Saturday, 06 September 2014 11:14

የጋዛ ጦርነት በገንዘብ ሲሰላ…

Written by 
Rate this item
(5 votes)

*    ጋዛን መልሶ ለመገንባት 6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል
*    እስራኤል ለጦርነቱ 2. 3 ቢሊዮን ዶላር አውጥታለች

ለሰባት ሳምንታት ያህል ከወደ እስራኤል ቀን ከሌት ሲሰነዘርባት በቆየው አሰቃቂ ድብደባ አሳር መከራዋን ስታይ የቆየችው የፍልስጤሟ ጋዛ፣ ከቀናት በፊት በተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይ ብትልም፣ ድብደባው ያደረሰባት ጥፋት ግን እጅጉን የከፋና በቀላሉ የሚሽር አይደለም፡
በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተፈጠረው ግጭት ለ70 እስራኤላውያን ሞት ምክንያት መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ግጭቱ እጅግ የከፋ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጥፋት ያስከተለው ግን፣ በፍልስቴም ላይ መሆኑን የኣለማችን መገናኛ ብዙሃን እየመሰከሩ ይገኛሉ፡፡
ግጭቱ ለህልፈተ ህይወት ከዳረጋቸው 2ሺህ በላይ ፍልስጤማውያንን መካከል አብዛኞቹ ጨቅላ ህጻናት ሰለመሆናቸው የዘገበው ሲኤንኤን፣ ለሳምንታት ስትደበደብ የቆየችው ጋዛ እንዳታገግም ሆና መፈራረሷንና የደረሰባት ኢኮኖሚያዊ ቀውስም እጅግ የከፋ እንደሆነ ገልጧል፡፡
በእስራኤል ጥቃት የፈራረሰችዋን ጋዛ መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ የጠቆመው ሲኤንኤን፣ መልሶ ግንባታውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን እስከ 6 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የገንዘብ  እንደሚያስፈልግ ገልጧል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አጋሮቹ በጋዛ ለሚከናወኑ የሰብዓዊ መልሶ ማቋቋም ስራዎች ተጨማሪ 367 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግና፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥም ከግማሽ በላይ የሚሆነው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ከ500ሺህ በላይ የጋዛ ነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፤ የተቀረው ገንዘብም ለቤቶች ግንባታ፣ ለውሃና ንጽህናና ለትምህርት ተቋማት ግንባታ እንደሚውል ገልጠዋል፡፡
ኦክስፋም በበኩሉ በጋዛ ነዋሪዎች ላይ የደረሰው የመሰረተ ልማት አውታሮች ውድመት፣ በአለማችን ባለፉት 20 አመታት ከተከሰቱ መሰል ውድመቶች ሁሉ ባደረሰው ቀውስ ከፍተኛነት ወደር እንደማይገኝለት ገልጧል፡፡ ከ15 በላይ ሆስፒታሎች እና በጋዛ ብቸኛው የነበረው የሃይል ማመንጫ፣ ከእስራኤል በደረሰባቸው የድብደባ ጥቃት ሙሉ ለሙሉ መፈራረሳቸውንም ተናግሯል፡፡
በጋዛ እስካለፈው ነሃሴ 3 ቀን ድረስ ከ10    ሺህ 600 በላይ መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም፣ የፈራረሱትን ቤቶች መልሶ የመገንባቱ ስራ እጅግ ፈታኝ እንደሚሆንና ምናልባትም አራት አመታትን ያህል ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል አስታውቋል፡፡
የእስራኤል የታክስ ባለስልጣን በበኩሉ፣ ከሃማስ በተሰነዘሩ ጥቃቶች የወደሙ የአገሪቱ ቤቶችን ቁጥር በተመለከተ ተጨባጭ መረጃ ባይኖርም፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ለመገንባት ግን 11 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደሚጠይቅ አስታውቋል፡፡
የእስራኤል መንግስት የንብረት ውድመት ለደረሰባቸው ዜጎቹ ማካካሻ ገንዘብ እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቆመው የሲኤንኤን ዘገባ፣ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት አውታሮች ውድመት በደረሰባት የሰሜን እስራኤሏ ከተማ የአሽዶድ ነዋሪዎችን ጨምሮ፣ 3ሺህ 700 ያህል የአገሪቱ ዜጎች ለመንግስት የማካካሻ ገንዘብ ጥያቄ ማመልከቻ ማቅረባቸውንና ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም ለመኖሪያ ቤት ውድመት ያመለከቱ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ግጭቱ በእስራኤል የቱሪዝም ገቢ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን፣ ምርታማነት ላይ ቅናሽ እንዲፈጠር ማድረጉንና ይህም የሆነው በርካታ የአገሪቱ ሰራተኞች የሮኬት ጥቃትን በመፍራት ስራ አቋርጠው በመኖሪያ ቤቶቻቸው በመደበቃቸው እንደሆነም አስረድቷል፡፡
እስራኤል ለሰባት ሳምንታት ያህል በጋዛ ላይ በሰነዘረችው ጥቃት ያወጣችውን አጠቃላይ ወታደራዊ ወጪ በተመለከተ ይፋዊ መረጃ ባትሰጥም፣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ግን ወጪው እስከ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል እያሉ ነው፡፡

Read 2999 times