Saturday, 11 October 2014 13:12

የሁለት ዘመን አራዳዎች ወግ

Written by  ከጉማራ ዙምራ zmtm1229@gmail.com
Rate this item
(2 votes)

           መቼም ስለ አራዳ እና አካባቢው ከተቆረቆረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አለንበት ዘመን ድረስ በጊዜ ሂደት ቅደም ተከተል አንዳንዶች በወቅቱ የኖሩበትን ግለ ታሪክ፤ ሌሎች በጥናት የደረሱበትን እውነት፤ አዝማሪው በዜማና በቅኔ፤ተራው ዜጋ ደግሞ በንግርትና በይትባሃል የሰማውን አፈ- ታሪክ በማስታወስና በመዘከር ብዙ ተብሏል፤ ተጽፏል፤ ተገጥሟል ወዘተ… የዚህ ጽሁፍ መነሻም በ2004 ዓ.ም “በእድሜ ጎዳና ላይ የጉዞ ትዝታ” በሚል ርእስ አሁን የ93 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ በሆኑት በአቶ በለጠ ገብሬ የተጻፈው ግለ - ታሪክ ነው፡፡ ጸሀፊው በዚሁ መጽሃፋቸው ውስጥ ከልጅነት እስከ እውቀት ከዚያም ባለፈ በአብዛኛው በቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዘመን ስለነበረው የትምህርት፤ የስራና የትዳር ህይወታቸው ዘርዘር አደርገው አቅርበዋል፡፡ በተለይ ታላቅ ወንድማቸው በ1930ዎቹ የወጣት ዘመን ኡደት እና በወቅቱ ያሳለፉትን የአራዳነት ህይወት ዳስሰዋል፡፡ እኔ ደግሞ የያኔውን ዘመን አራድነት ከዛሬው ዘመን አራድነት ጋር እያነጻጸርኩ በወግ መልክ ልተርከው ወደድኩ፡፡

በዚያ ዘመን፡ …….. ብዙ ሳይቆይ ሞገሴ ገብሬ በሊቄ ግቢ ውስጥ ለአሽከሮች ግቢ ከተከለለው ቦታ ግንባር ከሆነው ማእዘን ላይ እንደ ላንቲካ የምትታይ ጌጠኛ የሳር ክፍክፍ እልፍኝ ሰርቶ ከአንዳንድ የትምህርት ጓደኞቹና አጃቢዎቹ ከሆኑት ወጣት የሊቄ አሽከሮች ጋራ አስረሽ ምችው ማለት ጀመረ፡፡ ጦም ካልሆነ በቀር በሳምንት ሁለት ጊዜ ያህል ምርጥ ብልት ስጋ ይገዛል፡፡ ማለፊያ ጠላ ሰርይ የመሰለ ጠጅ በአስረ ፈጅ ማንቆርቆሪያ ከጌቶች ቤት አብዛኛውን ጊዜ በድብቅ አልፎ አልፎ በፈቃድ ይመጣል፡፡ ከአጃቢ ጓደኞቹ አንዱ የጠጅ አሳላፊ ነበርና፡፡ ከዚህ ሁሉ ጋር በሀይለኛነቱ ምክንያት አንዲት ትንሽ መለኪያ አፍንጫ የሚያሲይዘው ዘቢብ ማስቲካ አረቄና የግሪክ ኮኛክ ባርባሬሶ ወይም መጣክሳ ከቤት ስለማይጠፋ፤ ከእነ እንኮየ ጋር ማታ ማታ በሚወርደው ግብዣ ላይ “በሞቴ ጉረሽ” “አፈር ስሆን ይህቺን ጠጣ” ሲባባሉ ማምሽት ነው፡፡ በዚህ ዘመን፡…….ሚኪያስ ከአባቱ ሞት በኋላ በውርስ ያገኘው ሰፊ ግቢ ውስጥ ዋናውን ቤት ለሱማሌዎች አከራይቶ እርሱ ጥግ ላይ ከሚገኘው ሰርቪስ ቤት ውስጥ የሚኖር ሲሆን ሁለት ወንድሞቹና እህቱ በሀገረ ካናዳ ይኖራሉ፡፡

