Saturday, 30 August 2014 10:15

ነባር አዙሪት፣ ሰሞነኛ ወሬ

Written by 
Rate this item
(13 votes)

          ለአመታት ያላቋረጠው የአገራችን የፖለቲካ ድራማ፣ ዛሬም ከአዙሪት የመላቀቅ ምልክት አይታይበትም። ሰሞኑን በስፋት የተሰራጩ ሁለት ወሬዎችን ብቻ እንመልከት። አንደኛው ወሬ፣ በኢህአዴግ ባለስልጣናት ላይ ያተኮረ ነው። ሌላኛው ደግሞ በግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ላይ ያነጣጠረ።
በእርግጥ ወሬዎቹ እንደ ትኩስ “ዜና” ቢሰራጩም፣ አዲስ “መረጃ” አይደሉም። ከነጭራሹ የመረጃ ሽራፊ እንኳ የላቸውም። “የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች፣ ከተለያዩ የውጭ ሃይሎች ወይም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ” እየተባለ በመንግስት ሚዲያ ሲነገር ሰምታችሁ አታውቁም? በተደጋጋሚ ተወርቷል። ከሰሞኑም እንደገና ተከልሶ እንደ አዲስ ሲወራ ሰንብቷል። ግን፣ የትኛው ጋዜጣና መፅሔት መቼ፣ ምን ያህል ገንዘብ ከማን እንደተቀበለ በግልፅ አይልተጠቀሰም። ተጠቅሶም አያውቅም። ተጨባጭና ግልፅ መረጃ ይቅርና፣ ጠቋሚ መረጃ እንኳ ለማቅረብ አልተሞከረም። ጭፍን ውንጀላ ብቻ!
ሁሉም የግል ጋዜጦችና መፅሔቶች ከነውር ንፁህ ናቸው ማለቴ አይደለም። አንዳንዶቹ ንፁህ ላይሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን፣ “ነውር ይፈፅማሉ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ልሳን ናቸው” በማለት ያለ አንዳች መረጃ በተደጋጋሚ ወሬ ማሰራጨት ግን፣ ከተራ የስም ማጥፋት ወይም የስም ማጉደፍ ዘመቻ አይለይም። ታዲያ ለምን የመንግስት ሚዲያና የኢህአዴግ ደጋፊዎች ይህን መረጃ አልባ ወሬ ያሰራጫሉ? ያው... ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማሳጣትና ለማብጠልጠል፣ እንዲሁም ዜጎችንና ጋዜጠኞችን ለማስፈራራት እስካገለገለ ድረስ፣ የሃሰት ወሬ ማሰራጨት ችግር የለውም - ለጭፍን የገዢ ፓርቲ ደጋፊዎች።
ሁለተኛው ወሬም እንዲሁ ያለ ምንም ተጨባጭ መረጃ ነው የተሰራጨው - በጭፍን ተቃዋሚዎች። “በርካታ የኢህአዴግ መሪዎችና ባለስልጣናት በአለማቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ተከሰሱ” የሚለው ወሬ እንደካሁን በፊቱ ባለፉት ቀናትም በብዛት ተሰራጭቷል። ወሬው ሲሰራጭ፣ “እስቲ በፍርድ ቤቱ (በአይሲሲ) ድረገፅ ላይ መረጃ ካለ ለማየት እንሞክር” የሚል ሰው አልተገኘም።
በፍርድ ቤቱ አሰራር፣ ከክስ በፊት መደበኛ ምርመራ ይካሄዳል። ከመደበኛ ምርመራ በፊት ደግሞ መነሻ ፍተሻ አለ። በተለያዩ አገራት፣ በርካታ መንግስታትና ባለስልጣናትን እንዲሁም ታጣቂ ድርጅቶችንና እንደ ኢራቅ አሸባሪዎች የመሳሰሉ ቡድኖችን በተመለከተ ምርመራና ፍተሻ እያካሄደ እንደሆነ አይሲስ በድረ ገፁ ይዘረዝራል። ግን፣ በአገራቱ ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያ ስም አልተጠቀሰም። እና ለምን፣ ወሬው ያለ መረጃ ተሰራጨ? ያው... ገዢውን ፓርቲ ለማጥላላት፣ ለማንቋሸሽ እስካገለገለ ድረስ ችግር የለውም።
