Saturday, 20 September 2014 10:50

ከአዙሪት ያልወጣው የግል ትምህርት ቤቶች ጉዳይ

Written by  በተካልኝ ከድር (taklignkm@gmail.com)
Rate this item
(2 votes)

             በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ት/ቤቶች የተጋነነ የትምህርት ክፍያ ይጠይቃሉ የሚል አቤቱታ ያልቀረበባቸው ጊዜ የለም፡፡ በቅርቡ ግን መንግስትም ጭምር ለችግሩ ትኩረት የሰጠው ይመስላል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን የመነጋገርያ አጀንዳም ሆኖ ሰንብቷል፡፡ እኔም ብዕሬን ያነሳሁት ይሄንን ርዕሰ ጉዳይ በተመለከተ ሃሳቤን ለመግለፅ ነው፡፡ ትምህርትን የማዳረስ ተግባር ትምህርት ለሀገራቸው ህዝብ በማዳረስ ረገድ መንግስታት ሊኖራቸው የሚገባውን የተሳትፎ ወሰን በመግለጽ በቀዳሚነት ሊወሳ የሚችለው እ.ኤ.አ በ1990 በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የማህበራዊና የባህል ምክር ቤት /UNESCO/ አማካኝነት የወጣው ትምህርት ለሁሉም አለማቀፍ መግለጫ /World Declaration on Education for All/ ነው፡፡ ሰነዱ 10 አንቀጾች ሲኖሩት፣ ሁሉም አንቀጾች መንግስታት በተለይ መሰረታዊ ትምህርት /Basic education/ በማዳረስ በኩል ሊኖራቸው የሚገባውን ሚናና የተግባር አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ሰነድ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት፤ ሀገራት መሰረታዊ ትምህርትን በእኩል ለማዳረስ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ማለትም በራሳቸው ከፍለው መማር ለማይችሉ የህብረተሰቡ ክፍሎች፡- ለድሆች፣ ለጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት፣ ለገጠሩ ህብረተሰብ፣ ለአርብቶ አደሮች፣ ለስደተኞች ወዘተ… ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ቁርጠኛ አቋም ሊኖራቸው እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ይህን የትምህርት ተግባራት ለማስፈፀም የሚያስፈልገውን ሀብት በተመለከተ ከመንግስት በተጨማሪ የግሉ ዘርፍና ለጋሾች ያላቸውን ገንዘብና የሰው ኃይል በማንቀሳቀስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡ እንደ ዓለም አቀፍ የትምህርት ደረጃ ምደባ /The International Standard Classification of Education/ መሰረት መሰረታዊ ትምህርት፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትንና የሁለተኛ ደረጃ የአንደኛ ሳይክል ትምህርትን ያጠቃልላል፡፡ በታዳጊ ሀገሮች ደግሞ ከዚህም አልፎ የአፀደ ህፃናትና የጎልማሶች መሰረተ ትምህርትንም ያካትታል፡፡ ትምህርትን የሰብዓዊ መብት አካል አድርጎ የሚያወሳው ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ /Universal Declaration of Human Right/ በበኩሉ፤ ትምህርት የሰው ልጆች መብት እንደሆነና መንግስታት ደረጃ በደረጃ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በነፃ ማዳረስ እንደሚገባቸው፣ ዜጎችም የመማር ግዴታ እንዳለባቸው ያመለክታል፡፡ በአገራችን ህገ-መንግስት አንቀጽ 41 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ደግሞ መንግስት ለትምህርት የሚያስፈልገውን ሀብት እንደሚመድብ ጠቅለል ባለ አገላለጽ ሰፍሯል፡፡ በሌላ በኩል ከሕገ-መንግስቱ ቀደም ብሎ በወጣው የሀገሪቱ አጠቃላይ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ላይም ዘርዘር ባለ መልኩ ተገልጿል፡፡ ትምህርትን ማስፋፋት በተለይም መሰረታዊ ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ እንደ አንዱ የፖሊሲው ዓላማ የተወሰደ ጉዳይ ነው፡፡

