Saturday, 11 October 2014 12:47

ድመት አይጥ እንዲይዝ ተብሎ ችቦ አይበራለትም

Written by 
Rate this item
(8 votes)

(አንጋቻ ፉር ይጠብጥቲ ቤቶ ጦት ኤያተኩሺ)
ከዕለታት አንድ ቀን አንድን ዲታ የገጠር ሰው አውቶብስ መናኸሪያ አካባቢ ሌቦች አይተው ገንዘቡን ከኪሱ

ሊወስዱ ያንዣብቡበታል፡፡ ሰውዬው በጣም ደክሞታል፡፡ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ቤተክርስቲያን ሄዶ ጥቂት

አረፍ ማለት ይሻና ወደዚያው ቤተክርስቲያን ሄዶ ጥቂት አረፍ ማለት ይሻና ወደዚያው ያመራል፡፡
ሌቦቹም ባገኙት አጋጣሚ ብሩን ሊመነትፉት “እንከተለው፣ እንከተለው” ተባብለው ማንዣበባቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ሌቦቹ ሰውዬውን ከግራ ከቀኝ ከበው ሲከተሉት ፖሊስ ጠርጥሮ እነሱን እየተከተላቸው ኖሯል፡፡
ሰውዬው ቤተክርስቲያን ገባ፡፡
ሌቦቹም ተከትለውት ገቡ፡፡
ሰውዬው ሳር ላይ ጋደም አለ፡፡ ሌቦቹም ዙሪያውን ተጋደሙ፡፡
አፍታም ሳይቆይ ሰውዬው እንቅልፍ ድብን አድርጎ ወሰደው፡፡
ሌቦቹ በጣም ቀርበው ደረት ኪሱ ያለውን ገንዘብ ለማውጣት ሲሞክሩ ፖሊሶቹ ወደሌቦቹ መጡ፡፡
ከሌቦቹ አንደኛው ፖሊሶች እንደደረሱባቸው በመገንዘብ፣ ከኪሱ ምላጭ አውጥቶ ሰውዬውን መላጨት ጀመረ፡፡
አንደኛው ፖሊስ - “ምንድነው? ምን እያደረጋችሁ ነው?” ሲል ጠየቀ፡፡
አንደኛው ሌባ - “አይ ጓደኛችን ነው፡፡ ደክሞት ጋደም ብሎ ነው፡፡ ፀጉሩ በጣም ስላደገ ላጩኝ ብሎን ነው፡፡