ሚኪያስ ኑሮውን የሚገፋው እህትና ወንድሞቹ በሚልኩለት ዶላርና በቤት ኪራይ ገቢ ሲሆን ይኸው ገንዘብ ወር የማያደርስ ከሆነ ደግሞ አሉ የተባሉ የችግር ጊዜ አበዳሪዎች አሉት፡፡ ከፋይ ነዋ፡፡ ምግብ አብስሎ መብላት ሲያልፍም አይነካው፡፡ “የትብለጽ ጥብስ እና ሽሮ ቤት፤ የበረካ ግሮሰሪ፤ የነስሮ ትክክለኛው በለጬ አሉልህ፡፡ እነርሱ ጋ ትደውላለህ፤ ያለህበት ድረስ ያመጡልሀል፡፡ ወሳኙ ነገር ስልክህን ቻርጅ ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ባላንስ ካለህ ትደውላለህ፤ ከሌለህ በሚስድ ኮል የተልፈሰፈሰ ትንኮሳ ትፈጽማለህ፤ ከዚያም ራሳቸው ደውለው ምን እንታዘዝ ይሉሃል?” ፍሬንድ ይሞታል እንዴ? በፍየል ዘመን ማን በግ ሆኖ ይኖራል” ይላል ሚኪያስ ለምን ምግብ እንደማያበስል ሲጠየቅ፡፡ በቤቱ ውስጥ የወንድና የሴት ጓደኞቹ ቀን ከሌሊት ሲርመሰመሱ ይውላሉ፡፡ በተለይ ሴቶቹ በአይነትም፤በመልክም፤በቅርጽም የተለያዩ ሆነው የውበታቸው ነገር (የአንድ እናት ልጆች እስኪመስሉ ድረስ) አስገራሚ ነው፡፡

ተመላላሽ ሰራተኛዋ ሰርክ ተግባርዋ ቤት ማጽዳትና እሳት ማቀጣጠል ሲሆን ጥዋት ጥዋት የምታወጣው የጫት ገረባ ክምር “እነዚህ ሰዎች ቅጠል ይሆን እንዴ የሚቀለቡት ሳያሰኝ አይቀርም፡፡” ከዚሁ ጋርም ተያይዞ የሺሻ እቃው፤ ቡሪው፤ ቀፈሻው፤ ማንደጃው እና አመዱ፤መቆንጠጫው፤ ወስፌው፤ ፒፓው፤ ቅራሪ ፈሳሽ ያደረባቸው የታሸገ ውሃና የቢራ ጠርሙሶች፤ቆርኪው፤ የቆሸሸ ሶፍት፤ ኤርገንዶ ጫማው፤ ቁርጥራጭ ሲጋራው ከእነ ፓኬቱ፤ የተለያዩ ቻርጀሮች፤መጽሄትና ጋዜጦች፤ ሳሳ ያለው አረቢያን መጅሊስና ትራሶች ወደ ውጭ ለመናፈስ ሲወጡ ማየት ራሱን የቻለ ድራማ ነው፡፡ በዚያ ዘመን፡ …….. ለመሆኑ እንኮዬዎቹ እነማን ናቸው? የሞገሴ ቀኝ እጆች የሚባሉት ሶታ ሶታ (ሎጋ ሎጋ) የቄሱ አሽከሮች እነ አውግቸው ደግፍ፤ መለሰ ወ/ማሪያም፤ ወልደ ትንሳይ ወሰኔ እና ሌሎችም በቱርየ ሳቡናና በቡሎ ቱር ተደርጎ ታጥቦ በቄንጥ በተተኮሰ ልብሳቸው አጊጠው እየተቆነኑ፣ ቅዳሜና እሁድ ወደ አራዳ ይዘልቁና በመረጡት ጠጅ ቤት ይገባሉ፡፡

