Saturday, 20 September 2014 10:34

ከባህር ወጥታ ጤዛ ላሰች

Written by 
Rate this item
(8 votes)

(በባር ወጣችም አወናሰችም) - የጉራጌ ተረት

          ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት በባልትናባለሙያ ነኝ የሚሉ ወይዘሮ በአንድ ከተማ ይኖሩ ነበረ ይባላል፡፡ አንድ ቀን “ዛሬ የምሠራው ገንፎ ነው፡፡ ጐረቤት ሁሉ ይጠራ” ብለው አዘዙ፡፡ ጐረቤቱ ሁሉ ተጠራና የገንፎው ግብዣ ተጧጧፈ፡፡ የዱሮ ጊዜ የገንፎ አበላል እንደዛሬ በማንኪያ አልነበረም፡፡ ሁሉም እጁን ታጥቦ ክብ ክብ ሠርቶ የሚችለውን ያህል መጉረስ ነው፡፡ ሴትዮዋ ባለሙያነታቸውን ደጋግመው እየተናገሩ እየፎከሩ፤ “ብሉ እንጂ ጐረስ ጐረስ ነው እንጂ!” እያሉ ያበረታታሉ፡፡ በየክቡ እየዞሩ፤ “እህስ እንዴት ነው ገንፎዬ” ይላሉ፡፡

እንደ ዕውነቱ ከሆነ ገንፎው በጣም ቀጥፎ፣ እጅግ ላቁጦ ጣት ላይ የሚጣበቅ ነው፡፡ አንደኛ ጐረቤት “እንዴ ድንቅ ነው፤ የእርሶ ሙያ ምን ይጠረጠራል” አለ ወደ ሁለተኛው ቀርበው “እህስ ገንፎዬ እንዴት ነው?” ሁለተኛ ጐረቤት - “አይ እጅ! እንዲህ ያለ ሙያ ከየትም አይገኝ!” ሴትዮዋ የበለጠ እየተኩራሩ ወደ ሶስተኛው ዞሩ፤ “እህስ ገንፎዬን እንዴት አገኘኸው?” ይሉታል፡፡ እሱም እንደሌሎቹ የድርሻውን ውዳሴ በመስጠት፤ “ገንፎ ከበሉ አይቀር ይሄን ዓይነቱን ነው! እንደው እንዴት አርገው ቢያገነፉት ነው እሜቴ እንዲህ ያማረልዎ?” ይላል፡፡ በመጨረሻ ወደ አንድ ውሸት የማይወድ አንደበተ - ቀና፣ ቁምነገረኛ ሰው ዘንድ መጥተው፤ “እህስ ወዳጄ ገንፎዬ እንዴት ነው?” ሰውዬው ዝም አለ፡፡ “ምነው ዝም አልክ? አልጣፈጠህም እንዴ?” ብለው አጠንክረው ጠየቁት፡፡ ሁሉ ሰው የሰውዬውን መልስ ይጠብቃል፡፡ ሰውዬው ጉሮሮውን አጠራና፤ “ኧረ እሜቴ፤ እንደው መጣፈጡ ቀርቶ እጄን በለቀቀኝ!” አላቸው፡፡

                                            ***

“ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር” እጅግ ወሳኝ ነው፡፡አገር ያድናል፡፡ ህዝብን ከግርታ ያወጣል፡፡ በአንፃሩ መሸነጋገል ከቶም የአገር ጠር ነው፡፡ በይሉኝታም ይሁን በፍርሀት፣ አውቀን በድፍረትም ይሁን ሳናውቅ በስህተት፤ መሸነጋገልና መወዳደስ፤ “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” ነው፡፡ በትክክል ያልሰራነውን ሠርተሃል ተብለን አደባባይ ወጥተን መፎከር ኋላ ደብቁኝ ደብቁኝን ያመጣል፡፡ እንደ እሜቴ ገንፎ ነውና! ለረዥም ዘመን በታዋቂ - ተደናቂነት፣ አሊያም በሥልጣን መከታ፤ ሲሸነግሏቸው እየተኩራሩ የኖሩ አያሌ ናቸው፡፡ “እናቷ መራቂ ልጅቷ አሜን ባይ” እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡ (Yes-men of Athens እንዲሉ ፈረንጆች) ዛሬም ዕውነተኛውን ዲሞክራሲ ከሐሳዊው ዲሞክራሲ መለየት አለብን፡፡ ሀቀኛውን ፍትሕ ከአስመሳዩ ፍትሕ አጥርተን መጓዝ አለብን፡፡

መልካም አስተዳደርን ከብልሹው አስተዳደር ነጥለን ዕቅጩን መናገር አለብን፡፡ በአደባባይ ስለ ፀረ ሙስና እየተናገርን ዙሪያ መለስ የሙስና አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን ከሆነ ጉዱ መለየት አለበት፡፡ በምንንቀሳቀስበት የሥራ ሂደት ውስጥ ሁሉ “የነካነው ሁሉ ወርቅ ይሆናል” ብለን ደርሶ ሚዳስ እንሁን ብንል፣ ውሎ አድሮ የምንጋለጥበት ሰዓት ስለሚመጣ እያንዳንዷን እርምጃችንን በጥንቃቄ ብንመዝን ይሻላል፡፡ ዕውነቱን በትክክል ተናግሮ የወደፊት መንገድን አርሞ መጓዝ እንጂ መገበዝ ወንዝ አያሻግርም፡፡ ኢኮኖሚው እጅግ ያዘቀዘቀው ህዝብ “እንኳን እናቴ ሞታ እንደውም አልቅስ አልቅስ ይለኛል” እያለ መሆኑን እንገንዘብ፡፡ አገር ያለህዝብ ድጋፍ ወደፊት አትራመድም፡፡

ህዝብን አክብሮ፣ ያለ አንዳች ሽንገላ መታደጊያውን ሰዓት እንወቅ፡፡ ህዝብ አብሮ ለመጓዝ ዝግጁነቱን ያሳየበትን ወቅት በትክክል ለይቶ መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ ቸገረኝ ሲል እህ ብሎ ማዳመጥ ትክክለኛ የአመራር መርህ ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ብሶትንም ሆነ ፖለቲካዊ እሮሮን ሰምቶ በአመቸው መንገድ ሁሉ መፍትሔ መስጠት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው፡፡ ወቅቱን ያላወቀ ወይም ያልተገነዘበ አካሄድ “ከባህር ወጥታ ጤዛ ላሰች” እንደተባለው ይሆናል፡፡ አሁንም አሁንም እናስተውል፡፡ 2007 ዓ.ም የማስተዋያ ዓመት ይሁንልን!

Read 4180 times