Monday, 29 September 2014 10:24

“የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስልጠና በግዴታ አልተሰጠም”

Written by 
Rate this item
(7 votes)

የኮበለሉ ጋዜጠኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበናል
ሥልጠናው ከምርጫ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም
የአቅም ግንባታ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ማስረጫ አይደለም

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተሰጠ ባለው ስልጠናና በአምስት የግል መጽሄቶችና በአንድ ጋዜጣ ላይ የተመሰረተውን ክስ ተከትሎ ከአገር በወጡት በርካታ ጋዜጠኞች ዙሪያ የአዲስ አድማስ  ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር ዲኤታ አቶ እውነቱ ብላታን  ሰሞኑን በፅ/ቤታቸው አነጋግሯቸዋል፡፡

ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተዘጋጀው ስልጠና ዓላማ ምንድን ነው?
የስልጠናው ዋና ዓላማ፣ አንደኛ በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በተቀላጠፈ መልኩ ማስቀጠል ነው፡፡ ሁለተኛ ሃገሪቱ በምትከተለው የልማት ስትራቴጂ ዙሪያ እስካሁን የደረስንበት፣ እንዲሁም ከፊታችን የሚጠብቁን ተግዳሮቶችና ስራዎች ምን እንደሆኑ የጠራ ግንዛቤ ማስያዝ ነው፡፡ ሀገሪቱ ባለፉት 23 ዓመታት የተጓዘችባቸውን መንገዶች በተለይ ወጣቱ ትውልድ በደንብ እንዲያውቀውና የበኩሉን ሃገራዊ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጭምር ከየት ተነሳን ወዴት እየሄድን ነው የሚለውን ለማስጨበጥ ነው፡፡ ሌላው ሃገሪቱ እየተከተለች ባለችው ልማታዊና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ላይ ያሉ ክፍተቶች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ይቀረፋሉ? የመልካም አስተዳደር ትግላችን ምን ያህል ተጉዟል? ምንስ ይቀረዋል? በዚህ የመልካም አስተዳደር ጉዞ ውስጥ ከወጣቱና ከከተማው ህዝብ ምን ይጠበቃል? በአጠቃላይ ሃገሪቱ ለተያያዘቻቸው የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ወጣቱ ሚናውን መጫወት በሚችል መልኩ ግንዛቤ ለመስጠት ተፈልጎ ነው ስልጠናው እየተሰጠ ያለው፡፡ ይሄ ስልጠና ዘንድሮ የተጀመረ አይደለም፤ በየጊዜው በየትምህርት ተቋማቱ ሲሰጥ የቆየ ነው፡፡ የዚያው ቀጣይ ፕሮግራም ነው፡፡
ሥልጠናው በዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን ለመንግስት ሰራተኞችም የሚሰጥ ነው፡፡ በህዝባዊ አደረጃጀቶች ውይይቶች እየተካሄዱ፣መንግስት በ5 ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈፃፀም ላይ የደረሰባቸው የእድገት ደረጃዎች የነበሩት ውጤታማ ተሞክሮዎች ምን ነበሩ? ከዚህ ምን ተምረን ለቀጣዩ እቅድ እንዴት እንሰራለን? የሚለውንና በአጠቃላይ ትልልቅ በሆኑ አገራዊ አጀንዳዎችና በህዳሴው ጉዞ ላይ  የሰፊውን ህዝብ  ተሣትፎ ለማጠናከር ታስቦ እየተካሄደ ያለ ስልጠና ነው፡፡ አሁን በዩኒቨርስቲዎች ለነባር ተማሪዎች ሁለተኛ ዙር ስልጠና እየተሰጠ ነው ያለው፡፡ ዩኒቨርሲቲ ማለት ይህቺን አገር የሚረከበው ወጣቱ ሃይል የሚገኝበት ነው፡፡ ይሄ በእውቀት የተካነው ወጣቱ ሃይል፣ ነገ ወደ ስራ ሲሰማራ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችል ዘንድ በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ተፈልጐ ነው ስልጠናው  የሚካሄደው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ያለው የተማረ ሃይል ስለብዝሃነት፣ ስለመቻቻል፣ ስለመከባበር የጠራ ግንዛቤ እንዲኖረው ጭምር ነው ስልጠናው እየተሰጠ ያለው፡፡
ስልጠናው በተማሪዎቹ ፍቃደኝነት ሳይሆን በግዴታ ነው የሚካሄደው የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡  እውነት በግዴታ ነው ?
