Print this page
Monday, 03 November 2014 08:08

ብሩክ ኢትዮጵያ” በሃላባ ያስገነባውን ማዕከል አስመረቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

         ብሩክ ኢትዮጵያ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል በሃላባ ልዩ ወረዳ በ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባቸውን የሃላባ ቁሊቶ ከተማና አካባቢው የጋማ እንስሳት ደህንነት ጥበቃና ስልጠና ማዕከልና የጋማ እንስሳት ውሃ ማጠጫ ገንዳዎችን አስመረቀ፡፡
በርካታ የጋማ እንስሳት በሚስተናገዱበት በሃላባ ከተማ ዋና የገበያ ስፍራ ላይ የተገነባው ማዕከል፤ ከእንስሳት እንክብካቤ ጋር የተያያዘ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ፣ እንስሳቱ ተገቢውን መኖና ውሃ እያገኙ በምቹ ሁኔታ የሚቆዩበት ሲሆን እንስሳቱን ከስርቆት በመከላከልና ከሚደርስባቸው ስቃይ በማዳን ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በልዩ ወረዳው ለሚገኙ የመንግስት ክሊኒኮችና የእንስሳት ህክምና መስጫ ማእከላት የአቅም ግንባታ ድጋፎችን የሚያደርገው ብሩክ ኢትዮጵያ የአካባቢውን የጋማ ከብቶች የጤና እንክብካቤ ለማሳደግ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በቁሳቁስ፣ በመድሃኒትና በህክምና መሳሪያዎች ማሟላቱን የድርጅቱ ሃላፊ አቶ ጥበቡ ደበበ ተናግረዋል፡፡
ህክምናውን ለማሻሻል የእንስሳት ሀኪሞችንና የህብረተሰብ የእንስሳት ጤና ሰራተኞችን አቅም በስልጠና በዘላቂነት ከማጎልበትና ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በማስጨበጥ የተሻሉ የጋማ ከብት አያያዝ ልማዶችን ከማዳበር ባሻገር፣ በልዩ ወረዳዋ በሚገኙ ክሊኒኮችና የጤና ኬላዎች አስተማማኝ የጋማ እንስሳት መድሃኒት አቅርቦት እንዲኖር ለማስቻል በ370 ሺህ ብር የመድሃኒትና የክትባት ተዘዋዋሪ በጀት አሰራር ቀይሶ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሃላባ ልዩ ወረዳ የመንግስት ተወካይ፤ አቶ መሐመድ ኑር ሳኒያ በወረዳው ያሉት ከ39 ሺህ በላይ የጋማ ከብቶች ለህብረተሰቡ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ ይሄም ሆኖ ግን የጋማ እንስሳትን ጤንነትና ደህንነት ከማስጠበቅ አንጻር ችግሮች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ “ብሩክ ኢትዮጵያ” በልዩ ወረዳው እያከናወናቸው የሚገኙ ስራዎች የአካባቢውን የጋማ ከብቶች ደህንነት ለማስጠበቅ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡
“ብሩክ ኢትዮጵያ” የተቀናጀ የጋማ ከብት ደህንነት ትብብር ፕሮግራም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ጉራጌ፣ ሃዲያ፣ ወላይታና ጋሞ ጎፋ ዞኖች እንዲሁም ከአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር በሰሜን ጎንደር ዞን ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡


Read 1336 times
Administrator

Latest from Administrator