Saturday, 13 September 2014 12:56

“በአንድ ጊዜ ከላሟ፤ ሥጋዋንም፣ ወተቷንም፣ ጥጃዋንም ማግኘት አይቻልም!”

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የራሺያው መሪ ስታሊን ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ አደረገ አሉ፡፡
ሰዉን ስብሰባ ጠርቷል፡፡
ተሰብሳቢው ፀጥ ብሎ ያዳምጣል፡፡
ከተሰብሳቢው መካከል ድንገት አንድ ሰው አስነጠሰው፡፡
ስታሊን ንግግር ከሚያደርግበት ምስማክ ቀና ብሎ፤ በቁጣ፣ ኮስተር ባለው ድምፁ፡-
“ማነው አሁን ያስነጠሰው?” አለና ጠየቀ፡፡ ማንም አልመለሰም፡፡ ሁሉም ጭጭ አለ፡፡ ሰው ሁሉ አቀርቅሯል፡፡ በየሆዱ “ማንን ፈልጎ ይሆን?” ማን ይሆን የፈረደበት? እኔን ይሆን? እሷን ይሆን” ይላል፡፡ ያስነጠሰውም ሰው ተፈጥሮአዊ ጉዳይ ስለሆነ “እኔ ነኝ ብል ምን እሆናለሁ?” ብሎ መልስ አልሰጠም፡፡ ስታሊን ሆዬ አንጋቹን ጠራና፤
“እሺ ከኋለኛው መስመር ሁለቱን ተርታ ሰው አስወጣና ግደልልኝ!” አለና አዘዘ፡፡
አንጋቹም እንደታዘዘው ሁለቱን ተርታ ሰው እያንጋጋ ወስዶ ረሸነና ተመለሰ፡፡
ስታሊን ቀጥሎ፤ “እሺ ማነው ያስነጠሰው? አሁንም ተናገሩ!” አለ፡፡
አሁንም ዝም ዝም ሆነ፡፡ መናገር ቀርቶ ቀና ብሎ የሚያይ ሰው ጠፋ፡፡ አሁንም ወደ አንጋቹ ዞሮ፤
“ከኋለኛው መስመር ሁለቱን ተርታ ሰው አስወጣና ረሽንልኝ!” አለ፡፡
አንጋች ሁለት ተርታ ሰው አስወጣ፡፡
የጥይት እሩምታ ድምፅ ተሰማ፡፡ አለቁ ማለት ነው፡፡
ስታሊን እንደገና፤ “ማነው ያስነጠሰው? ተናገሩ!!” አለ እያንባረቀ፡፡
አሁን የቀረው ሁለት ተርታ ሰው ነው፡፡
ይሄኔ፤ አንድ መነፅር ያደረጉ አዛውንት እጃቸውን አነሱ፡፡
“እሺ ምን ይላሉ?” አላቸው ስታሊን፡፡ አዛውንቱም፤ በኮሰሰ ድምፅ “እኔ ነኝ ጓድ!” አሉ፡፡ “ይማርዎት!” አላቸው፡፡
አዛውንቱም፤ “ያኑርህ!” አሉ፡፡
* * *
ከስታሊን በትር ይሰውረን!
መሪና ተመሪ፣ አለቃና ምንዝር፣ ኃላፊና የሥራ ሂደት ኃላፊ ወዘተ. የሚፈራሩበት ሥርዓት ዲሞክራሲያዊነት ይጎድለዋል፡፡ የበላይን ከልኩ በላይ የመፍራት ልማድ፣ የበታቹን ማርበትበት፣ ቅጥና፣ አቅል-ማሳጣቱ፤ አልፎ ተርፎም ውሉን ስቶ፣ ቦታውን ስቶ ወደሌላ፣የሱ ወዳልሆነ ቦታ ወይም አገር፤ እስከመሰደድ ሊያደርሰው ይችላል፡፡ ኢፍትሐዊ ወይም የፈሪና የተፈሪ፣ ዘልቆም የጌታና - የሎሌን ዓይነት ግንኙነት፣ ከቶም ከዐይነ-ውሃው ስናየው ጤናማ አለመሆኑን ለማየት ብዙ ፀጉር ማከክን አይፈልግም፡፡ የባሰ ሥጋት የሚሆነው ነገር፣ የተገዢው ፈሪ መሆን ገዢው ላይ የሚፈጥረው የተዓብዮ ስሜትም ነው፡፡ ሥልጣንና ኃላፊነት ከሚፈቅደው ለከት በላይ “ለካ እንዲህ ይፈሩኛል” የሚል የማስፈራራት፣ የመቆጣት፣ የማርበድበድ… እርካታ፤ ሆዱ ውስጥ ያድራል፡፡ ከእንዲህ ያለው ጉልላት ወርዶ ትህትናን ተላብሶ፣ ህዝባዊ የሆነ ተዋህዶ መፍጠርና ሰው መሆንን መገንዘብ፣ ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ ኢወገናዊ፤ ኢክፋታዊ፣ ኢአምባገነናዊ አሰራርን የመቀበልን ግለ-ሰባዊና ቡድናዊ፣ አልፎ-ተርፎም ጀማዊ ሥነ-ምግባርና ሙያዊ ብቃትን፣ እንዲሁም፤ የተጠያቂነትን መርህ የመቀበልንና ቅን ሥነ-ልቦናን የመዋሐድን ሥነ-ሥርዓት ይሻል፡፡
