Monday, 06 October 2014 08:46

የታይላንዱ ጠ/ሚ ጠንቋይ ቤት መሄድ ክፋት የለውም አሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አብዛኞቹ የአገሪቱ ባለስልጣናት ፖሊሲ ሲያወጡ ጠንቋይ ያማክራሉ
የታይላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፕራዩዝ ቻኖቻ፣ ወደ ጠንቋዮች ጎራ ብሎ የመጪውን ጊዜ ዕጣ ፋንታ በተመለከተ የሚሰጡትን ትንቢትና ምክር መስማት ክፋት የለውም፤ ጥንቆላም ራሱን የቻለ ጥበብ ነው ሲሉ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
“ጠንቋዮች የሚነግሩኝን ትንቢት ልብ ብዬ እሰማለሁ፡፡ ምክራቸውንም እቀበላለሁ፡፡ እንዲያውም በቅርቡ በአገሪቱ ከሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ጋር ግጭት ውስጥ ልገባ እንደምችል አስጠንቅቀውኛል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መገናኛ ብዙሃን መሪያችን ጠንቋይ ቤት ይሄዳሉ ሲሉ ያሰራጩት ዘገባም ትክክለኛ እንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡
ቻኖቻ በመገናኛ ብዙሃን ስለጠንቋይ አማኝነቴ የሰማችሁት ትክክል ነው ሲሉ ባለፈው ማክሰኞ መናገራቸውን የገለጸው ዘገባው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠላቶቻቸው ካሰሩባቸው ድግምትና አስማት ለመንጻት ሲሉ፣ ከእግር እስከ ራሳቸው ጠበል መጠመቃቸውን በወሩ መጀመሪያ ላይ በይፋ መናገራቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአገሪቱን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታክሲን ሺንዋትራን ጨምሮ በርካታ ደንበኞችን ወዳፈራው ኢት የተባለ የማይናማር ታዋቂ ጠንቋይ በመሄድ ምክር ይሰማሉ መባሉን ያስተባበሉት ቻኖቻ፣ ይሄም ሆኖ ግን ወደ ጠንቋዩ የመሄድ ፍላጎት እንዳላቸው አልደበቁም፡፡
ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች አብዛኞቹ፣ የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ ሲያስቡ ወደ ጠንቋዮች ሄደው፣ “ይበጃል፣ አይበጅም?” ብለው የማማከር ልማድ እንዳላቸው የጠቆመው ሮይተርስ፣  ታይላንድ ወደዘመናዊነት እየተሸጋገረች ያለች አገር ብትሆንም፣ ለረጅም ዘመናት የዘለቀው ጥንቆላና መሰል የባዕድ አምልኮ አሁንም ድረስ በስፋት እንደሚከናወንባት አመልክቷል፡፡

Read 6084 times