Monday, 03 November 2014 07:22

ንግድ ምንድን ነው - ትንባሆ፡፡ ትርፉ ምንድን ነው - ሳል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

(ዘልኤ አይቤ ጋዬ - ዎሬ አይቤ ቁፌ) የወላይታ ተረት

ከላፎንቴን ታሪኮች አንዱ እንዲህ ይለናል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የሰማይ ቁጣ በእንስሳት ላይ እየመጣ ነው ስለተባለ የዱር እንስሳት ተሰብስበው ማ አጠፋ? ማ አጠፋ? በመባል ጥፋተኛውን አጋልጠው ለመስጠት አውጫጪኝ ይቀመጣሉ፡፡ እንስሳት ሁሉ ለረሀብ ተጋልጠው የእርስ በርስ ፍቅራቸው ሁሉ ሞቷል፡፡ ሁሉ ተኮራፍፏል፡፡ ተኩላ ከተኩላ እርግብ ከእርግብ እንኳ አይነጋገሩም! ከመጣው መዓት ለመዳን ሁላችሁም ሀሳብ ስጡ ተባለ፡-
አንበሳ ወንበሩን ያዘና በሊቀመንበርነት፡-     
“ወዳጆቼ ሆይ! የሰማይ ቁጣ ጥፋተኞች ላይ መውረዱ ደንብ ነው፤ አንቃወመውም፡፡ ነገር ግን ሁሉ ኃጢያት እኩል አይደለምና የበለጠና የከፋ ኃጢያት የሰራውን መለየት ይኖርብናል! ያ ጥፋተኛ ቅጣቱን ሲቀበል ለእኛ ስርየት፣ መዳኛ ይሆንልናል! ህሊናችንን ሳናጭበረብር ዕውነቱን እንናገር፡፡ እኔ በበኩሌ  ጥቂት ያስቀየሙኝን በጎች በልቻለሁ - አንዳንዴም እረኞቻቸውንም የቀመስኩበት ጊዜ ነበረ፡፡ ወድጄ አይደለም ስላስቀየሙኝ ነው፡፡ ይህ ጥፋት ነው ካላችሁ ሞት ይፈረድብኝ፡፡ ብቻ ዋናው ነገር ሌሎቻችሁም ኃጢያት ኃጢያታችሁን ተናዘዙ፡፡ ድርሻ ድርሻችሁን ውሰዱ፡፡ ከዚያ የከፋ ጥፋት የሰራውን እንለያለን፡፡ (It is only fair that all should do their best
to single out the guiltiest)”
ከዚያ ቀበሮ ተነሳና
“ንጉሥ ሆይ! ለእንደ ርሶ ያለ የተከበረ የዱር አራዊት ጌታ፤ በግ መብላት በጭራሽ ሀጢያት ሊሆን አይችልም፡፡ እነዚህን ባለጌና ልክስክስ በጎች መብላት ፈፅሞ ሊያስጠይቅ አይገባም፡፡ እረኞችም ቢሆኑ በእኛ ላይ ሲዶልቱ የሚኖሩ ናቸውና የእጃቸውን ነው ያገኙት” ብሎ ተቀመጠ፡፡ ጭብጨባው ቀጠለ፡፡
ቀጥሎ ማንም በነብር፣ በድብና በመሳሰሉት ክቡር እም ክቡራን ይቅርታ - የለሽ ወንጀል ላይ ምንም ሀሳብ ሳያነሳ ጭራሽ እንዲህ ያለ የተቀደሰ ተግባር የፈፀመ ከዚህ የለም፤ እየተባለ ውዳሴው ተዥጎደጎደ፡፡
በመጨረሻ አህያ ተነሳች፡-
“አንድ ቀን አንድ ሰፊ የሣር መስክ ሳቋርጥ ረሀብ አንጀቴን ቢመዠርጠኝ የምላሴን ያህል ቅንጣት ሳር ግጬ አልፌያለሁ፡፡ ያንን ሳር የመጋጥ መብት እንደሌለኝ በእርግጥ አውቃለሁ” አለች፡፡
ሁሉም እጃቸውን እያወጡ በአህያ ላይ የእርግማን መርግ ይጭኑባት፣ ይወርዱባት ጀመር፡፡ አንድ የተማረ፣ ብዙ ያነበበ የሚባል ተኩላም ተነስቶ፤
“ከዚህ በላይ በዓለም ላይ ኃጢያት ተሰርቶ አያውቅም፡፡ የኃጢያቶች ሁሉ ኃጢያት የሰው ሣር መጋጥ ነው! የሁላችንንም ኃጢያት ልትሸከም የሚገባት ይህቺ አህያ ናት! ቁጣውም እሷ ላይ መውረድ አለበት፡፡ የተንኮል ሁሉ ደራሲ እሷ ናት! ፎ! የሰው ሳር እንዴት ይጋጣል?! ስለዚህ ሞት ነው የሚገባት! ሆኖም አንድ ሀቅ ልጨምር ብሎ በግጥም ቀጠለ፡፡