በዚህ አዲስ ዓመት፤ በተደጋጋሚ የተከሰቱ ችግሮችን፣ በተደጋጋሚ አውስተን፣ በተደጋጋሚ እንፈታቸዋለን ብለን ፎክረን፣ በተደጋጋሚ እዚያው እተነሳንበት ሥፍራ (Back to square – one እንዲሉ) የተመለስንባቸውን ጉዳዮች የምናስተውልበት፤ ያንን በማጤን፣ በመመርመርና ዘላቂ ዘዴ በመፍጠር፣ ጥበቡን የምንቀዳጅበት ያድርግልን!
መጪው ዘመን፤
ነገን የማንፈራበት፣ በልበ-ሙሉነት የምንጓዝበት፣ በዕውቀት እንጂ በጉልበት የማንራመድበት፣ አፈጮሌ፤ ሚዲያ አገኘሁ ብሎ ‹ያለእኔ ማን አለ?›፣ የማይልበት፣ አድር-ባይ ቀን ሞላልኝ ብሎ መቀመጫውን ለማደላደል በፍየል መሳይ ምላሱ የባጥ -የቆጡን የማይቀባጥርበት፣ “ሰው ባንበደቱ ውሻ በምላሱ” ይኖራል የማይባልበት ዘመን፤ ያድርግልን!
በሀገር ጉዳይ ንቅንቅ የማንልባቸው እንደኢትዮጵያዊነት፣ ሉዓላዊነት፣ የሀገር ህልውና፣ የዜግነት ክብር፣ ሥረ-መሰረታዊ ማንነት ወዘተ. ዛሬም የማይነኩ፣ የማይደፈሩና የማይገሰሱ ይሆኑ ዘንድ፤ ይሄ ዘመን ዐይናችንን ይክፈትልን!
ዛሬም ሙስናን የምንዋጋበት፣ ዛሬም ወገናዊነትን ሽንጣችንን ገትረን የምንፋለምበት ዘመን ያድርግልን! በየተቋሙ፣ በየቡድኑ፣ በየቢሮው “ሰው -አለኝ” የምንልበትን አሰራር ይህ ዘመን ያስወግድልን!
እንደታሪክ ስላቅ ሆኖ፤
“የአሜሪካ የሀገር ደህንነት አማካሪ ለእስራኤል የፍትህ ሚኒስትር የ“AIPAC” (የአሜሪካና የእስራኤል ህዝብ ጉዳይ ኮሚቴ) ውስጥ ያለ የሚረዳኝ ሰው ታውቃለህ ወይ?” ብለው ጠየቁ አሉ፡፡ ዋናው እንጀራ ጋጋሪ አሜሪካ ሆና ሳለ የውስጥ ሰው ከእስራኤል ፈለገች ማለት ነው፡፡ የሙስና ጥልቀቱ ኃያላኑም ውስጥ አለ፡፡ ሥር - ከሰደደ መመለሻ የለውም! ሆኖም ትግሉ ጥንቃቄና ትግስት ይጠይቃል፡፡ የሀገራችን ጣጣ አላልቅ ያለው ሁሉን ባንድ ቀን ፈተን፣ ሁሉን ባንድ ጀንበር አሸንፈን፣ ለዘመናት ያጠራቀምነውን ሕመም ባንድ ሌሊት ካልፈወስን ብለን፤ ዘራፍ በማለታችን ነው፡፡ “ዐባይን በአንድ ጊዜ ከመነሻውም ከመድረሻውም መጨለፍ አይቻልም”፤ ይለናል “ራስ ኤላስ መስፍነ - ኢትዮጵያ”፡፡ ሁሉን ችግር ባንድ ቅፅበት እንፈታለን ካልን አንዱንም ሳንጨብጥ እንቀራለን ነው ነገሩ፡፡ ማንም ቢሆን ማን፤ በብልህነት፣ በጥንቃቄና ደረጃ በደረጃ እንጂ በሁሉም ነገር ላይ ባንድ ጊዜ አብዮት ማፈንዳት አይችልም፡፡ በጥድፊያ የተካሄዱ፣ ሆይ ሆይ ተብለው ሥር-ሳይሰዱ መክነው የቀሩ አያሌ ጅምሮች እናውቃለንና ልብ እንበል፡፡ “ከላሟ፤ በአንድ ጊዜ ሥጋዋንም፣ ወተቷንም፣ ጥጃዋንም ማግኘት አይቻልም” የሚባለው ለዚህ ነው፡

 

Read 4477 times