Monday, 20 October 2014 08:06

የEBC “ጥቁር ወተት” የታለመው ለማን ነው ?

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)

20 የቴሊቪዥን ቻናሎች… ለጐረቤት አገርም ይተርፋሉ!
ኢህአዴግ ይቅርታ ሲጠይቅ አለመስማታችን ያሳዝናል!   

     ባለፈው ሳምንት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የተከበሩ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፤ ለሃይል መቆራረጡ ይቅርታ መጠየቃቸውን አጉልቼና አፍክቼ መፃፌ ይታወሳል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ ቀደም ሲል የከተማዋ ከንቲባም ይቅርታ መጠየቃቸውን አንስቼ፣ ኢህአዴግ አዲስ የይቅርታ ባህል መጀመሩንና እኛንም (መራጩን ህዝብ ማለቴ ነው!) እያስለመደን መሆኑን አወድሼ ነበር፡፡ ግን ተሳስቻለሁ፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የተከበሩ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በፓርላማ እንደተናገሩት፤ እኛ የኢህአዴግን ባህርይ ስለማናውቅ እንጂ ይቅርታ መጠየቅ ለፓርቲው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ (እንዴት ሳንሰማው ቀረን?) በነገራችሁ ላይ ባለፈው ሳምንት ኢህአዴግ የዓመታት የይቅርታ ዕዳ እንዳለበት የጻፍኩት የፓርቲውን ባህርይ ባለማወቅ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ (ይቅርታ ባህሉ ነው ተባለ እኮ!)
እግረመንገዴን ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ ከተናገሩት ውስጥ ሌላ ያስደመመኝን አባባል ልንገራችሁ፡፡ በፓርላማ ብቸኛው የተቃዋሚ ተወካይ የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤ “ኢህአዴግ ከጠብመንጃ ይልቅ ውይይትን ይፈራል” በሚል ለሰነዘሩት አስተያየት ጠ/ሚኒስትሩ ሲመልሱ፤ “በነገራችን ላይ ኢህአዴግ ጠብመንጃም ውይይትም አይፈራም” ብለዋል - በልበሙሉነት፡፡ (ሁለተኛውን ካልሆነ በቀር አንደኛውማ ግልጽ ነው!) ለማንኛውም ግን ኢህአዴግ የውይይት መድረኩንና ተሳትፎውን በማስፋት (በተቃዋሚዎች ቋንቋ የፖለቲካ ምህዳሩን--) በአፍ የተነገረውን በተግባር ማስመስከር አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር ውይይት አለመፍራቱን ማሳየት ይኖርበታል (ለሃሜተኞች እድል መስጠት አይገባም!) በእርግጥ ውይይት ሲባል ከደጋፊዎች ጋር ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ከተቃዋሚዎች----ፖሊሲውን ከማይደግፉ ቡድኖች-----ከሚተቹት ምሁራንና ጋዜጠኞች እንዲሁም ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ የተለየ ርዕዮተ ዓለም ከሚያቀነቅኑ ኢትዮጵያውያን ጋር ሁሉ መወያየትን ይጨምራል፡፡ (“ልማቱን ትቶ ሲወያይ ይክረም”አላልኩም!)  