Saturday, 30 August 2014 10:30

ጋዛ - ከእንባ ወደ እልልታ…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

           ለሰባት ሳምንታት የማያባራ የሮኬት ድብደባ ሲወርድባት የዘለቀች፣ 490 ያህል ጨቅላዎቿን ጨምሮ 2 ሺህ 142 ዜጎቿን በሞት የተነጠቀች፣ አይሆኑ ሆና የፈራረሰችው ጋዛ፤ ከከረመባት መከራና ስቃይ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን እፎይ አለች፡፡ ባለፈው ማክሰኞ አመሻሽ ላይ፣ ተረኛውን ሮኬት በፍርሃት እየተርበተበቱ የሚጠብቁት የጋዛ ሰዎች፤ ያልጠበቁትን ከወደ ካይሮ ሲደገስ የሰነበተ አንዳች በጎ ነገር አደመጡ፡፡ የፍልስጤሙ ፕሬዚደንት ማሃሙድ አባስ ከወደ ዌስት ባንክ ይፋ ያደረጉት መረጃ፣ እርግጥም ጧት ማታ በሮኬት ድብደባ አሳር መከራዋን ስታይ ለነበረችው የፈራረሰችው ጋዛ ትልቅ የምስራች ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ እስራኤል በፍልስጤም የቀረበውን የተኩስ አቁም ስምምነት በጄ ብላ መቀበሏን ማብሰራቸውን፣ ሃማስም የድል ብስራት ዜናውን ለጋዛ ነዋሪዎች በአጭር የጽሁፍ መልዕክት ማድረሱን ተከትሎ፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በጋዛ ጎዳናዎችና በአደባባዮች ወጥተው ደስታቸውን ገለጹ፡፡ ጣቶቻቸውን ከፍ አድርገው በማውጣት የ v ምልክት አሳይተዋል - “ድል ለፍልስጤም ሆነ!” ለማለት፡፡ የሃማሱ ምክትል መሪ ሞሱአ አቡ ማርዙክም ቢሆኑ፣ እስራኤል የቀረበላትን የተኩስ አቁም ስምምነት ሃሳብ መቀበሏ፣ ለሃማስ ትልቅ ድል ነው ብለዋል፡፡ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቃል አቀባይ ኦፊር ጌንዴልማን በበኩላቸው፤ አገሪቱ በጋዛ ስታደርገው የነበረው ወታደራዊ ዘመቻ በድል መጠናቀቁን ነው የሚናገሩት፡፡

ሃማስ ከዚህ ቀደም በግብጽ ቀርቦለት አሻፈረኝ ያለውን የሰላም ሃሳብ ነው መልሶ የተቀበለው ይላሉ ቃል አቀባዩ፡፡ በግጭቱ 69 ያህል ዜጎቿን ያጣችው እስራኤል የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት ማርክ ሬጌቭ በበኩላቸው፣ ሃማስ ባለፈው ሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ የቀረበለትን የሰላም ስምምነት ሃሳብ በወቅቱ ቢቀበል ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ደም መፋሰስ ባልኖረ ነበር በማለት ተጠያቂነቱን ወደ ሃማስ አድርገዋል፡፡ ስምምነቱን እውን ለማድረግ ደፋ ቀና ሲሉ ለቆዩት ለግብጽ፣ ለኳታርና ለአሜሪካ ምስጋና ይግባቸውና፣ አሁን ደም አፋሳሹ የሁለቱ አገራት ግጭት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ጋብ ብሎ የሚቆይበት ሁነኛ የተኩስ አቁም ስምምነት በሁለቱ ሃይሎች መካከል እንዲደረስ አስችለዋል፡፡ የአልጀዚራው ዘጋቢ አንድሪው ሲሞንስ ከጋዛ በላከው ዘገባ እንዳለው፣ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰው ስምምነት፣ እስራኤል የዘጋቻቸውን የጋዛ መግቢያዎች በአፋጣኝ እንድትከፍትና በሂደትም በጋዛ ሰርጥ አካባቢ የጣለችውን የእንቅስቃሴ ገደብ እንድታነሳ የሚያደርግ ነው፡፡ በእስራኤልና በፍልስጤም መካከል ተጀምሮ የተቋረጠው ውይይትም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚቀጥል ዘግቧል፡፡ሃማስ በቀጣይ በጋዛ ውስጥ የአየር ማረፊያና የባህር ወደብ ማቋቋም ይገባኛል፣ ፍልስጤማውያን እስረኞችም መፈታት ይኖርባቸዋል እያለ ሲሆን እስራኤልም የጋዛን ነዋሪዎች ሙሉ ለሙሉ ትጥቅ ማስፈታት እፈልጋለሁ እያለች ነው፡፡ እንዲህ እና እንዲያ ያሉ ከግራና ቀኝ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ በሁለቱ ሃይሎች መካከል ይካሄዳል በተባለው ቀጣይ ውይይት እልባት ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ጨምሮ ገልጧል፡፡

ስምምነቱ ጋዛን ከግብጽ ጋር የሚያዋስነው 9 ማይል የሚረዝመው የራፋህ ድንበር እንዲከፈት፣ የጋዛ ድንበሮች በፍልስጤም ሃይሎች ቁጥጥር ውስጥ እንዲሆኑና የመልሶ ግንባታ ስራውን የመምራት ሃላፊነቱንም የፍልስጤም መንግስት እንዲወስድ የሚያደርግ ሲሆን፣ እስራኤልም በጋዛ ውስጥ ያላትን የደህንነት እንቅስቃሴ አሁን ካለበት 300 ሜትር ክልል ወደ 100 ሜትር እንድትቀንስ፣ ከአየርና ከምድር የምትሰነዝረውን ወታደራዊ ጥቃት እንድታቆም የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡ በሁለቱ ሃይሎች መካከል የተደረሰው ይህ ስምምነት እንደሚለው፣ የፍልስጤም መንግስት የጋዛን ድንበር ከሃማስ ሃይሎች ተረክቦ የመቆጣጠር ሃላፊነቱን ይወስዳል፤ እስራአልም ከጋዛ ድንበር በሶስት ማይል ርቀት ገድባው የነበረውን የአሳ ማስገር ስራ ወደ ስድስት ማይል ማስፋት ይጠበቅባታል፡፡ ስምምነቱ በጋዛ ሰማይ ላይ የሰላም አየር መንፈስ ለመጀመሩ ማሳያ ነው ቢባልም ታዲያ፣ የማህበረሰብ መሪዎች ግን፣ ህዝቡ ወደቤቱ እንዳይመለስ እየመከሩ ነው ተብሏል፡፡ ጋዛ አሁንም ገና ከስጋት አልወጣችም የሚል አመለካከትም በብዙዎች ዘንድ ይንጸባረቃል፡፡

Read 2563 times