Monday, 03 November 2014 07:22

ፖለቲካችንን በአዳም ረታ “መረቅ” ውስጥ ስንቃኘው…

Written by  ኤሊያስ
Rate this item
(7 votes)

የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” ሰለባ ሆኑ!
ከ27 ዓመት የስልጣን ዘመን በኋላም ስልጣን አልጠገቡም!
 “የዜግነት ሰብአዊ ክብር ከመግፈፍ የበለጠ በጥባጭነት አለ?” - መረቅ

          ሰሞኑን በዚህችው ባልታደለችው አፍሪካችን (አለመታደል ነው ኋላቀርነት?) አንድ አሳዛኝ ክስተት ተፈጽሟል፡፡ የምስራች ዜና ባይሆንም ነገርዬውን እንደሰማችሁት እገምታለሁ (ዕድሜ ለቴክኖሎጂ!) እናላችሁ… ቡርኪናፋሶን ላለፉት 27 ዓመታት የገዙት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፤ በ2015 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የህግ ማሻሻያዎች (መጨመር፣ መቀነስ፣ መሰረዝና መደለዝን ያካትታል) ለማድረግ ሞከሩ፡፡ ይሄም ነው የአሳዛኝ ክስተቱ መነሻ ሰበብ፡፡
ለነገሩ በፕሬዚዳንቱም አይፈረድም (ሱስ እኮ ነው!) አያችሁ…ሰውየው በ27 ዓመታት የቤተመንግስት ኑሮ የስልጣን ጥማቸው አልረካም (ድሮስ ሙጋቤን!) እናም… በአቋራጭ የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ጥረት አደረጉ (ብዙ እኮ አላጠፉም!) የአገሪቱን ህግ ለማሻሻል (በ “ህጋዊ መንገድ” ማለት ነው!) የቡርኪናፋሶ ህዝብ ግን ታክቶታል መሰለኝ… ሊታገሳቸው አልፈቀደም (ይሄኔ ብዙ ችሏቸዋል!) ፕሬዚዳንቱ እንደሃሳባቸው ቢሆን በቀጣይ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን የህግ አንቀፅ ባለፈው ሐሙስ በፓርላማ ያስፀድቁ ነበር፡፡ ግን ተቀደሙ፡፡ (ማን ነበር “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” ያለው?!)
ህዝቡ ሰሞኑን ለተጨማሪ ዓመታት በስልጣን ላይ የመቆየት ጥማታቸውን በመቃወም አደባባይ የወጣ ሲሆን ፓርላማውን በእሳት እንዳጋየ ተዘግቧል፡፡ (ይሄም ሌላ የኋላቀርነታችን ምልክት ነው) ሃይል …ዱላ…እሳት …ጥይት…ታንክ …መድፍ …ጥላቻ …ኢሰብአዊነት…ጭካኔ… ወዘተ ካልተደባለቁበት ተቃውሞን መግለጽ አንችልም፡፡ የአፍሪካ መንግስታትም ካላሰሩና ካልገደሉ የተቆጡ አይመስላቸውም (ሲቆጣ የሚገድል መንግስት ያለው አፍሪካ ውስጥ ነው!) አሁን በአገሪቱ የድንገተኛ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን በአፋጣኝ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ ህዝቡ ፕሬዚዳንቱ አሁኑኑ ከስልጣን እንዲወርዱ እየጠየቀ ሲሆን እሳቸው ግን አንድ ዓመትማ እገዛችኋለሁ እያሉ ነው፡፡ (“የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” ነው የሆኑት!) እኔ የምለው… እኛ አፍሪካውያን ከስልጣኔና ከዲሞክራሲ ጋር በቅጡ የምንተዋወቀው መቼ ይሆን? (እንደ ኢህአዴግ “ዲሞክራሲ ሂደት ነው” እንዳትሉኝ!) ለማንኛውም ለቡርኪናፋሶ “ሂደት” ምናምን የሌለው ሰላምና መረጋጋት ተመኝተን፣ ወደ ራሳችን ገበና እንዝለቅ (ዲሞክራሲን መጋት ወይም በክትባት መስጠት አይቻልም!)