ስልጠናው ግዴታ አይደለም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወዶና ፈቅዶ የሚሳተፍበትና ግንዛቤ የሚያገኝበት ነው፡፡ ተማሪው በአጠቃላይ አገራዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ የሚወያይበት ስለሆነ በግዴታ ላይ የተመሠረተ ነው የሚያስብለው ነገር የለም፡፡ ስልጠናው በፍፁም በግዴታ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡
ተማሪዎች በስልጠናው ተሳትፈው ሠርተፊኬት ካልተሰጣቸው ለትምህርት መመዝገብ እንደማይችሉ ተነግሯቸዋል ይባላል፡፡ ይሄ ውሸት ነው ማለት ነው?
የአንድ ወይም የሁለት ሣምንት የተለመዱ ስልጠናዎች ይሠጣሉ፡፡ ማንኛውም ስልጠና ሲካሄድ ለማንኛውም ሠልጣኝ ሠርተፊኬት ይሰጣል፡፡ ስልጠናው ምን ያህል ገብቶታል ወይም የተሳትፎ ብቃቱ ምን ያህል ነው የሚለውን ለመመዘን አይደለም፡፡ እንኳንስ ለ15 ቀን በተከታታይ ሰፊ ስልጠና ተሰጥቶ ይቅርና ለሁለትና ሦስት ቀናት ስልጠናም ሠርተፊኬት ይሰጣል፡፡ ተማሪዎችም በትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ነው የተወያዩት፤ በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው መቻቻል፣ ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርአትን ተከትሎ መስራት ምን አንድምታ እንዳለው የሚዳስስ ሥልጠና ነው የወሰዱት፡፡ ትላልቅ አገራዊ አጀንዳ ላይ ለሠለጠነ አካል ሠርተፊኬት መስጠት አግባብ ነው፡፡ ሠርተፊኬቱ መሳተፉን ማረጋገጫ ነው፡፡ ከዚያ ውጭ የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ሠርተፊኬት መሰጠቱን እንደ ግዴታ ማሳያ ማድረግ ስህተት ነው፡፡ ማንም ተገዶ እንዲሰለጥን አይደረግም፡፡
የስልጠናው ውጤታማነትስ ምን ያህል ነው?
እኔም አሰልጣኝ ሆኜ ተሳትፌያለሁ፡፡ እንደውም አሁን ከመቱ መመለሴ ነው (ቃለምለልሱ የተደረገው ሃሙስ ከሰአት ነው) መጀመሪያ ላይ የተለያዩ ብዥታዎችን በማሠራጨት ስልጠናውን ለማደናቀፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህ የተነሣ ተማሪውም ዘንድ በግንዛቤ ማጣት ከውጭ በሚነዙ አሉባልታዎች የመነዳት ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ችግሮች የመጀመሪያዎቹ ቀናት አካባቢ ድረስ ብቻ ነው የዘለቁት፡፡ የስልጠናውን ጠቃሚነትና አስፈላጊነት ከተረዳና ጥቅሙ ለራሱ፣ ለማህበረሰቡና ትምህርት ቤት ለላኩት ወላጆቹ መሆኑን ከተገነዘበ በኋላ ግን ስልጠናውን በፍላጎትና በተነቃቃ ስሜት ነው የተሳተፈው፡፡
 ከአንዳንድ ወገኖች ስልጠናውን የማደናቀፍ ተልዕኮ ተቀብለው ወደ ስልጠናው የገቡት እንኳ መጨረሻ ላይ ራሳቸውን አጋልጠው “ይሄ የኔ ሃሳብ አይደለም፣ ይሄን ስልጠና ማዘግየታችሁ እኛን ለብዥታ እንድንጋለጥ አድርጐናል” ብለዋል፡፡ በስልጠናው ላይ መልካም መልካም ነገሮች  ብቻ አይደለም የቀረቡት፤የአገሪቱ ተግዳሮቶችና ማነቆዋች በሙሉ ተነስተዋል፡፡ በአፈፃፀም ሂደት የነበሩ ጉድለቶች፣ የስርአቱም ሆነ የዚህች አገር አደጋዎችና የአደጋ ስጋቶች ምን ምን እንደሆኑ ጎልተው ወጥተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ሁሉም ነገር ሳይደበቅ ግልጽ በሆነ አካሄድ ነው ስልጠናው የተሰጠው፡፡ እንደውም ወደ መጨረሻ ላይ ተማሪዎቹ በፍቅር እየወደዱት መጥተዋል፡፡
