Saturday, 06 September 2014 10:56

የደርግ ዘመን ሳንሱር የናፈቀው --- እርሙን ያውጣ!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(9 votes)
  • በ“ስደት” ትርጉም ላይ አገራዊ መግባባት ያስፈልገናል!
  • ጋዜጠኛ “ተሰደደ” የሚባለው መቼና እንዴት ነው?
  • “The Moment of Truth” ማንንም  ያስለቅሳል!

   ባለፈው ሳምንት፤ በአሜሪካ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ “The Moment of Truth” በሚል ስያሜ ስለሚቀርበው አዝናኝና ተወዳጅ ፕሮግራም ነበር ያወጋነው፡፡ ስለአዝናኝነቱ እንኳን በእርግጠኝነት መናገር ይከብደኛል፡፡ ለምን መሰላችሁ? ብዙ ተጠያቂዎች ለዘመናት የግል ምስጢራቸው አድርገው ያቆዩትን “መራር እውነት” ስለሚያፍረጠርጡት፣ ፍንጥርጣሪው ብዙዎች ጋ መድረሱ አይቀርም፡፡ በተለይ ቤተሰብና ፍቅረኛ ዘንድ፡፡ ለዚህ ነው ጥያቄው ሲጀመር ስትፍለቀለቅ የነበረችው ውብ ተጠያቂና አጅበዋት የመጡት ቤተሰቦቿ (አባት፣ እናት፣ ባል/ፍቅረኛ፣ የቅርብ ጓደኛ ወዘተ…) ጭምር ሁለተኛና ሶስተኛ ዙር ጥያቄ ላይ (ባለ25 ሺና 100 ሺ ዶላር ጥያቄ ሊሆን ይችላል!) ማዘንና ባስ ሲልም ዓይንን በሶፍት መዳበስ የሚጀምሩት፡፡ (እውነቱን መናገር ያሸልማልም ያስለቅሳልም!)
የፕሮግራሙ አዘጋጅ፤ ሁልጊዜ ፕሮግራሙን ሲጀምር ምን ይላል መሰላችሁ? “በአሜሪካ ምድር የቀረ አንድ ሃቀኛ ሰው ይኖር ይሆን? እውነቱን የምንጋፈጥበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፤ እውነቱን መናገር እስከ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ያሸልማል”፡፡ እንደኔ ከሆነ--- እውነት እምብዛም በማትከበርበትና ከላይ እስከታች ውሸት በሰፈነባት ኢትዮጵያችን፣ እንዲህ ያለ እውነትን አቀንቃኝ የቲቪ ፕሮግራም በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ አሁን ደሞ እነ ኢቲቪ ወደ ኮርፖሬሽንነት ስላደጉ እንዲህ ያሉ ዝግጅቶች ወሳኝ ናቸው፡፡ የእውነተኝነትንና የሃቀኝነትን ባህል ለማጐልበት ይጠቅማሉ፡፡
በእርግጥ ፕሮግራሙ በቤተሰብና በትዳር መሃል ችግርን ሊፈጥር ይችላል - እንደ አሜሪካ ተመክሮ፡፡ ግን ለእውነት ሲባል የሚከፈል መስዋዕትነት ነው፡፡  በነገራችሁ ላይ … ብዙዎች ራሳቸውን እያወቁ (የሰሩትን ማለቴ ነው!) ወደ ቲቪ ፕሮግራሙ ለጥያቄ የሚቀርቡት ለገንዘቡ ጓጉተው እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይታያችሁ…አነስተኛው ሽልማት 10ሺ ዶላር (200ሺ ብር ገደማ) ሲሆን ትልቁ ሽልማት ደግሞ 500ሺ ዶላር (10ሚ. ብር ገደማ) ነው፡፡ በእርግጥ ተጠያቂዎቹ የሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምን ያህል ከባድ እንዲሁም የፍቅርና የቤተሰብ ህይወታቸውን  ሊያናጋ እንደሚችል ጨርሶ አያውቁም፡፡ ግን ይጠረጥራሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የመጣ ይምጣ ብለው ይገቡበታል -  ዓይናቸውን በጨው አጥበው፡፡ እንዴ---ሲሰሩ የከረሙትን እያወቁ የሃቀኝነት ፈተና ላይ መቅረብ ምን የሚሉት ድፍረት ነው፡፡ እኔ የምለው---- ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ቢጀመር ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች ለጥያቄው እሺ ብለው የሚቀርቡ ይመስላችኋል? (ዋናው እኮ እነሱ ናቸው!) በተለይ የገዢው ፓርቲ አባላት ለሹመት ከመመልመላቸው በፊት “The Moment of Truth” ላይ ቢቀርቡ የኋላ ችግሮችን ከወዲሁ ለመፍታት ያግዘናል ብዬ አስባለሁ፡፡ (ሰው እኮ በአንድ ጀንበር ሙሰኛ አይሆንም!)