“ሀብታም ሆንክ ደሀ፣
ክክቡር ነህ የተባልክ ወይ ከንቱ ቁጥር
ሁልህ ይደርስሃል የተራህ ሥፍር
ችሎት ይቀባሃል፣ ወይ ነጭ ወይ ጥቁር!”
                                              *         *         *
ፍሬድሪክ ኒች “ከመጥፎ ሥራ ጋር አብሮ ከመኖር ከመጥፎ ህሊና ጋር አብሮ መኖር ይከብዳል” ይላል፡፡ በሌላው ላይ በጅምላ ስምምነት፣ በመንገኝነት መፍረድ ትልቅ ኃጢያት ነው፡፡ ውሎ አድሮ እንቅልፍ መንሳቱ አይቀሬ ነው፡፡ ከህሊና ጋር በእፎይታ ማደር፣ ያለ አንዳች ወንጀለኝነት ስሜት አንገትን ቀና አድርቶ ለመሄድ መቻል ታላቅ ጸጋ ነው፡፡ የራስን አሳር የሚያህል የተቆለለ ወንጀል አድበስብሶ አንዲትን ቀጭን ሽፋን አጋኖ በሌላው ላይ መደፍደፍ አገር ገዳይ ነው! ህዝብ አሰቃይ ነው፡፡
“በክፉ ሰዓት የእናት ልጅ አይታመንም!” ይላል አበሻ ሲተርት፡፡ በክፉ ሰዓት የማ ባህሪ መቼ እንደሚቀየር አይታወቅም፡፡ በክፉ ሰዓት የትኛው ወዳጅ ተገልብጦ ጠላት እንደሚሆን አይታወቅም፡፡ ብዙ የፌሽታ ጊዜ ጓደኞች ጊዜ ከምበል ሲል አብረው ይከነበላሉ! ዕበላ - ባዮች፣ አቋም - የለሾች፣ አድር-ባዮች፣ አሥጊና አጥፊዎች ናቸው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ስለሆነም ለህዝብም ለአገርም አይበጂም!
በጥንታዊት ቻይና የዌይ ግዛተ - መንግስት አንድ ለንጉሱ ታማኝ ሚሱ ሳይ የሚባል ባለሟል ነበር፡፡ የግዛቱ ህግ “የንጉሱን ሰረገላ በሚስጥር የነዳ ሰው እግሩ ቆረጣል” ይላል፡፡ ያ ታማኝ ሰው እናቱ ትታመምና ልትሞት ታጣጥራለች፡፡ ሊደርስላት የንጉሡን ሰረገላ ምንም አይሉኝም ብሎ እየነዳ ሄደ፡፡ ንጉሡ ይሄን ሲሰሙ “አይሱ ሳይ! እጅግ ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ነው፡፡ ለእንቱ ሲል እግሮቹን እንደሚያጣ ረሳ!” አሉ፡፡ ታማኝ ሰዎች ታማኝነታቸው የት ድረስ መብት እንደሚሰጣቸው የረሱ‘ለት ራሳቸውን ያጣሉ ነው ትምርተ - ታሪኩ (Lesson/Moral of the story እንዲሉ ፈረንጆች፡፡)
የሀገራችን ፕሮጀክት ቀራጮች፣ ንድፈ - ሀሳብ አንጓቾች (theoreticians) አማካሪዎች፣ ስትራቴጂስቶች፣ ቀዳሽ ዳሳሾች በእርግጥ ከልባቸው ለህዝብና ለአገር ተቆርቁረው ነው ወይ ሥራውን የሚሰሩት ብሎ መፈተሸ የአባት ነው! ማ በተዘዋዋሪ ወገንተኛ ነው? ማ ልታይ ልታይ እያለ ከሙሰኞች ጋር የተሰለፈ ነው? ማ አፍአዊ፣ ማ ልባዊ ነው? ማ አጉራሽ አልባሽነትን እንደትራንስፎርሜሽን እያስቆጠረ ነው? ውስጣችንን እንፈትሽ፡፡ አንደበተ - ርቱዑን ከበቀቀኑ እንለይ፡፡
ፖለቲካችን፣ ኢኮኖሚያችን፣ ማህበራዊ ግንኙነታችን በአስመሳይ ሰዎች ሲታጠር ህይወታችን ጉድፍ የተሞላ፣ በደል የበዛው፣ ዕድገታችን ሀሳዊ፣ ፍቅራችን ነውር ያጎደፈው፣ ተስፋችን ጨለግላጋ፣ የጋራ ቤታችን የተራቆተ እንደሚሆን ገሀድ ነው፡፡ ምን እየዘራን ምን እያጨድን እንደሆነ በቅጡ ልብ እንበል፡፡ “ንግድ ምንድንነው? ትንባሆ፤ ትርፉ ምንድን ነው? - ሳል” የሚለውን የወላይትኛ ተረት አበክረን እናስምርበት!

Read 4766 times