Saturday, 30 August 2014 10:47

የደጃች ውቤ የልማት ተነሺዎች በተሰጣቸው ተለዋጭ ቦታ ቅር ተሰኝተዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

            በተለምዶ ደጃች ውቤ ሰፈር እየተባለ በሚጠራውና በቀድሞ 05 ቀበሌ፣ በአሁኑ 03/09 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ ከ200 በላይ የልማት ተነሺዎች በተሰጣቸው ምትክ ቦታ ቅር መሰኘታቸውን ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡
መስከረም 11 ቀን 2006 ዓ.ም በሃገር ፍቅር ትያትር ቤት አዳራሽ ለስብሰባ ተጠርተው ከአራዳ ክፍለ ከተማ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይት “ከመሃል ከተማ ለልማት ተነሺ ስለሆናችሁ አራት ኪሎ ትገባላችሁ” በመባላቸው መደሰታቸውን የልማት ተነሺዎቹ ያስታውሳሉ፡፡ “ይህንን ቃል ተማምነን ተነሱ እስክንባል እየጠበቅን ነበር” ያሉት አንድ የ76 ዓመት የአካባቢው ነዋሪ፤ “አሁን ከአዲስ አበባ ውጭ መሰረተ ልማቱ ያልተሟላበት ቦታ ሂድ መባሌ በዚህ እድሜዬ የማልቋቋመው ችግር ነው” ብለዋል፡፡
 ባለፈው ረቡዕ እጣ አውጡ ተብለው ሲጠሩ የደረሳቸው ቦታ “ገላን“ የሚባል ውሃ፣ መብራት፣ ት/ቤትና ጤና ጣቢያ ያልተሟላለት አካባቢ በመሆኑ ማዘናቸውን የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ “ለ50 እና 60 ዓመት ቆሎ እና እንጀራ እየሸጠ የኖረ ማህበረሰብ ምንም እንቅስቃሴ ወደሌለበትና ከከተማ ውጭ ወደ ሆነ ቦታ መወርወሩ ጦም እደሩ ከማለት አይተናነስም” ብለዋል፡፡ ረቡዕ እለት የአዲስ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኤጀንሲ አቤቱታቸውን ለማሰማት መሄዳቸውን የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ኃላፊዎቹ “በጉዳዩ ላይ ተመካክረን ምላሽ እንሰጣችኋለን” በማለት ለትላንትና ጠዋት ቀጠሮ ሰጥተዋቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በቀጠሮአቸው መሰረት ወደ ከተማው ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ሲሄዱ ግን “ጉዳዩ ከእኛ አቅም በላይ በመሆኑ ለከንቲባው ጽ/ቤት አመልክቱ” የሚል ምላሽ ከኃላፊዎቹ እንዳገኙ ገልፀዋል፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተሰባስበው ወደ ከንቲባው ጽ/ቤት መሄዳቸውን ጠቁመው እዚያም “ጉዳያችሁን ለከንቲባው ለማድረስ የቀጠሮ ደብዳቤ አፅፉ ተብለን ደብዳቤውን አፅፈናል” ብለዋል፡፡ ሆኖም ይሄ ጉዳይ ነገሩን የሚያጓትት በመሆኑ ደስተኛ አይደለንም ይላሉ፡፡
የደብዳቤውን ምላሽ ለማግኘትና ሌላ ቀጠሮ ለመያዝ የከንቲባው ጽ/ቤት ለሰኞ ስምንት ሰዓት እንደቀጠራ ቸውም ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩን ለማጣራት የከተማው ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ መስፍን መንግስቱን ለማግኘት በስልክ ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Read 3212 times