Saturday, 11 October 2014 13:25

የቀጨኔ ልጆች ምን ይላሉ?

Written by 
Rate this item
(12 votes)

       ዛሬም “ቡዳ በልቶት ነው” ከማለት አልተላቀቅንም!

            ከፒያሳ በ2.8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ቀጨኔ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ ሰፈሮች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ከሰሜን ሸዋ ተነስተው በአካባቢው የሰፈሩት የቀጨኔ ነዋሪዎች ከእስራኤል እንደመጡ ይነገራል፡፡ የአካባቢው ሰዎች በእጅ ሙያ በተለይ በሸክላ ስራና በሽመና የተሰማሩ በመሆናቸው “ቡዳ” በሚል አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ስያሜ የሚጠሩ ሲሆን “የቀጨኔ ሰዎች ሌሊት ወደ ጅብ በመቀየር ሰው ይበላሉ” የሚለው አመለካከትም ሙሉ በሙሉ አለመቀየሩን የሰፈሩ ነዋሪዎች በቅሬታ ይገልፃሉ፡፡ የህብረተሰቡ አመለካከት ከቀድሞው እየተሻሻለ መምጣቱን ባይክዱም ችግሮቹ ግን አሁንም እንዳሉ ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት፡፡

በቀጨኔ ተወልዶ ያደገው ሰለሞን አስፋው እንደሚለው፤ የአካባቢው ሰዎች በሚደርስባቸው ጫና የተነሳ አብዛኛውን ጊዜ ሰፈራቸው ቀጨኔ እንደሆነ አይናገሩም፡፡ ሲጠየቁ ወይም መናገር የግድ ከሆነባቸው ሾላ ወይም አዲሱ ገበያ ገባ ብሎ በማለት ነው የሚመልሱት፡፡ ሰፈሬ ቀጨኔ ነው ብሎ መናገር ለብዙ ሰው “እኔ ቡዳ ነኝ” እንደማለት ነው የሚቆጠረው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ስለቀጨኔ ሲወሩ የምሰማቸው ነገሮች በጣም ይገርሙኛል፤ ሁሉም የሚያወሩት ራሳቸው በቀጥታ ያጋጠማቸውን ሳይሆን አንዱ ሰው ከሌላ ሰው ሰምቶ የነገራቸውን ነው፡፡ “ሰው በቡዳ ተበልቶ” የሚለው ወሬ መቆሚያ የለውም፡፡ ሁልጊዜ ይወራል፡፡ መቼም ሰው እንደዚህ “በቡዳ እየተበላና እየሞተ” የሟች ቤተሰቦች የሆነ ነገር ማለታቸው አይቀርም ነበር፡፡ ነገሩ ወንጀል ስለሆነም ይፋ ይሆን ነበር ይላል ሰለሞን፡፡

አንድን ህዝብ “ሰው ትበላለህ” ብሎ መናገር ራሱ ትልቅ ወንጀል ነው፡፡ በየቦታው የምትሰሚው ነገር ላይ ክርክር ብታነሺ ውሉ ያልተገኘለት ክር እንደመምዘዝ ስለሚሆን ዝም እላለሁ፡፡ የሚያድጉ ትንንሽ ልጆች በማንነታቸው እንዳያፍሩና ለተፅዕኖ እንዳይበገሩ ግን የተቻለንን ሁሉ እንሰራለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች “ከቀጨኔ” ብለው ሬዲዮ ላይ ጥያቄ ሲመልሱ ወይም ዘፈን ሲመርጡ በጣም ደስ ይለኛል፤ ምክንያቱም ሰፈሩን መጥራት እየተለመደ እንዲመጣ ያደርገዋል፡፡ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ሰለሞንን ጨምሮ ያነጋገርኳቸው ዳዊት ጥላሁንና ሰላማዊት ወንድምአገኘሁ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ሰፈራቸው በሚገኘው “ቀጨኔ ደብረሰላም” ትምህርት ቤት በመማራቸው የተለየ ነገር ሳያዩ ነበር ያደጉት፡፡ ፈተናዎችን መጋፈጥ የጀመሩት ወደ ሁለተኛ ደረጃ አልፈው ሌላ ትምህርት ቤት ሲመደቡ ነው፡፡ ሰላማዊት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ገጠመኟን እንዲህ ታወጋለች፡- “ኤለመንተሪ የራሳችን ማህበረሰብ የሰራው ትምህርት ቤት ውስጥ ስለተማርን ጓደኝነታችን ከማህበረሰባችን ሰው ጋ ነበር፡፡ እኔ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መነን ነበር የተመደብኩት፡፡ ክፍል ውስጥ ከአንድ የሰፈሬ ልጅና ከሌላ ሰፈር ልጅ ጋር ነበር የምንቀመጠው፡፡