በየጎራው የተቧደኑት ጭፍን ፊታውራሪዎችና ቲፎዞዎች፤ በየፊናቸው የሚያሰራጩት የወሬ አይነት ይለያያል። ነገር ግን፣ በባሕሪያቸው በጣም ተመሳሳይ ናቸው። “ተቀናቃኝ ወገንን ለመወንጀል የሚያገለግል እስከሆነ ድረስ፤ ተጨባጭ መረጃ ሳያስፈልግ ማንኛውንም ወሬ ማሰራጨት ይቻላል” በሚለው ሃሳብ ይስማማሉ። ዛሬ የሚያሰራጩት ወሬ፣ ውሎ አድሮ ሃሰት እንደሆነ ቢታወቅ እንኳ፣ ያን ያህልም አያሳስባቸውም። “የሃሰት ወሬ የተሰራጨው ለበጎ አላማ ስለሆነ አያስነውርም” ብለው ያስባሉ። ምን አይነት በጎ አላማ? “ለአገር እድገትና ልማት፣ የአገርን ክብር ለመጠበቅና የአገርን ገፅታ ለማሳመር፣ የድሃውና የሰፊውን ሕዝብ ጥቅም ለማስከበር” ሲባል ነው ወሬው የተሰራጨው በማለት ማመካኛ ያቀርባሉ። “ለብሔር ብሔረሰብና ለባህል በመቆርቆር፣ ለሃይማኖት ቀናኢነትን ለማሳየትና የአምላክን ትዕዛዝ ለማስፈፀም በማሰብ ነው ወሬው የተሰራጨው” በማለትም ራሳቸውን ያሳምናሉ።

በነሱ ቤት፣ ለበጎ አላማ የሃሰት ወሬ ማሰራጨት መደበኛ የሕይወት ዘይቤ ነው።
በአሳዛኙ ነገር ምን መሰላችሁ? የበጎ ነገሮች ሁሉ ምንጭ የሆነውን ነገር እየናዱት ነው - ማለትም እውነትን ዋጋ እያሳጡ የእውነትን ክብር እያረከሱ ናቸው። በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ስለ “እውነት” መነጋገር፣ ከንቱ “ቲዎሪ” ሊመስል ይችላል። ስለሚመስልም ነው፣ ከአመት አመት እየተደናበርን ከአዙሪት መውጣት ያቃተን። ዋናውን ቁልፍ ችላ ብለን ከተውነው፣ እንዴት ብለን መንገዳችንና መድረሻችን እናውቃለን። ለ“እውነት” ታላቅ ክብር የማይሰጥ ባህል ውስጥ፣ መቼም ቢሆን በጎ ለውጥ ሊፈጠር አይችልም። ለእውነት ክብር ከሌለን እንዴት ልንግባባ እንችላለን? ተቀናቃኛችን፣ የቱንም ያህል አስተማማኝ መረጃ ቢያቀርብ፣ ከመጤፍ አንቆጥረውም። በተቃራኒው፣ ምንም መረጃ ሳይኖረን ተቀናቃኛችንን የሚያሳጣ ወሬ እናወራለን - በዙሪያችን የተሰባሰቡ ቲፎዞዎች በጭፍን እንደሚያጨበጭቡልንና ወሬውን እንደሚያራግቡልን እርግጠኛ ነን። ለነገሩ፣ ትክክለኛ መረጃ ሰብስበን ብናቀርብን፣ ተቀናቃኛችንና ቲፎዞዎች፣ ለሴኮንድ ያህል የመስማት ፈቃደኛ አይሆኑም። አልቧልታ እየነዙና እየተቀባበሉ ያስተጋባሉ እንጂ።

“መውጪያ የሌለው አዙሪት” ይሉሃል ይሄ ነው። ታዲያ ይሄ በጎ ነው? በየጎራችን “ለበጎ አላማ” በማሰብ የምናሰራጨው አሉባልታ፣ እንደምታዩት የመጨረሻ ግቡ “ፋታ የለሽ መናቆር” እንደሆነ ተመልከቱ።
ለዚህም ነው፤ በአገራችንም ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን ቀን ከሌት እያወራን መወዛገባችን፣ ክረምት ከበጋ እየተናቆርን መጠማመዳችን፣ መሻኮታችንና መጠላለፋችን ሊያስገርመን የማይገባው። በእርግጥ፣ አብዛኞቹ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ስለ ኢትዮጵያ እየተናገሩ የሚወዛገቡትና የሚናቆሩት ለምን እንደሆነ ብትጠይቋቸው፣ መልሳቸው ተመሳሳይ ነው። በየጎራቸው ለአገሪቱ በጎ ለውጥ ለማምጣት እየተጣጣሩ እንደሆነ ይነግሯችኋል። አብዛኞቹ ምሁራንና ዜጎች ስለ አገራቸው እየፃፉ የሚከራከሩት ወይም የሚሰዳደቡትስ? በየፊናቸው “በቀና መንፈስ መልካም ለውጥን ስለምንመኝ ነው” ይሏችኋል። ምን ዋጋ አለው? ለእውነት ክብር ባለመስጠት፣ የ“በጎ” ነገሮች ጠላት ሆነን እናርፈዋለን።
በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መጠቀስ ከሚገባቸው በጎ አላማዎች መካከል አንዱ፣ “ነፃነት” የሚባለው ነገር ነው - በራስህ አእምሮ የመጠቀም፣ የራስህን ኑሮ የመምራት፣ የራስህን ሕይወት የማጣጣም ነፃነት። በጥንታዊው የግሪክና የሮም የስልጣኔ ዘመናት፤ እንዲሁም በሬነሰንስ እና በኢንላይትመንት ዘመናት፣ የፖለቲካ ነፃነትና ብልፅግና ከሳይንስና ከእውቀት ጋር በጣምራ የተስፋፉት አለምክንያት አይደለም - እነዚህ ሁሉ የሚመነጩት “እውነት”ን ከማክበር ነው። የነፃነት ተቃራኒ ምንድነው ቢባል፣ በቅድሚያ የሚጠቀሱት፣ አፈናና ጭፍን ፕሮፓጋንዳ ናቸው። አሃ፣ ከመነሻው አፈናና ጭፍንነት የሚስፋፋው ለምን ሆነና? ሰዎች፣ “እውነት”ን እንዳያውቁ ወይም “ሃሰትን” እንዲቀበሉ ማድረግ ነው። በሌላ አነጋገር፣ ለእውነት ከፍተኛ ክብር የሌለው ሰውም ሆነ ፖለቲከኛ፣ ገዢም ፓርቲ ሆነ ተቃዋሚ፣ ለነፃነትም ትልቅ ክብር ሊኖረው አይችልም። እንዲያውም፤ የአቅሙን ያህል አፈናንና ጭፍንነትን የማስፈን ዝንባሌ ይኖረዋል። የትኛውም ወገን ቢያሸንፍ ለውጥ የለውም። ለምሳሌ፣ የሙስሊም ወንድማማቾችና ሆስኒ ሙባረክ፣ የሶሪያ አክራሪዎች እና በሽር አልአሳድ፣ ... የሚጣሉት አንዱ አምባገነን አፋኝ ሌላኛው የነፃነት ታጋይ ስለሆነ አይደለም። የሰዎችን ሃሳብና ንግግር ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር፣ ማለትም ተቀናቃኝ የሌለው አፋኝ ለመሆን ነው። ጉልበት ያለውና ስልጣን የያዘ አፋኝ ፓርቲ፣ ግድያ፣ እስር፣ ወከባ፣ ፕሮፓጋንዳ ይፈፅማል። ለጊዜው ስልጣን ያልያዘና ጉልበት የሌለው ፓርቲ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ በአልቧልታ የማሸማቀቅ፣ ስም የማጥፋት፣ በጭፍን የመፈረጅ ዘመቻ ያካሂዳል። ማለቂያ የለሹ አዙሪት የዚህ ውጤት ነው።    
በአገራችን ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች በሁለት ጎራ ስለ ኢኮኖሚ እድገትና ስለ ድህነት የሚያካሂዱትን ውዝግብ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።  “የኢትዮጵያ ዋነኛ መገለጫ... የሞት አፋፍ ላይ መሆኗ ነው” በማለት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የተናገሩ ጊዜ የተፈጠረውን ውዝግብ ታስታውሱ ይሆናል። ኢትዮጵያ በድህነት ተዳክማ በልመና የምትንገታገትና የሕልውና አደጋ የተጋረጠባት መሆኗን ጠቅሰው፤ “እርዳታ ባይገኝ ስንት ሚሊዮን ሕዝብ ያልቃል? እርዳታ እንደልብ ቢገኝ እንኳ፣ ረሃብተኛው እጅግ ብዙ ሲሆን እርዳታ ማጓጓዝ ራሱ ትልቅ ፈተና ይሆናል። ከጥፋት ለመዳን መሮጥ አለብን። መፍጠን አለብን፤ ሴንስ ኦፍ ኧርጀንሲ ያስፈልጋል” የሚል ሃሳብ ነው የተናገሩት ጠ/ሚ መለስ። ይሄ ለብዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚዋጥላቸው አልነበረም።