ጎልተው የወጡ የግል ት/ቤቶች ውጫዊ እና ውስጣዊ ችግሮች ከግል ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ያለው ውጫዊ ችግር (“ውጫዊ ችግር” ከወላጆችና ከመንግስት አንጻር ያለውን ችግር ሲያመለክት፣ “ውስጣዊ ችግር” ከግል ትምህርት ቤቶቹ አንጻር ያለውን ችግር ያመለክታል) ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆች አቅም አንጻር ከፍተኛ የትምህርት ክፍያ እያስከፈሉ ነው መባሉ ነው፡፡ ዋነኛው ውጫዊ ችግር ከፍተኛ ክፍያ መጠየቃቸው ቢሆንም ትምህርት ቤቶቹ ለዚህ የዳረጋቸው አስገዳጅ ውስጣዊ ችግር ወይም ምክንያት መታወቅ (መለየት) ያለበት ይመስለኛል፡፡ ከዚህ አንጻር በትምህርት ቤቶቹ በኩል በተደጋጋሚ እየቀረበ ያለው ምክንያት የሚያስተምሩበትና የሚሰሩበት የቤት ኪራይ፣ ለትምህርቱ ማስኬጃ፣ ለሰራተኞችና መምህራን ክፍያ የሚያወጡት ወጪ እየጨመረ መምጣት ነው፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ የትምህርት ቤቶቹ የትምህርት ክፍያ ጭማሪ ብቸኛ ምክንያት ከፍተኛ ትርፍ የመሰብሰብ ዓላማ እንደሆነ ገልጿል፡፡ ለመሆኑ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃ አለው? ለማንኛውም ከፍተኛ ክፍያው በትምህርት ቤቶቹ ወጪ መጨመር የተከሰተ ይሁን ወይም በከፍተኛ ትርፍ ፍለጋ በቅጡ ለይቶ ማወቅ ይገባዋል፡፡ አንድ ነገር ግን ግልፅ ነው፡፡ በት/ቤቶቹ የተጠቀሱት ችግሮች ሐሰት ናቸው የሚባሉ አይደሉም፡፡ የቤት ጉዳይ የከተማዋ ዋነኛ ችግር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

የግል ት/ቤቶችም በየጊዜው እየናረ የመጣው የቤት ኪራይ ዋጋ ሰለባ ከመሆን አይድኑም፡፡ እናም የትምህርት ክፍያ ጭማሪው በከፊል የቤት ኪራይ መናር ያመጣው ነው ቢባል ያሳምናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትምህርት ቤቶቹ በአብዛኛው ለመማር ማስተማር ሂደት የሚያስፈልጉትን መስፈርቶች (standards) ያላሟሉ እንደሆኑ ይነገራል፡፡ ትምህርት ቤቶች ከግለሰቦች በተከራዩዋቸው ጠባብ ግቢ ውስጥ ህፃናቱ ከወረቀትና ከጥቁር ሰሌዳ ጋር ሲፋጠጡ ውለው፣ ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ የሚል አቤቱታም አለ፡፡ “ህፃናቱ የሚቦርቁበትና የሚሯሯጡበት ሜዳ የለም” ለማለት ነው፡፡ ምናልባት ያንን የምናገኘው በአዋጆች፣ በደንቦችና በመመሪያዎች ላይ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይሄም አንዱ የግል ት/ቤቶች ተግዳሮት ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የመንግስት አካላት ተሳትፎ የግል ት/ቤቶች ከፍተኛ የትምህርት ክፍያን በተመለከተ ከመንግስት ወገን ጉዳዩ ያገባናል ብለው የተንቀሳቀሱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ እና የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ችግሩን ለመቅረፍ በዋናነት ትኩረት ያደረጉት ደግሞ “ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ክፍያ ያስከፍላሉ” በሚለው ውጫዊ ችግር ላይ ብቻ ነው፡፡

በገሃድ እንደተመለከትነውም ችግሩን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ፡- 1ኛ/ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የትምህርት ቤቶቹ ክፍያ የተጋነነና አግባብ አለመሆኑን በመንገርና በማስነገር ጫና (Lobby) ማድረግ፣ 2ኛ/ በክፍያው መጠን ላይ በወላጆችና በትምህርት ቤቶቹ መካከል ድርድር እንዲደረግ መግፋት፣ 3ኛ/ከፍተኛ የክፍያ ጭማሪ ባደረጉ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ምርመራ ማድረግ ናቸው፡፡ እነዚህ አካሄዶች በዋናነት ያተኮሩት ክፍያው ላይ እንጂ ለችግሩ መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ላይ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ግልፅ ሊሆን የሚገባው፣ መንስኤዎቹ ሳይፈተሹ ከፍተኛ ነው በተባለው ክፍያ ላይ ትምህርት ቤቶቹ ቅናሽ እንዲደርጉ ቢገደዱም እንኳን በመማር ማስተማሩ ሂደት ያሉትን ችግሮች ከመሰረቱ ሊቀርፈው የሚችል እውነተኛ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ ሌላው ጥያቄ ደግሞ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፤ የትምህርት ጉዳይ ላይ እጁን ማስገባት ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ባለስልጣኑ የሀገሪቱን የነፃ ኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረት ያደረገ አመቺነት ያለው ነፃ የንግድ የገበያ ውድድር ሥርዓት እንዲፈጠር የሚያስችሉ ስራዎችን ብቻ እንዲሰራ ገደብ የተበጀለት እንደሆነየተቋቋመበት አዋጅ በግልጽ ያመለክታል፡፡ የባለስልጣኑ ተግባራት ለገበያ ውድድር ከተተዉ የግል ዕቃዎችና አገልግሎቶች /private goods & Services/ ንግድና ዝውውር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ትምህርት ግን እንደግል ሸቀጥ /private goods/ ንግድና ዝውውር የሚቆጠር አይደለም፡፡

