Saturday, 13 September 2014 13:06

አድርባይነት የተጠናወተው የምሁሩ አስተያየት

Written by  ታምራት ደጀኔ (ከአዲስ አበባ)
Rate this item
(7 votes)

በኢቲቪ ዶክመንታሪ ላይ ለተሰነዘረ አስተያየት ምላሽ

     ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የወጣው አዲስ አድማስ፣ በ“ነፃ አስተያየት” አምዱ፣ “ያልተገሩ ብዕሮችን ለመግራት” በሚል ርዕስ መድሃኔ ግደይ የተባሉ የአምቦ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህር ከአንድ ወር በፊት ኢሬቴድ (ኢብኮ) በግል ፕሬሱ ላይ ለሚያዘጋጀው ዶክመንታሪ ለሰነዘሩት አስተያየት በማስተባበል ይሁን በአድርባይነት የሰጡትን ሃሳብ አስተናግዷል፡፡ እኔም ከሰነዘሩት ሃሳብ ተነስቼ፣ በባለሙያ ስም የተሸፈነውን አድርባይ አቋማቸውን እንዲያስተካክሉና አንባቢ ሚዛናዊ ፍርዱን እንዲሰጥ በማሰብ ምላሽ ልሰጥ ወደድኩ፡፡ 

መምህሩ በጋዜጣው ላይ በሰጡት “የእምነት ክህደት ቃል” ይሁን “ኑዛዜ” ልጀምር፡፡ “ብዙ ነገር የምትቆራርጡ ከሆነ ግን…”፣ “በግምት ለአርባ ደቂቃ የሰጠሁት ሃሳብ ተቆራርጦ ተጣለ”፣ “ያልተገሩ ብዕሮች የመግራት ስልጣን ለኢቲቪ ማን ሰጠው?” ይሉና ተመልሰው ኢቲቪ ፍሬም አውጥቶ መስራቱ ከሙያ አንጻር ትክክል ነው በማለት፣ ሁለት ቦታ ላይ የሚረግጥ ውሉ ያልለየ ሃሳብ ያራምዳሉ፡፡
የሚዛናዊ ጋዜጠኝነት አዘጋገብ መርህን በተመለከተ የአገራችን የግል ሚዲያዎች አብዛኞቹ (ሁሉም አይደሉም) ሚዛናዊ አለመሆናቸውን እንዲሁም የጋዜጠኝነት አዘጋገብ መርህ የሆነው ገለልተኝነትን (Objectivity) በተመለከተ የግል ሚዲያው ከፍተኛ ችግር እንዳለበት መናገራቸውን ጠቁመው፣ በኢቲቪ መቅረቡ ግን እንዳንገበገባቸው ይገልጻሉ፡፡ የሚዲያና ዲሞክራሲ ግንኙነት በተመለከተም የሚዲያው ተቋም አራተኛው የመንግስት ክንፍ ተደርጐ እንደሚወሰድ፣ በመንግስትም ሆነ በሌሎች አካላት የሚፈፀሙ የአሰራርና የአስተዳደር ችግሮችን ማጋለጥ እንዳለበት የሰጡት ሃሳብ በአርትኦት መቆረጡ (ከሙያ አንፃር ሳይሆን መንግስትን በነገር ሸንቆጥ ሳያደርጉ በመቅረታቸው) እንዳስቆጫቸውም ሳይሸሽጉ ጽፈዋል፡፡