እናንተዬ… ሰሞኑን የተሰራጨውን ዜና ሰምታችሁልኛል? (ያስጐመዣል!) እኔ በበኩሌ የቀረበልኝን ምግብ እንደ መጐምዠት ዓይነት ነገር ነው የተሰማኝ፡፡ እናላችሁ… የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ለ20 የቴሌቪዥን ቻናሎች ፈቃድ እንደሚሰጥ የሚያበስር ነው - የሰማሁት ዜና፡፡ እኔማ መጀመሪያ ላይ ጆሮዬን ሁሉ ተጠራጥሬው ነበር፡፡ ምናልባት---ውስጤ ያረጀው የዓመታት  ምኞቴ በጆሮዬ አስተጋብቶ ቢሆንስ---አልኩኝ፡፡ ደግነቱ የሥራ ባልደረባዬ አብራኝ ነበረች፡፡ እናም ዜናው (የምስራቹ) እውነት መሆኑን  አረጋገጠችልኝ፡፡ አዎ… ኤጀንሲው ለ20 የቲቪ ቻናሎች ፈቃድ ለመስጠት አቅዷል፡፡ (ለጐረቤት አገር ሁሉ ሳይተርፍ አይቀርም!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… እቅዱ በትክክል ተግባራዊ ከሆነ እኮ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ባለ ሁለት ዲጂት እድገት ማስመዝገባችን አይቀርም (ጠላት አንጀቱ እርር ይበል!)
ይሄ እቅድ በኢህአዴግ ቋንቋ “የተለጠጠ” ነው ቢባል እንኳ ግማሹ እውን እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ስለዚህ በአመቱ ማገባደጃ ላይ አንድ 10 ቻናሎች አናጣም ማለት ነው፡፡ (ለእነ ደቡብ ሱዳን ሁሉ እንተርፋለን!) በእርግጥ ከምንም ተነስቶ 20 ቻናሎች መክፈት ፈተናዎች ይኖሩታል፡፡ (“ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም” አሉ!) አንድ ነገር ልንገራችሁ አይደል…. ብሮድካስቲንግ ኤጀንሲ ቢያደርገውም ባያደርገውም ለድፍረቱ ብቻ ሊደነቅ ይገባዋል፡፡ ከ20 ዓመት በላይ ያልተደፈረ ነገር እኮ ነው የደፈረው፡፡ (አባይን እንደደፈርነው ማለት ነው!) ትንሽ መጠንቀቅ ያለበት ምን መሰላችሁ? እንደ ግል ፕሬሱ “አሳይቶ ነሳን” የሚል ሃሜት እንዳይመጣበት ብቻ ነው፡፡ 20 ቻናሎች ከተከፈቱ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች 15ቱ የሚዘጉ ከሆነ “አንድ እርምጃ ወደ ፊት ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ” ይሆናል፡፡ (ወደ ኋላ ከመራመድ  ይሰውረን!) የግል ፕሬሱን የኋሊት ጉዞ ኤጀንሲውም አሳምሮ  ያውቀዋል፡፡
አሁን ደግሞ ሰሞኑን በኢቢሲ (በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን) ወደቀረበው የግሉ ፕሬስ ላይ ያጠነጠነ ዶክመንታሪ እንግባ፡፡ እኔ የምለው ግን… EBC ምን ያህል በጀት ቢመደብለት ነው ይሄን ያህል ተከታታይ ዶክመንተሪ የሰራው? ቀላል አከታተለው! (በሽብር ላይ ራሱ ይሄን ያህል ዶክመንታሪ አልሰራም!) ከሁሉም ያስደመመኝ ደግሞ የርእስ አወጣጡ ነው፡፡ በተለይ ለሰሞኑና ከዚያ በፊት ለነበረው ዶክመንታሪ የሰጠው ርእስ ለአዋርድ እጩ የሚያስደርግ ነው፡፡ የበፊቱ “ያልተገሩ ብዕሮች” የሚል ሲሆን የሰሞኑ ደግሞ “ጥቁር ወተት” ይሰኛል፡፡ (“ማኪያቶ” ለማለት ነው የሚሉ ፌዘኞች አልጠፉም!) የሰሞኑን ዶክመንታሪ በተመለከተ ትንሽ ግራ የገባኝ ነገር ግን አለ፡፡ ዶክመንታሪው የተዘጋጀው ተከሰው ለተፈረደባቸው የግል ፕሬሶች ነው ወይስ በሥራ ላይ ላሉት? የተፈረደባቸውማ…. ገና ክስ ሲመሰረትባቸው አገር ጥለው ስለተሰደዱ የህትመት ውጤቶቹም ቆመዋል፡፡ እናም ማንን እንዳለመ ግራ ያጋባል (ራሱም ያወቀው አልመሰለኝም!) ለማንኛውም ግን በእዚህ ዶክመንታሪ ላይ በግሌ የታዘብኳቸውን አንድ ሁለት ነገሮች ልበል፡፡ (ዕድሜ ሃሳብን ለመግለፅ ነፃነት!) ዶክመንታሪው በዋናነት የግል ፕሬሱ ለአንድ ወገን የሚያደላና ሚዛናዊነት የጐደለው እንዲሁም ከአልሚነት ይልቅ አጥፊነት ላይ እንደሚያተኩር ይጠቁማል፡፡ በተለያዩ አስተያየቶች ተደግፎም የቀረበ ነው፡፡ እናም ለጊዜው የመቃወም ሃሳብ የለኝም፡፡ (ዘመቻ መምሰሉን ግን ማንም አይክደውም!)
