Saturday, 31 December 2011 11:44

2012 የእግር ኳሱ ዓለም ምን ይዞ ይመጣል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ2012 በምርጥ ችሎታና ወጣት ተጨዋቾች የተገነባው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በዩሮ 2012 ላይ የስፔንን የበላይነት እንደሚያቆም፤ በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፣ በቻይና እና በአሜሪካ ሜጀር ሶከር ሊግ ያሉ ክለቦች በፋይናንስ አቅማቸው መጠናከር መቀጠላቸው፤ በኢኳቶርያል ጊኒና ጋቦን አዘጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በርካታ ሃያላን ብሄራዊቡድኖች የማይሳተፉበትን ሁኔታ በመጠቀም ጋና ድል እንደምታደርግ ይጠበቃል፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአውሮፓና በዓለም ታላላቅ የእግር ኳስ ውድድሮች ዋንጫዎችን የሚያነሱ የተለመዱ ፊቶች ከካታላኑ ክለብ ባርሴሎናና ከዚያወ ስፔን አገር የወጡ ተጨዋቾች መሆናቸው በ2012ም እንደሚቀጥል ግምቶች ቢኖሩም ይሄው ሃያልነት ሊያበቃ እንደሚችልም ግምቶች እየተሰጡ ናቸው፡፡በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 70ኛ ዓመት እድሜያቸውን በ2011 የመጨረሻ ቀን የሚያከብሩት ፈርጉሰን የሊጉን ሻምፒዮናነት ክብራቸውን በማስጠበቅ 20ኛውን የሊጉን ድል ያስመዘግባሉ የሚል ግምት አለ፡፡ ይህን ህልማቸውን ለማሳካት ግን በተለይ ከከተማው ተቀናቃኛቸው ማን ሲቲ አሰልጣኝ ሮበርቶ ማንቺኒና ከቼልሲው አንድሬስ ቦአስ የሚገጥማቸው ፉክክር ፈተና ይሆንባቸዋል፡፡የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና 2011ን በሶስት የዋንጫ ድሎች ቢያጠናቅቅም በ2012 በተለይ በላሊጋው ሻምፒዮናነት ለሚኖረው ድል አድራጊነት ከሪያል ማድሪድ የሚጠብቀው ትንቅንቅም ትኩረት ይስባል፡፡በ2012 ከሚጠበቁ የእግር ኳስ አበይት ውድድሮች ዋንኛው በዩክሬንና ፖላንድ አዘጋጅነት የሚደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ሲሆን በዚሁ ታላቅ ሻምፒዮና ላይ የሃያሉን ስፔን ብሄራዊ ቡድን ለ3 አመት የዘለቀ የበላይነት የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ሊያቆም እንደሚችልም ግምት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በ2011 የፊፋን የእግር ኳስ ደረጃ በ1ኛነት ያጠናቀቀው የሆላንድ ብሄራዊ ቡድንን በዩሮ 2012 ስኬታማ የመሆን እድል ካላቸው ብሄራዊ ቡድኖች ተርታ ግንባር ቀደም ሆኖ ይሰለፋል፡፡ከአውሮፓ ሊጎች በተለይ የፈረንሳዩ ሊግ 1 ከ20 እና 30 ዓመታት በፊት የነበረውን ከፍተኛ የፉክክር ደረጃውን በማሻሻል ምርጥ ተጨዋቾችን ከዓለም ዙርያ እንደሚማርክም እየተገለፀ ነው፡፡ከፈረንሳይ ህዝብ 12 በመቶው ይደግፈዋል የሚባለው ፒኤስጂ በኳታሪ ኢንቨስትመንት አውቶሪቲ 70 በመቶ ባለቤትነቱ ከተያዘ በኋላ በአውሮፓ የክለብ እግር ኳስ እየመጣ ያለው አዲስ ሃይል ተብሏል፡፡ ፒኤስጂ በኳታር ኢነቨስትመንት አውቶሪቲ ከተያዘ በሃላ የብሮድካስት ኩባንያው አልጀዚራ የሊግ 1 ጨዋታዎችን በ90 ሚሊዮን ዩሮ ዓመታዊ የስፖንሰርሺፕ ውል ሊያስተላልፍ መወሰኑና የአገሪቱ ክለቦች በሻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርጉትን ግጥሚያ በአመት 60 ሚሊዮን ዩሮ በመክፈል ሊያሰራጭ መወሰኑ የፈረንሳይ ክለቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ይሆናል፡፡በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ከወር በኋላ በ16 ክለቦች በሚቀጥለው የጥሎ ማለፍ ምእራፍ ማን እንደሚሳካላት ለመገመት ቢያስቸግርም ሁለቱ የስፔን ክለቦች ባርሴሎናና ሪያል ማድሪድ እንዲሁም የጀርመኑ ባየር ሙኒክ ለዋንጫው ድል የተሻለ ግምት በመያዝ አዲሱን አመት ይጀምሩታል፡፡ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ለግ በተከታታይ ሁለት አመታት የዋንጫ ድል የሚያስመዘግብ ክለብ በታሪክ አለማጋጠሙ የባርሴሎናን ድል አድራጊነት ሲያደበዝዝዘው ሪያል ማድሪድ በሞውሪንሆ ስር 10ኛው የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድል በመቀዳጀት የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰኑን በ2012 ሊያስመዘግብ እንደሚችል በስፋት የሚተነበይ ሆኗል፡፡

 

 

Read 3124 times Last modified on Saturday, 31 December 2011 11:49