 ባለፈው ሳምንት እኛ አገር ለሚጀመረው አቻ የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ “እውነትን ፍለጋ!” የሚል ስያሜ ቢሰጠው የሚል ሃሳብ አቅርቤ ነበር፡፡ ሰሞኑን ደግሞ ለምን “ንስሃ!” አንለውም የሚል ሃሳብ ሽው ብሎብኛል፡፡ “የኑዛዜ ቅፅበት”ም ሊባል ይችላል፡፡ የኮፒራይት ጥያቄ ካላስነሳ “ቃሌ” ቢባልም ደስ ይለኛል፡፡ አሁን ወደ The moment of Truth ልመልሳችሁ፡፡
 አንዲት የእሳት አደጋ የበጎ ፈቃድ ሰራተኛ ከቀረቡላት ጥያቄዎች ውስጥ ትኩረቴን የሳቡትን ላጋራችሁ፡ የ10ሺ ዶላር ይሁን የ25ሺ ዶላር ጥያቄ ትዝ አይለኝም፡፡
ጥያቄ -“ከሱፐርማርኬት ወይም ከሱቅ እቃ እየሰረቅሽ ለልጆችሽ ትሰጫቸዋለሽ?” (ደግነቱ ልጆቿ አልነበሩም!)
ልጆቿ ባይኖሩም ግን ባሏ ፊት ለፊት ተቀምጦ እታዘባት ነበር፡፡ እናቷና አባቷ እንዲሁም ምስጢረኛ ጓዳኛዋም ሞራል ሊሰጧትና ሊደግፏት በፕሮግራሙ ላይ ታድመዋል፡፡ ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እነሱንም ይነካቸዋል፡፡ እቺ በአሜሪካ የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ ውስጥ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት የላቀ ክብር የተቀዳጀች የሶስት ልጆች እናት፣ ምላሿ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “አዎ፣ ሰርቄ ለልጆቼ ሰጥቼ አውቃለሁ!” ነበር ያለችው፡፡ የአዳራሹ ታዳሚ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን በጩኸት ሲገልፅላት፣ ቤተሰቦቿ ግን ማቀርቀርን ብቻ ነበር የመረጡት፡፡ ለነገሩ የዚህን ጥያቄ ምላሽ ባይፈልጉት ኖሮ ምርጫ ነበራቸው፤ ፊትለፊታቸው የሚታየውን ደወል መጫን ይችላሉ፡፡ ያኔ ጠያቂው ጥያቄውን ይለውጥላታል (ተተኪው ጥያቄ የባሰ ቢሆንስ?)
የእሳት አደጋ ሰራተኛዋ ሌላም ተመሳሳይ ጥያቄ ቀርቦላታል “ከዘመድ ቤት የሆነ ዕቃ ሰርቀሽ ታውቂያለሽ?” የሚል፡፡ አሁንም ፍርጥም ብላ “አዎ” ስትል መለሰች፡፡ (ከአያቷ ቤት እኮ ነው የሰረቀችው!)
