Monday, 20 October 2014 07:54

“ሰው ይጫኑብህ ግንድ ቢሉት፣ ግንድ ከተጫነኝ ሰው ያነሳልኛል፤ ሰው ከተጫነኝ ማን ያነሳልኛል” አለ

Written by 
Rate this item
(7 votes)

       ከእለታት አንድ ቀን አንድ የፐርሺያ ንጉሥ ሁለት ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ፈረደባቸው ይባላል፡፡ በመጨረሻም፤
“የሞት ፍርዱ ከመፈፀሙ በፊት የፈለጋችሁትን ተናገሩ” ሲል እድል ይሰጣቸዋል፡፡
አንደኛው፤ “ምንም የምናገረው የለኝም” አለ
ሁለተኛው፤ ንጉሡ ምን ያህል ፈረሳቸውን እንደሚወዱት ስለሚያውቅ፤
“ንጉሥ ሆይ የአንድ ዓመት ጊዜ ከሰጡኝ ፈረስዎ ወደሰማይ እየከነፈ እነዲሄድ ላስተምረው እችላለሁ” አላቸው፡፡
ንጉሡ በሰማይ ላይ የሚከንፍ ፈረስ እየጋለቡ ሲሄዱ ታያቸው፡፡ ካሁኑ ነሸጣቸውና ይቁነጠነጡ ጀመር፡፡
“ይሁን አንድ ዓመት ሰጥተንሃል፡፡ ፈረሱን አምጥተው እንዲያስረክቡህ አደርጋለሁ” አሉ፡፡
የመጀመሪያው እሥረኛ በምንም አይነት ፈረስ እንደማይበር ስለሚያውቅ ፈረስ አስተማሪውን እሥረኛ ጓደኛውን እንዲህ ሲል ጠየቀው፤
“ወዳጄ፤ ፈረስ በሰማይ እንደማይበር አሳምረህ ታውቃለህ፡፡ እንዲህ ያለ የዕብድ ሀሳብ ከየት አምጥተህ ነው ቃል የገባኸው፡፡ የመሞቻችንን ጊዜ ከማራዘም በስተቀር ምን ይፈይድልሃል?”
ፈረስ አስተማሪውም፤
“አይምሰልህ ወዳጄ፤ ነፃነቴን የማገኝባቸውን አራት ዕድሎች ራሴ መስጠቴ ነው”
አንደኛው እሥረኛም፤
“አራቱ ዕድሎች ምን ምን ናቸው?” ሲል በመጓጓት ጠየቀው፡፡
ፈረስ አስተማሪው፤ እንዲህ ሲል ዘረዘረለት፡-
1ኛ ወይ በዚህ ዓመት ውስጥ ንጉሡ ሊሞቱ ይችላሉ
2ኛ እኔም ልሞት እችላለሁ
3ኛ ወይ ደሞ ፈረሱም ሊሞት ይችላል
4ኛ ደሞስ ማን ያውቃል እኔ ፈረሱ በሰማይ እንዲበር ላስተምረው እችል ይሆናል
***
አበው ጠበብት ሦስት አይነት ጊዜ አለ ይሉናል፡፡ አንደኛው ረዥም ጊዜ የሚባለው ነው፡፡ ረዥም ጊዜ በትዕግሥት በጥንቃቄ እቅዶቻችንን ሁሉ ቀምረን የምንጓዝበት ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው ተገደን የምንገባበት ጊዜ ነው፡፡ (Forced Time የሚሉት ነው ፈረንጆች፡፡) ይሄ አጭርና ጉዳያችንን ተጣድፈን፣ ተወጥረን በግዴታ ወደ ተግባር የምናስገባበት ነው፡፡ ሦስተኛው የፍፃሜ ጊዜ ነው፡፡ እቅዶችን የምንፈፅምበትና ግባችንን የምንመታበት ነው፡፡ እነዚህን ጊዜያት ወደ አገር መንዝረን ስናያቸው “ከእቅድ በላይ አመረትን”፣ “ከታሰበው ገዜ ቀደም ብለን ግባችንን መትተናል”፣ “ሥር-ነቀል ለውጥ አካሂደን ሰፊውን ህዝብ የአብዮቱ ተጠቃሚ አድርገነዋል”… ወዘተ በማለት አያሌ መፈክሮችን ስናሰግር መክረማችንን እንድንመረምር ግድ ይለናል፡፡ በእርግጥ ግን ያቀድነውን እቅድና ጊዜያችንን በአግባቡ አጣጥመን ለአንዳች ፋይዳ በቅተናልን? ተጀምረው የተቋረጡ “እንደ እገሌ ህንፃ አቁሞ ያስቀርሽ!” “እንደ እገሌ መንገድ ያሽመድምድህ!” “እንደ አገሬ መብራት ድፍን ያርገኝ ብለህ ማል እስቲ!” “እንደ ዛሬው ውሃ ድርቅ ያርገኝ በል እስቲ!” “እንደ ኔትወርካችን ይበጣጥሰኝ! በል…” እስከመባባል ድረስ በምፀት፣ በስላቅና፣ በለበጣ ህይወት ውስጥ የምንጓዘው ከቶም እቅዳችን በጊዜው ተከናውኖ ነውን? ያሰኘናል፡፡
ናፖሊዮን ቦናፓርት “የተነጠቅነውን ቦታ ለማስመለስ እንችላለን፣ ያጠፋነውን ጊዜ ግን በጭራሽ” ይለናል፡፡ የበለጠ የከፋው ደግሞ ስለባከነው ሰዓት በመገማገም የምናባክነው ሰዓት ነው፡፡ ባለፈው መንግሥት “የኮሚቴዎችን መብዛትና እንዴት እንደሚቀነሱ የሚያጠና ኮሚቴ ፍጠሩ!!” እንደተባለው ነው፡፡
“ጊዜ የሥልጣን እጅ ነው፣ የሚያውቅ ሎሌው ያረገዋል
የተጃጃለውን ግና፣ ሎሌው አርጐ ይገዛዋል” ይለናል ገጣሚው፡፡ ይህን ልብ እንበል፡፡
የሙሰኞች መናኸሪያ የሆነችው አገራችን የጊዜ ሌቦችም መደበቂያ መሆኗንም አንዘንጋ፡፡ ሙስና ከየትም የሚከሰት ተዓምት ሳይሆን የሰው ልጆች ራሳቸው ጊዜን እያዩ የሚፈፅሙት እኩይ ተግባር ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚያጠፋም ሰው፣ የሚያለማም ሰው ነው፡፡ ሰው የምንለው ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ነው”
“ለመቶ አምሳ ጌታ፣
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ…
አለቀ በላዬ”
ካለችው የበታች አካል ጀምሮ፤
“የእባብ መርዝም እንደዚያው፤ ሁሌም የሚፈለፈለው
ንጉሡ አናት ላይ ካለው፤ ከዘውዱ ወይራ ቅጠል ነው”
እስከሚለው ቄሣራዊ አገዛዝ ድረስ፤ የሙስና ፖለቲካዊ ዘይቤ መገለጫ ነው፡፡
ሰውም እንደ ሐምሌት፤
“…በምናውቀው ስንሰቃይ፣ የማናውቀውንም ፈርተን
በህሊናችንም ማቅማማት፣ ወኔያችንንም ተሰልበን… መሆን ወይም አለመሆን?...” እያለ ስለበደሉ ማውጠንጠንን ኑሮ ብሎታል፡፡ ወዳጅም ሰው፣ ባላንጣም ሰው፣ ደጋፊም ሰው፣ ተቃዋሚም ሰው፣ የበላይም ሰው፣ የበታችም ሰው ሰው ነው….
“ሰው ይጫኑብህ ግንድ?” ቢሉት፣
ግንድ ከተጫነኝ ሰው ያነሳልኛል፤
ሰው ከተጫነኝ ማን ያነሳልኛል?!” አለ፤ የሚለው የጉራጌ ተረት፤ ይሄንኑ በብርቱ ያፀኸያል!

Read 3715 times