Monday, 06 October 2014 08:02

“ኩረጃን ለትውልድ አናወርስም” የሚል ዘመቻ የግድ ነው!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(3 votes)

የዓለም አቀፍ ሆቴሎችን ስም መመንተፍ ጉድ አፈላ!
        የዛሬውን ወጋችንን የምንጀምረው አንድ ሁለት ቀልዶችን ጣል በማድረግ ነው፡፡ የቀልዶቹ ዓላማ እናንተን ፈገግ ማሰኘት ነው፡፡ (ምን በወጣችሁ በመስቀል ሳምንት ደረቅ ወግ!)
የህንዱ የነፃነት ታጋይ የነበሩት ማህትማ ጋንዲ ለጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ወደ እንግሊዝ አገር ይሄዳሉ፡፡ ያኔ ጋንዲ ሸሚዝ የሚባል ነገር መልበስ እርም ብለው ነበር፡፡ እናም በለንደን አውራጎዳና ላይ ከፊል እርቃናቸውን ሆነው ይዘዋወራሉ፡፡ አንድ ትንሽ ልጅ ከእናቱ ጋር ሆኖ ወደ ጋንዲ ቀረብ ይልና፡-
“ሚስተር ጋንዲ፤ ለምን እናቴ ሸሚዝ አትገዛልዎትም?” ሲል ይጠይቃቸዋል
ጋንዲም፤ “በጣም አመሰግንሃለሁ የእኔ ልጅ፤ ግን ወንድሞቼስ?”
ትንሹ ልጅ፤ “እናቴ ለእነሱም ልትገዛላቸው ትችላለች፤ ስንት ናቸው ወንድሞችዎ?”
ጋንዲ፤ “400 ሚሊዮን!” አሉ - ፍርጥም ብለው፡፡ (የያኔውን አጠቃላይ የህንድ የህዝብ ብዛት ነበር የተናገሩት!)
አሁንም ስለጋንዲ ሌላ ቀልድ ወይም ጨዋታ ልድገማችሁ፡፡ እንግዲህ ጋንዲ ፊልም የሚባል ነገር አይተው አያውቁም አሉ፡፡ (ይታገሉ ወይስ ፊልም ይመልከቱ?) አንድ ሰው ቻርሊ ቻፕሊንን ሊያስተዋውቃቸው ይሞክራል፡፡
“ሚ/ር ጋንዲ፤ ይተዋወቁት፤ በዓለም እጅግ ዝነኛው ኮሜዲያን ቻርሊ ቻፕሊን ነው”
ጋንዲም ቶሎ ቀበል አድርገው፤ “አዝናለሁ፤ ጥርሶች ስለሌሉኝ መሳቅ አልችልም”
በዚህ አባባላቸው ቻፕሊን በሳቅ ፈረስ (ያስቃል የተባለው ስቆ ተመለሰ!)
አንድ የመጨረሻ ቀልድ ልንገራችሁና ኮስተር ወዳሉ አገራዊ ጉዳዮች እንገባለን፡፡ (ያው እሱንም ቢሆን በፈገግታ ነው!) አሁንም ከጋንዲ አልወጣንም፡፡ የታላቋ ብሪታንያ ገዢ የነበሩት ንጉስ ጆርጅ በስድስት ባለሟሎቻቸው ከኋላው እንደሙሽራ ቬሎ የተያዘ በጣም ረዥም ካፓ ለብሰዋል፡፡ ጋንዲ ግን እንደተለመደው (በህንድ ባህላዊ ሸርጣቸው) ከፊል እርቃናቸውን ነበር ንጉሱ ፊት የቀረቡት፡፡ ቤተመንግስት ድረስ የወሰዷቸው ባለሟልም ጋንዲን ከንጉሱ ጋር ያስተዋውቋቸዋል (የማን እብድ መጣብኝ ሳይሉ ይቀራሉ!)