“The Moment of Truth” ይቀጥላል፡፡ አሁን ደሞ ተጠያቂው ባለትዳርና የልጆች አባት ነው፡፡ ሚስቱ ከቤተሰቡ አባላት ጋር ፊት ለፊቱ ተቀምጣ ታበረታታዋለች፤ ታፅናናዋለች፡፡ በመጨረሻዎቹ ጥያቄዎች ላይ ግን ራሷም አፅናኝ አስፈለጋት፡፡ ባል ከቀረቡለት ጥያቄዎች አንዱ እንዲህ የሚል ነው፡-
“ሚስትህን ካገባህ በኋላ ስልክ ቁጥርህን ለሌላ ሴት ሰጥተህ ታውቃለህ?” (“አደጋ አለው!”)
ተጠያቂው ብቻ ሳይሆን መላ ቤተሰቡ በተለይም ውዱ ባለቤቱ የዚህን ጥያቄ ምላሽ በእጅጉ  የፈራችው ትመስላለች፡፡ ነገሩን የተረዳው የፕሮግራሙ አዘጋጅ፤ “ከፈለጋችሁ ደውሉን መጫን ትችላላችሁ!” አላቸው፡፡ ሚስት ግን በእልህ ጥርሷን ነክሳ “እውነቱን መስማት እፈልጋለሁ” አለች፡፡ (ጉዷን አላወቀች!) የፕሮግራሙ መሪ ጥያቄውን ለባልየው ደገመለት፡፡ ባልም አሰበ አሰበና “አዎ ሰጥቼ አውቃለሁ!” ሲል መለሰ፡፡ እውነትና ውሸቱን የምታረጋግጠው ማሽንም (“የልብ አውቃ” ብያታለሁ!) ሃሰት ነው አላለችም፡፡ “That answer is true!” አለች እንጂ፡፡ (“devastating” ማለት ይሄኔ ነው!)
የ23 ዓመቱ ተጠያቂ ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል ሁለት ቦንብ ጥያቄዎችን እንይለት፡፡ ፍቅረኛው በስስት  ዓይን እያየችው ነው፡፡
ጥያቄ – “ድሮ ያፈቀርካቸውን ሴቶች ስም ዝርዝር በወረቀት ላይ የማስፈር ልማድ አለህ?”
ቀልድ ቢመስልም የ25ሺ ዶላር ኮስታራ ጥያቄ ነው፡፡ ሃቀኛ መልስ የሚፈልግ፡፡ ተጠያቂው ልዋሽ ካለ፣ ቀድሞ አሸንፎት የነበረውን 10ሺ ብር ጨምሮ ያሁኑን 25ሺ ብር አጥቶ እያጨበጨበ ወደ ቤቱ ይመለሳል፡፡ ስለዚህ እውነቱን  ተናገረ፡፡ ሁሌም “እነሆ በረከት” ያላቸውን ሴቶች የመመዝገብ፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ ደረጃ የማውጣት (rating) ልማድ እንዳለው በዝርዝር አስረዳ (“የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” አሉ!) አሁን ዓይናችሁን ወደ ሚስቱ እንዳትልኩ! ክፉኛ ስሜቷ ተጐድቷል፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ግን ከዚህም የከፋ ነው፡፡
ጥያቄ – “ከ100 በላይ ከሚሆኑ ሴቶች ጋር አንሶላ ተጋፈሃል?”
ተጠያቂው የ23 ዓመት ወጣት መሆኑን ልብ በሉ፡፡ ሆኖም የእሱ መልስ “Yes!” የሚል ነበር፡፡ (አድርጌዋለሁ ማለቱ ነው!) ከዚያም በረዥሙ ተነፈሰ - ተገላገለ፡፡ ምስኪኗ ሚስቱ ግን በሃፍረት ተሞልታ በእንባ ታጠበች  - የምትገባበት ጠፋት፡፡ እቺ ናት እንግዲህ “The Moment of Truth” የእውነት ቅፅበት፤ የንስሃ ጊዜ ማለት!! (ከዚህ በኋላ ፍቅራቸው ነፍስ ይኖረዋል ብላችሁ ነው??)