ከልጅቷ ጋር በጣም ጥሩ ቅርበት ነበረን፡፡ የቀጨኔ ልጆች መሆናችንን ስታውቅ ግን ወዲያው ተቀየረች፣ ከኛ ጋር ምግብ መብላት አቆመች፣ ለሌሎችም ነግራ ሁሉም እንዲያገሉን አደረገች፡፡ እንዲያም ሆኖ እኔ ሰፈሬን ደብቄ አላውቅም፤ መናገር ባለብኝ ቦታ ሁሉ የቀጨኔ ልጅ እንደሆንኩ እናገራለሁ፡፡ ነገር ግን ሌላው ሰው ስለኛ ማህበረሰብ የሚያወራውን ነገር ስትሰሚ በውስጥሽ ጥያቄ ይፈጠራል ትላለች፡፡ የሆነ ጊዜ ላይ እናትና አባቴ ጅብ ሆነው ሲቀየሩ ለማየት ቁጭ ብዬ አድር ነበር፡፡ እኔ ወደ ጅብ የምቀየረው ሳድግ ነው እንዴ ብዬ ራሴንም እጠይቅ ነበር፡፡ እናትና አባቴ ግን ሌሊት ተነስተው ቤተክርስቲያን ሲሄዱ ነበር የማየው፡፡” አንድ ጊዜ አንድ ሰው ማታ ሰክሮና ተፈነካክቶ ጉድጓድ ውስጥ እግሮቹን ጅብ ለኮፍ ለኮፍ አድርጓቸው፣ ጠዋት ላይ በህይወት ይገኝና ሀኪም ቤት ይወሰዳል፡፡ የሀኪም ቤቱ ሰራተኞች “የት ነው የተገኘው?” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ ቀጨኔ ጉድጓድ ውስጥ መሆኑ ሲነገራቸው፤ “አይ እዚያማ ሰዎቹ ራሳቸው ጅቦች ናቸው፤ ራሳቸው በልተውት ነው” አሉ ይባላል፡፡ የሚወራው ነገር የሚፈጥረው ጫና እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የሽመና ሙያ አውቃለሁ፤ ከዚያ አልፎም ዲዛይነር ነኝ፡፡ የሆነ ወቅት ላይ “ዲዛይነር” ብዬ ራሴን ማስተዋወቅ ስጀምር፣ የተወሰኑ ሰዎች ግርግር ፈጥረውብኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም እዚያው ጉድጓድ ውስጥ ሆኜ ሽመናውን እንድሰራ እንጂ እንዳድግ አይፈለግም፡፡

