Saturday, 30 August 2014 10:49

የእኛ ችግር “የእውነት እጦት ነው”!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(11 votes)

በኢቴቪ “The Moments of Truth” የተባለ ፕሮግራም ያስፈልጋል!
ዓመታዊ “የእውነት ቀን” ይታወጅልን! (እውነት የምንናገርበት)
       መቼ ነበር ኢትዮ ቴሌኮም ከእንግዲህ የኔትዎርክና የኢንተርኔት መቆራረጥ ችግር አጠገባችሁ ድርሽ አይልም ብሎ መግለጫ የሰጠው? ባይገርማችሁ እንዲህ በተናገረ በሳምንቱ የቢሮአችን የስልክ መስመርም ሆነ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል፡፡ ይሄው አሁን ወር ሞላን - ያለ ቢሮ ስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት፡፡ ቀደም ሲል ደግሞ ለአራት ወር ገደማ ስልክም ኢንተርኔትም አልነበረንም (ድንቄም ከመጪው ዘመን ጋር መገናኘት!) የመብራቱን ነገርማ አታንሱብኝ፡፡ እንደፈቀደው ሆኗል፡፡ በቀን ሶስቴም አራቴም እየጠፋ ሲፈልገው ይመጣል፤ አሊያም ውሎ ያድራል - ሃይ ባይ እንዳጣ ጐረምሳ! በነገራችሁ ላይ ይሄን ብሶቴን ለእናንተ ለማጋራት ያህል እንጂ መንግስት እንዲሰማኝ አይደለም (መንግስትን ማሳቀቅ አልፈልግማ!)
እውነቱን ልንገራችሁ አይደል…የእኛ አገር ችግር ሌላ ሳይሆን “የእውነት” እጦት ነው፡፡ ከምሬ እኮ ነው… ከመብራትም፣ ከስልክም፣ ከትራንስፖርትም፣ ከዘይትም፣ ከስንዴም፣ ከስኳርም፣ ከሌላው ከሌላውም የበለጠ የተቸገርነው “እውነት”ን በማጣት ነው፡፡ (ወዶ አይደለም ገጣሚው “እውነትን ፍለጋ” ያለው!)
10 ዓመት ወደፊት ተጉዞ 5 ዓመት የኋሊት የመመለስ አባዜ፣ የገዢው ፓርቲ “ትክክለኛው መንገድ የእኔ ብቻ ነው” ባይነት፣ የተቃዋሚዎች ባሉበት መርገጥ፣ የነፃው ፕሬስ ያብባል ሲባል መክሰም፣ የመንግስት ሚዲያው የካድሬነት ባህርይ መባባስ፣ የባለስልጣናቱ ሙሰኝነት፣ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ እጦት… ወዘተ… ወዘተ… ወዘተ… የእነዚህ ሁሉ ስረ-ሰበብ አንድ ነው - “የእውነት እጦት” ለእውነት ክብር አለመስጠት፤ ለውሸት እጅ መስጠት!! በቃ ይሄው ነው፡፡
እዚህ አገር ጥናት አልተካሄደም እንጂ ቢካሄድ “የዓለም ቁጥር 1 ውሸታም” መባላችን አይቀርም ነበር፡፡ ውሸታችን በሞባይል ይጀምራል፡፡ ከፒያሳ ሳንነሳ ካዛንቺስ ደርሰናል፤ ካዛንቺስ ላይ ቆመን ቤተመንግስትን አልፈናል… እያልን እንዋሻለን፡፡ (“እናቴ፤ ምነው በእንቁላሉ ጊዜ በቀጣሽኝ” ማለት ይሄንን ነው”!)
ነገርዬው ኢህአዴግ ተቃዋሚ፣ ህዝብ ባለስልጣን፣ ተማሪ መምህር፣ የተማረ መሃይም፣ የናጠጠ ሃብታም የለየለት ድሃ፣ ወጣት ሽማግሌ፣ ወንድ ሴት … አይልም፡፡ ሁሉም የውሸት  ካፓውን አውልቆ የእውነት ካፓውን ካልደረበ በቀር የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ እናላችሁ… የዛሬ 50 እና 100 ዓመት ውሸትን የሚጠየፍ፣ ለእውነት ክብር የሚሰጥ “ሃቀኛ” ትውልድ እንዲፈጠር አሁን ትናንሽ ጥረቶች መጀመር አለባቸው - የእውነት ጥረቶች!!