እኔ የምላችሁ… የዝነኛውን ደራሲ የአዳም ረታን አዲስ ልቦለድ አነበባችሁ? “መረቅ” የተሰኘውን ባለ 600 ምናምን ገጽ ማለቴ ነው፡፡ እኔ መቼም እንደሱ ብዙ የሚያመርት (prolific) የጦቢያ ደራሲ አላውቅም፡፡ (ይችልበታል ነው የምላችሁ!) “መረቅን” ከቀደምት ሥራዎቹ የሚለየው ደግሞ ፖለቲካ ላይ የሚያተኩር መሆኑ ነው (የፖለቲካ መረቅ በሉት!) መጽሐፉ የ60ዎቹን የተማሪ አብዮት ተከትሎ እንደ አሸን የፈሉትን ታጋይ ፓርቲዎች ሚና ያስቃኛል - በገፀ ባህርያቱ በኩል፡፡ አልአዛር የተባለው ዋና ገፀ ባህርይ በደርግ መንግስት በፀረ አብዮተኛነት ተጠርጥሮ በታሰረ ወቅት፣ አንድ መቶ አለቃ የወታደር ካድሬ እውነቱን እንዲያወጣ እንዴት እንደሚያስፈራራው እንመልከት:-
“…አየህ አገሬ በጦር ቢመጡባት ትመልሳለች፡፡ ከልጆቻችን ጋር አብሮ ከበላ ከጠጣ ቦርቧሪ ጋር መታገል ግን ትንሽ አያስቸግርም? እኔ የዋህ አይደለሁም፡፡ እንዲህም አይነት አፍራሾች በአንተ አይነቱ ቀዳዳ ተጠቅመው ነው የሚመጡት፡፡ ኑጐች የሚመጡት ከሰሊጥ ተደባልቀው ነው፡፡ ያን ቀዳዳ መድፈን አለብኝ፡፡ አሁን እተውሃለሁ፡፡ አንዳንዴ ቂል መመታት አለበት፡፡ “አውቃለሁ” የሚል ቂል ከጠላት ያላነሰ አደገኛ ነው፡፡ ደደብነት ከቦንብ ሊብስ ይችላል፡፡ አስብበት፡፡ ካልተጠነቀቅህ እንደ ኑግ ትወቀጣለህ፡፡ ከዛ በኋላ ስህተቱ የእኔ አይደለም፡፡ ፋሺሽት ፋሺሽት ብትለኝ አይገባኝም፡፡ የሚገባቸው ቢኖሩ በአንተ አይነት ከብት የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ ትክክለኛ ዜጋ ነህ? ወይስ ማንም አገር ቆራሽ የሚነዳው ከብት? “ከብት አይደለሁም” ካልክ ማረጋገጫ እፈልጋለሁ፡፡ ተግባባን? የአገር ሕልውና ላይ ዲሞክራሲ፣ ሰብአዊ መብት ቀባጢሶ አይሰራም… ማንም ከሕግ አያመልጥም፡፡ የአገሬ ሕልውና ነጋሪት ጋዜጣ ውስጥ አይደለም ያለው፡፡ ታሪክና ጥይት ውስጥ ነው፡፡ “ወታደር መሃይም ነው” አይደለም የምትሉት? የእናንተን ትምህርት አላየን፡፡ በፖለቲካል ሳይንስ ባችለር ዲግሪ አለኝ፡፡ ትከሻዬ ላይ የምታየው ምልክት የመቶ አለቃ ሊሆን ይችላል፡፡ ምሁር ለመሆን አትሞክርብኝ፡፡ አሁን ወረቀት ይመጣልሃል፡፡ እዚያ ወረቀት ላይ ሆቴል ተቀምጣችሁ ያወራችሁትን ትዝ የሚልህን አንድ ሳታስቀር ታሰፍራለህ፡፡ እኔ “ሰላማዊ አይደለህም” እላለሁ፡፡ አንተ “ነኝ” ትላለህ፡፡ ቀላል ነው፡፡ የምናመሳክረውን እናመሰናክራለን፡፡ እኔ ስላጋጠምኩህ እድለኛ ነህ፡፡ መተባበር ካላማረህ መንገድ መንገድ አለ፡፡ ከምትነግረንና ከምትፅፈው ኑግ ወይም ሰሊጥ መሆንህን ማወቅ አለብን፡፡ ይገባሃል የምልህ? ማርክሲዝም ስለ ሰሊጥ አያውቅም፡፡ አንድ ቦታ አሳየኝ ማርክሲስቶች ስለ ኢትዮጵያ የፃፉበትን ቦታ፡፡ ለእኔ ጋቢ የለበሰ አድሃሪ ሱፍ ከለበሰው ማርክስ የሚሻል አይመስለኝም፡፡ አንተ ማርክሲስት ሆንክ አልሆንክ ግድ የለኝም፡፡ ዕውነቱን እፈልጋለሁ፡፡ ተግባባን? መግባባት ማለት እኔ የማዝህን ማድረግ ማለት ነው፡፡ መግባባት ማለት እውነቷን ሳታስቀር መናገር ማለት ነው፡፡ ይሄን እዚህ ላይ ማፈንዳት እችላለሁ…”