ይህን ግርግር የፈጠሩት ሰዎች ደግሞ ሙያውን በትክክል ጠንቅቆ የሚያውቀው ሰው የሰራውን ስራ በማይረባ ዋጋ ገዝተው፣ ደህና ስምና ሱቅ ስላላቸው በውድ ዋጋ የሚሸጡ ናቸው፡፡ በጣም የሚገርመኝ እኛ ሰፈር ጅብ ሞቶ ቢገኝ ሰዎች መጥተው አይኑን፣ ቅንድቡን፣ ጆሮውን… ቆራርጠው ይወስዳሉ፤ ምን ይሰራላችኋል ስትያቸው፤ “የቡዳ መድሃኒት ነው” ይሉሻል፡፡ ሰዎች ወደኛ ሰፈር ሲመጡ እንደ ነጭ ሽንኩርት አይነት ለቡዳ መከላከያ ነው ብለው የሚያምኑበትን ነገር ደብቀው ይይዛሉ፡፡ በሚወራው ወሬ ምክንያትም የቤት ኪራይ ርካሽ ስለሆነ፣ የኛ ማህበረሰብ ያልሆኑ ተከራዮች፤ ልጆቻቸው አንገት ላይ የቡዳ መከላከያ የሚሉትን ነገር ያስራሉ፡፡ የኛን ሸማ ለብሰው፣ በኛ ሸክላ አብስለው በልተው፣ የሚያወሩት ነገር ምን እንደሆነ ሳስበው ግራ ይገባኛል ብላለች - ሰላማዊት፡፡ የከፍተኛ ትምህርቱን ለመማር አዲሱ ገበያ ተመድቦ እንደነበር የሚናገረው ዳዊት፤ ከተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በሚመጡ ተማሪዎች የሚወራው ወሬ የተሳሳተ ስለነበር ከቀጨኔ ነው የመጣሁት አልልም ነበር ብሏል፡፡ “ሰው ወደ እኛ ሰፈር እንደሚመጣ ሲታወቅ እንዳትሄድ ወይም ተጠንቀቅ ይባላል፡፡

በቅርብ ጊዜ የክፍለሀገር ልጅ የሆነች የጓደኛዬ ባለቤት እኛ ጋ መምጣት ፈልጋ፣ ወንድሟ ‹እዚያ ሰፈር ከሄድሽ አበቃልሽ፤ በህይወት አትመለሽም› ብሏት እንደነበር አጫውታናለች፤ ቤታችን አድራ ስትሄድም በሚወራው ነገር ግራ እንደተጋባች ነግራን ነበር ብሏል፡፡ አብዛኛው የቀጨኔ ነዋሪ የተሰማራበትን የእጅ ሙያ ሥራ በተመለከተ ሦስቱም ወጣቶች በሰጡኝ አስተያየት፤ የቀጨኔ ሰዎች የራሳቸውን ምርቶች አደባባይ አውጥተው ለመሸጥ ያለባቸው ጫና ከፍተኛ በመሆኑ የስራቸው ውጤት ተጠቃሚ አይደሉም፡፡ የሥራው ተጠቃሚዎች ለሸማ ስራ ከዋሉት ነገሮች አንዳቸውንም እንኳ የማያውቁ ሌሎች ሰዎች ናቸው፡፡ የቀጨኔ ሰው እዚያው ሰፈሩ አፈር ላይ ሆኖ የሰራውንና በተለያዩ ጫናዎች ምክንያት ራሱ ይዞት የማይወጣውን ምርት ተቀብለው፣ በከተማዋ ባሉ ሱቆች መሸጥ የሚችሉ ናቸው እየተጠቀሙ ያሉት፡፡ ማህበረሰቡ ተፅዕኖውን ሰብሮ ለመውጣት አልቻለም፡፡ በታሪኩም ከቦታ ቦታ ሲሳደድ የመጣ በመሆኑ፣ ፍራቻው እስካሁን ከውስጡ አልወጣም፤ ብለዋል፡፡ በቅርቡ በህብረት ስራ ተደራጅተው እንዲሰሩ በመንግስት ተወስኗል፡፡ በዚህ አጋጣሚ “ራስ አገዝ የሴቶች ድርጅት” ሴቶችን ቀጨኔ እያመጡ የሸክላ አሰራር እንዲሰለጥኑ በማድረጋቸው ምስጋና ይገባቸዋል ይላሉ - ወጣቶቹ፡፡ ዳዊት እንደሚለው፤ “ቡዳ” የሚለው ቃል በጊዜ ሂደት ትርጉሙን እየለወጠ መጣ እንጂ አዋቂ ጠቢብ ማለት ነበር፡፡ በነገራችን ላይ የመጀመሪያው ሸክለኛ፣ የሰውን ልጅ በጭቃ የሰራው እግዚአብሔር ነው፤ እሱንስ ምን ሊሉት ይሆን? ዳዊትና ጓደኞቹ ይጠይቃሉ፡፡

Read 9181 times