Print this page
Saturday, 30 August 2014 10:33

ጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱ በአርቲስት ዳንኤል ተገኝ መደብደቡን ገለፀ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

“ነገር የፈለገኝ እሱ ስለሆነ ክስ መስርቻለሁ”

በዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 የሬዲዮ ጣቢያ የሚተላለፈው “ኢትዮፒካሊንክ” አዘጋጅ ጋዜጠኛ ግዛቸው እሸቱ በአርቲስት ዳንኤል ተገኝ መደብደቡንና ግራ አይኑ ላይ ባረፈበት ቡጢ ክፉኛ ተጐድቶ ህክምና እየተከታተለ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ገለፀ፡፡ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በበኩሉ፤ ቀድሞ ነገር የፈለገኝ እሱ በመሆኑ ላደረሰብኝ በደልና መጉላላት ክስ መስርቼበታለሁ ብሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ ገልፍ አዚዝ ህንፃ 4ኛ ፎቅ ላይ ከሚገኘው ቢሮው ወጥቶ መኪናውን ወዳቆመበት ቦታ በመሄድ ላይ እያለ “አንተ የእኔን ህይወት አበላሽተህ በሰላም ትኖራለህ?” የሚል ድምጽ መስማቱንና ወደኋላው መዞሩን የገለፀው ጋዜጠኛው፤ ከመቅጽበት ግራ አይኑን በቡጢ መመታቱን ተናግሯል፡፡ ከዚያም ለፖሊስ ተደውሎ ወደ ካራማራ ፖሊስ መወሰዳቸውን የገለፀው ግዛቸው፤ ለፖሊስ ቃሉን ከሰጠ በኋላ ወደህክምና ማምራቱን ጨምሮ ገልጿል፡፡
“በዚህ ዓመት ታህሳስ ወር ላይ አርቲስቱ ወ/ሮ ቤተልሄም አበበ ከተባሉ ግለሰብ ጋር ፊልም ለመስራት ከተፈራረመ በኋላ ወ/ሮዋ  “ፊልሙንም አልሰራም፤ ገንዘቤንም አልመለሰም” በሚል ክስ መስርተው ጉዳዩ ፍ/ቤት ቀርቦ በሰራነው ዘገባ ቂም ይዞ ደብድቦኛል” ብሏል፤ ጋዜጠኛው፡፡ “ዜናው በተሰራ በሳምንቱ የስራ ባልደረባዬን ዮናስ ሃጐስን ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ውስጥ ለመደብደብ ሙከራ አድርጐ ነበር” ያለው ጋዜጠኛው፤ ይሁን እንጂ ሁኔታዎች አመቺ ስላልሆኑለት ዝቶበት ሄዶ ነበር ብሏል፡፡ “ጉዳዩ በእኔ ብቻ ሳይሆን በሙያውና በድርጅታችን እንዲሁም በመላው ጋዜጠኛ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ያለው ግዛቸው፤ ሃኪሞች ዓይኔ ላይ ለደረሰብኝ ጉዳት የ10 ቀን የህክምና ክትትል እንደሚያስፈልገኝ ነግረውኛል ብሏል፡፡ በካራማራ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ፖሊስ የሆኑትና ጉዳዩን የያዙት ምክትል ሳጂን ዋቅቶላ ቡሊ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ድርጊቱ በተፈፀመበት ዕለት (ነሐሴ 12) አርቲስት ዳንኤል ተገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ማደሩንና በነጋታው ቦሌ ምድብ ፍ/ቤት ቀርቦ፣ በሶስት ሺህ ብር ዋስ ተፈትቷል፡፡ አርቲስት ዳንኤል ተገኝ በበኩሉ፤ “መጀመሪያ ነገር የፈለገኝ እሱ ነው፤ እንደተያየን “እኔና አንተ ቆይ ለብቻችን እንገናኛለን” አለኝ፤ “ከእኔ ምን ጉዳይ አለህ ስለው?” ጃኬቴን ቀደደብኝ” ብሏል፡፡
“ከዚህ በፊት ምንም ዐይነት ፀብ የለንም፤ ምናልባት  በሰራው ሚዛናዊ ያልሆነ ዘገባ በስም ማጥፋት ወንጀል ማዕከላዊ ክስ መስርቼበት ስለነበር ቂም ይዞ ይሆናል” ያለው አርቲስቱ፤ ጠቡ ወ/ሮ ቤተልሄም ከተባሉት ግለሰብ ጋር የሚገናኝ ነገር እንደሌለው ተናግሯል፡፡
አይኑን በቡጢ መቶት እንደሆነ የተጠየቀው አርቲስቱ፤ “በወቅቱ ተያይዘን ስለወደቅን የሆነውን አላስታውስም” ብሏል፡፡ ጋዜጠኛው “በእኔ ላይ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ጋዜጠኞች ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” በማለት ለፖሊስ ቃል መስጠቱን ያስታወሰው አርቲስት ዳንኤል፤ “ከጋዜጠኞች ጋር የነበረኝን መልካም ግንኙነት ለማበላሸት ሆን ብሎ የጠነሰሰው ሴራ ነው” ብሏል፡፡
 

Read 2155 times