ገባችሁ አይደለ… ምን እንደሚያፈነዳ? አፉፋ (ፊኛ) አይደለም$ ጥይት ነው፡፡ የወታደር መንግስት ወይም አምባገነን ገዢ ይሄው ነው፡፡ መጽሐፉን መቃኘት እንቀጥል፡፡ በነገራችሁ ላይ የአዳም ረታን “መረቅ” ፖለቲካዊ ልቦለድ ብየዋለሁ (ታሪካዊ ልቦለድ እንደሚባለው) አሁን ደግሞ የአላዛር አባት በፖለቲካ ውስጥ እጁ የሌለበት ልጃቸው ጉዳይ ሲያሳስባቸው የሚሉትን እንስማ፡፡ ተባረኪ የተባለች አብሮ አደግ ፍቅረኛው ግን ቀንደኛ ኮሙኒስት ናት - የኢህአፓን ካፓ የደረበች፡፡ የፖለቲካ ድርጅት  ፍቅር አስክሯት ፍቅረኛዋን አላዛርን የዘነጋች፡፡ አሁን ግን ወደ አላዛር አባት ምክር ልውሰዳችሁ፡፡ “…በሚያነዱት እሳት የተማረው ጥቂት ወጣት እንዲነድ ነው፡፡ ፖለቲከኛ ባትሆን እንኳ በወታደር አስጠምደው ሊያጠፉህ የሚፈልጉ መአት ናቸው፡፡ አገሪቷ አሁን ጥምዝዝ ያለ የወሬ በሽታ ውስጥ ናት፡፡ “ምሁሩ በመሰደድ ላይ ነው” ይላሉ፡፡ አገራችን ብዙ ምሁር የላትም - የሚንጋጋም፡፡ የፖለቲካውን አለም ያሽከረክራሉ የሚባሉትን አንዳንዶቹን አውቃለሁ፡፡ ማክረር ይወዳሉ፡፡ በግድ ቼ ጉቬራን እንሁን ብሎ ነገር፡፡ አገሪቷ ቬትናም ብትሆን ደስ ይላቸዋል፡፡ “ለምን?” ብትል ሆ ቺ ሚንን ለመሆን ይቀላቸዋል፡፡ ሌላው አለም ያሉ ግለሰቦች ጀግና የተባሉበትን ነገር ባያስፈልግም እዚህ ቢያደርጉ ደስ ይላቸዋል፡፡ በዚያ ብናደንቃቸው ይወዳሉ፡፡ ሺህ አይነት የአገርና የኢትዮጵያ ካባ ቢያለብሱት አንድ ነገር አውቃለሁ፤ ቂል አይደለሁም I am not a fool. አንተም እንድትሆን አልፈልግም፡፡ በግድ “እንጣላ” ብሎ ነገር ፍለጋ አለ? ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ላይ እንኳን አክራሪ አይደለችም፡፡ ሃይማኖታችንና ቋንቋችን የተዳቀለ ነው፡፡ ይሄ ልዩ ሊበራሊዝም ነው፡፡ የትም አገር የለም፡፡ ምን ማለት ነው? ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ላይ እንኳን አክራሪ አይደለችም፡፡ ሃይማኖታችንና ቋንቋችን የተዳቀለ ነው፡፡ ይሄ ልዩ ሊበራሊዝም ነው፡፡ የትም አገር የለም፡፡ ምን ማለት ነው? እንዲህ የሚያባላ ነገር የለም ማለት ነው፡፡ አንዳንድ አለባበስ አበላልን ምናምን የመሰለ ከባዕድ እንደሚቀዳ ልክ እንደ ጆሊ ጃኪዝም ምናምን በለው ፖለቲካውን…፡፡ መተማማት መጋደልና መሰዳደብ አኮሳተረው እንጂ ውስጡ ያው ነው፡፡ የፖለቲካ ጆሊ ጃኮች ናቸው፡፡ ወደ ፓስታ ሊለወጡ የሚለፉ ድፎ ዳቦዎች ናቸው፡፡ አሁን የማየውና የምሰማው ሁሉ ልክ አይደለም፡፡ አንድን ነገር ሳይመረምር በተራ ልዩነት ላይ ተመስርቶ ሺት የሚሰጥህ ገና ያላደገ ልጅ ነው፡፡ ያውም ሪታርድድ የሆነ፡፡ ልዩነትን በቋንቋ በማግነን በማይሆን ነገር ቶሎ ተገዳድሎ መስዋዕት በመፍጠር፣ የአላማ ነገር ተትቶ (ቀድሞም የለም) በነዚህ በፈጠሩአቸው ሰማዕታት ስም ለዘላለም እንድንቀያየም የሚፈልጉ ይመስላል… ስለዚህ ጊዜህን አታጥፋ፣ ለተባረኪ አትጨነቅ፡፡ ማታ ማታ እሷን ስትጠብቅ አይሃለሁ…  ፍቅር ከሁለት በኩል ሲመጣ ነው፡፡ በአንተነትህ ሳይሆን በፖለቲካ አቋምህ የምትወደድ ከሆነ እርሳው፡፡ የተለወጠችው እሷ ናት፡፡ ቆንጆ ባገሩ ሞልቷል፡፡ የሆነች ዘጠዘጥ ቂጣም፡፡ “ሶሪ ሺ ዳዝንት ሃቭ ክላስ” እኔ እንደውም ድሮ ከፀናፅል ጋር ነበር የጠረጠርኩህ፡፡ (እሷም ሌላ አብሮ አደጉ ናት!) ለማንኛውም በፍቀር መፍረድ አልችልም፡፡ ግን ለራስህ በቶሎ ስለ ላይፍህ መወሰን ካልቻልክ፣ ጣልቃ መግባት አለብኝ፡፡ ሁለተኛ በሃሳብ ባክነህ በመንገድ ላይ ብቻህን እያወራህ ስትሄድ ማየት አልፈልግም፡፡”
ይሄ ሁሉ የአባትየው ዲስኩር ለሌላ አይደለም፤ ልጃቸውን ከፖለቲካ እሳት ለማትረፍ ነው…እናም በሚያውቁት ባለስልጣን በኩል ለትምህርት ወደ ምስራቅ ጀርመን ሊልኩት እንዳሰቡ ይነግሩታል፡፡ ብቸኛ የመኖሩን ተስፋ ኢህአፓ የተባለ ድርጅት ስለነጠቀው ለመሄድ አላመነታም፡፡ ፍቅረኛው ተባረኪን ለኢህአፓ ያለ አደራ አስረክቦ ጀርመን ገባ (ሶሻሊዝምን ሽሽት ወደ ሶሻሊስት አገር!)
እስቲ አሁን ደሞ የአላዛርን ንፁህ ፍቅር በኢህአፓ የለወጠችው ተባረኪ የምትለውን እንስማት…ስለ ፖለቲካ፣ ስለ እነ ማርክስ፣ ስለ “ለጭቁኑ ህዝብ መታገል”፣ ስለ መስዋዕትነት ወዘተ…
”ፖለቲካ ለአገር ማሰብ ነው፡፡ ፖለቲካ መታደል ከተጨመረበት ለአገርና ውስጥዋ ለሚኖረው ለሕዝብ መልካም ለመስራት መጣር ነው፡፡ “ከራስ በላይ ነፋስ” በሚባለው ነገር አላምንም፡፡ ከራስ በላይ ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ሰፈር፣ ወረዳ፣ አውራጃ፣ ክፍለሀገርና አገር አሉ፡፡ የቻለበትም አህጉርና አለምን በልቦናው ይከታል፡፡ የአገራችን አንድ የሚታይ ማንም የሚያወራባት ፀባይዋ በደሃና በተራራ የተሞላች መሆኗ ነው፡፡ አንድ ሰው በአገሩ ደሃ መሆን የለበትም፡፡ ቢያንስ መሰረታዊ ፍላጐቶቹና መብቶቹ መጠበቅ አለባቸው፡፡ የድሆች መናጢነት የሚመጣው ሰነፍ ስለሆኑ አይደለም፡፡ የለፉበት ውጤት በጥቂት ማን አለብኝ ባዮች ስለሚዘረፍ ነው፡፡ እነዚህም ዘራፊዎች ዝርፊያቸውን ያለ ሃሳብ ለማካሄድ ማስፈራራትንና ራሳቸው ያወጡትን ሕግ ይጠቀማሉ፡፡ ድሆች ወይም ጭቁኖች መብታቸውን ለማስከበር የሚነሱት ከወደቁበት የደሃነት አዘቅጥ ለመውጣት እንጂ በሃብታሞቹ ቀንተው አይደለም፡፡ ወይም በረብሻ ሃራራ ስላደጉ አይደለም፡፡ የሰዎችን የዜግነት