ለዚህ ነው መግቢያዬ ላይ ስለፕሮግራሙ አዝናኝነት አፌን ሞልቼ መናገር አልችልም አልኩ፡፡ እኔ የምለው--- አሜሪካን አገር እውነት እንዲህ መራራ ከሆነች፣ እኛ አገር ምን ልትሆን እንደምትችል አስቡት! ምናልባት “የእሳት ኳስ”? “ሲኦልን ለአንዳፍታ?” አሊያም “እንጦሮጦስ ደርሶ መልስ?”
 እንዲህም ሆኖ ግን እውነቱን ተናግሮ ቤተሰቡን ወይም ፍቅረኛውን እርር ያደረገ ተጠያቂ፣ ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ከማግኘቱም በተጨማሪ “ሃቀኛ ሰው!”፣ “truthful man”… የሚል ሙገሳ ይጎርፍለታል፡፡ ይሄውላችሁ ---- ፕሮግራሙ አዝናኝ መሆኑን ብጠራጠርም፣ ተወዳጅ መሆኑን ግን መቶ በመቶ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ገበና ምናምን የሚሉትን ኮተቶች ወዲያ አሽቀንጥሮ  ሃቁን ብቻ የተናገረ ሰው፣ 200ሺ ብር ማንም አይከለክለውም!! የበለጠ ሃቁን ከደፈረ ደግሞ እስከ 100ሺ ዶላርም  ሊገሰግስ  ይችላል (2 ሚ. ብር ማለት እኮ ነው!!)
ለአፍታ ያህል ከ“The Moment of Truth” ወጣ ብለን አንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮችን እናውጋ፡፡ እንደ እረፍት (break) ቁጠሩት፡፡ በነገራችሁ ላይ የቱንም ያህል ከዚህ ፕሮግራም ለመሸሽ ብንሞክር፣ ከእውነት ግን ጨርሶ ልንሸሽ አንችልም፡፡ (የሸሸን ሊመስለን ይችላል እንጂ!) እኔም - እናንተም - የመንግስት ባለስልጣናትም - ፖለቲከኞችም - የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችም - ካድሬዎችም - ልማታዊ ጋዜጠኞችም - የነፃው ፕሬስ አባላትም - ምሁሩም - መሃይማኑም - ሁላችንም ለጊዜው ነው እንጂ እውነትን ሸሽተን አንሸሻትም፡፡
ይሄንን ካልን ዘንዳ ወደ ዋና ጉዳዬ ልምጣ፡፡ የመፅሄቶች መከሰስን ተከትሎ ማተምያ ቤቶች “አናትምም” ብለውናል በሚል አሳታሚዎችና ጋዜጠኞች አገር ጥለው መሄዳቸው  ይታወቃል፡፡ (“ስደት አይደለም” ተብሏል!) የስደትን ትርጉም የሚነግረኝ ይሸለማል፡፡ በጋዜጠኞቹ ስደት ወይም ከአገር ብን ብሎ መጥፋት  ማን ይደሰታል? ማንስ “እንደ አገር ኪሳራ” ይመለከተዋል? እውነቱን “The Moment of Truth” ላይ እንጂ የትም አናገኘውም፡፡ በነገራችሁ ላይ አሁንም ማተምያ ቤቶች ክስ የሌለባቸው የግል ፕሬሶችን ጭምር “አናትምም” እያሉ ነው ሲባል ሰማሁ (ስኳር ደብቀው “የለም” የሚሉ ግን “ህገወጥ ነጋዴ” ተብለው ይቀጣሉ!)