ንጉስ ጆርጅ፡- “ሚ/ር ጋንዲ፤ ያለሸሚዝ እኔ ፊት ስትቀርብ ሃፍረት አይሰማህም?”ጋንዲ፡- “ንጉስ ሆይ፤ እርስዎ የለበሱት ለሁለታችንም ይበቃል እኮ!” (ንጉሱ ምነው ምላሴን በቆረጠው ያሉ ይመስለኛል!)አሁን በቀጥታ ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡ ባለፈው ሳምንት አዲስ አድማስ ጋዜጣ በፊት ለፊት ገፁ ላይ ያወጣው ዘገባ፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች፣ የተማረሩበትን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚያጋልጥ ነበር፡፡ (ኢህአዴግ “የሥርዓቱ Top 10 ችግሮች” ብሎ ባወጣው ዝርዝር ውስጥ “የመልካም አስተዳደር ችግር” በቀዳሚነት መስፈሩን ልብ ይሏል!) እናም ጋዜጠኞቹ የመልካም አስተዳደር እጦት አማረረን ማለታቸው ፈፅሞ “surprise” አያደርገንም (ሰርፕራይዙ ችግሩ የለም ቢሉ ነበር!) እኔ የምለው ግን… ኢህአዴግ “ከሰለጠኑት አገራት መኮረጅ ነውር የለውም” እያለ (ያውም ኮማ ሳትቀር!) ስንት ነገሮች ሲኮርጅ… እንዴት መልካም አስተዳደርን ሳይኮርጅ ቀረ? (መልካም አስተዳደር ለኩረጃ አይመች ይሆናላ?) የሆኖ ሆኖ የፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ብለው ከጠቀሷቸው መካከል በሃምሌ ወር የተደረገው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እስካሁን እኛ ጋ አልደረሰም የሚል ይገኝበታል (“ሃብታም በሰጠ…”ልል አልኩና ተውኩት፡፡) የሚገርማችሁ ግን ዜናው ውጤት ተኮር ነበር፡፡ (ወይስ ገዳም?) ዘገባው በወጣ በ48 ሰዓት ውስጥ በመልካም አስተዳደር እጦት የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረባቸው የደሞዝ ጭማሪ ተከፈላቸው የሚል “የምስራች” ሰማን (Better late than never! አለ ፈረንጅ!) ይሄን ስሰማ ወዲያው ወደ አዕምሮዬ የመጣብኝ የፕ/ር በየነ ጴጥሮስ አባባል ነው፡፡ (“በአገሬ ተስፋ አልቆርጥም” ነው ያሉት!!)
በዚህ አጋጣሚ ለጋዜጠኞች እሮሮ ምላሽ በመስጠት መልካም አስተዳደር ለማስፈን ያለውን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር ላሳየው የፕሬስ ድርጅቱ አመራር አክብሮቴን ልገልፅ እወዳለሁ (ራሴን ወክዬ ማለት ነው!!) ግን የጋዜጠኞቹ ትግል ተጀመረ እንጂ ከዳር አልደረሰም፡፡ በጋዜጠኞቹ የተዘረዘሩት ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችም መፍትሄ ማግኘት አለባቸው፤ ያገኛሉም፡፡ (ሃበሻ ተስፋ አይቆርጥም አሉ!!) ይሄ በዚህ እንዳለ ግን ገበናችንን ማነው ለሚዲያ ያወጣው (ያውም ለግል ፕሬስ!) በሚል “አውጫጭኝ” ቢጤ ተጀምሯል የሚባል ወሬ ተናፍሷል፡፡ (ይሄ ከፕሬስ ድርጅት አይጠበቅም!) ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ህገ-መንግስታዊ መብት መጣስ እኮ ነው! (ይታረማል ብለን እንመን!)
ወደሌላ አጀንዳ እንሻገር፡፡ እኔ የምለው … ባለፈው ሳምንት ከ400 በላይ የሚሆኑ የሆቴል ኩባንያዎች በመዲናችን ጉባኤ ተቀምጠው እንደነበር ሰማችሁ አይደል? ይሄ መቼም ግሩም አጋጣሚ እኮ ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ዓለም አቀፍ የሆቴል ኩባንያዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ሆቴሎቻቸውን እንዲከፍቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ጥሪ ማድረጋቸው ሸጋ ነው፡፡ ምናልባት ጠ/ሚኒስትሩ (አስታዋሽ በማጣት ይመስለኛል!) የዘነጉት ነገር አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ምን መሰላችሁ? ለአገር በቀሉና በሆቴል ኢንቨስትመንት ላይ ለተሰማራው ባለሀብትም ጥሪ ማቅረብ ነበረባቸው፡፡ ሆቴል ገንቡ የሚል እኮ አይደለም፡፡ (የአቅማቸውን ያህል ገንብተዋል!) “የዓለም አቀፍ ሆቴሎችን ስምና ዝና፣ ሎጎና ሌሎች ነገሮች ያለፈቃዳቸው ወርሳችሁ አትጠቀሙ” የሚል፡፡ እንዴ… በሰሞኑ ጉባኤ የተሳተፉት እኮ በዓለም የገነነ ስም ያላቸው የሆቴል ባለቤቶችና ኩባንያዎች እኮ ናቸው፡፡ እናም ስማቸውን በሆቴል ህንፃዎች ላይ በአብረቅራቂ መብራት ብልጭ ድርግም ሲል ቢመለከቱት ራሳቸውን ስተው አይወድቁም ትላላችሁ? ራሳቸውን ስተው ባይወድቁ እንኳን በጦቢያ ምድር ኢንቨስት የማድረግ ሃሳባቸውን ሊቀይሩ ይችላሉ (ስማቸውን የተመነተፉ ይኖራሉ!) ለዚህ ነው ጠ/ሚኒስትሩ በነካ እጃቸው ለሆቴል ባለቤቶቹ ምክርም ማሳሰቢያም ቢጤ ማስተላለፍ ነበረባቸው የምለው፡፡ ለነገሩ የእሳቸው ምክርና ማሳሰቢያ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ጥብቅ ህግ ያስፈልጋል፡፡ ዓለም አቀፍ ስሞችን መመንተፍ የሚከለክል ዓለም አቀፍ ህግ! (የWTO አባል እስክንሆን ምናምን… አይሰራም!)
