Saturday, 11 October 2014 13:38

አዳም እና ሥራዎቹ - በአድናቂዎቹ አይን

Written by 
Rate this item
(14 votes)

         “እኛ አገር የመፃፍ ክህሎት ያላቸው በርካታ ናቸው፤ እየፃፉልን ያሉት ጥቂቶች ቢሆኑም፡፡
እነዚህ ጥቂቶችም የመፃፍ አቅማቸውን ያህል አልሰጡንም ፤ ወይ ሰንፈዋል - ወይ ያልተመቻቸው ነገር አለ፡፡ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ፣ በዕውቀቱ ስዩም፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ እንዳለጌታ ከበደ፣ ሰርቅ ዳ.፣ ሌሊሳ ግርማና መሰሎች ባላቸው ልክ /በዕድሜያቸው ልክ እንደማለት/ ብዙ ለማሳተምና ያላቸውን ለመስጠት የሚታትሩ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በእርግጥ ካላቸው ተሰጥኦና አቅም አንጻር ያሳተሟቸው ሥራዎች ማነሳቸው የሚከነክኑን እንዳሉበትም ልብ ይሏል፡፡ አዳምን ግን በተለየ ዓይን እንየው፤ በብቃትና በጥራት ያለውን ያለስስት እየሰጠን ነው፡፡
 /በዓሉና አዳም ከሚመሳሰሉባቸው ነገሮች አንዱ፣በተከታታይ በጥራት መፃፋቸውና ያንንም ለህዝብ ማድረሳቸው

ነው፤ ከአስር ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሁለቱም ከሰባት በላይ መጻህፍት ፅፈዋል፡፡/
አዳም ወደ ራሱ አብዝቶ የሚመለከት በመሆኑ ሰቅዞ ይይዛል፡፡
ለእኔ አዕምሮ የሚያክ ደራሲ ነው፤ የትዝታ ዘመኑን /ረጅም ጊዜ ውጭ ነውና እየኖረ ያለው/ በጥፍሩ ሲቧጥጥ፣

እኛም ባልኖርንበት ዘመን ትዝታችንንና ኑሮአችንን እንድንቧጥጥ ዕድል ይሰጠናል - አገናኝ ድልድይ በመሆን፡፡ አሰላሳይ ደራሲ ስለሆነ  የቃላት ጨዋታው ሁሉ ልቡና ላይ ነው - እያነበብከው አብረኸው ታሰላስላለህ፤ ኑሮህን፣ ዘመንህን፣ አገርህን!!
አዳም <<post modernism>> አፃፃፍ የገባው ነው፡፡
ከታሪክ አወቃቀርና ከመቼት ብሎም ከሴራ በላይ በድርሰቱ ይዞት የሚመጣው ቅርፅ የሚያሳስበውና ለእሱም

አብዝቶ የሚሳሳ ይመስላል፡፡ ቅርፅና አዳም ጋብቻ ፈፅመዋል - እንደሱ ገለፃ ‹‹የእንጀራ ቅርፅን›› አስተዋውቆናል፡፡ ይህ የራሱን መንገድ ይዞ የሚፈስ ቦይ ነው እንድንል ያስችለናል፡፡ በዚያ ወንዝ ውስጥ በተለይም ከ“ግራጫ

ቃጭሎች” እስከ አሁኑ “መረቅ” ድረስ ባለው ቅርፁ እከሌን  ይመስላል ለማለት ፊት አይሰጥም - አዳም በቃ አዳምን ይመስላል፡፡
 አዳም በሰው ኮቴ ላለመራመድ ያደረገው ፣ ከ“ግራጫ ቃጭሎች” በኋላ ተሳክቶለታል - በእኔ እምነት፡፡ አዳም የሰው ዳና አላዳመጠም፣ አዳም በራሱ መንገድና በራሱ ፋና ነው የነጎደው፤ በቋንቋና በሃሳብም ቢሆን ልቀቱ

ከፍታውን ይመስክሩለታል”
          - ደመቀ ከበደ  (ገጣሚ)


