Saturday, 30 August 2014 10:44

“ሲኒመር አክሲዮን ማህበር” ሪዞርቶችና ሎጆችን ይገነባል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

           በአዲስ አበባ በ5 ዓመት ውስጥ 20 ዘመናዊ ሲኒማ ቤቶችን እንደሚገነባ ያስታወቀው “ሲኒመር” ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር፤ በተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ሪዞርቶችንና ሎጆችን እንደሚያስገነባም አስታወቀ፡፡
80 ሚሊዮን ብር ገደማ በጀት የተያዘለት 22 አካባቢ የሚገነባው ህንፃ፤ 7 ሲኒማ ቤቶች ሲኖረው፣ ቦሌ ደንበል አካባቢ ይገነባል ተብሎ የታቀደው ህንፃ 4 ሲኒማ ቤት ይኖረዋል ተብሏል፡፡ በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ በሌሎች የተመረጡ አካባቢዎችም ተጨማሪ ሲኒማ ቤቶች እንደሚገነቡና ሁሉም ህንፃዎች የገበያ ማዕከል እንደሚኖራቸው ታውቋል፡፡
የአብነት፣ 22 አካባቢ እና የቦሌ ደንበል አካባቢ ህንፃዎች በተጨባጭ እንደሚገነቡ አረጋግጠናል ያሉት የአክሲዮን ማህበሩ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ሰለሞን፤ ቸርችል ጎዳና አካባቢ ይገነባል ተብሎ ለታሰበው ማዕከል የሚያስፈልገውን ቦታ ለመረከብ በድርድር  ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
እስከ 2011 ዓ.ም 20 ሲኒማ ቤቶች ለመገንባት እቅድ መያዛቸውን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ፤ “ከሲኒማ ቤቶቹ ግንባታ ባሻገር በሃገራችን ባልተለመደ መልኩ በሲኒማ ቤቶች የሚታዩ ፊልሞች በየማእከላቱ በሚቋቋሙ የፊልም ጥገና ክፍሎች ለተመልካቹ በሚስማማ መልኩ ታርመው እንዲቀርቡ ይደረጋል፣ ይህም በፊልሙ ፕሪዱዩሰሮችና በሲኒማ ቤቱ መካከል በሚደረግ መግባባት ይከናወናል” ብለዋል፡፡ የፊልም ጥገና ክፍሉ (ሙቪ ሰርጀሪ ሩም) በብቁ ባለሙያዎች የተደራጀ እንደሚሆንም ስራ አስኪያጁ አክለው ገልፀዋል፡፡
የሲኒማ ማዕከላቱ ከመደበኛው አገልግሎታቸው ባሻገር የህጻናት መጫወቻዎችና የህክምና ተቋማትን ጨምሮ የንግድ ማዕከሎችን እንደሚያካትቱም ታውቋል፡፡ ትልልቆቹ ሲኒማ ቤቶች ከ350-420፣ መካከለኞቹ ከ180-220 ሰዎችን የሚያስተናግዱ ሲሆን የዲ-ቴክኖሎጂ ታሳቢ በማድረግ ከ50-60 ሰዎችን ሊይዙ የሚችሉ ሲኒማ ቤቶችም ይዘጋጃሉ ብለዋል፤ አቶ መስፍን፡፡
ሲኒመር ትሬዲንግ አክሲዮን ማህበር ከሲኒማ ቢቶች በተጨማሪም በቱሪዝም ውስጥ የሚሳተፍ ሲሆን በላንጋኖ፣ በአብያታና ሾላ ብሄራዊ ፓርክ ውስጥ እንዲሁም በዝዋይ ሃይቅ ዙሪያ ዘመናዊና ባህላዊነትን አዋህደው የያዙ ሎጆች እና ሪዞርቶች ለመገንባት ቅድመ ሁኔታዎችን አጠናቋል ተብሏል፡፡
ላንጋኖ ለሚገነባው ሪዞርት 25ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ መረከባቸውን እንዲሁም በአብያታ ሻላ  ፓርክ ውስጥ 30ሺህ ካሬ.ሜትር ቦታ በማስፈቀድ ሂደት ላይ መሆናቸውን አቶ መስፍን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ አክሲዮን ማህበሩ ለወደፊት ጥናት ላይ ተመስርቶ የመኖሪያ ቤቶችንም ለመገንባት እቅድ መያዙ ታውቋል፡፡
የአክሲዮኑ አደራጅና መስራች አቶ መስፍን ሰለሞን፤ የፊልም ደራሲና ዳይሬክተር ሲሆኑ ከዚህ ቀደም ፖለቲካዊ ይዘት ያለው “ኢታቦል” የተሰኘ ፊልም አቅርበዋል፡፡ በቅርቡም አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑን ጨምሮ ታዋቂ አርቲስቶች የተሳተፉበት “ቬኔሲያ” የተሰኘ ፊልም ለእይታ እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል፡፡  

Read 2318 times