ይኸውም በአራዳ ጠፈር ውስጥ ሲያንጸባርቁ ከነበሩት የወቅቱ ከዋክብት ገና አዲስ የወጡት ጉብሎች እነ አበበች ጨርቆሴ፤ እነ ነገደ ብስራቴ፤ እነ “ ስድስት ጎራሽ” ጽጌ፤ እነ” አፋጀሽኝ” ጥሩነሽ፤ እነ አልታየ ወለቱ፤ እነ ቀመሪያ (ማን ያህልሻል) አብዲ፤ እነ የውብ እምብርትና ሌሎችም የተሰራጩበት ሰፈር ሲሆን፤ በእነዚያ ያጥቢያ ኮከቦች ፍትወተ- መግኒዝ ከአራቱም ማእዘን አዲስ አበባ እየተሳበ የሚጎርፈው ቅምጥልና የዘበናይ ልጅ አጃቢው የጎረምሳ ቦለዴ (ከማህበሩ የተገለለ ዝንጀሮ) ሁሉ፤ በመሀል አራዳ ተከማችቶ ሹርቤ ብርሌ እያጋጨ ሲንዠባረርና ሲተራመስ የሚያመሸው፤ የአንድ ትውልድ እድሜ ካለፈ በኋላ ታላቁ የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ህንጻ ከተሰራበት ክልል አጠገብ ጸሀፊ ትእዛዝ ኃይሌ ወልደሩፌ አዲስ ሰርተው ባከራይዋቸው ብዙ የጠጅ መሸታ ቤቶችና በሌሎችም ሱቆች ውስጥ ነበር፡፡ ያንንም ሰፈር ከሌሎች የአዲስ አበባ ሰፈሮች ሁሉ የሞቀና የደራ ገበያ ሊሆን የበቃው፤ ህንጻው የቆመበትና አካባቢው በዚያ ጊዜ ከመላ ኢትዮጵያ ለሚመጣና ወደ ውጭ አገር ለሚወጣ ንግድ እቃ መናኸሪያና ቀረጥ መሰብሰቢያ ሆኖ የሚያገለግል የጉምሩክ ዋና መስሪያ ቤት ክልል ስለነበረ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ወይዘሮ ጽጌ ስድስት ጎራሽ የሚለውን ቅጽል ያገኙት ከፍቅረኛቸው አንዱ በቅናት ተቃጥሎ የተኮሰባቸው ስድስት የሽጉጥ ጥይት በጭንቅላታቸውና በሌላ አካላቸው ውስጥ በመቅረቱና ከሞት ተርፈው ያንኑ ስራቸውን ለመቀጠል በመቻላቸው ነው፡፡ በዚህ ዘመን… አብዛኛዎቹ የሚኪያስ ጓደኞች የሀይስኩል ትምህርታቸውን በከተማው ምርጥ የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ የተማሩ፤ ከፊሎቹ ዩኒቨርሲቲ ገብተው የገናን ፈተና መሻገር ያልቻሉ፤ የተወሰኑት ደግሞ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች በመመደባቸው ቤተሰብ ከአይኑ ርቀው ለስነምግባር ብልሹነት ተጋላጭ ከሚሆኑ እዚሁ አይኑ ስር እንዲባልጉ የፈቀደላቸው የሚመስሉና የግል ኮሌጆች ውስጥ ከፍተኛ የመዋእለ ንዋይ ፈሰስ ተደርጎባቸው በግፊ የሚማሩ ናቸው፡፡ ለወትሮው ሚኪያስ ቤት ኑሯቸውን ካደረጉት የወንድ ጓደኞቹ ውስጥ የface book ሱስ የተጠናወተው ሄኖክ (Like) ፤ ጫትና ሲጋራ በመቀፈል የታወቀው ናሆም (Missed call)፤ መጠጥ ሲጠጣ ሌሊትና ንጋትን ካላጨባበጠ የማይተኛው ቢኒ (ዲፌንደር)፤ ዘወትር አንገቱን ወደ ግራ ዘንበል አድርጎ ፍሪዝ ጸጉሩን በጣቶቹ ሳብ ጠቅለል ደምደም፤ ሳብ ጠቅለል ደምደም ማድረግ የእለት ተግባሩ የሆነው አብዲ (ፍሪዙ)፤ የሰው ቺክ በመንጠቅ የታወቀው ናኦል (ሲላው)፤ በቅርቡ ከኤርትራ የሳዋ ማሰልጠኛ ጠፍቶ በሱዳን አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው (ፍሬ እዝጊ) የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