ድንገት እንቅልፍ ወሰደው፡፡”
ፖሊሱም፤
“ደህና፡፡ ቀጥሉ” ብሎ ሄደ፡፡
ሌቦቹ፤
“ስለጥንቃቄህ እናመሰግናለን” አሉት፡፡
ሌቦቹም ከራሱ ላይ ፀጉሩን፣ ከደረት ኪሱ ብሩን፣ ላጭተው ሲያበቁ ተነስተው ይሄዳሉ፡፡
ሰውዬው ከሰዓታት በኋላ ከእንቅልፉ ይነቃል፡፡
የሰላም እንቅልፍ በመተኛቱ፤
“ተመስገን” እያለ ደረቱ ላይ ሲያማትብ፤ ደረት ኪሱ ቅልል አለበት፡፡ እጁን ኪሱ ከቶ ቢያይ ብሩ የለም፡፡
“ወይኔ ብሬ! ብሬን ዘረፉኝ!” እያለ በሁለት እጁ ጭንቅላቱን ይዞ ሊጮህ ሲሞክር የራስ ፀጉሩ የለም፡፡
ይሄኔ ጥቂት አሰብ አድርጎ ፀጉር - አልባ መሆኑን በደንብ ሲገነዘብ፤
“እፎይ! ለካ እኔ አይደለሁም!” ብሎ ተፅናንቶ መንገዱን ቀጠለ፡፡
                                     *       *          *
በቁም ከሚላጩ ሌቦች ይሰውረን!
መቼም ቢሆን መች ማንነታችንን ከሚያስዘነጋ አደጋ ይጠብቀን፡፡ ህልውናችንን ጥያቄ ውስጥ ከሚያስገባ ሁኔታ ያድነን፡፡ የቱንም ያህል ብናንቀላፋ፣ የቱንም ያህል ቸልተኛ ብንሆን፣ የቱንም ያህል ግብዝ ብንሆን፤ “እፎይ! እኔ አይደለሁም!” ከማለት ያውጣን፡፡
በሀገራችን ከተከሰቱ ችግሮች አንዱ “እኔን እስከደገፈ ድረስ አምነዋለሁ” የማለት አባዜ ነው፡፡ ሌብነቱን ያበዛው፣ እምነቱን ያቀጨጨው፣ በቀላሉ ማታለልን ያበረታታው፤ “ከታላላቅ ባለሥልጣናት ጋር የዋለ አጭበርባሪ ሊሆን አይችልም” ብሎ ማለትን እጅግ ያጎለበተው ሰውን የማመን ባህል ነው፡፡ ማመናችንን እንመርምር! ሀገራችን ችግር በገጠማት ቁጥር ከመራወጥና ይይዙት ይጨብጡትን ከማጣት፣ ተገዶም ከመንገድ ከመውጣት አስቀድሞ “ያቀድነው ባይሳካስ፣ ያልጠበቅነው ነገር ቢከሰትስ?” ብሎ ራስን መጠየቅ ትልቅነት ነው፡፡ ማናቸውም ችግር ራስን ለማዘጋጀት ይጠቅማልና ያቀድኩትን በችኮላ እፈፅማለሁ ብሎ መሯሯጥም “ሲሮጡ የታጠቁት ሲሮጡ ይፈታል መሆኑን ቀድሞ ማውጠንጠን ነው፡፡
ባልታዛር ግሬሺያን የተባለ ፈላስፋ፤ እንዲህ ይለናል፡-
“ታላላቅ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ቸኩለው እርምጃ ከመውሰድ ይቆጠባሉ፡፡ ምነው መውጣት አንድ ጉዳይ ውስጥ ቸኩሎ እጅን ካስገቡ በኋላ፤ ያ ከመግባት ይልቅ የከበደ ነውና፡፡ አንዳች አዲስ ነገር ሲከሰት ፍርድህን ይፈታተንሃል፡፡ በአሸናፊነት መውጣት ከሚጠይቅህ አቅም ይልቅ፤ ቸኩሎ ከመወሰን መቆጠብ ትንሽ ጉልበት ነው የሚጠይቀው፡፡ አንድ ኃላፊነትና ግዴታ ሌላ ኃላፊነትና ግዴታን እንደሚወልድ አትርሳ፡፡ ያ እየተጫነህ ስትመጣ ወደ መንኮታኮት እጅግ ተቃረብክ ማለት ነው፡፡”ይሄ ለእኛ ትልቅ ተሞክሮ ሊሆነን ይገባል፡፡ በሩቅ ከለየላቸው ጠላቶች ይልቅ በውስጣችን ያሉትን መጠንቀቅም አንዱ መርሀችን ሊሆን ይገባል፡- “ለሰለሰ ብለህ እባብ ትታጠቃለህ ወይ?” የሚለው የትግሪኛ ተረት ይሄንን ጠቅልሎ ያስቀምጥልናል፡፡
በሀገራችን፣ የፖሊተካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ንፍቀ-ክበብ ውስጥ ብርቱ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነገር አደብ መግዛትና ሆደ-ሰፊ መሆን ነው፡፡ በቀላሉና በትንሹ ነገር ሁሉ ቱግ ማለት፣ ሲያሸንፉ ከልኩ በላይ ዘራፍ ማለት፣ ሲሸነፉ መድረሻ ማጣትና ዓለም ጨለመች ማለት፤ ለክፉ ይዳርጋል፡፡ “ላናድህ ያለ እሳት ሲጭር እሳት ፍለጋ አትሂድ፡፡ ማገዶውን አርጥብ” እንዲል መፅሐፈ - ተረት፤ በብስለት እንጂ በጉልበት ለውጥ እንደማናመጣ ልብ እንበል፡፡ ዛሬ ላደርገው ያሰብኩትን ነገር በቀጣዩ ዓመት ባደርገውስ? ብሎ ቆም ብሎ ማሰብ “የቸኮለች አፍሳ ለቀመች” ከመባል ያድነናል፡፡ ብዙ በችኮላ የተከናወኑ እንቅስቃሴዎች ሽባ አድርገው ሊያስቀሩን እንደሚችሉ ያስወረዱ አብዮቶች (abortive revolutions) ታሪክ ይነግረናል፡፡ ለማናቸውም፤ ግዴታችን የሆኑትን ነገሮች ለይተን እንደግዴታነታቸው መቀበል፣ ኃላፊነት የሚጠይቁትን ጉዳዮች እንደኃላፊነት አጥብቆ ይዞ መወጣት፣ አሌ የማይባልና ተጠያቂነትን የተሸከመ ተግባር ነው፡፡ ለሀገር ዕድገትና ለህዝብ ጥቅም ሲባል፤ መሪና ተመሪ፣ ገዢና ተገዢ፣ አለቃና ምንዝር፣ ሥልጣን ላይ ያለፓርቲና ተቃዋሚ … ሹመኛና ሿሚ፤… ሁሉም ሁነኛ ኃላፊነትና ግዴታውን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ ምነው ቢሉ፤ “ድመት አይጥ እነዲይዝ ተብሎ ችቦ አይበራለትምና!” 

Read 6919 times