የእኔ ጥያቄ ግን ምን መሰላችሁ? የግል ፕሬሱ ላይ ያነጣጠረውና “ጥቁር ወተት” የሚል ቅኔያዊ ርእስ የተሸለመው ዶክመንታሪ (ራሱ) ሚዛናዊ ነው ወይ? ከአንድ ምንጭ የተቀዳ የሚመስል አስተያየት ብቻ ስለሰማን እኮ ነው፡፡ (ሆድ ይፍጀው ማለት ይሻላል!)
በነገራችሁ ላይ… በግል ፕሬሱ ላይ ተሰርተው በተከታታይ በEBC ከተላለፉ ዶክመንታሪዎች ሁሉ አስተያየት ሰጪዎች እንዳሁኑ “በአገር ፍቅርና በህዝባዊነት ስሜት” የተንዘረዘሩትበት ዶክመንታሪ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ትንሽ ያልተመቸኝ… አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ጋዜጠኝነትን በአገር ፍቅር ስሜት ለመለካት ያደረጉት ሙከራ ብቻ ነው፡፡ (መብታቸው መሆኑን አልካድኩም!) እንደኔ ከሆነ ግን ጋዜጠኝነትን በራሱ የሙያ መርሆችና ሥነምግባሮች መመዘኑ የሚሻል ይመስለኛል፡፡ (የግል ሃሳብ ነው!) ለምን መሰላችሁ? የአገር ፍቅር ስሜትን መለካት እኮ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በጋዜጠኝነት ሙያ! አልሞከርኩትም እንጂ ምናልባት በ”ልማታዊ ጋዜጠኝነት” ሳይሻል አይቀርም፡፡በመጨረሻ EBC በቀጣይ ለሚሰራቸው እንደ “ጥቁር ወተት” ያሉ የግል ፕሬሱ ላይ ያጠነጠኑ ዶክመንታሪዎች ግብአት ሊሆነው የሚችል አንድ መረጃ ልጠቁመው (በሥራ ብዛት ሊዘነጋ ይችላላ!) EBC በግል ፕሬሱ ላይ ያተኮረውን የመጀመሪያና ሁለተኛ ዶክመንታሪ ከሰራ በኋላ የግል የህትመት ውጤቶች ቁጥር በትንሹ በ10 ያህል ቀንሷል፡፡ ግማሾቹ መንግሥት ከመሰረተባቸው ክስ ጋር በተያያዘ፣ ሌሎቹ ደግሞ አሳታሚ በማጣት ተዘግተው አሳታሚዎቹና ጋዜጠኞቹ አገር ጥለው ተሰደዋል (ለአገር ውስጥ መረጃ ባዳ መሆን ተገቢ አይደለም!) አሁን ደግሞ ወደ ተቃዋሚው ጐራ ልለፍ፡፡
እኔ የምለው… ከተመረጡ ገና አመት ያልሞላቸው የ“አንድነት” ሊቀመንበር ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ስልጣናቸውን እንደለቀቁ ሰማችሁ? (ምነው እንዲህ ጥድፍ አሉ?) ለምን ተሾሙ ለምን ይለቃሉ? ሌላ ጊዜ ቢሆን እኮ በመልቀቃቸው ልናመሰግናቸው ሁሉ እንችላለን፡፡(በራስ ተነሳሽነት ሥልጣን የመልቀቅ ባህል የለንማ!) አሁን ግን ምርጫን የሚያህል ከባድ ዕዳ ከፊታቸው አስቀምጠው ሥልጣን መልቀቃቸው ማነጋገሩ አይቀርም፡፡
ቆይ ግን ብዙ የተባለለትን ከመኢአድ ጋር የተጀመረ የውህደት ሂደት ከምን አደረሱት? በ10 ወራት የሥልጣን ቆይታቸውስ ለፓርቲው ምን ጨመሩለት? (ከለቀቁት የሥራ አስፈጻሚ አባላት ውጪ ማለቴ ነው!) ድንገት ስልጣን መያዝ፣ ድንገት መውረድ ሆነብን እኮ! አንዳንዴ…. ከስልጣን የሚወርዱም “ለምን?” መባል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ (አንዳንዴ ነው ታዲያ!)

Read 3381 times