አልፎ አልፎ የሚኪን ቤት ከሚጎበኙት ውስጥ ደግሞ በቀኝ ክንዱ ላይ የማድሪዱን ክርስቲያኖ ሮናልዶን፣ በግራው ደግሞ የባርሴሎናውን ሊዮኔል ሜሲን በታቱ የተነቀሰውና /የ El Classico Derby Match ጊዜ የማን ደጋፊ ይሆን?/ በጓደኞቹ ዘንድ “በምክንያት ሳይሆን በደመነፍስ የሚኖር ነው” እየተባለ የሚታማው ዳኒ (ጉልቤው)፤ ከቅጥነቱ የተነሳ ወገቡ ላይ ሳይሆን ታፋው ላይ የሚውለውን ሱሪ አዘውትሮ ከፍ ከፍ በማድረግ የሚታወቀው ብሩኬ (ሞዚላ)፤የኡዞ አረቄ ጠርሙስ ላይ እንዳለችው አጋዘን ቀንድ ራስታ ጸጉሩን ወደ ላይ ገትሮና አቆላዝሞ የጃንሆይ ምስል ያለበትን ቲሸርት፤የቦብ ማርሌይ ምስል ያለበትን ኮፍያ፤ የቴዲ አፍሮ ፎቶን እንደ የአንገት ጌጥ፤በግራ እጁ ላይ ሞ አንበሳ ዘ እምነገደ ይሁዳ አንበሳ ያለበትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሪባን፤እንደ ፋቲክ ሆኖ ግራና ቀኝ ጉልበቱ ላይ ኪስ ያለው ሱሪና ከክብደቱ በላይ ጫማ የሚያዘወትረው አቡሽ (ራስታው) የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ ከእንስት ቆነጃጅት ጨፍሮ - አዳሪዎች መካከል ደግሞ የሚኪያስ ገርል ፍሬንድ ናት እየተባለች የምትታማው ሜላት፤ ሰኒ (ስሊሟ)፤ ቤት ውስጥ ከመጣ ወንድ ጋር ካልወጣች የማይሆንላትና በቅጽል ስሟ (ሸሌ ጦር) የምትባለው ጄሪ ፤ የመኪና ፎንቃ ያለባት ፊፊ (ቪትዝ)፤ ሚኪያስ ቤት ከመድረሷ በናታችሁ ሺሻ… ሺሻ…ስጡኝ በማለት ካገኘችው ሰው እጅ ላይ ገመዱን በመንጠቅ አፏ ላይ ሰክታ ላፕቶፕ ላይ እንደተሰካ ፍላሽ ዲስክ ራሷን ስካን ካላረገች የማትነቃዋ ቲቲ (ሺሻ)፤ በሀገረ አሜሪካ የሚኖረው ወንድሟ በጋብቻ አፈራርሞ ወስዷት በዓመቱ በጭንቀትና ድብርት ወደ ሀገሯ የተመለሰችውና አንድ ሉሉ ቀቻ እንዳወረደች ሞባይሏን ከፍታ በጌም የምትጠመደው ኤደን (ሶሊቴይር) ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በዚያ ዘመን፡ …….. እንዲህ ሆኖ በየቡድኑ ሲጠጣ የሚያመሽ ጎረምሳ የሱቅ መዝጊያውን ሰዓት መቃረብ ይጠብቅና በመጨረሻው እነ እንኮየን አንግቦ ለመሹለክ ሽርጉድና መፋጠጥን በማስከተል ወደ ረብሻና አምባጓሮ ስለሚለወጥ፣ ብዙ ጊዜ ያራዳ ቆሌ በዱላ ጋጋታና በድንጋይ በረዶ፤ ገፋም ሲል በጩቤ ብልጭታና በጥይት ፉጨት ያልተረበሸበት ሳምንት መኖሩ ያጠራጥራል፡፡

ነገር ግን የነ ጋሼ ሞገሴ ጎራ ምንጊዜም ከእንደዚህ አይነቱ ለፎ (የጨፋሪ ቡድን) ጋር መማከት እንደሚኖርበት አውቆ የሚሰለፍ ብቻ ሳይሆን፤ እንዲያ ባለው ስፍራ የሚፈለግ ደስታ ካደጋ ተነጥሎ እንደማይገኝ ከልማድ የተማሩት ከተፎዎች መጀመሪያውኑ በሁለት ሶስት ምድብ ተከፋፍለው በየሚፈልጓቸው ሴቶች ቤት ይገባሉ፡፡ ጠጁንም ሲጠጡ እንዳይሰክሩ በልክ ነው፡፡ ድሮውንም የጠጅ አምሮት የለባቸውምና፡፡ ለመሸታ ተጋባዦቻቸው ግን “ ከበር ምላሽ” እያሉ ያስቀዱና ሁሉንም ሞገሴ ይከፍላል፡፡ ለነገሩ ከየት ያመጣዋል ካልሆነ ብዛቱ ያን ያህል ሆኖ አይደለም፡፡ ራስ ኃይሉ አሉ እንደሚባለው፣ የውሀ ሽያጭ ገንዘብ እንደ ውሀ ሲቀዳ ቢውል ከቶ የማያልቅ ነበር ይሆን? በዛሬ ስሙ ታክሲ የሚባለው የኪራይ አውቶሞቢል ታላላቅ አርዲታ፤ ፎርድ፤ ኦቨርላንድ፤ ናሽ እና ሌላም አይነት ነበር፡፡ ታዲያ ወደ ማታ አዳሜ በጠጅ ሞቅታ በወሬ ቻቻታና በአዝማሪ ቱማታ ሲደናቆር፣ የእኛ ልጆች ሙሽሮቻቸውን በአይን ጥቅሻ የከንፈር ንክሻ ሲያሳይዋቸው ወደ ጓዳ ዘልቀው በዚያው ይሾልኩና ከሩቅ በሚጠብቃቸው አውቶሞቢል ውስጥ ይገባሉ፡፡