“የሥነፅሁፍን ሥራ ከማንም በላይ የሚፈትሸውና  የሚያቆየው ጊዜ ባለሟሉ ነው።  የአዳም መጻህፍት  ከጊዜ ጋር ለወደፊትም በአገራችን የሥነፅሁፍ ታሪክና አፃፃፍ ዘይቤ፣ የራሳቸው  ትልቅ ድርሻና ቦታ ይኖራቸዋል።አዳም «ህጽናዊነት» የሚል ስያሜ የሰጠው የራሱ የሆነ የአፃፃፍ ዘይቤ መፍጠር የቻለ ደራሲ ነው።  ይህም ጥቃቅንንም ሆኑ ግዙፍ ነገሮችን፣ ሰዎችን (ገፀ ባህሪያት)፣ ስሜቶችን፣ ሁኔታዎችን በማያያዝና በማዛመድ አንባቢዎች አእምሮ ውስጥ ትውስታና ትዝታም የሚጭር የአፃፃፍ ዘይቤ ነው። በታሪክ ይዘታቸው በጣም መሳጭና ወደ ራሳችን ውስጥ አስገብተን፣ እራሳችንን እንድንፈትሽና እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ናቸው።   አንዳንድ  የሴት ገፀ ባህርያቱ፣ የሴቶችን አስተሳሰብና  ባህሪያት በግልፅ (ሳይሸፋፍንና ሳያድበሰበስ)

የሚያሳዩ ናቸው።  ሴት ልጅ በወጣትነት እድሜዋ የሚያጋጥማትን  ስነልቦናዊ ፈተናዎችና ከባሕላችን ጋር ለመራመድ (ለመሄድ) የምታደርገውን ነገሮች--- አስመሳይነትን በግልፅ የምናይባቸው ገፀ ባህሪያት አሉ። ለምሳሌ “እቴሜቴ የሎሚ ሽታ” ውስጥ “ (ሽልንጓ) የመጨረሻዋ የቀበሌ 01 ድንግል” ውስጥ ያለችው የነፃነት ገፀ ባህሪ፣ የሴት ልጅን  ሥነልቦናዊ  ፈተና  በደንብ ያሳየናል። በእኛ ሕብረተሰብ ውስጥ ሴት ልጅ “ጨዋና ጭምት” መሆን አለባት ተብሎ ይጠበቃል። “ጨዋ” ማለት ምን ማለት ነው? ይህን እንድንጠይቅና እንድንፈትሽ የሚያደርጉ ገፀ ባህሪዎች ናቸው። በ“ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ” ውስጥ ያሉት እትዬ ወርቄ  ደግሞ አገር ወዳድነትን፣ እናትነትን፣ እማማ ኢትዮጵያን ራሷን የሚስልበት ገፀ ባህሪ ናቸው። ለዚህም ነው ጊዜና ዘመን የማይሽራቸው መፅሐፍት የሚመስሉኝ።
እነሆ አሁን ደግሞ 600 ገጾች ያሉት  ዳጎስ ያለ አዲስ ልብወለድ፣ «መረቅ» በሚል ርዕስ ለአንባቢያን አቅርቧል።”
ሮማን ተወልደ ብርሃን ገ/ እግዚያብሄር (አድናቂ፣ ከለንደን)



አዳም ስለራሱ….
 “ስጽፍ አልለፋም!...”
 “አጣርቼ የማስወጣበት ወንፊት የለኝም!”
 (‘በስራዎችህ ከጥቃቅን ዝርዝሮች፣ የማይደፈሩ እስከሚመስሉ ነገሮች ደፍረህ ታወጣለህ፣ የገጸ ባህሪያቱን ውስጣዊ ስሜት፣ የማህበረሰቡን ህጸጾች ጨክነህ ታፍረጠርጣለህ…’ ተብሎ ሲጠየቅ፣የሰጠው ምላሽ)“ነገሮችን ማየት እወዳለሁ እንጂ አልንቀለቀልም፡፡ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮችን አልንቃቸውም፡፡ አያቸዋለሁ፡፡

እረፍት ሳገኝ ደግሞ፣ ተመልሼ በደንብ አያቸዋለሁ… የሚጻፉ መስለው ከታዩኝ፣ እጽፋቸዋለሁ!...”
 “When I want to write, I write!”
 (‘ለመጻፍ የሚያነሳሳህ ምን አይነት ሁኔታ ነው?’ ለሚል ጥያቄ የመለሰው)
“ ‘ፍቅር እስከ መቃብር’ ውስጥ ያለችው ሰብለ ወንጌል፣ እንደ መልዓክ ናት - ከሰው ይልቅ ለመልዓክት የቀረበ

ባህሪ የተላበሰች፡፡ እኔ የሞከርኩት፣ ሰብለን ‘ሰው’ ሆና እንድትታይ ለማድረግ ነው!...”
.“Mezgebu is just living. He knows nothing about precision and the like.”
(ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ደራሲ አዳም ረታ፣ ከአድናቂዎቹ ጋር በተገናኘበት የቡና ስነስርዓት ላይ ከተናገረው የተወሰደ)

Read 8269 times