ነው?!” ሁሉም ሳቀ፡፡ መኪናዎቹ በሰልፍ ተኝተዋል፡፡
ጥቂት ተንቀሳቀስን፡፡ አሁን የተገለበጠ መኪና አየን፡- ሲኖ - ትራክ” - ቀይ - አሸዋ የጫነ፡፡ በእኛ መስመር አንድ መኪናውን ያነሳል የተባለ ክሬን (ሸበል) አለ፡፡ ስለዚህ ከደብረዘይት መምጫውም ወደዚየ መሄጃውም ተዘግቷል ማለት ነው፡፡ ግራ - የተጋባ ሁኔታ ነው፡፡ አንድ መኪና ጠቅላላ የተጓዥ መኪኖችን ሰንሰለት ከወዲህም ከወዲያም ዘግቶ ማስቆሙ ይገርማል፡፡ ባንድ መኪና ጦስ አዲሳባም፣ ቃሊቲም፣ አቃቂም፣ ደብዘረይትም ቆመዋል፡፡ ተኝተዋል፡፡ ግን ለውጥ እናመጣለን መቼም! አጋዥ መኪና ይምጣ ብንል በየት ይመጣል? በሂሊከፐ‹ተርም ቢሆን ዘግነን ማንሳት አለብን! አማራጭ መንገድ የለም፡፡
ወዲያው አስቂኝ ነገር አየን፡፡ መኪና አንሺው መኪና ቀጭን ሽቦ ገመድ ልኮ አሸዋ ጭኒ የተገለበጠውን ከባድ መኪና ሊያነሳው ሲፍጨረጨር ሰው በሳቅ ሞተ! የሆነ አንበጣ የወደቀ ዝሆን ሊያነሳ የሚንፈራፈር ነው የሚመስለው፡፡ ወይም ሣር እግጣለሁ ብላ የኋላ እግሯ ብድግ አለ የተባለችው ኮሳሳ በግ ታሪክ፡፡ በመጨረሻ አንበጣው ዝሆኑን ትቶ ራሱን ከመንገዱ አወጣ፡፡
ከዚህ ቀጥሎ እንግዲህ በተለቀቀው መንገድ መኪና ለመኪና እየተሻሸ፣ መስመር በሚስተውና ደንቃራ በሚሆነው፣ በስግብግቡ፣ በቁጠኛው ወዘተ ላይ እርስበርስ እየተነጫነጨ…በመከራ አዲሱ የናዝሬት ፈጣን መንገድ ማዞሪያ ደረስን፡፡ በዘመናዊው የናዝሬት መንገድ በአየር የመንሳፈፍ ያህል ፈሰስን፡፡
ደብረዘይት ስንደርስ 4 ሰዓት ተኩል እንደደረስን ልብ አልን፡፡ ወደ ደብረዘይት ከተጠመዘዝን በኋላ የተገለበጡ መኪኖች አየን፡፡ የሚያስደነግጥ አገለባብጥ አይተናል - ከማማተብ በስተቀር ምን ይደረጋል? አማትበን አለፍን! በእኔ አታድርሰው ነው -ያበሻ ፀሎት1
የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ቀድመውናል፡፡ ቀድመውን ከደረሱ የየማህበራቱ አባላት አስተዋወቁን
“ይሄው ጠዋት የወጣን መከራ ስናይ ውለን መጣን” አሉ ለሰው፡፡ ለሸገሩ ልጅ ዘወር ብለው - ያ የምታየው ምግብ ቤት ነው - ማሰልጠኛ ክፍሎች - ሰፊ ጊቢ Guest house የእንግዳ ማረፊያም አለው እናስጐበኝሃለን”
ኮረምብታው አናት ላይ አንገቱን አስግጐ በግርማ ሞገስ የቆመውንና ቁልቁል ወደ ደብረ ዘይት ሐይቆች የሚያስተውለውን ይሄን እንግዳ መቀበያ መንገድ ላይ ስንወያይበት ነበር፡፡
“አሪፍ ቪው አለው” አልኩኝ እኔ፡፡
“ቪዥንም አለው” አለ የሥራ ኃላፊው፡፡
“ቪክትሪ ነዋ የቀረው!” አልኩኝ እኔ፡፡
“Three “V” s አለች እየሳቀች አንደኛዋ የሥራ ባልደረባ፡፡ (ተሳሳቅን)
እጃችንን ታጥበን ቁርስ ወዳለበት ሄድን፡፡ አሁን እንግዲህ ከዚህ ቀደም የተረኩላችሁን የአዋሳ፣ የድሬዳዋ፣ የደብረብርሃን የእየሩሣሌም ልማት ድርጅት ኃላፊዎች ማግኘት ጀመርኩኝ፡፡
የአዋሳው ኃላፊ ለመስቀል በኢቢስ ስለተላለፈው ፕሮግራም እና እኔን ግጥም ስለማየቱ አድናቆቱን እየነገረንና ለሥራ አስኪያጁ እያብራራለት ወደመሰብሰቢያው አዳራሽ አመራን፡፡ ከሥራ አስኪያጁ ጋር እንደተለመደው በአበሻ ቴራፒ “ጠፋህ - ጠፋህ” እየተባባልን ከንፈር እየመጠጥን አዳራሹ ደጃፍ ደረስን፡፡ እግረ - መንገዱን የናዝሬቱን ልጅ የደብረዘይቱን የጄክዶ ተጠሪ አግኝቼ ስለ ናዝሬት በቅንጫቢ አወራን፡፡
ቀጥሎ ወደ አዳራሽ ከመግባታችን በፊት የዛሬውን ፕሮግራም ዓላማ በአጭሩ ንገረኝ አልኩት፡፡ የዛሬው ፕሮግራም 3 ዓላማዎች አሉት
1ኛው የእየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ከጃክዶ ሲዳና ከጃክዶ ኤልማ በተገኘ ድጋፍ የአቅም ግንባታ ፕሮግራም 40 ከሚሆኑ የማህበራት ምሥርት ድርጅቶች ጋራ የሚያደርገው ስምምነት፡፡
2ኛው/ ድርጅቶቹን ማስተዋወቅ እርስ በርስ የሚደጋገፉበትን ሁኔታ እንዲፈጥሩ
3ኛው/ የሚሠሩበትን ሁኔታ ግንዛቤ ማስጨበጥ!!
(ይቀጥላል)

Read 6166 times