ይኼውላችሁ .. ቢያድለን ኖሮ በየቀኑ፣ በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው፣ በየሰኮንዱ… ለእውነት መቆም፤ እውነት መናገር፤ ለሃቅ መታገል፤ ውሸትን መቃወም፤ ዋሾነትን መጠየፍ ይገባን ነበር፡፡ (ተውት! ለእኛ አላለውም!) እኒህን ብናደርግ ኖሮ ውስብስብ የችግር ተራራችን ተንዶ ይፈርስ ነበር፡፡
ሙሰኛ የበዛው ለምን ይመስላችኋል? ኢህአዴግ ቀን ተሌት የሚለፍፈውን መልካም አስተዳደር እውን ማድረግ ለምን አቃተው? (“የአፈፃፀም እንጂ የፖሊስ ችግር የለበትም” እንዳትሉኝ!) የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር እንዴት መፍታት አቃተን? ተቃዋሚዎቻችን ለምን በህብረት መታገል አልሆን አላቸው? ለሁሉም መልሱ “የእውነት እጦት” ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሃቀኞች እጥረት አለባት፡፡ (እውነት እንደጋዜጠኞቹ አገር ለቃ ወጥታለች!)
የሆኖ ሆኖ ዲሞክራሲም …መልካም አስተዳደርም… የመድብለ ፓርቲ ስርዓትም …ፍትሃዊ ምርጫም… ነፃ ፕሬስም…ትክክለኛ ዕድገትም…ያለ “እውነት” እውን አይሆኑም፡፡  
እናም ምን አሰብኩ መሰላችሁ? በዓመት አንዴ የምናከብረው “የእውነት ቀን” እንዲታወጅልን! የባንዲራ ቀን፣ የብሔር ብሔሰቦች ቀን፣ የከተሞች ቀን… ወዘተ እንደሚባለው ማለት ነው፡፡ ቢያንስ በዓመት አንዴ እውነት እንድናወራ፣ እውነት እንድንሰራ፣ እውነት እንድንመሰክር፣ ለአንድ ቀን የእውነት እንድንኖር… “የእውነት ቀን” ያስፈልገናል፡
በአሜሪካ “The Moments of Truth” የተባለ አዝናኝ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አለ፡፡ ሰዎች ስለግል ህይወታቸው የሚጠየቁበትና እስከ 100ሺ ዶላር የሚያሸልም ፕሮግራም ነው፡፡ ጥያቄዎቹ ግን የሚፈታተኑ ናቸው፡፡ እስቲ አስቡት… አንድ ሰው ሚስቱ፣ ቤተሰቡ፣ የመስሪያ ቤት አለቃው እና ሌሎች ታዳሚዎች በተሰበሰቡበት የህይወት ምስጢሩን፣ ከራሱ ውጭ ማንም የማያውቀውን የግል “እውነቱን” ይፋ እንዲያወጣ ሲጠየቅ! መዋሸት አይችልም - በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛ መልሱ እውነትና ውሸት መሆኑን የሚለይ ዘመናዊ መሳሪያ እዚያው ያጋልጠዋል (መሰልጠን ጥሩ ነው!)፡፡ የፈለገ ይምጣ ብሎ ቢዋሽ ደግሞ የገንዘብ ሽልማቱን ያጣል፡፡ ሽልማቱ እኮ ቀላል አይደለም - 500ሺ ዶላር ይደርሳል (በእኛ ወደ 10ሚ. ብር ገደማ መሆኑ ነው!)
እውነትን መናገር ያሸልማል - በ “Moments of Truth” ፕሮግራም፡፡ እንዳልኳችሁ ጥያቄው ግን ይፈታተናል፡፡ ለምሳሌ አንዱ ግለሰብ ከቀረቡለት ጥያቄዎች መካከል፤ “የሚስትህን ጓደኛ ለማቅበጥ ሞከርህ ታውቃለህ?” ይላል፡፡ ሚስቱ እዚያው ተቀምጣ እኮ ነው፡፡ ቀደም ብሎ ደግሞ እስከ ዕለተ ሞቱ ከእሷ ሌላ ሴት እንደማያይ እዚያው ይፋ አድርጐ ነበር፡፡ ከባድ አጣብቂኝ ነው፡፡ ከብዙ ጭንቀትና ማብሰልሰል በኋላ “አዎ … የሚስቴን ጓደኛ ለማቅበጥ ሞክሬአለሁ” አለ-በዚያች እውነትን የመናገርያ ቅፅበት!!