 እናም ውጤታማና በድል የተጠናቀቀ ስልጠና ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አሠልጣኝም አስተባባሪም ስለነበርኩ በዚህ ረገድ ያየሁትን በሚገባ መመስከር እችላለሁ፡፡ ሌሎች አካባቢ ስለተደረጉት ስልጠናዎች አንደኛው ዙር ከተፈፀመ በኋላ ግምገማ ተካሂዷል፡፡ አፈፃፀማችን እንዴት ነበር? በቀጣይ የነበሩትን ጉድለቶች እንዴት እናስተካክል? የሚል አጠቃላይ ግምገማ ስለተካሄደ ውጤታማና ከጠበቅነው በላይ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ከተማሪዎቹም ዘንድ ሥልጠናው በአመት አንድ ጊዜ ቢካሄድ-- የሚል ሃሳብ ሲቀርብ ስለነበር እጅግ ውጤታማ የሆነ ስልጠና ነው፡፡
ኢህአዴግ የመንግስት ሃብትና ገንዘብን ለራሱ ርእዮተ ዓለም ማስፈፀሚያ እያዋለ ነው የሚል ትችት ይሰነዘራል፡፡ በዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
በመጀመሪያ መንግስት ይሄን ስልጠና የማከናወን ሙሉ መብትና ነፃነት አለው፡፡ አሁን ፓርቲውን በዚህ ለመክሰስ ተፈልጐ ከሆነ፣ ፓርቲው በምርጫ አሸንፎ ስልጣን ላይ እስከሆነ ድረስ በመንግስት የሚሠራው አሸናፊው ፓርቲ የቀረፃቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ናቸው፡፡ እነዚህ የፓርቲው ፖሊሲዎች ከምርጫ በኋላ ወደ ስልጣን ሲመጣ፣ አገራዊ ፖሊሲ ሆነዋል፡፡ አገራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂውን ደግሞ መንግስት በመላ አገሪቱ የማስፈፀም ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ አስታኮ ገዥውን ፓርቲ ለመክሰስ የሚደረገው ጥረት ውሃ አይቋጥርም፤ምክንያቱም የአገሪቱን ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚያስፈጽመው ፓርቲው ነው፡፡
 አሁን የተሰጠውና እየተሰጠ ያለው ስልጠና በመንግስት እንጂ በፓርቲው አይደለም፡፡ ስለዚህ የሀገሪቱን የአቅም ግንባታ፣ መሠረተ ልማት፣ የአዕምሮ ግንባታንም ጭምር የመስራት ሙሉ ነፃነትና መብት ያለው መንግስት ነው፡፡ ይሄ አንዱ የአቅም ግንባታችን አካል ነው፡፡ የአቅም ግንባታው የሚሰጠው ደሞዝ ተከፋይ ለሆነውና በመንግስት ስልጣን ላይ ላለው ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለአርሶ አደራችን፣ ለተማሪዎችና ለተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ ይህ የአቅም ግንባታ እንጂ የርዕዮተ ዓለም ማስረጫ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ስለአገሪቱ እጣ ፈንታ የማወቅና የመወሰን ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የማድረግ ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ታሪካዊ ሃላፊነት ነው፡፡ ህገ-መንግስታዊ ግዴታውም ነው፡፡ መንግስታዊ ሃላፊነትንና ግዴታን የመወጣት ጉዳይ ነው፡፡
