Saturday, 30 August 2014 10:43

ለአዲስ አበባ የመጀመሪያው የከተማ ባቡር ተሰርቶ ተጠናቀቀ

Written by 
Rate this item
(10 votes)

ለአዲስ አበባ ከተማ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት 41 ባቡሮችን ለመስራት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ስምምነት የፈጸመውና ካለፈው ግንቦት ወር ጀምሮ ስራውን በማከናወን ላይ የሚገኘው ‘ቻይና ሲ ኤን አር ቻንግቹን ሬልዌይ ቪሄክልስ’ የተባለው የቻይና ባቡር አምራች ኩባንያ የመጀመሪያውን ባቡር ሰርቶ ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡
የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ሊዩ ጋንግ፣ ባቡሩ በሰዓት 70 ኪሎሜትሮች የመጓዝ አቅም እንዳለው፣ ነጭና አረንጓዴ ቀለም እንዳለው እንዲሁም ለተሳፋሪዎች ምቹ በሆነና የጸሃይ ብርሃንን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ ዲዛይን መደረጉን ለቻይናው የዜና ወኪል ዥንዋ ተናግረዋል፡፡“በመጪው መስከረም ወር 50 ኢትዮጵያውያን የባቡር አሽከርካሪዎችንና የጥገና ሰራተኞችን ወደ ኩባንያችን በማስመጣት አስፈላጊውን ስልጠና ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው” ያሉት ስራ አስኪያጁ፣ ኩባንያው ሁሉንም ባቡሮች በታሰበው የጥራት ደረጃ ሰርቶ ለማጠናቀቅና በተቀመጠው ጊዜ ለማስረከብ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡የመገጣጠም ስራው ሙሉ ለሙሉ የተጠናቀቀው የመጀመሪያው ባቡር፣ በቻይና የሰሜን ምስራቅ ግዛት ጂሊን ውስጥ በምትገኘውና የኩባንያው መቀመጫ በሆነችው ቻንግቹን ከተማ ባለፈው ማክሰኞ የተሳካ የሙከራ ጉዞ እንዳደረገ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የባቡር ስራውን ለኩባንያው የሰጠው ባለፈው ግንቦት ወር መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኩባንያው እስከ መጪው ጥር ወር ሁሉንም ባቡሮች አጠናቆ ለማስረከብ ተዋውሎ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስረድቷል፡፡
የከተማ ባቡር ትራንስፖርት በአፍሪካ አህጉር በጅማሬ ላይ ያለ ዘርፍ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከደቡብ አፍሪካ በስተቀር በሌሎች አገራት እምብዛም አለመስፋፋቱንና ይህም ለቻይና የባቡር አምራች ኩባንያዎች ከፍተኛ የገበያ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነ አመልክቷል፡፡
በአህጉሪቱ ቀላል የከተማ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተዘረጋባቸው አገራት አልጀሪያ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ እንደሆኑ የጠቀሰው ዘገባው፤ የምድር ውስጥ የባቡር መስመር ያለባቸው የአፍሪካ ከተሞች ደግሞ ካይሮና አልጀርስ ብቻ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡

Read 6336 times