የዜጎች ድህነት እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ አገሪቱ የገደል አፋፍ ላይ መድረሷ እውነት ቢሆንም፤ ብዙዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “እውነት ብለሃል” በማለት ስምምነታቸውን አልገለፁም። “አዎ አገሬው አደጋ ላይ ነው። ግን፣ መልካም ለውጥ ለማምጣት ገዢው ፓርቲ በብቃት አልሰራም። አገሪቱን ለማሳደግ የሃሳብና የተግባር ብቃት የለህም” ብለው መከራከር ይችሉ ነበር። ግን፤ አላደረጉም። እንዲያውም፤ “ምንም አዲስ የተፈጠረ ነገር ሳይኖር መዓት ማውራት ምንድነው? ኢህአዴግ የአገርን ክብር ደፈረ፤ የአገርን ስም አጠፋ...” በማለት ገዢውን ፓርቲ አብጠልጥለውታል።
አሁን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኗል። በገዢው ፓርቲ ዘንድ፣ ስለ ድህነት ማውራት፣ የአገርን ገፅታ እንደማበላሸት እየተቆጠረ መጥቷል። ተቃዋሚዎች ስለ ድህነት ሲያወሩ... ገዢው ፓርቲ “አዎ ትክክል ነው። አገራችን ድሃ ነች። ባለፉት አስር አመታት ኢኮኖሚው ከእጥፍ በላይ ቢያድግም፤ አሁንም እጅግ ድሃ ነን። ለዚህም ነው በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መቀጠል አለብን የምንለው” ብሎ ማስረዳት ይችላል። ግን አያደርገውም። አገሪቱ እጅጉን የበለፀገች ያስመስላል፤ ስለ ድህነት የሚያወሩትንም “ፀለምተኛ፣ ፅንፈኛ፣ ከሃዲ” በሚል እየፈረጀ ይሳደባል፤ ያስፈራራል።
ተቃዋሚዎችም፤ “አዎ፣ የኢኮኖሚ እድገት እየታየ ነው። ነገር ግን፤ አሁንም ከ13 ሚሊዮን በላይ ተረጂዎች አሉ። በማምረቻ ኢንዱስትሪ መስክ ለውጥ እየታየ አይደለም። በቂ የስራ እድል እየተፈጠረ አይደለም። መንግስት እየገነነና የግል ኢንቨስትመንት ወደ ኋላ እየቀረ ነው። የያዝከው አቅጣጫ አያዛልቅም” ብለው ማስረዳት ይችላሉ። ግን አያደርጉትም። ገዢውን ፓርቲ ለማንቋሸሽ፣ ለመሳደብ፣ በጭፍን ለመፈረጅ ይቸኩላሉ።
እናማ ሁለቱም ጎራዎች፤ ገዢው ፓርም ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በጭፍን ስሜታዊነት ይቀጥላሉ - አንዱ ሌላውን ለማሳጣት።
ግን በጋራ የሚጠሉት ደግሞ አለ - ሚዛናዊ የሆኑ ሰዎችን። እርስ በርስ ለመናቆር ችግር የለባቸውም - ቁንፅል እውነትና ያገጠጠ ሰበብ አለላቸው። ኢህአዴግ የኢኮኖሚ እድገት እየተመዘገበ ነው ሲል እውነት ነው - የአሪቱን ድህነት እየሸፋፈነ። ተቃዋሚዎች፣ ስለ ድህነትና ችግር የሚናገሩት ነገር እውነት ነው - ስለ ኢኮኖሚ እድገት እየዘነጉ። “እንዴት የህዝቡን ድህነት ትክዳለህ?”፣ “እንዴት የኢኮኖሚ እድገቱን ትክዳለህ?” እየተባባሉ ይናቆራሉ።
“ድህነትም አለ፤ የኢኮኖሚ እድገትም አለ” ብሎ እውነት የሚናገር ሲመጣ ለሁለቱም አይጥማቸውም። ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣን ስለያዘ፤ ማስፈራራት፣ ማዋከብና ማሰር ይችላል።
 ተቃዋሚዎች ደግሞ፣ ስልጣን እስኪይዙ ድረስ፣ ስም ማጥፋት፣ ማንቋሸሽና መሳደብ ይችላሉ። ጨዋታው በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፤ የትኛውም ወገን ቢያሸንፍ ብዙም ለውጥ አያመጣም።

Read 6095 times