Monday, 06 October 2014 08:09

ጉርሻ የለመደች ሴት በጥፊ ሊመቷት እጅ ሲያነሱ አፏን ትከፍታለች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

(የወላይታ ምሳሌያዊ አነጋገር)

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ዶሮና አንድ አውራ ዶሮ ወደ አንድ ፍሬ ወደ ሚገኝበት ተራራ ይወጣሉ፡፡ አንድ ስምምነት እንዲያደርጉም መነጋገር ጀመሩ፡-
አውራ ዶሮ ---------- እመት ዶሮ
እመት ዶሮ ---------- አቤት አያ አውራ ዶሮ
አውራ ዶሮ ------- አንድ ነገር እንስማማ
እመት ዶሮ -------- ምን አሰብክ ወዳጄ?
አውራ ዶሮ -------- ምንም ዓይነት ፍሬ ብናገኝ አንዳችን ላንዳችን እናካፍል
እመት ዶሮ ----- በሃሳቡ እስማማለሁ፡፡ ድንቅ መርህ ነው!
በዚህ ስምምነት ፀንተው ያን ተራራ ተያያዙት፡፡ ከሰዓታት በኋላ እመት ዶሮ አንድ ትልቅ ፍሬ አገኘች፡፡ ግን ስለማግኘቷ አንዲትም ቃል ትንፍሽ ሳትል መንገድ ቀጠለች፡፡ አንድ አሳቻ ቦታ ስትደርስ፣ ዘወር ብላ ፍሬውን ልትበላ ሞከረች፡፡ ሆኖም ፍሬው በጣም ትልቅ በመሆኑ አልዋጥ አላት፡፡ አንቆ የሚገላት መስሎ ስለተሰማት፣ በጣም ደነገጠች
“አያ አውራ ዶሮ! አያ አውራ ዶሮ!” ስትል ጮኸች፡፡
አውራ ዶሮም፤ “ምነው? እመት ዶሮ ምን ሆንሽ?” አላት፤ ካለበት ሆኖ፡፡
“እባክህ ትን ብሎኝ ልሞት ነውና ውሃ ፈልገህ አምጣልኝ”
አውራ ዶሮው በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ የውሃ ጉድጓድ ሄዶ፤ “ጉድጓድ ሆይ! እባክህ እመት ዶሮ ልትሞትብኝ ነውና ትንሽ ውሃ ስጠኝ?” ሲል ጠየቀው፡፡
ጉድጓዱም፤ “መስጠት እሰጥሃለሁ፡፡ ግን በመጀመሪያ ከዕለታት አንድ ቀን የአፌ መሸፈኛ የሆነውን ቀይ ሀር ጨርቅ፣ እመት ዶሮ ሰርቃ ወስዳብኛለችና ከጌታዋ ቤት ሄደህ አምጣልኝ” አለው፡፡
አውራ ዶሮው አሁንም የዶሮ ጌታው ዘንድ እየበረረ ሄዶ፤
“ጌታዬ፤ እመት ዶሮ በውሃ እጦት ልትሞት ቢሆን፤ ጉድጓድን ውሃ ስጠኝ ልለው ሄድኩ፡፡ እሱም ወደ ጌታዋ ዘንድ ሄደህ የሰረቀችኝን ሀር አምጣ አለኝ፡፡ እባክዎ ሀሩን ይስጡኝና ውሃ ላግኝላት?” ሲል ጠየቀው፡፡
ጌትዬውም፤ “በመጀመሪያ ከቤት ሰርቃ የወሰደችውንና ለዶሮ ጠባቂው የሰጠችውን ሰዓት አስመልስልኝ” አለው፡፡
አውራ ዶሮ ሲበር ሄዶ ዶሮ ጠባቂውን ለመነውና ሰዓቱን አስመልሶ ለጌትዬው መለሰ፡፡ ቀዩን ሀር ተቀብሎ ለጉድጓዱ ሰጠ፡፡ ውሃውንም ከጉድጓዱ ወስዶ ለዶሮዋ ሊሰጥ ወደ ተራራው ወጣ፡፡ እዚያ ሲደርስ ግን እመት ዶሮ ለአንዴም ለሁሌም አሸልባለች፡፡
                              *           *         *
አበው “ብቻውን የበላ ብቻውን ይሞታል” ይላሉ፡፡ አንድም ደግሞ “ሥራ ለሰሪው እሾህ ለአጣሪው” ይላሉ፡፡ የሰራነው ሥራ እስከ እለተ ሞታችን ድረስ ይከተለናል፡፡ እያንዳንዷ ዱካችን የማታ ማታ ተከትላ ታጋልጠናለች፡፡ የሙስና የመጨረሻ ፍፃሜ እንደዶሮይቱ በተያያዘ ጥፋት ዋጋ መክፈል ነው፡፡ Domino effect እንዲሉ ፈረንጆች፡፡ አይታወቅብኝ በሚል በአልጠግብ ባይነት በአሳቻ ቦታና ሰዓት የመነተፍነው የህዝብ ንብረትና ንዋይ፣ አንድ ቀን ክፉ ቦታ ላይ እንደሚጥለን እንገንዘብ፡፡ ቃልን ማፍረስ፣ የሀገርን ሀብት መበዝበዝ፣ የሀገርን ክብር ማዋረድ፤ ሁሉም ዓይነት ሙስናዎች የማታ ማታ ያስጠይቃሉ፡፡
የተጠርጣሪዎች መብዛት፣ ከስራ መባረሮች፣ የጥርጣሬና ፍርሃት መንገስ፣ ከተሾሙበት ስልጣን መባረር መብዛት ወዘተ ሁሉም የሙስና መገለጫዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የተገለጠ ዐይን ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ለማስተካከል አንጋረ ፈላስፋ የሚለንን ማዳመጥ መልካም ነው፡-
“ንጉሥ ሦስት ነገሮችን ገንዘብ ማድረግ ይገባዋል፡-”
1ኛ/ ዐዋቂዎቹን አክብሮ መያዝ
2ኛ/ ለተቸገሩት መስጠትና በማናቸውም መርዳት
3ኛ/ ህዝቡን በቅንነትና በርህራሄ ማስተዳደር፡፡”
    ቀጥሎም እንዲህ ይለናል፡-
“ብልህ ዐዋቂ ሰው፣ አንደበቱ የልቡ አማካሪ ነው፡፡ መናገር ሲያምረው አስቀድሞ በልቡ ያወጣ ያወርድና፣ ለመናገር መንገድ ሲያገኝ ይናገራል፣ ባያገኝ ግን ዝም ይላል፡፡ ቁም ነገሩ ይኸው በጎውንና ክፉውን ለይቶ መናገር ነው” ስለዚህም ነው የሙስናን ጣራ መንካት ደጋግመን ስንናገር የከረምነው፡፡ ዛሬም ያንኑ የሙስና መንገድ የሚከተሉ አያሌ ናቸው፡፡ የሌሎች መጠርጠር፣ የሌሎች መታሰር የማያስደነግጣቸው አያሌ ናቸው፡፡ የሚሰነዘረው በትር የማቀፍ ያህል ፈገግ የሚያሰኛቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡
“ጉርሻ የለመደች ሴት በጥፊ ሊመቷት እጅ ሲያነሱ አፏን ትከፍታለች፡፡” የሚለው የወላይታ ተረት የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡
ኢድ ሙባረክ!

Read 5165 times