Saturday, 20 September 2014 10:25

በሳዑዲ በሽብርተኝነት የተከሰሰው ኢትዮጵያዊ የ5 አመት እስር ተፈረደበት

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   የሪያድ ልዩ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት፤ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል በሚል ክስ በተመሰረተባቸው አራት የሳኡዲ አረቢያ ዜጎችና በአንድ ኢትዮጵያዊ ላይ ከአንድ እስከ አምስት አመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት መጣሉን አረብ ኒውስ ዘገበ ፡፡ ስሙ ያልተገለጸው ኢትዮጵያዊና አራቱ ግብረ አበሮቹ፣ የቅዱስ ቁርአንን አስተምሮት በሚጥስ መልኩ ከሚንቀሳቀሱ የአገሪቱ ጽንፈኛ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ብጥብጥ ለማስነሳት ሞክረዋል፤ ሌሎችንም ለአመጽ አነሳስተዋል በሚል በቀረበባቸው ክስ፣ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው፣ ኢትዮጵያዊው የአምስት አመት እስራት ተፈርዶበታል፡፡ የእስር ጊዜውን ጨርሶ ከወጣ በኋላ ወደ አገሩ እንዲመለስ የተፈረደበት ኢትዮጵያዊው፣ ለሃጂና ኡምራ ጸሎት ካልሆነ በቀር፣ ከአሁን በኋላ ወደ አገሪቱ እንዳይገባም ተከልክሏል፡፡

ሁለቱ ግብረ አበሮቹ የአንድ አመት ከስድስት ወራት እስራትና ለሶስት አመታት የሚቆይ የጉዞ ገደብ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ የአንድ አመት እስራትና ለሶስት አመታት የሚቆይ የጉዞ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ተከሳሾቹ በ30 ቀናት ውስጥ ይግባኝ ማለት እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በተከሳሾቹ ላይ የተላለፈው ውሳኔ፣ ባለፉት ወራት ከተላለፉት መሰል ውሳኔዎች ጋር ሲነጻጸር ቀላል የሚባል መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ ከ10 በላይ በሆኑ ተጠርጣሪዎች ላይ እስከ እድሜ ልክ የሚደርስ ቅጣት መጣሉን አስታውሷል፡፡

Read 2344 times