ስልጠናው መጀመሪያ የታቀደ ሳይሆን ድንገት የመጣ አጣዳፊ ፕሮግራም ነው፤ እንደውም የግንቦቱን ምርጫ ታሳቢ ያደረገ ነው፤ የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይሄ የተለመደ ነው፡፡ ታስታውሱ እንደሆነ የህዳሴው ግድብ ራሱ ለምርጫ ተብሎ እንጂ የታሰበበት አይደለም ሲባል ነበር፡፡ ነገር ግን የሚሠራውን የሚያስበው በስራው ላይ ያለው አካል ነው፡፡ ከዚያ ውጭ ያለው አካል ከመሬት ተነስቶ የታሰበበት አይደለም፤ መታሰቡንም አላውቅም ብሎ ሊበይን አይችልም፡፡ እነዚህ ወገኖች በመንግስት ውስጥ እስካልሆኑ ድረስ የታሰበውን ነገር ሁሉ አስቀድመው የሚያውቁበት እድል ሊኖር አይችልም፤ነቢያቶች እስካልሆኑ ድረስ፡፡
 ስለዚህ ስልጠናው በመንግስት እቅድ ውስጥ የነበረ እንጂ በዱብ እዳ የተሠራ አይደለም፡፡ ከምርጫ ጋርም የሚያቆራኘው ምንም ጉዳይ የለም፡፡ “ኢህአዴግን ብቻ ምረጡ” የሚል አረፍተ ነገር በአንዲት ቦታ ተብሎ ከሆነ፣ ይሄን በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ ይቻላል፤ ነገር ግን እንዲህ የተባለበት ቦታ የለም፡፡ ከምርጫ ጋር ፈጽሞ ሊያያዝ አይገባም፡፡ ይሄ ጉዳይ ከአንድ ዙር ምርጫ በላይ የዘለለ ነው፡፡ ስለ አገር ህልውና፣ በቀጣይ አገሪቱን ስለሚረከብ ዜጋ ጉዳይ ነው፡፡
 ስለ አገሪቷ እጣ ፈንታ ቀጣዩ ትውልድ እንዲገነዘብ የማድረግ ጉዳይ ነው፡፡ ትውልድን የመቅረጽ ጉዳይ ነው፡፡
 እነዚህ ነገሮች የተለመዱ ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት የስነ ዜጋ ትምህርት ሲጀመር ኢህአዴጋዊ ለማድረግ ነው ሲባል ነበር፤ስለዚህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ይልቁንም “ይሄ ነገር ለአገር በጐ ከማሰብ የተደረገ ነው” ቢባል ኖሮ ነበር በጣም የሚገርመው፡፡ የአሁኑ ግን የተለመደና መሠረተ ቢስ እንደሆነ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡
ከስልጠናው ምን ተገኘ? ወደፊትስ ምን  ታቅዷል  
በዩኒቨርስቲዎቹ ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል ግብአት አግኝተናል፡፡ በቀጣይም ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች፣ ለመምህራንና ለአስተዳደር አካላት የአስር ቀናት ስልጠና ይሠጣል፡፡
በቅርቡ ከአገር የተሰደዱ ጋዜጠኞች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ እንዳቀረቡ ሰምቼአለሁ---
አዎ አቅርበናል፡፡
በምን መልኩ ነው ጥሪው የቀረበው?
በጋዜጠኞች ስልጠና ላይ የመክፈቻ ንግግር ሳደርግ አንዱ ያነሳሁት ጉዳይ ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፍትህ ሚኒስቴር ከተከሰሱ 5 መጽሔቶችና 1 ጋዜጣ ጋር በተገናኘ የተሰደዱ ጋዜጠኞች አሉ የሚል ነገር በየቦታው ይወራል፡፡ እነዚህ ጋዜጠኞች በክሱ ተደናብረው ከሃገር ኮብልለው ከሆነ፤ እነሱን ሊያስጠይቅ የሚችል ነገር ስለሌለ መኮብለላቸው አግባብ አይደለም፡፡ ብዥታው አግባብነት ስለሌለው በአስቸኳይ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ስራቸውን እንዲቀጥሉ ነው ጥሪ ያስተላለፍነው፡፡
አሁንም ደግሜ የምለው፤ ጋዜጠኞቹ ከአገር የወጡት በጋዜጣውና መጽሔቶቹ ክስ ምክንያት ከሆነ፣አግባብ ስላልሆነ  ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ስራቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

Read 5048 times