በነገራችን ላይ መንግስት ከአስር አመት በፊት ባዘጋጀው ፖሊሲ ላይም ጉድለቶችንና ችግሮችን እየነቀሱ ችግሩን ለማባባስና ለማቀጣጠል ሳይሆን የመፍትሔ አቅጣጫ ለመጠቆም የጋዜጠኝነት ምርመራ ስራ መስራት የሚቻልና የሚገባ እንደሆነ ተገልጽዋል፡፡ ክፋቱ ግን አንዳንድ የአገራችን ምሁራን የአሜሪካንን “ፈርስት አሜንድመንት” በቃላቸው ሸምድደው ለመስበክ የሚጥሩትን ያህል ለአገራቸው ፖሊሲዎችና ህጐች ደንታቢስ መሆናቸው ነው፡፡ መምህሩ ግለኝነትን (ፕራይቬሲ) በተመለከተ የሰጡት አስተያየት ተቆርጦ እንደወጣባቸውም ስሞታ አቅርበዋል፡፡ አንድ በከፍተኛ ተቋም ውስጥ በመምህርነት የሚያገለግልና ሙያውን ቢያንስ በንድፈ-ሃሳብ ደረጃ ጠንቅቆ ያውቃል የተባለ ሰው ቀርቶ ማንም ተራ አንባቢ በቀላሉ እንደሚረዳው፣ የትኛውም ሚዲያ በተለያዩ ምክንያቶች (ለምሳሌ የቦታና ጊዜ እጥረት) የቀረበለትን አስተያየት ሁሉ እንደማያቀርብ ይታወቃል፡፡ አርትኦት የሚባል የጋዜጠኝነት የዕለት ተዕለት ስራ እንዳለ መምህሩ ይዘነጉታል ብዬ አላስብም፡፡ ቃለ መጠይቅ እንዳለ ላይተላለፍ ይችላል፡፡ የትኛው መልዕክት መተላለፍ እንዳለበትና እንደሌለበት የሚወስነው ዋና አዘጋጁ ወይም ኤዲተሩ እንደሆነ ከአንድ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ምሁር የተሰወረ ነው ብዬ አላምንም፡፡
ኢቲቪ ያቀረበውን ዘገባ ከመርህ አኳያ አንስተው መሟገት ሲገባዎ፣ ከዶክመንተሪ ፊልሙ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለውን የፖለቲካ ገለልተኝነት እሳቤ ያለቦታው ደንቅረውታል፡፡ እኔ እንዳየሁት፣ የዶክመንተሪ ፊልሙ አዘጋጆች፣ የገለልተኝነት መርህን ለመጠበቅ ረዥም ርቀት ተጉዘው እውነታውን ለማስጨበጥ ጥረት አድርገዋል፡፡ በፅንፈኛና አክራሪ ሚዲያው ጉዳት የደረሰባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች አስተያየት በገለልተኝነት አቅርበዋል፡፡ የተለያዩ ምሁራን በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አስተያየትም ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ ለማስተናገድ ጥረዋል፡፡ መንግስትም እንደ አንድ የጉዳዩ ባለቤት፣በተወካዮቹ አማካኝነት ሃሳቡ ተካትቷል፡፡ መምህር ሆይ፤ የቱ ጋ ነው ታዲያ የገለልተኝነት መርህ የተጣሰው? እኔ የተናገርኩት በሙሉ ካልቀረበ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ለአገራችን የግልም ሆነ የህዝብ ሚዲያ መጎልበት የሚያበረክተው ፋይዳ ያለ አይመስለኝም፡፡ የግለሰቦችን ሰብዕና በማይነካ መልኩ የግል ሚዲያው ምርመራ ማድረግ አለበት የሚል መርህ ቢያስቀምጡም በአንዳንድ ፅንፈኛ የግል ሚዲያዎች የተሳሳተና መርህ የሳተ ዘገባ ምክንያት ሰብዕናቸው ተጐድቶ ቤት ለመዋል ስለተገደዱትና በዶክመንተሪ ፊልሙ ስለቀረቡት የግል ተበዳይ (ግለሰብ) አንስተው የፅንፈኛውን ሚዲያ አካሄድ ለመኮነን አልደፈሩም፡፡ ይህም ሌላው የአድርባይነትዎ መገለጫ ነው፡፡ ይልቁንም ኢቲቪን ለመወንጀልና እርስዎ እንደ ጦር የፈሯቸውን ሦስተኛ ወገኖች ለማስደሰት ኑዛዜ አቀረቡ፡፡ እርስዎ ለማስተላለፍ የፈለጉት “የግል ሚዲያው ምንም እንከን የሌለው ቅዱስ ነው” የሚል ሃሳብ እንደሆነ የጻፉትን ያነበበ ሰው ሁሉ በቀላሉ ይረዳዋል፡፡ ይህም ገና ከጅምሩ የተከበረውን የመምህርነት ሙያ ለድርድር እንዳቀረቡትና የአድርባይነት ሰለባ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው፡፡
ለእውነት መቆምና ስለእውነት መመስከር እርስዎን ከመሠለ ምሁር የሚጠበቅ ቢሆንም እንደአለመታደል ሆኖ ግን ያንን ማሳየት አልቻሉም፡፡ ሁሉንም ነገር ኢቲቪ ላይ ደፍድፈውና ለጉዳዩ ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥተው ከመከራከርዎ በፊት ግራና ቀኙን ከሙያዎ አኳያ መርምረው፣ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ቢያሳዩን ተገቢ ነበር፡፡ ሆኖም የምሁር አድርባይነትዎ እውነታውን በትክክለኛው መነፅር ለማየት አላስቻልዎትም፡፡

 

 

Read 3696 times