በተለይ የትምህርቱ ዓይነት መሰረታዊ ትምህርት (Basic Education) ሲሆን ደግሞ የገበያ ውድድር የሚለው ጉዳይ ጨርሶ የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ይህን ስንመለከት ባለስልጣኑ በማይመለከተው ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እየሰራ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ከዚህም አልፎ “ሕግን ተላልፈሃል” በሚል ምርመራ የማድረግ፣ እርምትና ቅጣትን የመጣል ሁሉ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይሄም በራሱ ተገቢነቱ ሊፈተሽና መፍትሄ ሊበጅለት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ እንደማጠቃለያ በአብዛኛው እነዚህ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩት ትምህርት መሰረታዊ ትምህርት (Basic Education) ተብለው በተፈረጁት ውስጥ የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡ የመሰረታዊ ትምህርት ባለቤት ደግሞ መንግስት ነው፡፡ ከመንግስት ውጭ ያሉት የግሉ ዘርፍም ሆነ ሌሎች አካላት መሰረታዊ ትምህርትን በማስፈጸምና በማዳረስ የመንግስት አጋዥ እንጂ ባለቤቶች አይደሉም፡፡ መንግስት አጋዦቼ ናቸው ብሎ በጋራ እንስራ ለማለት ወይም አታስፈልጉኝም፤ በራሴ እወጣዋለሁ ሊል ይችላል፡፡ ይህን ለማለት የሚችለው ግን አገሪቱ ትምህርትን ለማዳረስ በቂ አቅም ሲኖራት ብቻ ነው፡፡ እውነታው ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ነው፡፡ አገሪቱና መንግስት ይሄ አቅም የላቸውም፡፡ ከዚህ አንፃር መንግስት ኢምንትም ቢሆን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ የግል ትምህርት ቤቶችን አልፈልጋቸውም ብሎ ከዘርፉ እንዲወጡ ሊያደርግ አይችልም፡፡ እንዲኖሩ መፍቀድ ብቻውን ግን በቂ አይደለም፡፡ መንግስት በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት፣ በጎ አስተዋጽኦዋቸውን ለማጎልበት የሚያበቁ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከእነዚህ የመንግስት እንቅስቃሴዎች አንዱ ለዘርፉ ድጎማ (subsidy) ማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ድጎማው የግድ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሆን አይጠበቅም፡፡

ድጎማው፣ ከመንግስት አንጻር ሲታይ ትምህርቱን ለማዳረስ ሊያወጣ ከሚያስበው ወጪ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የሚቀንስለት፣ ከትምህርት ቤቶቹ አንፃር ደግሞ መሰረታዊ ውስጣዊ ችግራቸውን ለመቅረፍ የሚያስችላቸው ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር መንግስት የመሬት አቅርቦትና የታክስ ቅነሳ (ድጎማ) ማድረግን እንደ አንድ አማራጭ አይቶ መፈተሽ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ ከዚህ የተሻለ አማራጭ አለ ከተባለም እሰየው ነው፡፡ ነገር ግን የችግሩን መንስኤ ለመመርመር ሳይሞክሩ በቅርቡ እንደታየው የግል ት/ቤቶች የሚያስከፍሉትን ከፍተኛ ክፍያ በማስቀነስ ላይ ብቻ መረባረብ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ እንዳያባብሰው ያሰጋል፡፡ የግል ት/ቤቶች በሃይልና በጫና ክፍያቸውን እንዲቀንሱ ቢደረግ ለጊዜው ህብረተሰቡ እፎይ ሊል ይችል ይሆናል፡፡ ት/ቤቶቹ ግን ወጪያቸውን መቋቋም እያቃታቸው ከአገልግሎት ውጪ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላ ጥፋት ይሆናል፡፡

Read 2781 times