ጎበዞቹም ሀሳባቸውን ከፍለው በፊት ለፊት እየተዝናኑ በመውጣት ወደ ቀጠሮው ስፍራ ሲደርሱ “ጉሮ ወሸባ፤ጉሮ ወሸባ፤ ጉሮ ወሸባዬ እንዲያ እንዲያ ሲል ነው ግዳዬ” እያሉ በአውቶሞቢል ታጭቀው ወደ ቤት መፍሰስ ነው፡፡በዚህ ዘመን፡ …….. ለወትሮው ከምሳ በኋላ እየተንጠባጠቡ ወደ ሚኪያስ ቤት መጓዝ ልማድ ቢሆንም የሆነ ቻፓ በአሪፍ ዝግ የተዘጋ ጊዜ ግን ከቁርጥ ስጋ ጋር ድራፍታቸውን ቸልሰውና ተሟሙቀው የምሽት አዳራቸውን ገጠመኞች ላለመስማማት የተስማሙ እስኪመስሉ ድረስ እየተጯጯሁ በመዘከር ቤቷን በአንድ እግሯ ያቆሟታል፡፡ ይሄው ጫጫታና ፉከራ ግን እንደ በጋ ደመና ሰብሰብ ብትን እያለ እየደበዘዘ፤ እየሳሳ ይመጣና በአይን ጥቅሻና በምልክት ቋንቋ መነጋገር ይጀምራሉ፡፡ አንድ አራት የሚሆኑት ካርታ ይዘው ከበሩ ጀርባ ይቀመጣሉ፤ አንዱ ኒውስ ዊክ መፅሄት ፈጠን ፈጠን እያደረገ ይገልጣል፤ ሌላዋ በምርቃና ተል ብላ፣ እንደ ተተኮሰበት አውሬ ጆሮዋን በፍርሀት ቀስራ አንዴ ወደ ግራ አንዴ ወደ ቀኝ ታማትራለች፤ ከወደ ጥግ አካባቢ ደግሞ ለጨበሲ የብር እጥረት እንዳለበት በሚያሳብቅ ሁኔታ ጭብጥ ኩርምት ብሎ ተቀምጦ ለሽንትና ስልክ ለማውራት የተነሳውን ሁሉ “መሄድሽ ነው?” እያለ ሲያካልብ፤ አንዱ ደግሞ ረጅም እንዳበራ አይሱዙ አይኑን ቦግ አድርጎ በላፕቶፕ ሙዚቃ ያዳምጣል፤ሌላዋ በአንድ ጥግ ላይ ሆና ሺሻው ሲያልቅ ብቻ “ቀይረው” የሚል ድምጽ ካልሆነ ሌላ ነገር ማውራት እስኪሳናት አፏ ይለጎማል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ኪሱ ሞላ ያለው አንዷን በቴክስት ሜሴጅ ጠቅሶ ቺቺኒያ ይገባና፣ ከአንዱ ባር ወደ አንዱ ባር እየዘለለ ከቀናው በንጹህ ካልሆነም በተወጋ ውስኪ ኪሱንና አናቱን አዙሮ ሲገባ፤የቸሰተው ደግሞ ጓደኞቹ ጋር ደዋውሎ ከሆነለት ሄዶ ድራፍቱ ላይ ዘፍ ሲል፤ ካልቀናው ሰፈሩ አካባቢ ወዳለች ግሮሰሪ ጎራ ብሎ ሶስት ደብል ሎካል ጅኑን ይወጋና ወደ ቤቱ ገብቶ በፍሊት አልጠፋ ያሉ በረሮና ትንኝን ከጣራ፤ አላስተኛ ያሉትን ተባዮች ከብርድልብስ ውስጥ በትንፋሹ ሲያረግፍ ሲያርገፈግፍ ያድራል፡፡ የዘመኑ አራዳ!! ቸር ሰንብቱ!!

Read 3464 times