Saturday, 27 September 2014 08:52

የሣሙኤል ዘሚካኤልን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠት ተቀጠረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

           “ዶክተር ኢንጅነር ነኝ” በማለት አጭበርብሯል የተባለው ሣሙኤል ዘሚካኤል፤ ያቀረበውን የዋስትና ጥያቄ ፍ/ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፡፡ ከጠበቃው ጋር በክሱ ዙርያ ለመወያየት በቂ ጊዜ አለማግኘቱን ጉዳዩን ለሚመለከተው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ከትላንት በስቲያ ያመለከተው ተጠርታሪው፤ እስከዚው ድረስ ዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ጠይቋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ ተከሳሹ በተደራራቢ ወንጀሎች መከሰሱን፣ በኢንተርፖል ከውጭ ተይዞ መምጣቱንና ከዚህ በፊት በቼክ ማጭበርበር ተከሶ መቀጣቱን ጠቁሞ የዋስትና ጥያቄውን ተቃውሟል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሳሽን የዋስትና ጥያቄ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 5 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በ35 ዓመቱ ሳሙኤል ዘሚካኤል ላይ አቃቤ ህግ ሶስት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን የመጀመሪያው ክስ በሃሰተኛ ስምና ሰነድ ሰዎችን አጭበርብሯል የሚል ነው፡፡ በዚህ ድርጊቱም የአምባሳደር ልብስ ስፌት ድርጅት ባለቤት አቶ ሰኢድ መሃመድን፣ ከ20 በላይ ታዋቂ ሰዎችን የህይወት ታሪክ የያዘ መፅሃፍ አሳትማለሁ በማለት 58ሺህ ብር መቀበሉን እንዲሁም የ6ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው አራት ሙሉ ልብሶች መውሰዱ ተጠቅሷል፡፡ ለወሰዳቸው ሙሉ ልብሶች ክፍያ የሚሆን ገንዘብ እንዲወስዱ ለንግድ ባንክ ቦሌ ቅርንጫፍ ቼክ ቢፅፍም በሂሳብ ደብተሩ ምንም ገንዘብ አልነበረም ተብሏል፡፡ በዚህም በደረቅ ቼክ ማጭበርበር ሁለተኛ ክስ ቀርቦበታል፡፡ ሌላኛው ክስ ደግሞ ባልታደሰ ንግድ ፍቃድና በተጭበረበረ የእጅ ፅሁፍ በተዘጋጀ ሰነድ ከንግድ ባንክ ቦሌ ቅርንጫፍ ብድር ሲጠይቅ በመገኘቱ በተጭበረበረ የንግድ ፍቃድና ሃሰተኛ ሰነድ መገልገል ወንጀል ክስ ቀርቦበታል፡፡

Read 2938 times