Saturday, 30 August 2014 10:45

አንድነት ፓርቲ አዲስ ካቢኔ አዋቀረ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(6 votes)

           አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ፤ በቅርቡ ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በፍቃዳቸው በለቀቁ  ግለሰቦች ቦታ አዳዲስ አመራሮችን ተክቶ አዲስ ካቢኔ ያዋቀረ ሲሆን ፓርቲው ከመኢአድ ጋር የጀመረው የውህደት ሂደት እስኪሳካ ድረስ የፖለቲካ እንቅስቃሴውን በተናጠል እንዲያካሂድ ተወስኗል፡፡
የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ አባላት የነበሩት ግለሰቦች ከስራቸው የለቀቁት ከፕሬዚዳንቱ ጋር በተለያዩ የአሠራር ጉዳዮች በሃሳብ ያለመግባባት በመፈጠሩ እንደሆነ የጠቆሙት የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ስዩም መንገሻ፤ አምስቱ ግለሰቦች ከሃላፊነታቸው ቢለቁም በብሔራዊ ምክር ቤትና በሌሎች ፓርቲው በሚፈልጋቸው ቦታዎች መደበኛ ተግባራቸውን እንደሚቀጥሉ መግለፃቸውን ተናግረዋል፡፡
የፓርቲው ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ከአመራሮቹ የቀረበላቸውን ከሃላፊነት የመልቀቅ ጥያቄ ተቀብለው ባለፈው እሁድ አዲስ ካቢኔ ማዋቀራቸውን የገለፁት አቶ ስዩም፤ ከተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚደንትነታቸው በለቀቁት አቶ ተክሌ በቀለ ቦታ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ ሲተኩ፣ በምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ በላይ ፍቃዱ ቦታ አቶ ብሩ ብርመጂ፣ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ በነበሩት አቶ ዳንኤል ተፈራ ቦታ አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን፣ የፖለቲካ ጉዳይ ሃላፊ በነበሩት አቶ ሰለሞን ስዩም ቦታ አቶ እንዳለ ወ/ፃዲቅ፣ የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሃላፊ በነበሩት አቶ ዳዊት አሽራደን ቦታ ደግሞ አቶ ትንሣይ ተባሳ እንዲተኩ መደረጉን ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የተሰጣቸውን ሃላፊነት በሚፈለገው አግባብ አልተወጡም በተባሉት የህግና ሰብአዊ መብት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ነገሠ ታደሰ ቦታ አቶ ደምሴ መንግስቱ የተተኩ ሲሆን የፋይናንስና ንብረት ሃላፊ በነበሩት አቶ አስቻለው ከተማ ቦታ አቶ ነገሠ ተፈረደኝ መተካታቸው ታውቋል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ በነበሩትና በእስር ላይ በሚገኙት አቶ ሃብታሙ አያሌው ቦታ ሰው ለመመደብ የፍ/ቤት ሂደቱን መጠበቅ አስፈልጓል ያሉት ዋና ፀሐፊው፤ ለጊዜው የህዝብ ግንኙነቱን ቦታ ፕሬዚዳንቱና ተወካዮቻቸው ይሸፍኑታል ብለዋል፡፡
አዲሱ ስራ አስፈፃሚ በቅርቡ ተሰብስቦ በመወያየት በቀጣይ አመት ፓርቲው በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖረውን እንቅስቃሴ ወስኖ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል፤ ዋና ፀሐፊው፡፡
የመኢአድ እና የአንድነት ውህደት ከጫፍ ደርሶ ምርጫ ቦርድ “መኢአድ ምላተ ጉባኤ አላሟላም” በሚል የውህደቱን ጥያቄ አልቀበልም ማለቱን ያስታወሱት አቶ ስዩም፤ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት ተሰብስቦ ጉዳዩን መመርመሩን ጠቅሰው፣ ከዚህ በኋላ አንድነት ቀደም ሲል በተናጥል ወደሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ ሃይሉ እንዲገባ፣ የውህደቱን ጉዳይም እንዲከታተል ተወስኗል ብለዋል፡፡
አንድነትና መኢአድ ውህደት ለመፈፀም እንቅስቃሴ የጀመሩት ከ4 አመት በፊት መሆኑን የጠቆሙት ዋና ፀሐፊው፤ የውህደት ፍላጐቱ ምርጫን ታሳቢ ያደረገ ሳይሆን ቀደም ብሎም የታሰበበት ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

Read 3240 times