አንዷ የ“ሚስ አሜሪካ” አሸናፊ ቆንጆ ደግሞ በእናቷና እንደሷው ውብ በሆነች ታናሽ እህቷ ፊት እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀረበላት፤ “ከእህቴ የበለጠ አምራለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?” መልስዋ “አዎ” ነበር፡፡ ውሸትና ማስተባበል በ “Moment of truth” አይሞከርም፡፡ ብዙ ህሊናን የሚፈታተኑ ጥያቄዎች ይሰማሉ - በፕሮግራሙ ላይ፡፡
እኔ ታዲያ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተመሳሳይ ፕሮግራም ቢጀመርስ አልኩ - “እውነትን ፍለጋ” የሚል!! የእኛ ታዲያ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ፖለቲከኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ወዘተ… የሚፋጠጡበት ነው፡፡ ባይሆን ሽልማቱን ትንሽ ከፍ ማድረግ ይሻላል፡፡ (እውነቱ እንዲወጣ ምንስ ቢከፈል?!)
እናላችሁ… በዚህ አዲስ የቲቪ ፕሮግራም አማካኝነት … የባለስልጣናቱንና ፖለቲከኞቹን እውነተኛ ማንነት እናውቃለን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ለአንዱ ከፍተኛ የኢህአዴግ አመራር እንዲህ የሚል ጥያቄ ሊቀርብለት ይችላል፡፡ “ኢህአዴግ ተቃዋሚ የሚባል ባይኖር ደስታውን አይችለውም?” እውነት ወይስ ሃሰት? በዚህ ፕሮግራም ፕሮፓጋንዳ ቦታ የለውም - እውነት ብቻ! ያለዚያ እኮ እውነትና ውሸቱን የምትለየዋ ዘመናዊ ማሽን አለች፡፡
ሌላ የ“እውነትን ፍለጋ” ጥያቄ እነሆ፡፡ ይሄኛውም ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር የሚቀርብ ነው፡፡ “የተከሰሱት ጋዜጠኞች ከአገር የወጡት በኢህአዴግ ግፊት ነው?” እውነት ወይስ ሃሰት? በዚህ ፕሮግራም ስም ማጥፋት ምናምን የሚባል ነገር የለም (እውነትን ማወጣጫ ፕሮግራም እኮ ነው!) “ኢህአዴግ በተለያዩ ምርጫዎች በአባላቱ የተፈፀሙ የድምፅ ማጭበርበሮችን እንዳላየ ሆኖ አልፏል?” ትንሽ ከበድ ቢልም ተገቢ የ“Moment of Truth” ጥያቄ ነው፡፡
ለተቃዋሚ ከፍተኛ አመራሮች ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል ደግሞ አንዱ እንዲህ የሚል ሊሆን ይችላል:-
“ተቃዋሚዎች ህዝብ ህዝብ የሚሉት ሥልጣን እስኪይዙ እንጂ ከስልጣን በኋላ ህዝቡን ይረሱታል?” እውነት ነው ውሸት? ፕሮግራሙ ሲጀመር የምናረጋግጠው ጉዳይ ይሆናል፡፡
ይሄውላችሁ .. በዓመት አንዴ በሚከበረው “የእውነት ቀን” እና በዚህ “እውነትን ፍለጋ” የቲቪ ፕሮግራም አማካኝነት …. ከእውነት ጋር እየተዋወቅን መሄዳችን አይቀርም፡፡ ሆኖም ኢህአዴግ ሁሌ እንደሚለው “እውነትም ብትሆን በአንድ ቀን ጀምበር አትመጣም፣ በሂደት ነው” ልክ እንደ ዲሞክራሲውና እንደ መልካም አስተዳደር ሁሉ፡፡ ለመንግስት ባለስልጣናትና ለተቃዋሚ አመራሮች እንዲቀርብላችሁ የምትፈልጉት ጥያቄ ካለ ላኩልን፡፡ መጪውን ዓመት ከእውነት ጋር የምንታረቅበት ዘመን ያድርግልን!! (አሜን ያድርግልን!)  

Read 3271 times