ሰብዓዊ ክብር ከመግፈፍ የበለጠ ሌላ በጥባጭነት አለ? እንደማንም ማሰቢያ አእምሮ እንዳለው ፍጡር የአካባቢዬ ሁኔታ ሲለወጥ መለወጥ አለብኝ፡፡ ይሄ ደንብ ነው፡፡ ስድሳ ሰባት አመተምህረት መጨረሻ ላይ ሚኒሊክ ትምህርት ቤት የማውቀው ልጅ፣ አንድ ጥናት ክበብ አስገብቶኝ፣ ማርክሲስት ፍልስፍና ስማር፣ የግል ህይወቴ ቅርፅ ብቻ ሳይሆን ማራኪ ትርጉም አገኘ፡፡ ማርክሲዝምን እንደ አላሌሆይ ወይ እንደ ሆያ ሆዬ የሚዘፍኑ ልጆች አጋጠሙኝ፡፡ ተፎካካሪ ነኝና ብዙ ጊዜ የፍልስፍና መሰረታዊያኑን በአጭር ጊዜ መረዳት አላቃተኝም፡፡ ከሁሉ የሳበኝ ዲያሌክቲካልና ሂስቶሪካል ማቴሪያሊዝም ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱን በመጠኑ ስረዳ በምኖርበት አለም ላይ ያሉ ተፈጥሮአዊም ሆኑ ማህበራዊ እውነታዎች በሚገርም መልክ ለግንዛቤዬ ተከፈቱ፡፡ በተወሰኑ ሕጐች ማለት በተቃርኖ ሕግ፣ በሻሪ ሻሪ ሕግ ወዘተ… የተወሳሰቡ ማሕበራዊ ጉዳዮች ሲተነተኑ አሰራራቸው ግልጽ ሆነልኝ፡፡ የሆነ ነገር በራልኝ፡፡ ብሩህነት ተሰማኝ…”
ለማሳያነት እኒህን ጠቀስኩ እንጂ “መረቅ” የያኔውን ፖለቲካ በስፋትና በጥልቀት ነው የሚዳስሰው፡፡ “የፖለቲካ ቅቅል” በሉት፡፡ ልቦለዱን ስታነቡ ዛሬም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዙም አለመለወጡን ትረዳላችሁ፡፡ ምናልባት ልዩነቱ ከተማ ውስጥ የታጠቁ ሃይሎች አለመኖራቸው ብቻ ነው (ያኔ እኮ መዲናዋ የጦርነት አውድማ ነበረች!) ዛሬ ተኩስና መገዳደል ባይኖርም የፖለቲካ ባህሉ ግን ስልጡንነትን አልተቀዳጀም፡፡ ዛሬም እንደ ያኔው ሁሉም ፓርቲ “የእኔ ብቻ ነው ልክ” ማለቱን በርትቶበታል፡፡ ለአንድ አገር እንደሚሰሩ ፓርቲዎች ቁጭ ብሎ መነጋገርና መወያየት ዛሬም እርማችን ነው፡፡ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽና የፕሬስ ነፃነት ወዘተ… በቅጡ አልገቡንም፡፡  ሁሉ ነገር ሃሳዊ ይመስላል፡፡ የይስሙላ፡፡ ለአፍ ዓመል የሚወራ፡፡  ከህይወት የራቀ፡፡ ወረቀትን የሙጥኝ ያለ፡፡ የአዳም ረታን “መረቅ” አንብባችሁ የፖለቲካ ታሪካችንን በቅጡ እንድትገነዘቡ እየጋበዝኩ፣ እዚያው ልቦለድ ላይ ስለ ዲሞክራሲ ባነበብኳት አንድ ጥቅስ ልሰናበታችሁ:-
“ዲሞክራሲ ያለ ይመስልሃል? ዲሞክራሲ ጨረቃ ላይ ያለች፣ አመድ ላይ እየተንከባለለች ሊፒስቲክ የምትቀባ የዞረባት ቺክ ናት” (የያኔዋን የጦቢያ ዲሞክራሲ ማለቱ ነው!) የዛሬዋን የጦቢያ ዲሞክራሲ እንዲህ አሳምሮ የሚገልጽ የተባ ብዕር ያለው ደራሲ ያስፈልገናል፡፡ በነገራችሁ ላይ የጦቢያ ፖለቲከኞች “መረቅ”ን ማንበብ አለባቸው (አቋም መያዝ ግን አይፈቀድም!) መጽሐፉ የፖለቲካ ማኒፌስቶ ሳይሆን በውብ ቋንቋ የተኳለ ልቦለድ ነው!!

Read 5354 times