እኔ የምለው ግን… ካልጠፋ ስም ባህር ማዶ ተሻግሮ የፈረንጅ ስም መመንተፍ በህግ ባያስጠይቅ እንኳ ከሞራል አንፃር ተገቢ ነው እንዴ? እርግጠኛ ነኝ የስም ዝርፊያው የሚመጣው የዓለም አቀፍ ሆቴሎችን መስፈርት ለሟሟላት አቅም ብቻ ሳይሆን ልብም ጭምር ስናጣ ነው፡፡ (ያለዚያ አይታሰብማ!) ግን እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ (ዓለም አቀፍ የሆቴሎች ጉባኤ) ሲፈጠር ደሞ መደነባበራችንና ግራ መጋባታችን አይቀርም፡፡ (“ምን ያለበት … ዝላይ አይችልም” አሉ!) ወዳጆቼ፤ በሆቴል በሉት በፖለቲካ፣ በግብርና በሉት በኢንዱስትሪ ወይም በሌላ ዘርፍ አየር ባየር አያዋጣም (ለፍቶ መና እኮ ነው!)
ሌላው ሁሌ የሚከነክነኝ ምን መሰላችሁ? እንዴት ይሄ ሁሌ ሆቴል እየተገነባ ባለበት ሰዓት አንጀት የሚያርስና የልብ የሚያደርስ የሆቴልና ቱሪዝም ት/ቤት አልተከፈተም? (ስምና ዝና ያለው ማለቴ ነው!) በዲግሪና ከዚያ በላይ የሚያስተምር! ምናልባትም ከምስራቅ አፍሪካ ቁጥር 1 ለመሆን ራዕይ ያለው (Think Big! ነው ነገሩ!) ጥያቄው ወይም ጥቆማው ለኢንቨስተሮች ነው፡፡ ባይ … ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰው ሃሳብ፣ የጥበብ ስራ፣ የንግድ ስያሜ… በጠራራ ፀሐይ መመንተፍ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ለዚህ አንድ መንስኤ የኩረጃ መበረታታት ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩ (መጠርጠር መብቴ ነው!) … እናም… ኢህአዴግም ሆነ መንግስት በኩረጃ ላይ ያላቸውን አቋም በግልፅ ሊያሳውቁ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ (ኢህአዴግና መንግስት ቢኮራረጁ እኮ ችግር የለውም!) ይኸውላችሁ… አንዳንዴ ባለስልጣኖቻችን ነሸጥ ሲያደርጋቸው በቲቪ መስኮት እየቀረቡ፣ ከሰለጠኑት አገራት መኮረጅ ችግር እንደሌለው ይናገራሉ፡፡ (ይሄ እኮ ነው ነገር ያበላሸው!) በሌላ በኩል የት/ቤት ፈተና ሊቀርብ ሰሞን በኢቴቪ የፀረ - ኩረጃ ማስታወቂያ ይጧጧፋል (የውጭ ፈንድ አለው እንዴ?) አንዴ “ኩረጃ ነውር የለውም”፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ “ኩረጃ አስነዋሪ ተግባር ነው” ይባላል፡፡ (ትውልዱ እንኳን ግራ አጋብተነው እንዲያውም እንዲያ ነው!) በራሱ በኢህአዴግ ቋንቋ ልጠቀምና ሁለቱን እያጣቀሱ መጓዝ መንገድ ነው የሚያስቀረን፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (አፈሩ ይቅለላቸውና!) አንዴ ለተቃዋሚዎች የሰጡት ማስጠንቀቂያ ትዝ አለኝ፡- “ህጋዊነትንና ህገወጥነትን እያጣቀሱ መጓዝ አይቻልም!” ነበር ያሉት (ካልተሳሳትኩ!) ዛሬስ? አሁንስ? አንዴ “መኮረህ ነውር የለውም”፤ ሌላ ጊዜ “መኮረጅ አስነዋሪ ተግባር ነው” በሚል እያጣቀሱ መቀጠል አይቻልም (ግራ ተጋብተን ግራ አናጋባ!)አሁንማ ምን እየተባለ መሰላችሁ? “እንኳን ግለሰብ ከግለሰብ፣ አገርም ከአገር ይኮርጃል!” እኔ በበኩሌ ግን፤ ዕውቁ የፍልስፍና ምሁርና ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በቅርቡ ለአዲስ አድማስ በተናገሩት እስማማለሁ (ኢህአዴግም … ተቃዋሚዎችም … ካድሬም … ሲቪልም ቢስማማ ነው የሚሻለው!) አዲሱ ዓመት የጤና፣ የብልፅግናና የሰላም… ምናምን የሚሉ ክሊሼዎችን ያጣጣሉት ምሁሩ፤ የኩረጃ ዘመን እንዲያበቃ ተመኝተዋል፡፡ ወዳጆቼ፤ ኩረጃ እኮ ወንዝ አያሻግርም፡፡ (የጥገኝነት ባህል ነው የሚያዳብረው!) እናም… “ኩረጃ በእኛ ይብቃ” እንበል!! (የተኮረጀውም እኮ ፍሬ አላመጣም!) መልካም ሰንበት!  

Read 4272 times