Saturday, 11 October 2014 12:16

በ10 ዓመት ውስጥ የኢኮኖሚውን መሪነት በማዕድን ለመተካት ታቅዷል

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(4 votes)

ዕቅዱ የተለጠጠ ነው ተብሏል

        የኢትዮጵያ ከርሰ ምድራዊ ሁኔታ እንደሌሎች የአፍሪካ አገራት አዋጭ ነው በሚል ግምት አማካኝ ገቢው ቢሰላ፣ ኢትዮጵያ ከማዕድን ዘርፍ በእምቅ ሀብቷ በዓመት 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት እንደምትችል አንድ የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት አመለከተ፡ ሌሎች ገቢዎችን በንግድ ገቢ ግብርና የሮያሊቲ ክፍያ በመለካት አገሪቱ እስከ 2024 (እኤአ) ከ100 እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት እንደምትችልና የማዕድን ልማት ዘርፉ ከ1,400 እስከ 8000 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ የኢትዮጵያን የማዕድን ልማት ዘርፍ ለመደገፍ ከዓለም ባንክና አጋሮቹ፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን፣ ከካናዳ የውጭ ንግድና ልማት ተቋም፣ ከአውስትራሊያ መንግስትና ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ተቋም በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ ከግንቦት 2013 እስከ መጋቢት 2014 በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ዕቅድ ላይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ሪፖርቱ ጠቅሶ፣ ኢትዮጵያ፣ ከወርቅ፣ ከታንታለምና ከኦፖል በተጨማሪ በኢንዱስትሪ ማዕድናትም በተፈጥሮ የታደለች መሆኗን አመልክቷል፡፡ ከፍተኛ ማዕድን አምራቶች በኢትዮጵያ የሉም ያለው ሪፖርቱ፤ የሲሚንቶ ምርት ጥሬ ግብአቶችና የማዕዘን ድንጋዮች በአነስተኛ ኢንዱስትሪዎች፣ ሌሎች የኢንዱስትሪ ማዕድናት በጥቃቅንና አነስተኛ ድርጅቶች በልማዳዊ አሰራር ይመረታሉ ብሏል፡፡

ዘርፉን ሊያበረታታ የሚችል ሁኔታ ላይ ያለው የኦላና ፓታሽ ክምችት ሲሆን አሁን ባለው ዕቅድ መሰረት ወደ ምርት ሲገባ በቀን 1 ሚሊዮን ቶን እያመረተ ለ24 ተከታታይ ዓመታት ይዘልቃል፤ ለ800 ሰራተኞችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ብሏል፡፡ የአገሪቷ ከርሰምድራዊ ሁኔታዎች፣ በሰሜን፣ በምዕራብና በደቡብ የአገሪቷ ክፍሎች እምቅ አዳዲስ የማዕድን ሀብቶች እንደሚኖሩ ያመለክታሉ ያለው ሪፖርቱ፤ ይኖራል ተብሎ የሚገመተው የማዕድን መጠን፣ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከሚገኙ የማዕድን አካባቢዎች የላቀ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ማዕድን ከመፈለግ እስከ ግዙፍ ማዕድን ማውጣት ያለውን ሥራ ለማከናወን ቀዳሚ ክንውኖች የሚካሄዱበት ጊዜ ረዥም ሲሆን ከ10 እስከ 15 ዓመት ይፈጃል ያለው ሪፖርቱ፤ አሁን ባለው የአገሪቱ ፖሊሲ ማዕቀፍ መሰረት (እ.ኤ.አ ከ2022-2023) ድረስ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የኢኮኖሚው የጀርባ አጥንት እንዲሆን ታቅዷል፡፡

ነገር ግን አገሪቷ ያለመችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይሳካ ይችላል፡፡ የማዕድን ዘርፍ ልማት ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በመለስተኛ የዕድገት አቅጣጫ የረዥም ጊዜ እቅድ ሲቀረፅ ነው በማለት አስረድቷል፡፡ በማዕድን ዘርፍ ልማት ለመጠቀም፣ አሁን የሚታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ፣ የማዕድን ፍለጋና የማዕድን ማውጣት የሥራ ፈቃድ የሚሰጥበት ግልፅ ፖሊሲ፣ ህጎችና ደንቦች ማስቀመጥ፣ የማዕድን ሚ/ርን ተቋማዊ አቅም መገንባት፣ የተቆጣጣሪ ተቋማትን የአቅም ውስንነት ከግምት በማስገባት የማዕድን አልሚ ኩባንያዎችን በዘርፉ ንቁ ተሳታፊ ማድረግ፣ ኢኮሎጂካዊ አዋጭ ስለሚባሉ አካባቢዎች በቂ መረጃ ማቅረብ፣ የማዕድን ገቢ ክፍፍል ሥርዓትን መቅረጽ፣… ያስፈልጋል ብሏል ሪፖርቱ፡፡ በረዥም ጊዜ ከፍተኛ የማዕድን ዘርፍ ከመፍጠር አኳያ፣ ፖሊሲ አውጪዎች ከዘርፉ የሚገኝን ጥቅም በበለጠ ማሳደግ የሚችሉበትን ዕቅድ ማጥናት ያስፈልጋል ያለው ሪፖርቱ፤ ምንም እንኳ መንግሥት ያስቀመጠው የተለጠጠ ዕቅድ በቀጣዩ 10 ዓመት ይሳካል ተብሎ የሚገመት ባይሆንም በዘርፉ ልማት የተገኙ ውጤቶችን የእሴት ሰንሰለቶች ለመፍጠር የግድ ማበረታታት ያስፈልጋል በማለት አሳስቧል፡፡

Read 4418 times