በጋዜጠኞቹ ከአገር መውጣት መንግስት ምን እንደተሰማው አላውቅም፡፡ እኔ መንግስትን ወይም ኢህአዴግን ብሆን ግን እደነገጥ ነበር፡፡ ይሄ እጅ የመስጠት፤ የመሸነፍ ወይም የፍርሃት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሃላፊነት ነው ወይም መንግስትነት ልትሉት ትችላላችሁ፡፡ (ወይስ መንግስት አይደነግጥም?) ግን እኮ በ97 ምርጫ መንግስት ክው ብሎ ደንግጦ ነበር፡፡ ከየትኛው አካል እንደሆነ ማረጋገጫ ማግኘት ባይቻልም ማተምያ ቤቶች “ለምታትሙት ነገር ትጠየቁበታላችሁ!” የሚል ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸው በሹክሹክታ ሰምቻለሁ፡፡ (“ስውር መንግስት” አለ እንዴ?)  
ኢህአዴግ ይሄን አያደርግም ብለን በ“ልማታዊ መንግስታችን” ብንተማመንም እንኳ ከመጠየቅ ግን አይድንም፡፡ ለምን መሰላችሁ? በፍርድ ቤት የተከሰሱት 5 መፅሄቶችና 1 ጋዜጣ ብቻ ናቸው፡፡ “ከህትመት እየወጣን ነው” የሚሉትና ከአገር ለመውጣት ያቆበቆቡት ግን ያልተከሰሱትም ጭምር ሆነዋል፡፡ መንግስት ይሄን የመመርመር ወይም የማጣራት ሃላፊነት የለበትም? ማተሚያ ቤቶችሽ ለምን ጋዜጦች በተከሰሱ ቁጥር በፍርሃት ይርዳሉ? (የህግ የበላይነት ለመቼ ነው!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል… ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሳንሱር የናፈቃቸው “የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች” ቀና ቀና ማለት እንደጀመሩ መጠርጠር ጀምሬአለሁ፡፡ ኢህአዴግ በመንገድና በባቡር ድርብርብ የልማት ስራዎች ተወጥሮ፣ የታገለለትንና የተሰዋለትን የፕሬስ ነፃነት - (ከሳንሱር ነፃ የመሆን መብት!) ችላ እንዳይለውና ሌላ ከባድ ኪሳራ ውስጥ ሁላችንም እንዳንገባ፡፡ ማተሚያ ቤቶች የሚታተመውን ጋዜጣ እያዩ “ይታተማል አይታተምም” የሚለውን መወሰን ከጀመሩ፣ ያለ ጥርጥር የደርግ ዘመን ሳንሱር ከች ትላለች፡፡ ከምሬ ነው የምላችሁ … አፍንጫችሁን በደንብ አሹላችሁ ካሸተታችሁ፣ ሳንሱር ናፋቂዎች ማቆብቆባቸውን ትደርሱበታላችሁ፡፡ (“ግርግር ለሌባ ይመቻል” አሉ!) እኔ ግን ማምሻም እድሜ ነውና “ሳንሱር የናፈቀው እርሙን ያውጣ!” ብያቸዋለሁ፡፡
የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ (መሬት ይቅለላቸውና!) በአንድ ወቅት “ሳንሱር የቀረው ኢህአዴግ አዲስ አበባ እንደገባ ነው፤ ከ82 በኋላ ሳንሱር የለም!” በማለት አስረግጠው ሲናገሩ ሰምቼ ነበር፡፡ ይሄንን ማረጋገጫ ዳግም ከጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መስማት እንፈልጋለን፡፡ እስከዚያው ግን ኢቴቪ ተቀርጾ የተቀመጠውን የአቶ መለስን ንግግር ማታ ማታ ከዜና በፊትና በኋላ እየደጋገመ ያሰማን፡፡ (የሳንሱር ናፋቂዎች እርማቸውን እንዲያወጡ እኮ ነው!)  
የአዲሱ ዓመት ጎዳና ወደ ጭቆና ሳይሆን ወደ ነፃነት፣ ወደ ጨለማ ሳይሆን ወደ ብርሃን፣ ወደ ኋላቀርነት ሳይሆን ወደ ሥልጣን የሚያደርስ ያድርግልን! ለገዢውም ለተቃዋሚውም ማስተዋያ ልብና መቻያ ሆድ ይስጥልን!! መልካም አዲስ ዓመት!!          

Read 5199 times