Saturday, 06 September 2014 10:47

ብሔራዊ ባንክ “ጎጆ እቁብ” ህገወጥ ነው አለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

“የተጠየቅነውን ፈቃድ አውጥተን እንሰራለን”- የጐጆ እቁብ መስራች

የጎጆ እቁብን አሰራርና ባህሪ ከመረመረ በኋላ ዕቁቡ ለመስራት ያቀደው በብሄራዊ ባንክ ፈቃድ የተሰጣቸው የፋይናስ ተቋማት የሚያከናውኑትን ስራ እንደሆነ ደርሼበታለሁ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ “ጎጆ እቁብ” ህገ ወጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የእቁቡ መስራቾች ስለአሰራራቸው ማብራሪያ እንዲሰጡት ካደረገ በኋላ እቁቡ በአመሰራረቱም ሆነ በአሰራሩ ከባህላዊ እቁቦች በእጅጉ የተለየ መሆኑን እንዳረጋገጠ ባንኩ ለአዲስ አድማስ በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
“እቁቡ፤ ገንዘብ ለመሰብሰብ፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ ለንብረት መግዣ ለማበደር፣ ንብረቱን ብድሩ እስኪከፈል ዋስትና አድርጎ ለመያዝ፣ ወለድ ከተበዳሪው ሳይሰበስብ ነገር ግን የአገልግሎት ክፍያ ከእቁብተኛው ለመውሰድና ከንብረት ሽያጭ ኮሚሽን ለመቀበል የተዘጋጀና የእቁብነት ባህሪ የሌለው አደረጃጀት ነው” ብሏል ባንኩ በመግለጫው፡፡ እቁቡ ህጋዊ ሰውነት ሳይኖረው ፣ ያለ ማንም ተቆጣጣሪ የመንግስት አካል እንዲሁም የስራ ፈቃድ ሳያወጣና የራሱ ካፒታል ሳይኖረው ለፋይናንስ ተቋማት በህግ የተሰጣቸውን ስራ ለመስራት ያቀደ በመሆኑ “ህገወጥ የግለሰቦች ስብስብ ነው” ብሏል፡፡
የ“ጎጆ እቁብ” መስራቾች ከእንቅስቃሴያቸው እንዲታቀቡ ያስጠነቀቀው ባንኩ፤ ህብረተሰቡም በመሰል እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፍ ያሳሰበ ሲሆን ህብረተሰቡ እንዲህ ያለ አሰራር ሲመለከት ጥቆማ እንዲያቀርብም ጠይቋል፡፡ “ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ፍቃድ ካልያዙ በስተቀር በገንዘብ ተቋማት ስራ ላይ መሰማራት በህግ የተከለከለ ነው፤ እቁቡን አስመልክቶ ከሚያደርጉት ማንኛውም ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ እናሳስባለን” የሚል ደብዳቤ ከባንኩ እንደደረሳቸው የገለፁት የጎጆ እቁብ መስራችና ዳኛ አቶ ናደው ጌታሁን በበኩላቸው፤ ወደፊት ህጉና አሰራሩ በሚፈቅደው አግባብ የተጠየቅነውን ፍቃድ አውጥተን እንሰራለን፤ እስከዚያው ከማንኛውም እንቅስቃሴ ታቅበናል ብለዋል፡፡

Read 3118 times